Monday, 09 September 2019 11:35

ቅናት!

Written by  በኃይሉ አስራት
Rate this item
(6 votes)

ከስራ  መጥቼ መክሰስ እንኳን  ሳልበላ ወደ ጥናት ክፍል አመራሁ፡፡ የያዝኩትን ጥቁር  ቦርሳ ከጠረጴዛ ላይ አሳረፍኩና መጋረጃውን ገልጬ መስኮቱን ከፈትኩት፡፡ ውጭ ህፃናት የእግር ኳስ ይጫወታሉ፡፡ ሌሎች ጥባጥቢ ያንጠባጥባሉ፡፡  ሌሎች ደግሞ አንድ ጅራፍ እየተቀያየሩ ያጮሃሉ፡፡
መጋረጃውን ዘግቼ ጀርባዬን ለመስኮቱ ሰጥቼ፣ እጄን አጣምሬ ቆምኩኝ፡፡ በስተቀኝ ግድግዳውን የተደገፈ ትልቅ  የመጽሐፍ መደርደሪያ ቆሟል፡፡ ከአናቱ ግድግዳው ላይ የተለጠፈ አለምን በአንድ ገጽ የሚያሳይ የዓለም ካርታ አለ፡፡ ከመደርደሪያው ግራና ቀኝ የተሰቀሉ ፎቶግራፎች ይታያሉ፡፡ የመጀመሪያው ፎቶግራፍ በልጅነቴ ከጨርቅ በተሰፋች ቦርሳ ደብተር ይዤ፤ ቀጥሎ የምርቃቴ ጉርድ ፎቶግራፍ፤ ከመደርደሪያው በስተቀኝ ከባለቤቴ ጋር የሰርጋችን ዕለት የተነሳነው ፎቶግራፍ ተሰቅሏል፡፡
አየር በረጅሙ ስቤ ተነፈስኩና ወደ ጠረጴዛው ተራምጄ፤ ከኋላው ያለውን ወንበር ስቤ ተቀመጥኩ፡፡ እጠረጴዛው ላይ የተቀመጠውን የአበባ ማስቀመጫ ወደ ጠርዝ ገፋሁት፡፡  ይህን ሰዓት እጠላዋለሁ፡፡ በሰላም ስራ ስሰራ ውዬ፣ ወደ ቤት መሄጃዬ በደረሰ ጊዜ ይጨንቀኛል፡፡ ፍቅሬን የምነጠቅበት ሰዓት ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ስንቴ በስራ ላይ ስለምትሆን ይበርደኛል፡፡
ያወቅኋት ቢሾፍቱ እየተማርኩ ነበር፡፡ አንድ ቀን በግቢው የተባዛ የተማሪ መማሪያ የፊዚክስ መጽሐፍ ጠፍቶብኝ አባዝቼ እንዳቀርብ የመጽሐፍት ቤቱ ኃላፊ ስላዘዘኝ፣ ዋናውን ይዤ ወጥቼ፣ ከአደባባዩ አካባቢ የሚያባዛ ቤት ስፈልግ አግኝቼ ሠጠኋት፡፡
ስንቴ ቀጠን ብላ ረዘም ያለች ናት፡፡ በወቅቱ አረንጓዴ  ጉርድ ቀሚስ አድርጋለች፡፡ ያደረገችውን ታኮ ጫማ እንዳሻት ታዝዘዋለች፡፡ መጽሐፉን አየት አደረገችና፤
“የኮሌጅ ተማሪ ነህ?”
“አዎ”
“የቤተሰብ ድጎማ ስለማይለያችሁ፤ ዋጋው ትንሽ ጨመር መደረግ አለበት” ብላ     
ትኩር ብላ ተመለከተችኝ፡፡
“እረ ምን አለን ብለሽ ነው” ብዬ አይኔን ወደ በሩ አቅጣጫ ወረወርኩት፡፡
“እንዴት ጠፋብህ? ”
“ ስፔስ  እያጠናሁ ቡና ለመጠጣት ወጥቼ--”
“ስርቆትም አብሯችሁ ይገባል እንዴ? ”
“ማን ይፈትሸዋል?”
