Saturday, 12 October 2019 12:11

“ላይፍ ኢዝ ላይክ ዛት”… ብሎ ነገር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

     “እናማ…በሁሉ ነገር እያነሳ የሚያፈርጠን በበዛበት በአሁኑ ጊዜ፣ ብቸኛው ትጥቃችን ተስፋና ወድቆ አለመቅረት ነው፡፡ “በህይወቴ ደጋግሜ ወድቄያለሁ፣ ስኬታማ የሆንኩትም ለዚህ ነው” የምንልበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!--”
                
                እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሬስቱራንት ውስጥ ትእዛዛችሁን ልትቀበል የመጣችው አስተናጋጅ ፊት ላይ ያለው መኮሳተር… አለ አይደል… “ራቭ ፎር አለኝ፣” “ጂ ፕላስ ስሪ አለኝ፣” እያለ ካለሳለሳት በኋላ የልቡን ሠርቶ የተሰወረውን ጮሌ ያገኘችው ነው የሚመስለው፡፡ መኮሳተሯ ራሱ ‘አፕታይት’ የሚባለውን ነገር… ምን አለፋችሁ፣ መቆለፍ ሳይሆን ያሽገዋል፡፡ “ምን ልታዘዝ?” የለ፣ ‘ሜኑ’ ማቅረብ ብሎ ነገር የለ፣ ቆማ  በሃያ አምስት ዲግሪ ጎንዮሽ ታያችኋለች፡፡ እናላችሁ… የዘንድሮ ፖለቲካችን አዲስና የአይንስታይንን ብልህነት ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚከት፣ የተባለና ያልተባለ ነገር  አተረጓጎም ባስተማረን መሰረት… ልጅቱ እንደዛ የምታያችሁ ወይ እብሪት የልጆች ፊኛ አሳክሏት ነው፣ ወይም ደግሞ “ጊዜው አልፎበታል ያላችሁትን የበፊት ቦይ ፍሬንዴን መልሼ አምጥቼ ምን እንደምትሆኑ ጉዳችሁን አያለሁ!” እያለች እየፎከረች ነው፡፡ (“መቆየት ደጉ” አይደል የሚባለው… ይኸው ሀገር ፉከራ፣ በፉከራ ሆናለች፡፡)
‘ፈረንጅ’… “ላይፍ ኢዝ ላይክ ዛት” የሚላት ነገር አለችው፡፡
ትራፊኩ የሆነ የደበረው ነገር አለ እንበል… ሚስቱ ማታ ከእራት ያስተረፈችውን ድርቆሽ ፍርፍር ለምሳም አቅርባለታለች፡፡ (ቢያንስ፣ ቢያንስ ምናለ የማታውን ልሙጡን ሳህን በባለ አበባው ብትለውጠው!) ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ የሆነች ሚጢጢ በምትመስል ጥፋት የቅጣት ወረቀታችሁን ያከናንባችኋል፡፡ መአት ልመና ብታቀርቡለት፣ ጉልበት ለመሳም ቢዳዳችሁ “ህግ፣ ህግ ነው” ብሎ ወይ ፍንክች ነው:: አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ…ዩኑፎርም ለብሶ እዛ ስፍራ የተገኘው የትራፊክ ህጉን ሊያስከብር እንጂ የመንግስተ ሰማያት መግቢያ ‘ሲቪ’ውን ለማወፈር አይደለምና!
ሌላ ቀን ደግሞ ማታ ለእራት ጎድን ጥብስ፣ ቀን ለምሳ በቅቤ ያበደ ክትፎ…ምን አለፋችሁ ‘ኤ ኪንግስ ትሪትመንት’ እንዲሉ የቀይ ምንጣፍ አንክብካቤ ያገኛል፡፡ እናላችሁ…‘ሾልካችሁ ለማለፍ ስትሞክሩ ቀይ መብራት ትጥሳላችሁ:: ይሄኔ… ዘጠኝ ወር መኪና መሪ አጠገብ እንዳትቀመጡ የሚያግድ ቅጣት ቢያከናንባችሁ “እንኳንም ቀጣልኝ፡፡ እነሱ እንደፈለጋቸው መንገዱ ላይ ይፈነጫሉና እኛ ሀገር ለቀን መሄድ አለብን እንዴ!” አይነት ሙገሳ ሊቀርብለት ይገባል፡፡
እሱዬው ግን የጎድን ጥብሱ ‘ሜሞሪ’ ሳይጠፋ፣ በቅቤ ያበደ ክትፎውን ልፎ፣ እሱ ‘ደግ’ ያልሆነ ማን ደግ ሊሆን ነው! እናላችሁ…በ“እንዳይለምድህ…” አይነት ገርመም አድርጎ ችላ ሊላችሁ ይችላል፡፡ (ነገርዬው ‘እንደ ምሳሌ’ የቀረበ መሆኑን ‘አብዮታዊ’ ባይሆንም እንኳን ‘የሆናዊ’ ግንዛቤ ውስጥ ይግባልንማ! ልጄ… ዘንድሮ “በሩን ባልቆልፈው፣ ጎረቤት አለ” ብሎ ነገር የለም፡፡ ጮሌ ገብቶ የሆነ ነገር እንዳያነሳ በር እንደሚቆለፍ ሁሉ፣ ‘አክትቪስት’ ወይም ‘ቦተሊከኛ’ ገብቶ “እንደምን አደርክ?” ያላችሁትን “የት እንድምታድር አያለሁ ብሎ እየዛተ ነው” በሚል ሌላ የ“ይለይልን” አጄንዳ እንዳያመጣ እንደ በሩ ሁሉ ነገርንም ‘እየከረቸሙ’ ማለፍ ነው፡፡)
