Print this page
Saturday, 21 September 2019 12:18

ለጥናት…በቂ መረጃ ያለው ስምምነት…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 አንድ ሰው ለአንድ ጥናት ተባባሪ ለመሆን ሙሉ ፈቃደኛ ሆኖአል ወይንም ተስማምቶአል የሚ ያሰኘው ጥናት ከሚያደርገው አካል ወይንም ግለሰብ አስቀ ድሞ ስለሚሰራው ጥናት በቂ የሆነ መረጃ ሲያገኝና የሚደረገው ጥናት ለማን… ምን እንደሚ ጠቅም እና ለዚህ ጥናት ደግሞ እርሱ ወይንም እርስዋ ምን ያህል አስፈላጊ እንደ ሆነ/ች በጉ ዳዩም ላይ ጊዜ ወስዶ/ዳ አምኖ በት/ናበት በትክክል መስማማቱን/ትዋን ሲያረጋግጥ ወይንም ስታረጋግጥ ፈቃደኛ ነው/ናት ይባላል፡፡ ማንኛውም ጥናት በሚደረግበት ጊዜ ለሰዎች ክብር መስጠት ተቀዳሚው ግዴታ ይሆናል፡፡  
ለሰዎች ክብር መስጠት ሲባል ሁሉንም ሰዎች ላላቸው አቅም፤እውቀትና ችሎታ እንዲሁም ለስብእናቸው ክብር መስጠት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
በተለያየ ምክንያት አቅማቸው ያነሰ እና ጥንቃቄ የሚፈልጉ ሰዎች የተለየ ክብካቤ እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ ለስልጠና
ካቀረቡት ሰነድ የተወሰደ
ባለፈው እትም ጥናት ለማድረግ የጥናት ስነምግባር ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ ለንባብ ብለን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ነጥብ የተነሳበት ምክንያትም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ጥናት ለማድረግ የሚያስቡ ሰዎች ፕሮፖዛላቸውን በቀጥታ በኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር ለሚቋቋመው የጥናት ስነምግባር ቦርድ እንዲያቀርቡ ለማስቻል የተጀመሩ ስራዎችን የሚመለከት ነበር፡፡ ማህበሩ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መ/ቤት በመጡ ባለ ሙያዎች አማካኝነት ለባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጥ አድርጎአል፡፡ በዚህ እትም የምናስነ ብባችሁ ደግሞ ጥናት በማድረጉ ረገድ የሰዎች ስምምነት ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑንና መብታቸውን ለመጠበቅ የሚያስችሉ አካሄዶችን እናስነብባችሁዋለን፡፡ ማንኛውም ጥናት ሲካሄድ በዘርፉ ይመለከ ታቸዋል የሚባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደአግባቡ የሚሳተፉበት መንገድ መኖር እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ይህንን ነጥብ በስልጠናው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ያቀረቡት ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
ከጤና ጋር የተያያዙ ጥናቶች በተጀመሩባቸው ቀደም ባሉት አመታት ለጥናቱ ያስፈልጋሉ የተ ባሉ የህብ ረተሰብ ክፍሎች ስምምነታቸው ወይንም ፈቃደኝነታቸው ሳይጠየቅ ብዙ አሰቃቂና ዘግናኝ የሆኑ ምርምሮች እንደተካሄዱባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ባለፈው እትምም እንደማ ሳያ የተወሰደው በጀርመን በናዚ አገዛዝ ወቅት እና በአሜሪካ በጥቁር አሜሪካውያኖች ላይ ሲደ ረግ የነበረው ሰብአዊነትን ያልጠበቁ ዘግናኝ ምርምሮች ሲታወሱ የሚኖሩ ናቸው::  
ለመሆኑ ለጥናቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መረጃው በትክክል ደርሶአቸው ስምምነታቸውን ሊያረጋግጡ ይገባል ሲባል ምን ማለት ነው?
በጥናቱ ሊሳተፉ ይችላሉ ወይንስ አይችሉም?
ፈቃደኛ ናቸው ወይንስ አይደሉም?
ጉዳዩ በትክክል ገብቶአቸዋል?
ጥናቱ ለቀጣይ ሕይወት ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን ተረድተዋል?
እነሱ በጥናቱ መሳተፋቸው ምን ያህል ጠቃሚ መሆኑን በሚገባ ተገንዝበዋል?
ጥናቱ በሚደረግበት ጊዜ የአካል ወይንም የስነልቡና ደህንነታቸውን እንዳይጎዳ ለማድረግ ለራሳቸው ምን ያህል ጥንቃቄ ያደርጋሉ...ወዘተ
ከላይ የተመለከቱትን ሀሳቦችና ሌሎችም ተያያዥ ነጥቦችን ማንኛውም ለጥናቱ ተባባሪ እንዲ ሆን የሚጋበዝ ሰው አስቀድሞ ሊገነዘበው የሚገባው መሆኑን የዶ/ር ሰሎሞን ትምህርታዊ መረጃ ያመለክታል፡፡
ሰዎች በጥናቱ እንዲካተቱ ስምምነታቸውን መግለጻቸው ግቡ ምንድነው? ሲባል ጥናትና ምርምሩን የሚያደርገው ባለሙያ ወይንም አካል ለጥናቱ አስፈላጊ የሆነው ሰው ምን ያህል ፈቃደኛ መሆኑን እና መስማማቱን ለማረጋገጥና ስራውንም በሙሉ ነጻነት ካለምንም ስጋት ለመቀጠል እንዲያስችለው ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ሰው ለጥናቱ ተባባሪ እንዲሆን ሲጋበዝ፤
መረጃው በትክክል ደርሶታል ወይንም ተነግሮታል፤ ተወያይቶአል?
