Tuesday, 08 October 2019 09:26

በወንጂ ስኳር ፋብሪካ - ከልጅነት እስከ ዕውቀት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

• የፋብሪካውን ሙስናና ዝርፊያ በማጋለጤ ተባረርኩ ይላሉ
        • የ7 ዓመት የፍርድ ቤት ጉዳያቸው በምን ተቋጨ?


           በ1955 ዓ.ም በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ነው የተወለዱት፡፡ በዚሁ ፋብሪካ ውስጥ አድገው፣ በተለያዩ ስራ ሀላፊነቶች ከ40 ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ ትዳር መስርተው የልጅ ልጅ እስከ ማየትም ደርሰዋል፡፡ የፋብሪካው ሰራተኛ የነበሩት አባታቸው በሞት ሲለዩ ነበር በእርሳቸው እግር ተተክተው መስራት የጀመሩት - በ1960 ዎቹ መጨረሻ ግድም፡፡ እንደ ሕይወታቸው ለሚሰስቱለት ፋብሪካ ብዙ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ይናገራሉ - አቶ ግርማ አለሙ፡፡ በስራ ላይ እያሉ ከፋብሪካ ላይ ወድቀው ተገቢውን ሕክምና ባለማግኘታቸው የእግር ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡
ፋብሪካው በሙሰኞች ሲዘረፍ፣ በአላዋቂዎች ሲመራ ዝም ብዬ አልተቀመጥኩም፤ እስከ ስኳር ኮርፖሬሽን የመጨረሻው ሃላፊ ድረስ ተጋፍጬአለሁ፤ ነገር ግን ከ116 ባልደረቦቼ ጋር ከስራ ተባረርኩበት እንጂ አልተመሰገንኩበትም ሲሉ በሃዘን ይገልጻሉ፡፡  ለምን? አቶ ግርማ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ፋብሪካው አሁን ያለበትን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል? ለአራት አስርት ዓመታት በፋብሪካው የነበራቸውን አጠቃላይ ቆይታም ያብራራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአቶ ግርማ አለሙ ጋር ተከታዩን አስደማሚ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡  


             በፋብሪካው  ውስጥ ሥራ የጀመሩት መቼና በምን ሙያ ነበር?
የተለያዩ ሥራዎችን በፋብሪካው ውስጥ ሰርቻለሁ፡፡ በቋሚነት የተቀጠርኩት ግን በ1969 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በጊዜያዊነት ነበር የምሰራው፡፡ ምክንያቱም አባቴ በልጅነቴ ህይወቱ ሲያልፍ እድሜዬ ትንሽ ቢሆንም ቁመቴ ረዘም ያለ ስለነበር፣ እድሜዬን ጨመር አድርጌ በመናገር ተክል ክፍል ውስጥ ሸንኮራ የመትከል ስራ እሰራ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ ዓመታትን አሳልፍኩኝ:: የሚገርምሽ የኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ተገርስሶ ደርግ በገባበት ወቅት በፋብሪካችን ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ ይፈጸም ነበር፡፡
ምን አይነት ዝርፊያ?
ለሰራተኛው የሚከፈለው እያስመሰሉ ገንዘብ በማውጣት ባለስልጣናት ወደ ራሳቸው ኪስ ይከትቱ ነበር፡፡ ይህን ሳልፈራ ፊት ለፊት እናገርና እጋፈጥ ነበር፤ በዚህም የተነሳ ሰራተኛው በሙሉ ‹‹የሰራተኛ ጉዳይ አስፈጻሚ›› ብሎ መረጠኝ፡፡ ያንን የሰራተኛ መብት ጉዳይ እየተሟገትኩ ስሰራ በነበረበት ወቅት ‹‹ኢሰፓ›› ተመሰረተና የኢሰፓ አባል እንድሆን አምስት ጊዜ ደብዳቤ ደረሰኝ:: እኔ ግን አባል መሆን አልፈልግም አልኩኝ:: ‹‹ለምን አባል አትሆንም›› በሚል በወታደር ተከብቤ ኢሰፓ ጽ/ቤት ድረስ ተወሰድኩኝ:: ‹‹ለምንድነው አባል የማትሆነው… ሥርዓቱን አትደግፍም?›› ሲሉኝ፤ ‹‹ስርዓቱን የመደገፍ ያለመደገፍ ጉዳይ አይደለም፤ ነገር ግን አባል መሆን አልፈልግም›› በማለት መለስኩላቸው:: አምስት ቀን ታሰርኩኝ፡፡ በስድስተኛው ቀን ‹‹እንዴት ነው አልተሻለህም?›› ብለው ጠየቁኝ:: ‹‹ይቅርታ አድርጉልኝ፤ እኔ አልታመምኩም›› አልኳቸው፡፡ ለቀቁኝና በነጋታው ወደ ሶማሊያ ጦርነት አዘመቱኝ፡፡
እርስዎን ብቻ ማለት ነው?
