Saturday, 19 October 2019 12:49

የኢዜማ ጠንከር ያሉ አቋሞች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 በፅንፈኝነት…በአዲስ አበባ…በፌደራሊዝም አወቃቀር ጉዳይ

           በአገሪቱ የፖለቲካ ንፍቀ - ክበብ ላይ በሚከሰቱ ጉልህ ችግሮች ላይ መግለጫ አያወጣም በሚል ሲወቀስ የቆየው የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከሰሞኑ ፅንፈኝነትንና የአዲስ አበባ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በዚህ መግለጫና ኢዜማ በወቅቱ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ስላለው አቋም የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡


        ኢዜማ ቅድሚያ “ለሀገር መረጋጋት” የሚል መርህ ሲያራምድ ነው የቆየው፡፡ መንግስት በሚጠበቀው ልክ ሀገርን እያረጋጋ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ?
መሬት ላይ ባለው ነገር ከመዘንነው፣ ወደ መረጋጋቱ እየቀረብን ነው፡፡ ባለፈው አመት ከነበረው አስጨናቂ ሁኔታ አንፃር ስናየው አሁን የተሻለ ነው፡፡ በለውጡ ማግስት የነበሩ ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ የማህበረሰብ እንግልቶችና ሌሎች አስጨናቂ ሁኔታዎች አሁን እየቀነሱ መጥተዋል ብለን እናምናለን፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ አስጨናቂ የነበረው ሁኔታ ከሲዳማ ክልልነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ግጭት ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ግጭቶች ሲፈጠሩ መንግስት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ በመጀመሩ፣ በየአካባቢው የሚታዩ የማን አለብኝነት ድርጊቶች እየቀነሱ የመጡ ይመስላል፡፡ ግን አሁንም ጨርሶ ጠፍተዋል ማለት አይደለም፡፡ ለምሣሌ መንገድ መዝጋት፣ በማንነት ስብስቦች ዙሪያ የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ጥቃቶች (ለምሣሌ የአፋር) የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ እንደ ሀገር ስንገመግመው፣ ከአስጨናቂ ሁኔታዎች ይልቅ ወደ መረጋጋቱ እያቀረብን መጥተናል ብለን እናምናለን፡፡ እኛም አባሎቻችንን ስናሰለጥን፣ በአመዛኙ ህብረተሰቡን ማረጋጋት ላይ እንዲሠሩ ነው የምንመክረው፡፡
ከሰሞኑ ባወጣችሁት ጠንከር ያለ መግለጫ “ስልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የጽንፈኞች መፈልፈያ እንዳይሆኑ እንሰጋለን” ብላችኋል፡፡ ተቃዋሚዎችስ?
ጽንፈኝነት እርስ በእራሱ የሚመጋገብ ነው፤ አንዱ ባከረረ ቁጥር ሌላውም አብሮ የሚያከርበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አሁን በሁለቱም ወገን ጽንፈኝነት በእኩል ደረጃ እየተነቀነቀ ነው፡፡ እርስ በእርስ እየተመጋገቡ ነው ነገሮችን እየጋጋሉ ያሉት፡፡ በጽንፈኞቹ ውስጥ የሚታዩት ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ በአንድ በኩል “አሁን የኔ ተራ ነው፤ ያለውን ስልጣንና ከስልጣን የሚገኘውን ትርፍ በሙሉ ሰብስቤ ካልወሰድኩ” የሚል ሩጫ አለ፡፡ በሌላኛው ወገን ደግሞ አሁን የተከፈተውን ትንሽ የዲሞክራሲ በር በማየት፣ “የመንግስት አቅም የተዳከመ ሆኗል፤ ያችን ክፍተት ተጠቅሜ ስልጣን ላጋብስ፣ ጉልበት ልሰብስብ” የሚል ሃይል ደግሞ አለ፡፡ እነዚህ ጽንፈኞች አላማቸው ይሳካ ዘንድ ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋ ነው የሚሠሩት፡፡ ምክንያቱም ማህበረሰቡ ከተረጋጋ መሹለኪያ ቀዳዳ አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ መረጋጋትን አይፈልጉም፡፡ እነዚህ ሀይሎች በሰሜንም በደቡብም… በሁሉም አካባቢዎች አሉ፡፡ ምን ያህል ተደራጅተዋል የሚለው እንግዲህ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ግን ያለው እውነታ - ጽንፈኝነት በሁለቱም ወገኖች ውስጥ እየተንፀባረቀ መሆኑ ነው፡፡
በመግለጫችሁ ያነሳችሁት ሌላው ጉዳይ ከአዲስ አበባ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ “የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ትንኮሳዎች ሲፈፀሙ ቆይተዋል” ብላችኋል፡፡ ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት ትንኮሳዎች ናቸው?