“አንተ!”
ከት ብዬ ሳቅኩኝ፡፡
ከሁለት ቀን በኋላ እንድመለስ ቀጠሮ ሰጥታኝ ተለየሁ፡፡ ወደ ግቢ ገብቼ ማጥናት አልቻልኩም፤ ተቅበዘበዝኩኝ፡፡ የምሄድበት ምክንያት ደግሞ የለም፡፡ ቀኑ ደርሶ በጥዋት ሄድኩኝ፤ አልመጣችም:: ተቁነጠነጥኩ፡፡  ወደዚያ ወደዚህ እያልኩኝ ከርቀት መከፈቱን ስጠብቅ፤ ጅንስ ሱሪ በታኮ ጫማ፣ ከላይ ነጭ ሸሚዝ አድርጋ ትውረገረጋለች…
“እንደምን አደራችሁ?” አለች፤ የበሩን ቁልፍ እየከፈተች፡፡
“ስንታየሁ እንደምን አደርሽ?” አሉ፤ሶስተኛ ሱቅ በር ላይ ያሉ ጠና ያሉ ሴት፡፡ ስሟን አገኘሁት ብዬ፣ ቡጢ ጨብጬ አየሩን ቀዘፍኩት፡፡
“ስንቴ እንደምን አደርሽ?” አልኩኝ፤ ከበሩ ደርሼ:: ደንገጥ ብላ ቀና አለች፡፡
“ስሜን ከየት አገኘኸው?”
“ወድቆ!”
“በል መልስ!”
“ላመጣሁበት ከተከፈለኝ”
“ተጨዋች ነህ! በጣም ይቅርታ መብራት እየመጣ እየሄደ አልጨረስኩም”
“ውይ  ዋናውን ከሰው ስለተዋስኩት እንጂ ችግር አልነበረውም፡፡”
“ዛሬ እጨርሳለሁ፤ አሁን ትንሽ መድረስ ያለበት ያደረ የሚጻፍ ስላለ ነው”
“ለእኔ አሳይኝና እኔ ላባዛው”
“አልከፍልም እንዳትል” አለችና አሳየችኝ፡፡
አንዴ ወደ ወረቀቱ  አንዴ ወደ ኮምፒውተሩ አይኖቿን ስትቀያይራቸው፣ ሰረቅ እያደረግሁ አያታለሁ፡፡  ሃሳቤ በእሷ እየተሰረቀ የደገምኳቸው ገጾች ነበሩ፡፡  
“ስራ እንዳትፈልግ፣ እዚሁ ቦታ እይዝልሃለሁ፡፡”
“በደስታ ነዋ! ቅር የማይልሽ ከሆነ አድራሻ ብንለዋወጥ?”
 “መጽሐፍህን ወሰድክ፤ እኔ ነኝ የቀረውህ!”
“ያው ሌላም….”
“ ችግር የለውም” ብላ በወረቀት ጽፋ ሰጠችኝ
“ገረሲ እባላለሁ፡፡”
“ማታ ማታ ነው የምታገኘኝ፡፡”
“እሺ አመሰግናለሁ” ብዬ ወጣሁ፡፡
ማታ ማታ እየደወልኩ መጨዋወት ጀመርን፡፡ ተቀጣጥረን እሁድ እሁድ መገናኘት ያዝን፡፡
አንድ ቀን፤
“ፍቅረኛ ነበረሽ?” አልኳት
“አዎ ነበረኝ”
“እስከ ምን ድረስ?”
“እስከዚህ ድረስ” ብላ ትኩር ብላ ታየኝ ጀመር፤ፊቴን ወደ በሩ አዞርኩት፡፡ በመሀላችን ጸጥታ ሰፈነ…
“ምነው ዝም አልክ? ተጫወት፡፡”
“እሺ” አልኩ፤ ፊቴን ሳልመልሰው፡፡
“አንተ ፍቅረኛ ነበረችህ?”