ይገርምሻል! ከፋብሪካው 472 ሰው በሕዝብ ተመርጦ ሲወሰድ፣ እኔ ሳልመረጥ ታፍኜ ተወሰድኩና ናዝሬት ታንከኛ የሚባል ማሰልጠኛ አስገቡኝ፡፡ እኔም በወቅቱ አገሬ ስለተወረረች፣ እጅ አንሰጥም ብዬ ከጦሩ ጋር ተዋጋሁ፡፡ በኋላ ከምስራቅ ወደ ሰሜን ዙሩ ተባልንና ወደ ኤርትራ ወሰዱን፡፡ ከዚያ ወደ ሰሜን ሸዋ ደግሞ አመጡን፡፡ እዚያ እየተዋጋን እያለ ክፉኛ ታምሜ ስለነበር ወደ ቤቴ መለሱኝ፡፡ ይሄ የሆነው እንግዲህ በ1979 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ወደ ቤቴ ከተመለስኩ በኋላ ኢሕአዴግ ገባ፡፡ እናም ወደ ስራዬ ተመለስኩኝ፡፡ እዚያው ፋብሪካ ውስጥ ሰራተኛው እንደ ቀድሞው በሠራተኛ ጉዳይ አስፈጻሚነት በድጋሚ መረጠኝ፡፡ አሁንም የሰራተኛውን ብሶት፣ በፋብሪካው ላይ የሚፈፀመውን ደባ ማጋለጤን ተያያዝኩት:: ለምን? የሰራተኛ ማህበሩ  እኔ ላይ እምነት ጥሎብኝ ነው እንድሟገት የመረጠኝ፡፡ ‹‹የሰራተኛ ደሞዝ መጨመር አለበት›› እያልኩ ስሟገት፣ እንደገና ወደ ተክል ክፍል ወሰዱኝ፡፡ ቀድሞ የነበረው በሰራተኛው ስም ባለስልጣናት ገንዘብ የሚወስዱበት አሰራር ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር የጠበቀኝ፡፡ ‹‹ኧረ እባካችሁ በሰራተኛው ስም ገንዘብ እየወጣ፣ አሰራሩ ለሙስናና ለሙሰኞች ተጋልጧል›› በማለት እስከ ፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅና እስከ ፋይናንስ ድረስ ሄድኩኝ፡፡ እነሱ ግን ይህን በማጋለጤ እኔን አፍነው ፅዳትና መዝናኛ ወደሚባለው ፓርክ ወንጂ ወሰዱኝ - ከፋብሪካው ነጥለው፡፡ እዚያ ከወረወሩኝ በኋላ አንዱ ባለሥልጣን መጥቶ ‹‹አቶ ግርማ አሁን ምላስህን ብላ›› አለኝ ‹‹ለምን? ምን ማለት ነው?›› ስለው ‹‹ራስህን አንቀህ ትገድላለህ፤ አትለፍልፍ ዝም በል ስንልህ እምቢ ብለህ ይሄው ለዚህ በቃህ፡፡ ሰራተኛው ላንተ ጮኸልህ? ማንም አልደረሰልህም›› ብሎኝ ሄደ፡፡ እዚያ ፓርክ ውስጥ ትልቅ የዝግባ ዛፍ ስር፣ ቅጠል እንድጠርግ አደረጉኝ፡፡ እኔ ያንን የሚያህል የዛፍ ቅጠል ሙልጭ አድርጌ ጠርጌ ጫፍ ሳደርስ፣ እንደገና ንፋስ ያንን ዛፍ ሲያወዛውዘው መልሶ ቅጠሉ ይረግፍና የጠረግኩትን ቦታ ይሞላዋል:: ስምንቱን ሰዓት ሙሉ ስኳትን እውላለሁ፡፡ በጣም ነበር የተሰቃየሁት፡፡
ከዚያ በኋላ እንዴት ወደ ፋብሪካው ተመለሱ?