በጣም ግልጽ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሣሌ “የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የለውም” ተብሎ በይፋ በሚዲያ የተገለፀበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ፓርቲዎች ተሰብስበው “አዲስ አበባ የኛ ብቻ ናት” የሚል መግለጫ ሁሉ ሰጥተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ግን የአዲስ አበባ ህዝብ ነጥሎ አንድን ማንነት “ይሄ የአዲስ አበባ ማንነት አይደለም” አላለም:: ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ሲመጡም በትዕግስትና በሆደ ሰፊነት ነው ሲያሳልፍ የቆየው፡፡ አሁን እየገፋ እየገፋ ሄዶ “እዚህ ቦታ ላይ ያሸነፉንን አሸንፈን፣ የሰበሩንን ሰብረን…” የሚል አይነት ትርክት ነው የተፈጠረው፡፡ ይሄ ሁኔታ በጣም ችግር እንዳለው ነው የምናስበው፡፡ በሌላ በኩል “አዲስ አበባ በረራ ትባል ነበር፤ የኛ ናት” የሚል ስሜት የሚያንፀባርቅ ሌላ ሃይል ደግሞ አለ:: ይሄም ትንኮሳ ነው፡፡ እኛ በመሠረታዊነት የምናምነው፤ ሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ራሳቸው በመረጡት ሰው ነው መተዳደር ያለባቸው በሚል ነው፡፡ ይሄ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሊሠራ ይገባል የሚል እምነት አለን:: ይሄን ስንል አንዳንዶች “እናንተ ለአሃዳውያን የምትቆሙ ናችሁ” ይላሉ፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ እኛ የምንከተለው ፌደራሊዝም አሁን ካለውም በበለጠ ያልተማከለ አስተዳደርን በሠፊው የሚዘረጋ ነው፡፡ አሁን በገዥው ፓርቲ ነው ለከተሞች እንኳ ከንቲባ እየተሾመ ያለው:: እኛ በምናስበው መዋቅር ግን ይሄ በፍፁም አይኖርም፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ ዜጐች በመረጡት ብቻ ራሳቸውን በራሳቸው የሚተዳደሩበትን ያልተማከለ ስርአት ነው እንዲዘረጋ የምንፈልገው፡፡ ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዞ ግልጽ አቋማችን፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ተፈጥሯዊ መብት አለው፡፡ ከዚያ የወረደ ነገር የአዲስ አበባ ህዝብ አይቀበልም፡፡ እኛም አንቀበልም፡፡ ይሄን መብቱን ለማስከበር እንታገላለን፡፡ በ23 የምርጫ ወረዳዎች መዋቅር ዘርግተን፣ ለዚህም እየታገልን ነው፡፡
በህገ መንግስቱ የተቀመጠው “የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ጉዳይ”ን በተመለከተ “አዜማ” ምን ይላል?
በዚህ ሀገር ፖለቲካ ውስጥ አንደኛው ልንቀይረው የምንፈልገው ነገር፣ የዘውግ ፖለቲካን ብቻ መሠረት አድርጐ፣ የተዋቀረ የፌደራሊዝም አወቃቀርን ነው፡፡ ፖለቲካውን እንዳለ የተቆጣጠረውም ከዘውግ ማንነት ጋር የተገናኘ አመለካከት ነው፡፡ ይሄ ምን ፈጥሯል ከተባለ፣ ሰዎች ሌላ አይነት ማንነት እንደሌላቸው ተደርጐ፣ ሁሉም ነገር በዘር ውስጥ የታጠረ ሆኗል፡፡ ለዚህ አመለካከት መለወጥ በቅድሚያ እንሠራለን፡፡ ከዚህ አኳያ የልዩ ጥቅም ጉዳይን በተመለከተ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ ገበሬዎች፣ አዲስ አበባ አጠገብ በመኖራቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ጫና ካለ፣ ለዚያ ጫና ተገቢና ተመጣጣኝ ካሣ ሊሠጣቸው ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡ አዲስ አበባ ሠፍታ የምታድግ ከሆነ፣ በሌላ ወገናችን ጉዳት ላይ ተመስርቶ መሆን የለበትም፡፡ አዲስ አበባ ከአካባቢዋ ነዋሪዎች ጋር ያላት መስተጋብር፣ በጋራ ጥቅም ላይ የተሠመረተ መሆን እንዳለበት እናምናለን፡፡ ባለፉት አመታት፣ እነዚህ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች በማይረባ ካሣ ከቦታቸው ተፈናቅለው፣ ህይወትን በማይለውጥ ገቢ ውስጥ እንዲዋዥቁ ነው የተደረገው፡፡ ይሄ ዓይነቱ አሠራር በመሠረታዊነት መቀየር እንዳለበት እናምናለን፡፡
እነዚህ ሰዎች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ማግኘት አለባቸው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን አዲስ አበባ ውስጥ እየሠራ፣ ግብር ለከተማዋ እየገበረ የሚኖር ሰው እያለ፣ ሌላ ሰው ከሌላ ቦታ መጥቶ “እዚህ ቦታ ላይ ልዩ ጥቅም ይገባኛል” በሚል የሚጠይቀው ጥያቄ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ልዩ ጥቅምን በተመለከተ ያለን አመለካከት ይሄ ነው፡፡
አዜማ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራውን  “ባልደራስ” በተመለከተ አቋሙ ምንድን ነው?
