Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 16 June 2012 11:42

የፑቲን መንግሥት በተቃውሞ እየተናጠ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአገራችን ዕጣ ፈንታ ግለሰቦች የሚወስኑበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው፡፡ ሥልጣን የሙጥኝ ብለው ድርቀ ያሉ አምባገነኖች አገራቸውንና ህዝባቸውን ለደም መፋሰስና ማብቂያ ለሌለው መከራ ይዳርጋሉ፡፡ የሌሴቶው የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር ግን ከዚህ የተለየ ተግባር ፈፅመዋል - ከሥልጣን በፈቃዳቸው በመልቀቃቸው፡፡

ቅርቡ በሩሲያ በተካሄደው ምርጫ ያሸነፉት ቭላድሚር ፑቲን፤ ሥልጣን ላይ በወጡ ማግስት በጥድፊያ የሰሩት ሥራ ካለ በተከለከለ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የሚሳተፉ ዜጐችና የተቃውሞ አደራጆች በከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ የሚያደርግ አዲስ ህግ በፓርላማ ማፅደቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን የህጉ መውጣት ተቃውሞውን አባባሰው እንጂ አላቀዘቀዘውም፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ተቃዋሚዎች ፑቲን ያፀደቁትን አዲስ ህግ በመቃወም ሰልፍ ለመውጣት ከከተማዋ አስተዳደር ለ50ሺ ሰዎች ፈቃድ አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከተፈቀደው ቦታ ውልፊት ያለ ከቅጣት እንደማያመልጥ አስተዳደሩ ማስጠንቀቁ አልቀረም፡፡
ከሰልፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ የሩሲያ ፖሊስ መኮንኖች፤ የታዋቂ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን መኖሪያ ቤቶች ሃይል በመጠቀም እንደፈተሹና እንደበረበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የፖሊስ ፍተሻና ብርበራ ኢላማ ከተደረጉት መካከል የፀረ ሙስና ብሎገር አሌክሲ ናቫልኒ፣ የግራ ዘመም ፖለቲካ መሪው ሰርጊ ዩዳልትሶቭ፣ ዕውቁ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ክሴንያ ሶብቻክ እና የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ኔምትሶቭ ይገኙበታል፡፡
“ቤቴ ውስጥ ፍተሻ እየተካሄደ ነው፤ በሩን ሁለት ቦታ ከፍለውታል” ሲሉ በሙስና ላይ ዘመቻ የከፈቱት ናቫልኒ ትዊተር ላይ ጽፈዋል፡፡
ቤታቸው ብቻ ግን አይደለም፤ የፀረ ሙስና ፈንድ የሚያስተዳድሩበትና ከፍተኛ የመንግስት አካላትና የትላልቅ ኩባንያዎችን የሙስና ተግባር ለማጋለጥ የሚያስተባብሩበት ቢሮአቸውም በፖሊስ ተበርብሯል፡፡
ፖሊስ ከቢሮ ውስጥ ኮምፒዩተሮች፣ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ ባንዲራዎች፣ ፎቶግራፎችና ልብሶችን እንደወሰደ የጠቆሙ መረጃዎች፤ የተቃዋሚ አመራር ወላጆችና አማቶች መኖሪያ ቤቶችም ፍተሻ እንደተካሄደባቸው ታውቋል፡፡
የሩሲያ ፓሪስ ሂልተን እየተባለች የምትጠራው ዝነኛዋ ሶብቻክ ስለ ሁኔታው በትዊተር ላይ ባሰፈረችው ጽሑፍ፤ “ፖሊሶች ቤታችንን ሰብረው ሲገቡ ልብሴን ለመለባበስ እንኳን ጊዜ አልነበረኝም” ብላለች፡፡
የሩሲያ መንግስት ባለስልጣናት በተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ላይ ተከታታይ እርምጃዎች ሲወስዱ የቆዩ ቢሆኑም የመኖሪያ ቤቶች የሃይል ፍተሻና ብርበራ ሲካሄድ የሰሞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡
በተቃውሞ ሰልፎች በሚሳተፉ ግለሰቦች ላይ የገንዘብ ቅጣት የሚጥለው የህግ ረቂቅ በጥድፊያ ለፓርላማ የቀረበው በያዝነው ወር ሲሆን ባለፈው አርብ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ፑቲን በፊርማቸው አጽድቀውታል፡፡ በአዲሱ ህግ መሰረት፤ በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦች የአንድ ሩሲያዊ አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ 150 እጥፍ የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ይደረጋል፡፡ 300ሺ ሩብልስ ወይም 6ሺ ፓውንድ ገደማ ማለት ነው፡፡