የእግዚአብሄር ሥራ መቼም ድንቅ ነው:: ሁሉም ሰው ክፉና ተንኮለኛ አይደለምና በአጋጣሚ አባዲ የሚባል የቦርድ አባል ነበር፡፡ አንድ ጊዜ መጥቶ ሲያነጋግረን፣ በዚያ ተዋውቀን ነበርና እርሱ ጋ ሄጄ አቤት አልኩኝ፤ ምክንያቱም ስቃዩ ፀናብኝ፡፡ አባዲ ሲሰማ በጣም አዘነ፡፡ የፋብሪካውን ም/ስራ አስኪያጅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ፣ እኔን ወደ ፋብሪካ መለሰኝ፡፡ እዚያ ደግሞ ስኳር ተቆጣጣሪ አደረጉኝ፡፡ ያው እኔም አይሰለቸኝ ነገርም አይርቀኝም፡፡ እዚያ ደግሞ መቶ ኩንታል ስኳር ለመጫን ከፍሎ የመጣ ነጋዴ፣ 200 ኩንታል ጭኖ ይሄዳል፡፡ ደረሰኙን ስመለከት የ100 ኩንታል ነው፡፡ የሚጭኑት ግን 200 ኩንታል ነው፡፡ ይህንን አያለሁ አውቃለሁ:: የሚጭነውን መኪና ታርጋ፣ የሾፌሩን መልክ በደንብ አጥንቼ እይዝ ነበር፡፡ ዋናው ስራ አስኪያጅ ጋ ሄጄ ‹‹ኧረ ዘረፋ እየተፈፀመ ነው›› ብዬ ሳመለክት ‹‹አርፈህ አትሰራም ወዮልህ!›› ይለኛል፡፡
ከነጋዴዎች ጋር ይሻረኩ ነበር ማለት ነው?
በሚገባ ይሻረካሉ፡፡ ነጋዴው መቶ ኩንታል ሊጭን እዚያ ከፍሎ ይመጣና ሌላውን ገንዘብ እዚህ ላሉ ባለሥልጣናት ይሰጣል፡፡ እንደነገርኩሽ ሥራ አስኪያጆቹም ‹‹አይመለከትህም አርፈህ ተቀመጥ›› ብለው ማስጠንቀቂያ ሰጡኝ፡፡ እህህ እያልኩ ስብሰለሰል፣ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሳውጠነጥን፣ ለማን አቤት ልበል? ተሳፍሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ልሂድ እያልኩ ስጨነቅ፣ አንድ ቀን አቶ አባይ ፀሐዬ እዚህ ድረስ መጡ፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተሩ ማለት ነው?
አዎ! ሲመጡ እኛ እውነተኛ ሚኒስትር መስለውን፣ የወንጂ ሕዝብ ጠቅላላ ወጥቶ፣ ከአዳራሹ አልፎ ውጭ ሳይቀር ቁጭ ብሏል - ብሶቱን ለመናገር፡፡ ጊዜው በ2004 ዓ.ም ነበር:: ‹‹ለምንድነው ተክሉ በደንብ ያላደገው? ውሃ መስኖው ለምንድነው በደንብ የማይጠጣው? ሸንኮራው ለምን እርዝማኔው ቀነሰ? ለምንስ ስኳር መስጠቱ ቀነሰ? ፋብሪካው ለምን ደከመ?›› እያሉ ብዙ ጥያቄ ሲጠይቁ፤ ሰራተኛው በሙሉ ፈርቶ ዝም አለ፡፡ ‹‹ችግሩን ተናገሩ ዝምታ መልስ አይደለም›› እያሉ ቢጎተጉቱ ሁሉም ፀጥ አለ፡፡ እንግዲህ ሁለት ሞት የለም ብዬ ከሰው መሃል እጄን አወጣሁ፡፡ ወዲያውኑ እጄን ከማውጣቴ ነው ተናገር ያሉኝ፡፡ ምክንያቱም ተናገሩ ብለው ቢጮሁም የሚናገር ጠፍቶ ነበር፡፡
ከዚያስ?