የባለአደራ ምክር ቤት የሚባለውን በተመለከተ መጀመሪያ አካባቢ “የህዝብ ተወካዮች ነን” በማለት ነበር ራሳቸውን የሚገልፁት፡፡ በኋላ ደግሞ “የማህበራዊ ንቅናቄ ነገር ነው የምንመራው፣ የአዲስ አበባ ህዝብ በራሱ የሚተዳደርበትን እድል እንዲያገኝ ማንቃትና ማደራጀት ላይ ነው የምንሠራው” ብለዋል፡፡ እዚያ አስተሳሰብ ላይ እስካቆሙ ድረስ እኛ ምንም ልዩነት የለንም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው፤ እኛም በዚህ ላይ እንሠራለን፡፡ እነሱም ለዚህ የሚሠሩ ከሆነ ከአስተሳሰቡ ጋር ምንም ችግር የለብንም፡፡ ነገር ግን እነሱ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ናቸው፡፡ እኛ መንግስት ለመሆን የምንወዳደር ፓርቲ ነን፡፡
እኛ ለውጡን ቀስ ብለን ይዘን ወደ ሽግግር ማድረስ አለብን፤ የከረረ ፉክክር ውስጥ መግባት አያስፈልገንም ብለን ነው የምናስበው:: ከሁሉም ሃይሎች ጋር እየተናበብን መስራት አለብን የሚል እምነት አለን፡፡ ባልደራሱ ግን ከዚህ ትንሽ የተለየ አካሄድ የመረጠ ይመስላል፡፡ ልዩነታችን እዚያ ላይ ነው፡፡
በእናንተ የፌደራሊዝም እሣቤ መዲናዋ ምን ቦታ ይኖራታል? ምን አይነት ከተማ ነው እንድትሆን የሚፈለገው?
አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከተሞች እንዴት ይተዳደሩ የሚለውን የሚተነትን የፖሊሲ አማራጭ ይኖረናል፡፡ እስካሁን የለየናቸው ችግሮች አሉ፡፡ ለምሣሌ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ብቸኛ ትልቅ ከተማ መሆኗ የፈጠራቸውን ችግሮች ለይተናል፡፡ ምን ያህል የፖለቲካ ጭቅጭቁም መንስኤ እንደሆነ፣ የሌሎች ከተሞችን የማደግ እድልም ምን ያህል እንደዘጋ፣ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተው ስርአት በፈጠረው ችግር ምክንያት ዜጐች ትንሽ ደህንነት ይሠማናል በሚሏት አዲስ አበባ ብቻ በመከማቸት እንደተቸገሩ ለማየት ችለናል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ምን መፍትሔ ያስፈልጋል የሚለው ባለሙያዎቻችን ዝርዝር ሰነድ እያዘጋጁበት ያለ አጀንዳ ነው፡፡ መፍትሔ ተብለው ከተመለከትናቸው መካከል፡- ሌሎች ከተሞችን መንግስት ሆን ብሎ የማስፋትና የማሳደግ እንዲሁም ሌሎች በአዲስ አበባ ደረጃ ያሉ አማራጭ ከተሞችን የማልማት ስራ መስራት የሚለው… በከተማ ልማት ፖሊሲያችን የተቀመጠ ነው፡፡ ለምሣሌ አዲስ አበባ የመንግስት መቀመጫ ስትሆን ሌሎች ደግሞ የንግድና ቢዝነስ፤ የትምህርት፣ የኢንዱስትሪ ከተሞች እንዲሆኑ ሆን ብሎ በመስራት፣ የአዲስ አበባን የትኩረት ደረጃ መቀነስ ይቻላል፡፡ በዚህ መሰረት አጨቃጫቂነቷም አጓጊነቷም እየቀነሰ ይሄዳል የሚል እምነት አለን፡፡ አዲስ አበባ በፌደራሊዝም መዋቅር ምን ቦታ ይኖራታል ከተባለ፣ እኛ አሁን ያለው አጠቃላይ የፌደራል አወቃቀር መከለስ አለበት ብለን እናምናለን:: ሲከለስ እንዳሁኑ የዘውግ ማንነት ላይ ብቻ ተመስርቶ ሳይሆን ከዚያ ባለፈ የዜጐች አሠፋፈርን፣ ስነልቦናን…እንዲሁም ለማልማትና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ምቹ በሆነ ሁኔታ መዋቅር አለበት የሚል እምነት አለን:: አዲስ አበባም በዚያ ጥናት መሠረት ተመልሳ የምትዋቀር ይሆናል ማለት ነው፡፡
