Saturday, 19 October 2019 12:26

“መታዘዝን አታውቅ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


             “እኔ ምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ማዘዝን የመሰለ ነገር እኮ የለም፡፡ ማንም ሰው ማዘዝ ይችላል፡፡ ቀላል ነው፡፡ “ያንን ስቀል…” “ያንን አውርድ…” ይሄንን አንሳ…” ማለት ቀላል ነው፡፡ ለዚህ ነው በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ትእዛዝ የሚሰጥ የበዛብን፡፡ የምር ግን፣ አለ አይደል… የአዛዥ ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ጥሩ አይመጣም፡፡ ሁላችንም ዙፋኑን ብቻ ስናልም ልክ አይመጣም፡፡ ከዙፋኑ ስር የሚኖር ከሌለ፣ ዙፋኑ ላይ ቢኮፈሱ ምን ዋጋ አለው! ቂ…ቂ…ቂ…”
          

                እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… በፊት ጊዜ እኮ ‘ማድሞዜሎች’ ወደ ቤት ትእዛዝ የሚያስተላልፉት ቢሮ ሆነው ነው ይባላል፡፡ ባለ ጉዳይ መምሪያ ሀላፊው ዘንድ ሊገባ ተኮልኩሏል፡፡ ‘ማድሞዜል’ ግን ከዛ የባሰ ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ አለባቸው፡፡  
“ሀሎ!” እሳቸው ከመሥሪያ ቤት ይደውላሉ፡፡
“ሀሎ፣ እመቤቴ፡፡”
“ስሚ፣ ቤቱን ጠርገሻል?”
“አዎ ሁሉንም ክፍሎች ጠርጌያለሁ፡፡”
“ደግሞ መኝታ ቤት ያለው ሽቶ -- ጠረጴዛ ላይ ትንሽ አንኳን አቧራ ላግኝና አንቺን አያድርግኝ!”
“ኸረ እመቤቴ አሳምሬ ነው የወለወልኩት፡፡”
“ደግሞ ምሳ ምን እየሠራሽ ነው?”
“ምንቸት አብሽና  ቆስጣ፣ አበባ ጎመን -- እየሠራሁ ነው፡፡”
“ስሚ ደግሞ በቀደም እንዳደረግሽው ወጡ ላይ ጨው ሞጅሪበትና በውሀ ጥም ጨርሺን…”
እኔ የምለው… በስልክ “ጨው እንዳትሞጅሪበት፣” “ቅቤውን እንዳታሳንሺ፣” የሚሉ ሰዎች፤ ነገርዬውን ያዘምኑልና! ልውውጡ በፌስቡክ ‘ላይቭ ስትሪሚንግ’ ምናምን በሚሉት ይሁና! ማን ‘ሰልጥኖ’ ማን ‘ኋላ ይቀራል!’
“ስሚ እስቲ እየሠራሽ ያለውን ወጥ ፎቶ አንሺና በሜሴጅ ላኪልኝ፡፡”
ትልካለች፡፡ የአይ.ቲ. ዘመኗ ‘ማድሞዜል’ ያዩና ስፒዶሜትራቸው ይዘላል፡፡
“አንቺ ምን አይነት ሥጋ ነው የከተትሽው! ከመቼ ወዲህ ነው ሥጋ እንዲህ ሰማያዊ የሆነው!”