‹‹የተከበሩ ሚኒስትር፤ ስለመጡና ሊያዩን ስለፈቀዱ እናመሰግናለን፡፡ ወንጂ ላይ ሚኒስትር ሲመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ግን እርስዎ እዚህ የመጡት እውን የእኛን ችግር ከልብ ሊሰሙ፣ ብሶታችንን ሊጋሩ ነው ወይስ ለምንድነው እስኪ ይንገሩን›› አልኩኝ፡፡ ሕዝቡ ጭብጨባውን አቀለጠው፡፡ ጭብጨባው አልቆም ሲል፤ አቶ አባይ ፀሐዬ ‹‹በቃ አቁሙ›› አሉ፡፡ ሕዝቡ አላቆም አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹አሁን የተናገርከው ሰው እስኪ እባክህ አንድ ነገር አድርግ፡፡” አሉ - ሚኒስትሩ፡፡ እኔ ተነሳሁና ‹‹በቃ አቁሙ›› ስል ሕዝቡ ወዲያውኑ ጭብጨባውን አቆመና ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ከዚያ በኋላ ምን አሉ አቶ አባይ፤ ‹‹ኢሕአዴግ የሚፈልገው እንደዚህ አይነት ታጋይ ሰው ነው፡፡ ለእውነት በመታገሉ ከሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል፤ ስለዚህ ሀሳቡን ያስረዳን›› አሉ፡፡ እኔም ‹‹ክቡር ሚኒስትር፤ ፋብሪካው ለመድከሙ ምክንያቱ በሀላፊዎች በሰራተኛው ላይ ጫና ይደርሳል፣ ያለአግባብ ገንዘብ ወጪ እየተደረገ ይመዘበራል፣ እኔም እዚሁ ፋብሪካ ስኳር ክፍል ተቆጣጣሪ ነኝ፡፡ በሥራ ወቅት እንዲህ እንዲህ አይነት ችግሮች አሉ›› ብዬ ከላይ ቀደም ብዬ የገለጽኩልሽን አሻጥሮችና ሥርቆቶች ነገርኳቸው፡፡ ‹‹አንድ የፋብሪካ ሀላፊ እዚህ ተመድቦ ገና ሁለት ዓመት ሳይሰራ፣ ናዝሬትና አዲስ አበባ በሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት ይሰራል፡፡ በአንድ ሚ. ብር የቤት መኪና ይገዛል:: እኛና ልጆቻችን ግን በነበርንበት ባለህበት እርገጥ አይነት ኑሮ ላይ ተቸንክረን ቀርተናል፡፡  ይሄ ይሄ ሁሉ ችግር ተደማምሮ ሰራተኛው ተስፋ በመቁረጡ ፋብሪካችን ሊከስር ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከውጭ አገር ግራንድ ማሽኖች ተጭነው ይመጡና እዚህ አገልግሎት ሳይሰጡ ስኳር ሊጭን ለመጣ ባለሀብት ይሸጣሉ፡፡ ሸንኮራ ለመጎተት የተገዙ 20 ትራክተሮች ይመጡና በገቢ መዝገብ ከተመዘገቡ በኋላ ሊታደሱ ነው በሚል ሰበብ 10ሩ ትራክተሮች ተወስደው በዚያው ቀልጠው ይቀራሉ፡፡ ይሄ ሁሉ ችግር አለ፡፡ ይህን ሳልናገር ብሞት ይቆጨኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የመጣውን ሁሉ እቀበላለሁ›› ብዬ ስጨርስ እንደገና ጭብጨባው ቀጠለ፡፡
አቶ አባይ ጸሐዬ ምን ምላሽ ሰጡ?
