Tuesday, 08 October 2019 09:24

ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀ የጥረት ውጤት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ወርልድቪዥን ኢትዮጵያ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ከሚያከናውናቸው የተቀናጀ የልማት ሥራዎች መካከል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት ሆሞሻ፣ ባሞባሲና ማኦኮሞ አካባቢ ላለፉት 15 ዓመታት፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጀባት ወረዳ ሸነን ከተማ መብኮ ደግሞ ላለፉት 17 ዓመታት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ላለፉት 22 ዓመታት ሲያካሂዳቸው የቆዩ የልማት ሥራዎችን ለአካባቢው ማህበረሰብና ለመንግሥት ያስረከበበትን ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ በእነዚህ ፕሮግራሞች በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎችን በትምህርት፣ በጤና፣ በምግብ ዋስትና፣ በአካባቢ ጥበቃና በልጆች እንክብካቤና ጥበቃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
በዚህ የፕሮጀክት ማጠናቀቂያና ለሕብረተሰቡ ማስተላለፊያ ፕሮግራም ላይ በመገኘት በአካባቢው ላለፉት ዓመታት ሲከናወኑ የቆዩትን የልማት ሥራዎችና የሕብረተሰቡን የኑሮ ለውጥ ለማየት ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች ከሰሞኑ  ወደ ሥፍራው ተጉዘው ነበር፡፡
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ሆምሸ አካባቢ ቱመት ቀበሌ ውስጥ ተወልዶ ላደገው ኑረዲን ኑር ሰይድ ሕይወት ቀላል አልነበረችም:: እንደ አብዛኛው የአካባቢው ሕጻናት ከሕይወት ጋር ትግል የጀመረው ገና በታዳጊነት ዕድሜው ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቀን ከሌት የሚታትሩና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነበሩ፡፡ የኑረዲን ዕድሜ ለትምህርት ሲደርስ፣ ወላጆቹ የትምህርት ቁሳቁሶችን አሟልቶ ልጃቸውን ወደ ት/ቤት መላኩ በእጅጉ ቢከብዳቸውም፣ የቻሉትን ሁሉ አድርገው የመንግስት ት/ቤት አስገቡት፡፡ ትምህርት ቤቱ፣ ትምህርት ቤት የሚለውን ስያሜ ያገኘው መምህራንና ተማሪዎች በጋራ የሚገናኙበት ብቸኛ ሥፍራ በመሆኑ ነበር ለማለት ያስደፍራል:: ክፍሎቹ የወላለቁ፣ የፈራረሱና በርና መስኮት የሌላቸው የጭቃ ቤቶች ነበሩ፡፡ ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙም አነስተኛ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ኑረዲን ከፊደል ጋር መተዋወቅ ጀመረ:: በትምህርቱ ጎበዝ፣ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት መሆኑን ማሳየት የጀመረውም ገና በማለዳው ነበር፡፡ የት/ቤቱ መምህራንም አይናቸውን ጣሉበት፡፡ ከዚህች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነገ የተማረ ሰው ሆኖ የሚወጣልን ተስፋችን ነው ብለው ያበረታቱት ጀመር፡፡ ዕለት ተዕለት ግን ሁኔታዎች ይበልጥ እየከበዱ ሄዱ፡፡ የወላጆቹ ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ፣ የኑረዲንን የትምህርት ሂደት አስቸጋሪ አደረጉበት፤ ባልተሟላ የትምህርት ቁሳቁስ ት/ቤት መሄድ እየከበደው መጣ፡፡ ቢሆንም ግን ማለዳ ተነስቶ ወደ ትምህርት ቤቱ መሄዱን አላቋረጠም። የሕጻን ልቡን አጠንክሮ ከዝናብና ከፀሐይ ለማስጣል እንኳን አቅም ወደሌላት ወደዚያች ት/ቤት ይሄዳል፡፡ በዚህ መሀል ነበር (የዛሬ 15 ዓመት ገደማ) የዚህን የስምንት ዓመት ሕጻን ተስፋ የሚያለመልም ብስራት የተሰማው። በወቅቱ ኑረዲን የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአካባቢያቸው በሚገኙ ወረዳና ቀበሌዎች ውስጥ ለሚኖሩ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን የሚደገፍና በትምህርት፣ በምግብ ዋስትና፣ በጤና እንዲሁም በልጆች ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሰራ የማሆኮሞ ባሞባሲ ኤሪያ ፕሮግራሙን ዘረጋ፡፡ ድርጅቱ  በአካባቢው በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመለየት የተለያዩ እገዛና ድጋፎችን በማድረግ ሥራውን ጀመረ፡፡ አሮጌው የእነ ኑረዲን ት/ቤት ፈርሶ በምትኩ ደረጃውን የጠበቀ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ አዲስ ት/ቤት ለቱመትና ገላን ቀበሌ ነዋሪዎች ተገነባላቸው፡፡ እነ ኑረዲን ድርጅቱ ስፖንሰርሺፕ እያለ በሚጠራው ፕሮጀክት ታቅፈው የመማሪያ ቁሳቁሶች፣ ዩኒፎርምና የተለያዩ መጻሕፍት እየተሰጣቸው፣ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ቀጠሉ:: ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ኑሮአቸውን ለማሻሻል የሚረዳና የሚያግዙ የተለያዩ ድጋፎች ከድርጅቱ በማግኘታቸው ኑሮአቸው መለወጥ ጀመረ፡፡
“የመማሪያ ቁሳቁሶችን በአግባቡ አግኝቶ ትምህርትን ያለ ሀሳብ መማር ቀላል ነገር ሊመስል ይችል ይሆናል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ለኛ የመማርና ያለመማር እጣ ፈንታችን የሚወሰንበት ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ደብተርና እስክርቢቶ አገኘሽ ማለት ዓመቱን ሙሉ ትምህርትሽን ለመቀጠል የሚያስችል ጉልበት አለሽ ማለት ነው” ሲል ይገልፀዋል፤ ኑረዲን፡፡
ቀድሞውኑ ተምሮ ሰው የመሆንን ታላቅ ራዕይ ሰንቆ ት/ቤት የገባው ኑረዲን፤ አጋርና ደጋፊ ማግኘቱ ይበልጥ አበረታታው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ የስፖንሰርሺፕ ተጠቃሚነቱን ለተረኛ ወገኖቹ ለቆ እሱ ወርልድ ቪዥን በአካባቢያቸው ባስገነባው የወጣቶች ማዕከል ውስጥ እየሰራና ራሱን እየደገፈ መማር ቀጠለ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በጥሩ ውጤት አጠናቆ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ የኑረዲን ሩቅ ህልም እየቀረበች መጣች፡፡ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሶሽዮሎጂና በሶሻል ወርክ የመጀመሪያ ዲግሪውን በ2007 ዓ.ም አገኘ፡፡ ወደ ትውልድ አካባቢው በመመለስ በተማረው ሙያ በክልሉ ጤና ቢሮ ፕላንና ፕሮግራም ክፍል ውስጥ ለሁለት ዓመታት አገልግሎ፣ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመቀጠል ተመልሶ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡ እዚያው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን በሶሻል ዎርክ ሰርቶ ወደ ትውልድ አካባቢው በመመለስ፣ አሁን በሙያው አገሩንና ወገኖቹን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ኑረዲን አሁንም ህልሙን እውን ለማድረግ ሌት ተቀን ይታትራል። በቅርቡም የፒኤችዲ ትምህርቱን ለመጀመር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ነግሮኛል፡፡ “ይህ ድርጅት ባይኖር ኖሮ እኔ ዛሬ የት ነበርኩ” እያለ ደጋግሞ ይጠይቃል፡፡ ይህንኑ በድርጅቱ የተጀመረውን ታላቅ ተግባር ለማስቀጠልና የአካባቢው ነዋሪ ወገኖቹን ኑሮ ለመለወጥ ጠንክሮ እንደሚሰራም ነግሮኛል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ፣ ሸነን ቀበሌ ውስጥ ተገኝቼ የታዘብኩትም ተመሳሳይ ነገር ነው፡፡ የእነ ጽዮን መንደር ከ17 