Saturday, 02 November 2019 12:21

ለ3ኛው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት የመጨረሻ እጩዎች ታውቀዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     • በሁለት ስፖርቶችና በ6 የተለያዩ ዘርፎች አሸናፊዎች ይመረጣሉ
          • የመጨረሻዎቹን እጩዎች ለመለየት ከህዝብ ከ17ሺ 800 በላይ ድምፅ ተሰብስቧል
          • በእግር ኳስና በአትሌቲክስ የዓመቱ ምርጦች እያንዳንዳቸው 75ሺ ብር ከዋንጫ እና ምስክር ወረቀት ጋር ይበረከትላቸዋል


        ሦስተኛውን  የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ለማሸነፍ የሚወዳደሩ የመጨረሻ ዕጩዎች በሳምንቱ  አጋማሽ ላይ በኢቢሲ በተሰጠ መግለጫ ታውቀዋል፡፡  ዓመታዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን  ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ በ6 የሽልማት ዘርፎች የሚካሄድ ይሆናል:: ባለፈው ዓመት የነበሩት አምስቱ  ዘርፎች በሁለቱም ፆታዎች በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ የሚመረጡ 4 የዓመቱ ኮከቦች እንዲሁም የህይወት ዘመን ሽልማቶች የሚሰጥባቸው ሲሆኑ ዘንድሮ ለመጀመርያ ግዜ በእግር ኳስ ስፖርታዊ ጨዋነት የተመረጠ አሸናፊ የሚሸለም ይሆናል፡፡
ዘንድሮ የሽልማት ስነስርዓቱ በስካይ ላይት ሆቴል ዕለተ ቅዳሜ ጥቅምት 29 ላይ እንደሚካሄድ የተገለፀ ሲሆን፤ እስከ 500 ታዳሚዎች በተገኙበት በድምቀት እንደሚከናወን በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ እና በኦንላይን ስትሪሚንግ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝም ታውቋል፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ አዘጋጆች እንዳስታወቁት ዘንድሮ በእያንዳቸው 4 የሽልማት ዘርፎች ቀርበው ከነበሩት እጩ ተፎካካሪዎች መሐል የመጨረሻውን እጩዎች ለመለየት በተለያየ የድምፅ አሰጣጥ ስርዓት ላይ 17872 ስፖርት አፍቃሪዎች ተሳትፈዋል:: ባለፈው ዓመት የተሳታፊዎቹ ቁጥር ከ20ሺ በላይ ነበር፡፡ በእግር ኳስ  እና በአትሌቲክስ በሁለቱም ፆታዎች በአራት የሽልማት ዘርፎች ለሚያሸንፉት እያንዳንዳቸው ብር 75,000.00 /ሰባ አምስት ሺህ/፣ ዋንጫ እና የምስክር ወረቀት፤ ለህይወት ዘመን ተሻለሚ የ50ሺ ብር ሽልማት እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ  በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተዘጋጀው መግለጫ ላይ በ4 የሽልማት ዘርፎች ለመጨረሻው ዙር ፉክክር ያለፉ ሶስት እጩዎች ተለይተው ታውቀዋል። በምርጥ አትሌት ዘርፍ በወንዶች የመጨረሻ 3 እጩዎች ሆነው የቀረቡት አትሌቶች  ሞሰነት ገረመው፣ ሰለሞን ባረጋ እና ጌትነት ዋለ ሲሆኑ በሴቶች ደግሞ ለተሰንበት ግደይ፣ ፋንቱ ወርቁ እና መቅደስ አበበ ናቸው፡፡ በምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ዘርፍ የመጨረሻዎቹ 3 ዕጩዎች በወንዶች አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና የሬድ ባየህ እንዲሁም በሴቶች ሴናፍ ዋቁማ፣ እመቤት አዲሱ እና ሰናይት ቦጋለ ሆነዋል፡፡ በተጨማሪም የሽልማት ስነስርዓቱ በሚካሄድበት ቀን የህይወት ዘመን ተሻለሚ እና በእግር ኳስ የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ የሚታወቁ ይሆናል፡፡
የመጨረሻ እጩዎቹ ከመታወቃቸው በፊት በተከናወነው የምርጫ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና የነበረው 8 አባላት የሚገኙበት ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው ከእግር ኳስ እና አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች የስፖርት ባለሙያዎች፤ የስፖርት ምሁራንና የስፖርት ጋዜጠኞች በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡ በመጀመርያ በዚሁ ኮሚቴ አማካኝነት በእግር ኳስና በአትሌቲክስ በሁለቱም ጾታዎች በእያንዳንዳቸው 4 የሽልማት ዘርፎች አስር እጩ ተፎካካሪዎች አቅርበዋል፡፡ ከቀረቡት እጩ ተፎካካሪዎች መካከል የመጨረሻዎቹን እጩዎች ለመለየት  በተለያዩ ድምጽ አሰጣጥ ስርዓት አድማጭ ተመልካች፣ የስፖርት ቤተሰቡና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡  ከአጠቃላይ ነጥብ የስፖርት ቤተሰብና የባለሙያዎች 75/ሰባ አምስት/ በመቶ ሲሆን የአድማጭ ተመልካች 25  /ሰላሳ/ በመቶ ክብደት ይኖራቸዋል፡። ለድምጽ አሰጣጥ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ሲኤምሲ በኢቢሲ ማህበራዊ ትስስር/ ፌስቡክ፣ ዩቱብ፣…/ እና ድረ ገጽ ለዕጩዎች በሚሰጥ መለያ ኮድ ማንኛውም ሰው ለመረጠው ስፖርተኛ ድምጹን ሊሰጥ ችሏል፡፡