‹‹ማንም ምንም አያደርግህም አትፍራ›› አሉኝና ጸሐፊያቸውን ‹‹ስልክ ሰጪው›› አሏት:: ስብሰባው ሲጠናቀቅ  ጥቁር ሙሉ ልብስ የለበሱ የእሳቸው አጃቢ ጠሩኝ፡፡ ጸሐፊዋ የቢሮ ስልክና አድራሻውን ሰጠችኝ፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል፣ የፋብሪካውና የሰራተኛው ችግር ይቀረፋል ብዬ ስጠብቅ፣ ይህን በተናገርኩ በ15ኛው ቀን እኔን ጨምሮ 116 ሰዎች ከስራ ተባረርን:: እኔ ስናገር ያጨበጭቡ የነበሩትን ሰራተኞች ነው የፋብሪካው ሥራ አስኪያጆች መርጠው ያባረሩት፡፡
ከስራ ከተባረርን በኋላ በአቶ አባይ ፀሐዬ ጸሐፊ በተነገረኝ አድራሻ መሰረት፤ በጥየቃ አዲስ አበባ ካዛንቺስ ድረስ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር መጣን፡፡ ሌላው ፈርቶ ቀረ፡፡ ልክ አቶ አባይ ቢሮ ስንደርስ ፖሊሶች አነጋገሩኝ፡፡ ከኔ ጋር የነበረው ጓደኛዬ፣ ፖሊሶችን ሲያይ ለካስ ከኋላዬ ተሰውሯል፡፡ ዞር ስል የለም፡፡ እኔን አስገቡኝ፡፡ የእሳቸው ጸሀፊ ቢሮ አደረሱኝ፡፡ እሷ መጥታ ስለነበር አውቃታለሁ፡፡ ተነስታ ወንበር ሰጥታ አስቀመጠችኝ፡፡ ‹‹ትንሽ ይጠብቁ ይመጣሉ›› አለችኝ፡፡ ትንሽ ቆይተው መጡና እኛን አልፈው የሆነ ክፍል ገቡ፡፡ ጸሐፊዋ ገብታ ነገረቻቸው፤ ይግቡ ተባልኩና ገባሁ፡፡ ‹‹አቶ አባይ ጸሐዬ፤ እርስዎ መጥተው ችግር ተናገሩ፤ ይስተካከላል ባሉት መሰረት ሁሉም ዝም ሲል እኔ እውነቱን ተናገርኩ፡፡ ነገር ግን ይሄው ከ116 ሰዎች ጋር ከስራ መባረሬ ተነግሮኝ፣ እዚህ ማስታወቂያ ላይ ስሜን አገኘሁት›› አልኳቸው፡፡ የተለጠፈውን ማስታወቂያ ገንጥዬ ይዤው ነበር፡፡
እሳቸው ከስራ መባረራችሁን ያውቁ ነበር?
አዎ! ‹‹እርስዎ ወደ ሥራዎት ይመለሳሉ፤ እኔ ስልክ ደውዬ እነግራቸዋለሁ፤ ካቆሙበት ቀን ጀምሮ ስራ ላይ እንዳሉ ይቆጠራል፤ እርስዎ በቃ ይሂዱ›› አሉኝ፡፡ ‹‹እኔን ብቻዬን ወደ ሥራ የሚመልሱኝ ከሆነ አልሄድም፤ 116ቱም የሚመለሱ ከሆነ እሰየው፤ ያለበለዚያ አይሆንም›› አልኳቸው፡፡
ምናሉ ታዲያ?