እንዲህም ሊሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው:: 
እኔ ምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ማዘዝን የመሰለ ነገር እኮ የለም፡፡ ማንም ሰው ማዘዝ ይችላል፡፡ ቀላል ነው “ያንን ስቀል…” “ያንን አውርድ…” “ይሄንን አንሳ…” ማለት ቀላል ነው፡፡ ለዚህ ነው በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ትእዛዝ የሚሰጥ የበዛብን፡፡ የምር ግን፣ አለ አይደል… የአዛዥ ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ጥሩ አይመጣም፡፡ ሁላችንም ዙፋኑን ብቻ ስናልም ልክ አይመጣም፡፡ ከዙፋኑ ስር የሚኖር ከሌለ፣ ዙፋኑ ላይ ቢኮፈሱ ምን ዋጋ አለው! ቂ…ቂ…ቂ… (ወዳጆቼ እነ እንትና…አለ አይደል… በሉ ደግሞ ‘ዙፋን’ የምትለዋን ቃል ተርትራችሁ አውጡና “የፊውዳል ፍቅር ስላለቀቀህ ነው በሌዘር ቼይር ዘመን ስለ ዙፋን የምታወራው፣” በሉኝ አሉ፡፡)
እናላችሁ… ማዘዝ ቀላል ነው፡፡ ግን ዘንድሮ ችግራችን ምን መሰላችሁ…ሁላችንም ትከሻችን ላይ አራት ኮከብ ጫንና የሚታዘዝ ጠፋ፡፡ አለ አይደል…የስራ ሃላፊነታችን እንኳን ቢሆን የወደቀውን ራሳችን ከማንሳት ይልቅ ሌላኛውን “ያንን አንሳ…” ማለት የሚቀናን በዝተናል፡፡ ወይ ትእዛዝ መስጠት የሚቻልባቸው ወንበሮች ሁሉ በ‘ሮቴሽን’ ለሁላችን የሚዳረሱበት ‘ሲስተም’ ይዘርጋልን፡፡ ጊዜ በማይሰጠው በሌላው፣ በሌላው ‘ሲስተም’ መዘርጋት ቢያቅተን፣ በዚች አንኳን እንሞክረው አንጂ!  
እነ እንትና…“ለእግሬ ውሀ አሙቂ፣” “ጀርባዬን በቅቤ እሺኝ፣” አይነት ትእዛዝ ጊዜ አልፎበታል አልተባላችሁም እንዴ! አምስት ደቂቃ እንኳን ሮጠው የማያውቁትን፣ ከአክሮባት ያልተናነሰ ትእዛዝ ምን የሚሉት ‘ሲቪላይዜሽን’ ነው! (‘ለተጨማሪ መረጃ’ የምትጫኑትን ‘ሊንክ’ ገና እኔም “ይህንን ተጫን” የሚለኝ ስላላገኘሁ ነው:: …ቂ…ቂ…ቂ…)
ትናንት… እሷዬዋ መሽትሸት አድርጋ ትመጣለች… አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል፡፡ አባወራ ቀደም ብሎ ገብቷል፡፡
“ከሥራ የምትወጪው አስራ አንድ ሰዓት አይደለም እንዴ! እስካሁን የት ነበርሽ?”
(በመሽቆጥቆጥ) “ጓደኛዬ ታማ እሷን ለመጠየቅ ሄጄ ነው”
“አንቺ ሴትዮ ይህን ማምሸት ተዪኝ ብያለሁ::”
“እሺ በቃ፣ ሌላ ጊዜ ቶሎ እመጣለሁ…”
“ስሚ ከዛሬ ጀምሮ ልክ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል እቤት ካልደረሰሽ ይህንን የምትዞሪበትን እግርሽን…” እያለ የወዮልሽ ትዕዛዝ ያስተላልፋል… ያኔም ማዘዝ ቀላል ነበር፡፡ ይህን ያህል የትአዛዝ አክባሪ እጥረትም አልነበረም፡፡ ትእዛዙ ሰናይም ይሁን እኩይ፡፡
ዛሬ…እሷዬዋ መሽትሸት አድርጋ ትመጣለች… ሦስት ሰዓት፡፡  አባወራ ሆዬ፤ በታሪክ አጋጣሚም ይሁን ከኪስ ጋር በተያያዘ ምክንያት ቀደም ብሎ ገብቷል፡፡
“እስካሁን የት አምሽተሸ ነው?”
“ምንድነው የምትጮህብኝ! ሰዓቱ ገና አይደለም እንዴ!”
“ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ነው ገና!”
“እኔ እንደውም ቆዪ ሲሉኝ ነው ያስቀዳሁትን ጥዬ የመጣሁት…”
“እነሱ እነማን ናቸው?”
“ጓደኞቼ ናቸዋ!”
“የትኞቹ ጓደኞችሽ?”
“ለምን አትተወኝም፣ የጓደኞቼን ዝርዝር ለአንተ መስጠት አለብኝ እንዴ!”