ዓመታት በፊት ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ት/ቤት በአካባቢያቸው ባለመኖሩ ምክንያት ወላጆች ልጆቻቸውን በተለይም ሴት ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት ለመላክ ፈጽሞ አይደፍሩም፡፡ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈርና ልዩ ልዩ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የእነ ጽዮን ቀበሌ ልጆችን ከትምህርት ገበታ አርቋቸው ኖሯል፡፡ ይህ እጣ ፈንታ እንደነ ፅዮን ባሉ ታዳጊዎች ላይ እንዳይደርስ ወርልድ ቪዥን ፕሮግራሙን ይዞ በመኖሪያ ቀበሌያቸው ውስጥ ገባ፡፡ ድርጅቱ በጤና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በምግብ ዋስትና፣ በንፁህ የመጠጥ ውኃና በልጆች ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሰራ ነበር፡፡  
የእነ ጽዮን አካባቢ መነቃቃት ጀመረች:: ት/ቤትና ጤና ጣቢያ ተከፈተላት፡፡ ንጹህ የመጠጥ ውሃም አገኘች፡፡ ውሃ ፍለጋ ለሰዓታት መጓዝ ቀረ፡፡ የተነፈጉትን የትምህርት ዕድል አገኙ:: ጽዮን ወርቅነህ እንደ አካባቢዋ ታዳጊ ሴቶች ያለ ዕድሜ የመዳር ክፉ እጣ ሳይገጥማት በወርልድ ቪዥን በተገነባው ት/ቤት ገባች:: የአካባቢዋ ሰዎች ጽዮንን የሚያበረታቱ አልነበሩም፡፡ “ሴት ልጅ ተምራ የት ልትደርስ ነው! ይህቺን የመሰለች ቆንጆ ልጅ ይልቅ ለአንዱ ባለሀብት ድረው ጎጆ ቢያስይዟት” ይሉ ነበር፤ ጎረቤቶቻቸው:: የጽዮን አባት ግን በውሳኔያቸው ፀኑ፡፡ “ልጄ ተምራ ትልቅ ደረጃ ትደርሳለች እንጂ ለሀብት ብዬ ነገዋን አላጨልምባትም” አሉ:: ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በበኩሉ፤ የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁሶችን እየሰጠና ልዩ ልዩ ድጋፍ እያደረገ፣ ጽዮን በትምህርቷ እንድትበረታ ጉልበት መሆኑን ቀጠለ፡፡ ይህ ሁኔታ የበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችን ልብ አሸነፈ፡፡ ቀስ በቀስም ወላጆች ሴቶች፣ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ጀመሩ፡፡ ትምህርት በእነ ጽዮን መንደር እየተስፋፋ ሄደ፡፡ ጽዮንም ጥርሷን ነክሳ መማሯን ቀጠለች፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጥሩ ውጤት አጠናቅቃ፣ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቷን ለመከታተል አምቦ ዩኒቨርሲቲ ገባች፡፡ ዛሬ ጽዮን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በኢንጅነሪንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሆናለች፡፡ ታናናሽ እህቶቿና የአካባቢው ሴት ልጆች፣ እሷ ያገኘችውን ዕድል አግኝተው፣ በትምህርታቸው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ትመክራለች፡፡ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፤ ለእሷና ለአካባቢዋ ነዋሪዎች ያከናወነውን በጎ ተግባራት ለማወደስና ለማመስገን ያዘጋጀችውንና በአካባቢው ሕጻናት የተዘመረውን መዝሙር በዚሁ የፕሮጀክት ማጠናቀቂያና ማስረከቢያ ፕሮግራም ላይ አቅርባ ነበር፡፡