“ትምህርት ቤት እያለሁ--”
ዝም አለች፡፡ ዝም አልኩ፡፡ ሂሳብ ከፍላ ተለያየን:: ይህ ከሆነ ከሁለት ቀን በኋላ ደወልኩ…
“ሁለታችንም ጋ የቅናት ስሜት ይንፀባረቃል፡፡ አይደለም?” አለች
“እንደዚያ ሳይሆን…”
“በቃ ያ ነው፡፡ እኔም የእኔን ስነግርህ ምንም አልመሰለኝም፤ የአንተን ስትነግረኝ ግን ተናደድኩ፡፡ ያለፈውን ትተን ከዚህ በኋላ ባለው ላይ ብናተኩር ጥሩ አይመስልህም?”
“እሺ” አልኳት፡፡
ይህን ጊዜ ሳስታውሰው፣ በልጅነቴ የሰማሁት ተረት ይታወሰኛል...
ሁለት የሚዋደዱ ፍቅረኛሞች ተጋብተው የጫጉላ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ፣ ባልየው ወደ ዘመቻ እንዲሄድ ጥሪ ይመጣለታል፡፡ ወደ ዘመቻ ሄዶ መሞቱ ሳይሆን፣ ሚስቱን ጥሎ ሲሄድ በሌላ ወንድ እንዳትነካበት መጨነቅ ጀመረ፡፡ ወደ አዋቂ ዘንድ ሄዶ፣ ሚስቱ ከጦር ሜዳ እስከሚመለስ እንዳትነካበት ቁልፍ እንዲሰጠው ጠየቀው፡፡ አዋቂውም በተጠየቀው መሰረት ሰርቶ ሰጠው፡፡
ነገሩን ለሚስቱ ሲያወያያት፣ “አንተንም ሌላ እንዳታባልግብኝ ለአንተም ካሰራህ እቀበላለሁ፡፡ የአንተ ቁልፍ  እኔ ጋ ፤ የእኔ ቁልፍ አንተ ጋ ይሆናል” አለችው፡፡
የራሱንም ቁልፍ አሰርቶ መጣና፤ እሷም የእሱን ቆልፋ፣ እሱም የእሷን ቆልፎ ወደ ዘመቻው ሄደ፡፡
በዘመተበት ቦታ ድል ሳይቀናቸው  ቀርቶ ተማረኩ፡፡ አንድ ቀን ጠባቂው፣ ያንን ቁልፍ አንገቱ ላይ አይቶ ቢጠይቀው እውነታውን አጫወተው:: ጠባቂው እንዲህ ያለ አዋቂ በሀገራቸው ባለመኖሩ እየገረመው  ለንጉሱ ነገረው፡፡
ንጉሱም ሰውየው ቁልፎቹን ካመጣለት ከምርኮው እንደሚለቀው ቃል ገብቶለት፣ ወደ ሀገሩ ሰደደው፡፡ እሱም ሃገሩ ሄዶ፣ ቁልፎቹን ይዞ ተመለሰ፡፡ ንጉሱም ቁልፎቹን ተቀብሎ ከምርኮነት ነፃ አደረገው፡፡
እኔም ይሄን ቁልፍ ባገኘው እላለሁ፡፡
ስንቴ በቀይ ፊቷ ላይ ጉራማይሌ የተነቀሰችው ጥርሷ ተጨምሮበት  ያነሆልለኛል፡፡ ተጨዋችነቷን ፣ የንግግር ችሎታዋን ሳይ ደግሞ ምነው ከእኔ ጋር ብቻ ባደረገችው እያልኩ እንገበገባለሁ፡፡ ሳገኛት የፋሽን ዲዛይን የማታ ትማር ነበር፡፡  የሰራችውን ለብሳ አንደኛ ስትወጣ፣ ከደስታ ይልቅ ከጭብጨባው ጀርባ ስንቱ የእኔ ብትሆን እያለ ቋምጧል ብዬ ተጨቃጭቄ፣ በውድድር እንዳትካፈል አደረግኋት፡፡
ከዚያ በግሏ  የባህል ልብስ ስፌትና ሽያጭ ጀመረች፡፡ ሁለት ወልደንም ጭምር ውጪ አምሽታ እንድትመጣ አልፈልግም፡፡ ልቤ ላይ የማቃጠል ስሜት ይሰማኝ ጀመር፡፡ አዕምሮዬ ትርጉም አልባ ነገሮችን ያመላልሳል፡፡ እታገለዋለሁ እንጂ አላመለጥኩትም፡፡ ለመሸሽ ብዬ ወደ መስኮቱ ተጠጋሁ፤ ውጭው ድቅድቅ ያለ ጨለማ ነው፡፡ ደነገጥኩ፡፡ እስከዚህ ሰዓት ድረስ መቆየት የለባትም የሚለው ሀሳቤ ጎላ፡፡  ወደ በሩ ሄጄ መብራቱን አበራሁትና በመስኮት ጨለማው ላይ አፈጠጥኩ፡፡ በሩ ተንኳኳ፤ ዞሬ አላየሁም፡፡
“እንደምን አመሸህ ውዴ?”  አልመለስኩም
“ምን ሆነሃል ውዴ?”