“ስሚ፣ ከዛሬ ጀምሮ ልክ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል እቤት ባላገኝሽ…”
“እ!…እቤት ባታገኘኝ ምን ታመጣለህ! ንገረኛ፣ ምን ታመጣለህ!”
ለውጥማ አለ! ዋናው ነገር ትእዛዙ መተላለፉ ነው! ቂ…ቂ…ቂ…
ሰውየው ለጓደኛው… “ሚስቴ የምትስመኝ ገንዘብ ስትፈልግ ብቻ ነው፣” ቢለው ጓደኝየው ምን ቢል ጥሩ ነው… “በቀን ስምንትና ዘጠኝ ጊዜ ትስምሀለች ማለት ነዋ!” ቆይማ… ይሄ እንደ ትርፍ ነው፣ እንደ ኪሳራ የሚታየው፡፡ ለማወቅ ያሀል ነው፡፡
ስሙኝማ…እግረ መንገድ ይቺን እዩልኝማ:: ሥራና ሠራተኛ የሚያገናኙ ሰዎች እንደው አንዳንዴ ትንሽ ሰብአዊነት አይሰማቸውም! ነገራቸው ሁሉ…አለ አይደል…“የትም ፍጪው፣ ገንዘቡን አምጪው፣” ብቻ እየሆነ ነው እኮ!
ደላላው የቤት ሠራተኛ ያመጣል፡፡
“ለመሆኑ ሙያ አላት?”
“ሙያ ብቻ! ማንኛውንም የፈረንጅ ምግብ ስትሠራ የሚስተካከላት የለም፡፡”
በቃ ላዛኛ፣ አሮስቶ ዲቢቴሎ ምናምን ያለሀሳብ ተበላ ማለት ነው፡፡
‘የፈረንጅ ምግብ ስትሠራ የሚስተካከላት የሌላት’ ተብሎ ዝናዋ የተወራላት ልጅ ትገባለች:: በሁለተኛው ቀን…
“ምን፣ ምን አይነት የፈረንጅ ምግብ ትችያለሽ?”
“እናንተ አንዴ ካሳያችሁኝ የሚያቅተኝ የለም::”
ምን! እንዴት ነው ነገሩ…
“እኛም እናሳይሻለን፣ አንቺ ግን ምን፣ ምን ትችያለሽ?”
“ግዴለም እማዬ፣ እናንተ አሳዩኝ እንጂ እኔ በአንድ ጊዜ ነው ለቀም የማደርጋት፡፡”
እና ችግሩ ያለው ልጅቱ ዘንድ አይደለም:: እንደተባለው አንዴ ካሳዩዋት ለቀም ማድረግ ላያቅታት ይችላል፡፡ ችግሩ አምጪዎቹ ላይ ነው…ድለላ የሚሠሩት ለማለት ያህል:: ምናልባት ለእሷ የተነገራት… “አንቺ አንዴ ግቢ አንጂ ሴትየዋ የፈረንጅ ምግብ ሲሠሩ ጎበዝ ስለሆኑ ያስተምሩሻል፣” ተብላ ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩ ያለው ‘ከመረጃ ምንጩ’ ነው፡፡
እናላችሁ… ሀገራችንን እያመሱ ካሉት ነገሮች አንዱ “የፈረንጅ ምግብ ስትሠራ የሚስተካከላት የለም፣” በሚል አይነት በ‘መረጃ’ ስም በሚሰራጩ ነገሮች ነው፡፡፡
ወይም…አለ አይደል… በቃ ማዘዝ የምንወደውን ያሀል መታዘዝን ለምን እንደምንጠላ  የሚያጠና ኮሚቴ ይቋቋምልንማ! ኮሚቴ! እዚህ ላይ ምን ትላላችሁ መሰላችሁ… “መጀመሪያ ጥናቱን የሚያጠኑት ላይ ጥናት የሚያደርግ ቡድን ወይም ሌላ ነገር ያስፈልገናል::” አሪፍ አይደል! “የኮሚቴዎችን መብዛት የሚያጠና ኮሚቴ ይቋቋማል፣” እንደሚሉት የእቃ፣ እቃ ጨዋታ ቢሮክራሲ አይነት መሆኑ ነው፡፡
“መታዘዝን አታውቅ፣ ማዘዝን ማን አስተማራት!” የምትባል ነገር አለች፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2743 times