የዘር ፖለቲካን ማቆም የሚቻለው “ፖለቲካችንን በማዘመን ነው” የሚል እምነት እንዳላችሁ በመግለጫችሁ ተወስቷል፡፡ ከዘር ፖለቲካውና እናንተ “የዘመነ ፖለቲካ” ከምትሉት የበለጠ ሃይል ያለው የትኛው ነው?
እኛ አሁን የፌደራል መንግስቱን በተቆጣጠረው አካል ላይ ሙሉ እምነት አለን - ወደምንፈልገው አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሄድ እንደሚፈልግ እናውቃለን፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከሠፈነ በኋላ ያለው ነገር የህዝብ ምርጫ ነው የሚሆነው፡፡ በምርጫው ህዝቡ ዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ አይጠቅመኝም ካለ ችግር የለብንም፡፡ የህዝቡን ምርጫ እናከብራለን፡፡ ማዘመን የምንለውም ይሄንን ነው፡፡ አሁን የሀገሪቱ ሁኔታ ሲታይ አስጨናቂም ተስፋ ሰጪም ነገር ይታያል፡፡ እኛ ተስፋ ሰጪው ሁኔታ አብቦ መልካም ውጤት ላይ እንድንደርስ ነው የምንሠራው፡፡ አሁን ባለው ግምገማ ግን በእርግጠኝነት ወደየትኛው ሚዛን እንደሚደፋ የለየለት ነገር የለም፡፡ ወደ ዘመነ ፖለቲካ ልንሄድ እንደምንችልም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም፡፡
እንዴት ነው የዜግነት ፖለቲካን ማስፈን የሚቻለው ትላላችሁ?
አሁን ባለው ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ በፍፁም አይቻልም፡፡ እኛም በሂደት ይሄን ተገንዝበነዋል፡፡ ለምሣሌ ህወኃት የሚመራው መንግስት ስልጣን ላይ እያለ ትልቁ ትግልና ዓላማ የነበረው ህወኃትንና አመራሩን ማስወገድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ይሆናል የሚለው ነገር አስቸጋሪ ሆኖ አይታይም፡፡ ትልቁ እንቅፋት ሆኖ ይታይ የነበረው ስርአቱ ነው:: እሱን ማስወገድ ከተቻለ በኋላ ደግሞ ትልቁ ፈተና የሚሆነው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ተወዳድረን አሸንፈን ደግሞ እንዴት ነው ያልናቸውን ነገሮች ተግባራዊ የምናደርገው የሚለው ሌላ ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ማህበረሰቡ ውስጥ በሠፊው የሠረፀው አስተሳሰብ ዘውገኝነቱ ይመስላል:: ለረጅም ጊዜ በትምህርት ቤት …በሚዲያ… እንዲሁም የመንግስት ተቋማትን በመጠቀም… የዘውግ አስተሳሰብ ስር እንዲሠድ ተሰርቷል፡፡ ስለዚህ ይሄን ለመቀየር ብዙ ስራ ይጠይቃል:: ነገር ግን ዲሞክራሲን ባሠፈንን መጠን ነው ወደዜግነት ፖለቲካ መሄድ የሚቻለው፡፡


Read 1851 times