‘ፈረንጅ’… “ላይፍ ኢዝ ላይክ ዛት” የሚላት ነገር አለችው፡፡
እኔ የምለው…የትልቁ ባንክ ሰዎች…እንዳለ አምጥቶ ረብጣውን ‘አፈሰሰባችሁ’ አይደል! የምር እኮ… ‘ግብጦች’ በሳተላይት ምናምን ነገር ቢያዩ ኖሮ “እኚህ ሰዎች አንደኛውን ሙሉ አባይን እዛው አስቀሩት እንዴ!” ባይሉ ነው፡፡ የምር አሁን… “ደሞዝተኛ ነው” ከማለት ይልቅ “ቡቲክ ሳይከፍት አይቀርም” ቢባል ይቀላል:: አትፍረዱብንማ፡፡ ድሮ እኮ “እከሌ በወር አንድ ሺህ ብር ይበላል አሉ” ሲባል…“ይዝቀዋል አትለኝም! ይህን ሁሉ ገንዘብ ምን ሊያደርገው ነው!” ይባል ነበር…ያኔ ሦስት ብር ከሠላሳ አምስት የሙሉ ‘ዴት’ ወጪ ትሸፍን በነበረበት ጊዜ፡፡ ዘንድሮ ግን…አለ አይደል… “ስንት ይከፍሉታል?” ሲባል መልሱ “አንድ ሺህ ብር፣” ይሆን የለ… “ይዝቀዋል አትዪኝም” ብሎ ነገር የለም፡፡ “አፈር በበላሁ፣ እንደው ምኑን ከምኑ ሊያደርገው ነው!” ቢባል ነው፡፡ እናማ…ባንኮች ይመቻችሁማ!
ስሙኝማ…መቼም ጨዋታም አይደል… የመንግስት ሠራተኞች፣ “አፈሰሰባችሁ፣” ነው ‘ፈሰሰባችሁ’ የሚባለው! ልከ ነዋ… በመቶ ምናምን፣ በሁለት መቶ ምናምን ‘ጭማሪ’ አይደለም መካከለኛ ገቢ፣ ‘መካከለኛ ድህነት’ ውስጥ ይደረሳል እንዴ! አሀ… ሲወራ ስለከረመ የሆነ ለ‘ሰበር ዜናነት’ የሚበቃ ነገር ይኖራል ብለን ነበራ! እናንተንም ይመቻችሁማ!
‘ፈረንጅ’… “ላይፍ ኢዝ ላይክ ዛት” የሚላት ነገር አለችው፡፡
በየስፍራው ያሉ ጥበቃዎችን ልብ ብላችሁልኛል…“ለፍተሻው ተባባሩን” የምትለዋ ማሳሰቢያ እንደየ ተርጓሚዋ ልትሆን ትችላለች:: እናላችሁ… አንዳንድ ጊዜ ፍተሻ ብቻ ሳይሆን ‘ትፈተጋላችሁ፡፡ እስካሁን ‘በህይወት የቆየችበት’ ምክንያት የማትታወቀው ‘ድንቡሎ’ ለምን አትሆንም፣ ጎርበጥ ያለች ነገር ሁሉ ትታያለች:: (ድንቡሎ፣ አምስት ሳንቲም ለማለት ነው፡፡ (ልጄ….እንቅልፍ ከማጣት እየከረቸሙ ማለፍ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…)  በአሁኑ ጊዜ አይደለም ወደ ‘ፍተጋ’ የሚጠጋ አፈታተሽ፣ ከዛ የጠነከረ ቢኖርም አይገርምም፡፡ ተወደደም ተጠላም ያለንበት ጊዜ አስቸጋሪና አሳሳቢ ነው፡፡ ፍተሻ ላይ ያሉ ሰዎች ይህን መገንዘብ አለባቸው፡፡
ደግሞላችሁ…ሌላ ጊዜ ትከሻ ቸብ፣ ቸብ ይቀርና ሰተት ብላችሁ ስትገቡ ዘወር ብሎ የሚያያችሁም የለም፡፡ ትናንት ሩሎ የሄደባችሁ እስኪመስላችሁ ድረስ  ትንፋሽ ያሳጠሯችሁ ፈታሾች፤ ዛሬ ምን አግኝተው ነው ‘ቸብ፣ ቸብ’ እንኳን ያላደረጓችሁ! በወጣቶች ቋንቋ ‘አሪፍ ሙድ’ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሥራዎች ‘የሙድ’ ጉዳይ መሆን የለባቸውም፡፡  ለ‘ሙድ ለሙዱ’ ዛሬ “አፈር አይንካችሁ” ብለው መሽቶ ሲነጋ “አፈር ድሜ ብሉ” አይነት ነገር የሚሉን በፖለቲካው ዙሪያ ያሉት ‘ሙደኞች’ ይበቁናል፡፡ “ሀገር እንዲህ መጫወቻ ትሁን!” የሚለውን ነገር ሚኒባስ ታክሲ ላይ ሰማሁት ወይስ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንዱ ‘ዘ አክቲቪስት ቫይረስ’ ሲል የጠቀሰው ‘ባእድ አካል’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ቀብ ሊያደርገኝ ነው!)