‹‹እርስዎ ስለሌላው ምን አገባዎት›› አሉኝ:: ‹‹ያገባኛል፡፡ የሥራ ባልደረቦቼ ናቸው፤ እኔ ዝም ብል ከስራ ለመባረርና ልጆቻቸውን ለችግር ለማጋለጥ አይበቁም ነበር›› ብዬ ስጮህ፣ ጠረጴዛውን በቡጢ መትተው ተበሳጭተው፣ ቢሯቸው ውስጥ ጥለውኝ ወጡ፡፡ ‹‹9፡00 ሰዓት ተመለስ›› ተባልኩ፡፡ በተባልኩት ሰዓት ስገባ እሳቸው አልገቡም፤ መሸ፡፡ ከዚያ በኋላ አሁን አላስታውስም… ስቴዲየም ፊት ለፊት አልጋ ተያዘልኝ፡፡ ከቢሯቸው በሴት ሾፌር ተወስጄ እዛ ከደረስኩ በኋላ አልጋ ተሰጠኝ፡፡ የወሰደችኝ ሴት ሾፌር ‹‹ማንኛውም አስፈላጊ ነገር ይደረግላቸው፤ በደንብ አስተናግዷቸው›› ብላ ሄደች፡፡ እኔ እሷ ከሄደች በኋላ 1፡00 አካባቢ ሲሆን ፈራሁና ምግብ ሳልበላ፣ ውሃም ሳልጠጣ ቦርሳዬን ከተያዘልኝ ክፍል አወጣሁና ልደታ አካባቢ ሄጄ፣ በራሴ አልጋ ይዤ አደርኩኝ:: ምክንያቱም አይታወቅም፤ አየሽ አንድ ነገር ብሆን ለልጆቼ አጎላለሁ ብዬ ሰጋሁ፡፡ ጠዋት 2፡00 ከመሆኑ በፊት ተመልሼ እዚያ ሆቴል ሄድኩ:: ለካ አስተናጋጆቹ ያልገቡበት ቦታ የለም፤ እኔን ፍለጋ:: ምክንያቱም የወሰደችኝ ሴት አደራ ሰጥታ ነበር የሄደችው፡፡ ከዚያ በ2፡30 መጣችና ወደ አቶ አባይ ፀሀዬ ቢሮ ወሰደችኝ:: እኔ ከደረስኩ በኋላ እሳቸው መጡ፡፡ ልክ ሲያዩኝ ሳያናግሩኝ ተመልሰው ሄዱ፡፡
መጨረሻው ምን ሆነ?
እኔ ወደ ክስ ገባሁ፡፡ ክስ መስርቼ 7 ዓመት ሙሉ ተሟገትኩ፡፡ አንዱ የመሃል ዳኛ ‹‹እርስዎ ሰውዬ ምናለ አርፈው ተቀምጠው ቀሪ ዘመንዎትን ቢገፉ›› ብሎኛል፡፡ ‹‹እዚህ ቦታ የእሳቸውን ስም አትጥራ (የአባይ ጸሐዬን) የከሰስክበትን ጉዳይ ብቻ ተናገር›› እየተባልኩ በማስፈራሪያ ነው ስሟገት የከረምኩት፡፡
እርስዎ የከሰሱት ማንን ነው? ስኳር ኮርፖሬሽንን ነው ወይስ አቶ አባይን?
የከሰስኩትማ ስኳር ኮርፖሬሽንን ነው፣ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑን ጠርቼ የዳይሬክተሩን ስም አለመጥራት አልችልም፡፡ ምክንያቱም ይህን ሁሉ ችግር ያደረሱብን እሳቸው ናቸው፤ ችግሩን ያጋለጥነው ለእርሳቸው ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑማ ስምና ሕንጻ ነው፤ ምንም ሕጋዊ ሰውነት ቢኖረውም፡፡ ከእሱ ቀጥሎ ያለው ዘነበ ይማም የተባለ ሰውም አብሮ በድሎናል፤ በጣም ተሰቃይተናል፡፡
ሰባት ዓመት የፈጀው ሙግት በምን ተቋጨ?
ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትማ ለእኔ ወሰነልኝ፡፡ ነገር ግን አትክልቲ የሚባል አንድ ሥራ አስኪያጅ እዚህ ተመድቦ መጣና ወደ ስራ ሳይመልሰን፣ ፖሊስ አሰረው፡፡ 500 ሺህ ብር ተፈርዶልኝ አፈጻጸም ከፍቼ ነበር፡፡ እሱም ሳይፈጸም ይሄው ለውጡ መጣና ነገሮች ተቀያየሩ፡፡
ከፋብሪካ ወድቀው እንደተጎዱ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስለሱ ይንገሩኝ?