የሰልፍ አደራጆች ደግሞ 1ሚ. ሩብልስ ይቀጣሉ ይላል - አዲሱ ህግ፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ የፑቲን አስተዳደር አዲሱን ህግ ያፀደቀው አፋችንን ዘግተን እንድንቀመጥለት ፈልጐ ነው ሲሉ ተቃውሞአቸውን ይገልፃሉ፡፡
ፑቲንና ጠ/ሚኒስትሩ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በበኩላቸው፤ አዲሱ ህግ በአውሮፓ ስታንዳርድ የተረቀቀ ነው በማለት በይፋ ተከራክረዋል፡፡ (የአገራችን መንግስት እንደሚለው)
ከምርጫው አንድ ቀን በፊት የተደረገውን ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት ፖሊስ በርካታ የተቃውሞ ሰልፍ ተሳታፊዎችን የያዘ ሲሆን ገና እርምጃውን መውሰድ ሲጀምር ከ400 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር ታውቋል፡፡
ባለፈው እሁድ ደግሞ አምስት ሰዎች ተይዘው ታስረዋል ተብሏል፡፡
ባለፈው ሰኞ መኖሪያ ቤታቸውና ቢሮዎቻቸው በፖሊስ የተበረበሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፤ በነጋታው ህዝባዊ ሰልፉ ሊደረግ አንድ ሰዓት ሲቀረው ለምርመራ ተጠርተው እንደነበር ታውቋል፡፡ ምርመራው ከምርጫው በፊት በተደረገው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሩሲያ ፖሊስ ከፍተኛ ሃላፊ ተናግረዋል፡
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፤ በተቃዋሚ መሪዎቹ ቤቶች ውስጥ የተደረገው ፍተሻም ሆነ በአመራሮቹ ላይ የተካሄደው ጥያቄና ምርመራ ህዝባዊ ተቃውሞውን ለማደናቀፍ የተወጠነ ብልህነት የጐደለው ሙከራ ነው ሲሉ ነቅፈውታል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ለምርመራ መጠራታቸውን አስመልክቶ በትዊተር ላይ የፃፉት ግራ ዘመሙ ፖለቲከኛ ዩዳልትሶቭ፤ “የተቃውሞ ሰልፉ አንዱ አደራጅ እንደመሆኔ ህዝባዊ ተቃውሞውን መምራት ኃላፊነቴ ነው” ብለዋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ከታቀደው ህዝባዊ ተቃውሞ ሰዓት ቀደም ብለው በፑሽኪን አደባባይ ከተገኙት በሺህ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች መካከል የድህረ ምረቃ ተማሪው የ25 ዓመቱ አንቶን ማርቫሶቭ ስለተቃውሞው ሲናገር፤ “በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ግፊቱ ሊሰማቸው ይገባል፤ ይሄንን ተቃውሞ በምንም ዓይነት መንገድ ማድረጋችን አይቀርም፤ በሰላማዊም ሆነ በሌላ መንገድ…ጆሮ ዳባ ልበስ የሚሉን ከሆነ ግን ደም መፋሰሱ አይቀሬ ይሆናል” ብሏል፡ በሩሲያ ታዋቂ ትዊተር የሆነው hashtag ባለፈው ሰኞ “እንኳን ወደ 1937 ዓ.ም በሰላም መጣችሁ” የሚል ጽሑፍ ያወጣ ሲሆን በወቅቱ አምባገነኑ የሶቭየት መሪ ጆሴፍ ስታሊን በተቀናቃኞቹ ላይ የፈፀመውን ከፍተኛ የኃይል እርምጃ ለማመልከት እንደሆነ ታውቋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የተካሄደውን ህዝባዊ ሰልፍ ያስተባበሩት የሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ የኃይል ፍተሻውና ብርበራው ሁኔታውን አባብሶታል ሲሉ የፑቲንን መንግሥት አስጠንቅቀዋል፡፡
“ይሄ ማህበረሰባዊ ውጥረቱ ሊቀለበስ በማይችል ሁኔታ እንዲባባስ ከመቀስቀሱም በላይ በሩሲያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ገንቢ መሻሻል (ዕድገት) እንዳይመጣ መንገዱን ይዘጋዋል” ብለዋል - አመራሮቹ በጋራ መግለጫቸው፡፡
ነገሩ ሲታይ የፑቲን መንግስት ለተቃዋሚዎች ጥያቄ ጆሮ እንዳልሰጡ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ፑቲን በአረቡ ዓለም ከታየው ህዝባዊ አመፅና ውጤቱ አንዳችም ትምህርት የቀሰሙ አይመስሉም፡፡ መጨረሻቸው ምን ይሆን? የሆነስ ሆነና እኛስ ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን? መወያየት አይከፋም፡፡

 

 

Read 17203 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 13:23