‘ፈረንጅ’… “ላይፍ ኢዝ ላይክ ዛት” የሚላት ነገር አለችው፡፡
ስሙኝማ…ሰሞኑን ዩናይትድ ኔሽንስ አወጣ የተባለውን ሪፖርት ሰምታችሁልኛል! እንዲህ ሆነንም ነው የምንተራመሰው! በዚህ ዘመን ስድሳ በመቶ የሚሆነው ህዝባችን ማንበብና መጻፍ አይችልም ሲባል፣ ከዚህ የባሰ የሚያሸማቅቅ ምን አለ! በዚህ መሀል ተማረ፣ ተመራመረ ተብሎ አሁንም ከአስራ ምናምነኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ያልወጣውን ስትጨምሩበት ይታያችሁማ! ‘የዛሬውን አያድርገውና፣’ በመሰረተ ትምህርት እኮ የዩኔስኮን ሽልማት እስከ መውሰድ ደርሰን ነበር!
እናማ... ምን መሰላችሁ፣ ደስ ሲለን ማድረግ፣ ደስ ሳይለን አለማድረግ አይነት ነገር ማናችንንም የትም አያደርስም፡፡ መሠራት ያለበት ስራ በጊዜው እየተሠራ ካልሆነ እንዴት ነው ወደፊት የሚኬደው! ዘንድሮ እየረበሹን ካሉ ነገሮች ዋነኛው፣ ሥራዎች በጊዜያቸው ሳይሠሩ፣ ውሳኔዎች በጊዜያቸው ሳይተላለፉ እየቀሩ ሦስቱ በቀደዱት ሠላሳ ሦስቱ እየገቡ ነው፡፡
ስሙኝማ…መቼም የዘንድሮ እንግልት፣ አንድ እሱው ይመልሰው እንጂ! የአገልግሎት ክፍያ ለመክፈል ለምንድነው በሌሊት ሄደን መሰለፍ የምንገደደው! አሀ…ክፍያ ‘ለሁሉ’ ነው ምናምን ከሚሏቸው የተወሰደው የበለጠ ለማዘመን ተብሎ አልነበረም እንዴ! “ከቤታችሁ ሳትወጡ በሞባይላችሁ፣” መክፈል ትችላላችሁ” ተብለን እኛም “ይበል፣ ይበል!” ብለን አልነበር እንዴ! ጭራሽ የቀድሞዎቹን “በትንሹም፣ በትልቁም ስንረግማችሁ የነበረውን ይቅር በሉን!” ለማለት መገደድ አለብን እንዴ! (እኔ የምለው…ቅሬታ ማቅረብ የሚፈልገው ሰው ሰልፍ…አለ አይደል… ሂሳብ ለመክፈል ከተሰለፈው ጋር ሊስተካከል ሲቃረብ የሆነ የተሳሳተ ነገር አለ ማለት ነው፡፡)
እዚች ላይ እንኳን…“ላይፍ ኢዝ ላይክ ዛት” ለማለት ያስቸግረናል፡፡
ማይክል ጆርዳን፣ አሜሪካ ካፈራቻቸው እጅግ የተዋጣላቸው የቅርጫት ኳስ ኮከቦች ፊት ረድፍ የሚገኝ ነው፡፡ ሀውልት ሁሉ የቆመለት ነው፡፡ ግን ደግሞ ይሄ ሁሉ ስኬት በቀላሉ የመጣ አልነበረም፡፡ “በህይወቴ ደጋግሜ ወድቄያለሁ፣ ስኬታማ የሆንኩትም ለዚህ ነው” ብሎ ነበር፡፡ የሚገርመው ማይክል ጆርዳን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ “ችሎታ የለህም” ተብሎ ከቅርጫት ኳስ ቡድኑ ተቀንሶ ነበር፡፡
እናማ…በሁሉ ነገር እያነሳ የሚያፈርጠን በበዛበት በአሁኑ ጊዜ፣ ብቸኛው ትጥቃችን ተስፋና ወድቆ አለመቅረት ነው፡፡ “በህይወቴ ደጋግሜ ወድቄያለሁ፣ ስኬታማ የሆንኩትም ለዚህ ነው” የምንልበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2344 times