በ2003 ዓ.ም ነው፣ በስራ ላይ ሳለሁ ከፋብሪካ ላይ ወድቄ ነው ጉዳት የደረሰብኝ:: እንደምታይኝ በከዘራ ድጋፍ ነው የምሄደው፤ ብረት ውስጤ አለ፡፡ እዚህ አገር ታክሜ ነበር፤ ብረቱን ለማውጣት ግን ደቡብ አፍሪካ መሄድ እንዳለብኝ የጥቁር አንበሳ ዶክተሮች ጽፈውልኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ ውጭ ሄጄ ሳልታከም ከስራ ተባረርኩ፡፡ ሰባት አመት ስሟገት ከረምኩ:: ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም እንደነገርኩሽ ወስኖልኝ ነበር፤ነገር ግን የሚገባኝን ገና አላገኘሁም፡፡ እኔም የእነዚህን ሰዎች መጨረሻ ሳታሳየኝ አትግደለኝ እያልኩ አለቅስ እፀልይ ነበር፡፡ ይኼው ፈጣሪ በሕይወት እያለሁ ፍርድ ሰጠ፡፡  ነገር ግን አቶ ዘነበ ከእስር ተፈትቶ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሆነ ሲባል በጣም ነው ያዘንነው፡፡ እኛም ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ብዙ ታሪክ ያለውን ወንጂ ሸዋ ስኳርን ፋብሪካን ለምን ካለቻቸው ሰዓት ላይ ብቅ ብለው አይጎበኙም ብለን›› አቤት ልንል ቤተ መንግስት ድረስ ሄደን ነበር፡፡ ጥበቃዎቹ ሊያስገቡን አልቻሉም፤ ነገር ግን አንዲት ሴት ደብዳቤያችንን ተቀብላናለች፡፡
አሁን እርስዎ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?
እኔ ሥራ የለኝም፡፡ እንደዚሁ ያለ ሥራ ከእነ ልጆቼ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ልጄም እዚሁ የማህበር ሾፌር ሆኖ ነበር፡፡ የግርማ ልጅ ነው ስለተባለ እንዳይሰራ ተከልክሎ፣ 3ኛ መንጃ ፈቃድ ይዞ ቁጭ ብሏል፡፡ ስምንት ልጆች፣ ሦስት የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ ያለ ስራ ቁጭ ብያለሁ፡፡
በምን ገቢ ነው የሚተዳደሩት?
ትንሽ ጡረታ አለችኝ፤ በዚያች ነው የምተዳደረው፤ ሌላ ምንም ገቢ የለኝም፡፡ ወጥቼ እንዳልሰራ ከፋብሪካ ውድቄ በደረሰብኝ ጉዳት፣ ብረት በውስጤ ተሸክሜ ነው የምኖረው፡፡
አሁን ፋብሪካው ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?
አሁን በከፋ ጉስቁልና ላይ ነው የሚገኘው:: እኛ በምንሰራበት ዘመን የአፈሩን አይነት፣ የትኛው አፈር የትኛውን የሸንኮራ ተክል ይቀበለዋል የሚለውን ሁሉ አሳምረን እናውቀው ነበር፡፡ አሁን ስራው ላይ ያሉት የአፈሩንም ሆነ የስኳሩን ባህሪ አያውቁትም። ለዚህ ነው ምርታማነት የቀነሰው፡፡ አየሽ እዚህ ወንጂ ላይ ሰባት የአፈር አይነትና 11 ያህል የሸንኮራ ዝርያ አለ፡፡ አሁን አፈሩና የሚስማማው የሸንኮራ አይነት አልተገናኘም፡፡ እኛ ወደዚህ ሥራ ብንመለስ ምን ማድረግ እንዳለብን እናውቃለን:: በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥተው፣ ለደቂቃዎች እንዲጎበኙን መልዕክታችንን ታስተላልፉልን ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Read 6618 times