የተነገረውን መረጃም በትክክል ተረድቶታል ወይንም ገብቶታል?
ለተግባሩ ሙሉ ፈቃደኛ ሆኖአል ማለት ነው? አንድን ጥናት ከመጀመር በፊት ለእነዚህ ጥያቄዎች በትክክል መልስ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡    
ስለዚህ ማንኛውም ሰው በአንድ የጤና ጉዳይ ላይ ጥናት ሊደረግ ስለሆነ በሚነሳው ርእሰ ጉዳይ ላይ ያለውን ልምድና እውቀት እንዲያካፍል እና ጥናቱን ሙሉ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች እንዲያተኩርባቸው ያስፈልጋል:: አንድ ሰው ለጥናቱ ሲጋ በዝ አቀራረቡ በመጠኑ እንደሚከተለው ይሆናል ይላል ዶ/ር ሰሎሞን ቁምቢ ለጥናት ያቀረቡት ሰነድ፡፡
‹‹…አንተ በ…ጉዳይ ላይ ለሚደረገው ጥናት እንድትተባበር ተጠይቀሀል፡፡ ጥናቱ… የሚመለከት ሲሆን ጥናቱ የሚያካትተው ርእሰ ጉዳይም ከ…ጋር ተዛማጅነት ይኖረዋል፡፡ ከጥናቱ አንተም…ስለሚባል በሽታ ባህርይ እውቀት እንዲኖርህ ስለሚያስችል ተጠቃሚ እንደምትሆን እሙን ነው፡፡ ጥናቱ በአንተ ላይ ምንም ጉዳት አያስከትልም፡፡ በጥናቱ ላይ የመሳተፍህን ጉዳይ ካልተ ስማ ማህበት በማንኛውም ጊዜ ማቋረጥ ትችላለህ፡፡ምስጢርህ የተጠበቀ ነው፡፡››
ከላይ ያነበባችሁት ስምምነት ጥናት ከሚያደርገው አካል ለጥናቱ ተባባሪ ለሚሆነው ግለሰብ አስቀድሞ በሚደርሰው መረጃ የሚገለጽ ነው፡፡ ይህ በምስጢር የሚያዝ ሰነድ መሆኑን ጥናት አድራጊው አካል ይገልጻል:: ከዚህም በተጨማሪ ምናልባት ጥናቱ በሚደረግበት ጊዜ ለተሳትፎ የሚሰጡ ጥቅማ ጥቅሞች ካሉ ወይንም የሚደርስ ጉዳት ካለ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ነገሮችን አስቀድሞውኑ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡  
በጥናት አድራጊዎቹ ዘንድ መሟላት የሚገባቸው ዋና ዋና ሀሳቦችም ተገልጸዋል፡፡     
ለጥናቱ ተሳታፊ እንዲሆን ከሚጋበዘው ሰው ጋር መግባባት እንዲኖር ለማድረግ፤
ቀላልና ግልጽ የሆነ ቋንቋ መጠቀም፤
የአገር ውስጥ ቋንቋን መጠቀም፤
አጫጭር ቃሎችንና አረፍተነገሮችን መጠቀም፤
ሙያዊ የሆኑ ነገሮችን ወይንም አባባሎችን አለመጠቀም፤
ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ካልተሟሉ ለጥናቱ ተባባሪ እንዲሆን የተጋበዘው ሰው ነገሩ ግልጽ እንዲሆንለት በግልጽ መጠየቅ እንጂ ሀሳቡ እንደገባው አድርጎ ዝም ብሎ ማለፍ አይገባም፡፡
በተጨማሪም ባለሙያዎች ጥናት በሚያደርጉበት ጊዜ ማስወገድ ከሚገቡዋቸው ነገሮች መካከል፤
ለጥናቱ ተባባሪ የሆኑ ሰዎች የሚያቀርቡዋቸውን ሀሳቦች ማስወገድ ወይንም ይህን ማለት አይገባም ብሎ እንዲለውጡ ማስገደድ፤መሰረዝ ወይንም መቃወም፤
ለጥናት ተባባሪ እንዲሆኑ የተስማሙ ሰዎች በፈለጉት መንገድ የመናገር መብታቸውን ጫና በማሳደር ጥናት አድራጊው እንዲናገሩ በሚፈልግበት መንገድ ወይም በተጋነነ መልኩ ቃላቸውን እንዲሰጡ ወይንም ሃሳብ እንዲያቀርብ ግፊት ማድረግ አግባብ አይደለም፡፡
በጥናቱ እንዲሳተፉ የተጋበዙ ሰዎች በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበት ጥናት የሚደረግበትን ሀሳብ አስቀድሞ መስጠትና ለተሳትፎው በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሀሳቦች ጥናት አድራጊዎቹ ሊወጡት ከሚገቡዋቸው አንዳንድ ግዴታዎች መካከል ሲሆኑ ለተሳትፎ የሚጋበዙ ማንኛቸውም ሰዎች አስቀድመው ቢያውቁት ለመብታቸው መቆምን እንዲሁም ጥናቱ በሰመረ መንገድ እንዲካሄድ እገዛቸው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡

Read 9897 times