“አልበዛም?”  ብዬ ስዞር፣ ወደ እኔ እየመጣች ነው፡፡
“አትጠጊኝ! የዋልሽበት!”
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?”
“ከማንም ጋር እየተላፋሽ እኔ  መቀለጃ አይደለሁም…”
“በቃህ!” አለችና የአበባ ማስቀመጫውን ወረወረች፤ አመጣጡን አይቼ አሳለፍኩት፡፡ በቡጢ ጆሮ ግንዷ አካባቢ አሳረፍኩባት፡፡ ወደቀች፡፡ በወደቀችበት  እላይዋ ላይ ተከመርኩ፡፡ አንገቷን በሁለት እጆቼ አነቅኳት፡፡
“እባክህ ለልጆቻችን እንኑርላቸው! እባክህ … እባክህ… እባክህ…”  ጆሮዬ ይሰማል እንጂ እጄ አለቀቃትም፡፡ እግሯቿን አወናጭፋ ስትዘረጋቸው ለቅቄያት፤
“ውዴ…ውዴ…” እያልኩ ፊቷን መታ  መታ  አደረግሁት፡፡ መልስ የለም፡፡ ጭንቅላቷ ወደ አንድ ጎን አዘነበለ፡፡ ሰዎች ተሯሩጠው ሲገቡ ይሰማኛል፡፡…
“ውዴን በላኋት… ውዴን ገደልኳት” እያልኩ ሮጬ ምግብ ማብሰያ ገብቼ፣ ዋናውን የኤሌክትሪክ ገመድ ጨበጥኩት…
ስነቃ የግራ እጄ ላይ የጉሉኮስ ገመድ፣ የቀኝ እጄ  ከተኛሁበት አልጋ ጋር በካቴና ታስሯል፡፡ ሞትን መቀያየር ቢቻል በቀየርኳት፡፡ ያንን የተወረወረ የአበባ ማስቀመጫ ምነው በግንባሬ በተቀበልኩት:: ከምኞት የዘለለ አልነበረም፡፡ ከነቃሁ ከሁለት ቀን በኋላ ፍርድ ቤት ቀረብኩ፡፡ የእምነት ክህደት ቃሌን ተጠየቅሁ፡፡  በራሴ ቅናት የልጆቼን እናት እንደገደልኩ አስረዳሁ፡፡  አስራ ስምንት ዓመት ተፈረደብኝ፡፡ እኔ ግን  ያንሰኛል አልኩ፡፡ ወጥቼም አልጠቅምምና፡፡
በሩ ተንኳኳና ወደ መጸዳጃ የምንሄድበት ጊዜ መሆኑ ተነገረን፡፡ ካለ ተስፋ መንጋት መምሸት ትርጉም የለውም፡፡ ተስፋዬ ከእሷ ጋር ተቀብሯል፡፡  ጊዜ ወደ ኋላ አይመለስም፡፡

Read 3555 times