ይህ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆኑና መሬት ከጨበጡ የልማት ተግባራት መካከል ለማሳየነት የመረጥኩት የሁለት ታዳጊ ወጣቶች እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ በአሶሳ ከተማ ተዘጋጅቶ በነበረው ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ድርጅቱ በአካባቢው ሲያከናውናቸው ለቆየው የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞች ከፍ ያለ ምስጋናቸውን በመግለጽ የልማት ሥራዎቹን የማስቀጠሉን ኃላፊነት የተቀበሉት በክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ  አቶ ቶማስ ጉይ እንደነገሩኝ፤ ድርጅቱ በክልሉ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርናና በአካባቢ ጥበቃ ላይ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ለአቅመ ደካሞች ጉልበት ሆኖ በማበረታታት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አድርጓል፡፡ “ያሉብንን ክፍተቶች በመድፈን፣ ጐደሎአችንን በመሙላት ላደረገልን እገዛና ድጋፍ ሊመሰገን ይገባል” ብለዋል አቶ ቶማስ፡፡
የድርጅቱ የመስክ ፕሮግራምና የስፖንሰርሺፕ ክፍል ዳይሬክተር ወ/ሮ እሌኒ መርጊያ፤ ድርጅቱ በትምህርት፣ በጤና በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በልጆች አስተዳደግና እንክብካቤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላለፉት 15 ዓመታት ላከናወናቸው ተግባራት 19 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመው፤ በአካባቢው የተከናወኑት የልማት ሥራዎችና የተገኘው ውጤት እጅግ የሚያስደስት ነው ብለዋል፡፡
በማህበረሰቡ አመለካከት ላይ ለውጥ ማምጣት ላይ አተኩሮ ሲሰራ የቆየው ወርልድ ቪዥን፤ ዛሬ  የማህበረሰቡ አመለካከት ተለውጦና ከልማት ሥራዎቹ ተጠቃሚ ሆኖ ማየት ትልቅ እርካታን ይሰጠናልም ብለዋል - ዳይሬክተሯ፡፡ ማህበረሰቡ የተጀመረውን የልማት ፕሮግራም ሊያስቀጥል ይችላል የሚል እምነት አለዎት ወይ ለሚለው ጥያቄዬ፤ የወ/ሮ እሌኒ ምላሽ ፈጣን ነበር፡፡ “ሲጀመርም ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሆነው በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ነበር፡፡ ማህበረሰቡ አሁንም ይህንኑ ለማስቀጠል የሚያስችል እውቀትና ችሎታ እንዳለው አምናለሁ” ብለዋል፡፡
ኖኖ ኤሪያ ፕሮግራም በተባለው ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ ሸነን ከተማ ውስጥ ድርጅቱ ላለፉት 17 ዓመታት ሲያከናወናቸው የቆየውን የልማት ሥራዎች ለአካባቢው ማህበረሰብና ለመንግስት አስረክቦ በወጣበት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር ሚስተር ኤድዋርድ ብራውን፤ በአካባቢው በተከናወኑት የልማት ሥራዎች ውስጥ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ አሁን ድርጅቱ ከአካባቢው ለቆ ቢወጣም ማህበረሰቡ የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች በማስቀጠል የድርጅቱን ራእይ እንደሚያሳካ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡ “ዕለቱ ላለፉት 17 ዓመታት በጋራ ለተሰሩት ስራዎች የምንመሰጋገንበትና እንኳን ደስ ያለህ የምንባባልበት ዕለትም ነው” ብለዋል፤ ሚስተር ኤድዋርድ ብራውን፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችም በፕሮግራሙ ላይ የተገኙትን የድርጅቱን ዳይሬክተርና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኤሪያ ፕሮግራሙን ሰራተኞች በማመስገን፤ ድርጅቱ ላለፉት 17 ዓመታት በአካባቢው ባከናወናቸው ሰፊ የልማት ሥራዎችና በተገኘው ውጤት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በ1998 እ.ኤ.አ በልደታ አካባቢ የጀመረውንና ወደ ጉለሌ አካባቢ አስፋፍቶት የነበረውን የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም አጠናቆ ፕሮጀክቱን ለአካባቢው ማህበረሰብ አስረክቦ የወጣበትን ፕሮግራም ባለፈው ሐሙስ በሳሬም ሆቴል አካሂዶ ነበር፡፡

Read 2188 times