እጩ ተፎካካሪዎችን ለመምረጥ እና ወደ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ደረጃ ለማድረስ ቴክኒኒክ ኮሚቴው በ2011 ዓ.ም የተካሄዱ አገር አቀፍ እና አህጉራዊ ውድድሮች እና ስፖርተኞች ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች ከግምት ያስገቡ ሲሆን በአትሌቲክስ ደግሞ በዶሃ ኳታር የተካሄደውን 17ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከግምት ውስጥ አስገብተዋል፡፡   
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሸራተን አዲስ የተካሄደው የሽልማት ስነስርዓቱ ዘንድሮ የሚከናወነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስካይ ላይት ሆቴል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ አዘጋጆቹ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት የሽልማት ስነስርዓቱ በየዓመቱ አዳዲስ የሽልማት ዘርፎችን እየጨመረ፤ የምርጫ መስፈርቶቹን እያሻሸለ፤ በአጠቃላይ ደረጃውን እያሳደገ የሚሄድ ሲሆን ዘንድሮ የስፖንሰሮችንም ትኩረት ማግኘቱም ይህንኑ እድገት የሚያቀላጥፍ ነው:: በዚህ መሰረት ሶስተኛው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት  4 ስፖንሰሮችን ያገኘ ሲሆን እነሱም ስካይ ላይት ሆቴል፤ ብርሃን ባንክ፤ ማያ ፈርኒቸር እና ኤሰርቤ ሪልስቴት ናቸው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት የመጀመርያው የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት ሲካሄድ ሙሉ ወጭውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በመሸፈን ሲሆን በሁለተኛው ደግሞ በአንድ ብቸኛ ስፖንሰር ዝግጅቱን ለማካሄድ ተችሎ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን ከአፍሪካ ቀዳሚ የሚሆንበት መሰረት ከ84 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረ እና ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በቅኝ አገዛዝ ስር በነበሩበት ዘመን የተጀመረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ በይፋ አገልግሎት መስጠት የጀመረው መስከረም 2 1928 ዓ.ም ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደግሞ ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት /EBC SPORT AWARD/ በ2009 ዓ.ም በሁለት የስፖርት ዓይነቶች በአራት ዘርፎች በድምቀት የተጀመረ ሲሆን ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ ሲካሄድ በ6 የሽልማት ዘርፎች አሸናፊዎቹን ለመሸለም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በየዓመቱ የስፖርት ሽልማት የሚያዘጋጅበትን ዓላማ ሲያመለክት በስፖርተኞች ጠንካራ የፉክክር ስሜት በመፍጠር የአገራችንን ስፖርተኞች በአለም አቀፍ መድረክ ውጤታማነት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው፡፡ በተጨማሪም የስፖርት ቤተሰቡ ለአገር ውስጥ ስፖርትና ስፖርተኞች ያለው ተሳትፎ ለማሳደግም ያቅዳል፡፡ በኢቢሲ የስፖርት ሽልማት በ2009 ዓ.ም ላይ አሸናፊዎች የነበሩት በአትሌቲክስ ዘርፍ በወንዶች ሙክታር ኢድሪስ እና በሴቶች አልማዝ አያና በእግር ኳስ ደግሞ በወንዶች አስቻለው ታመነ እና በሴቶች ሎዛ አበራ ነበሩ፡፡ በ2010 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት በምርጥ አትሌት ዘርፍ በወንዶች ሰለሞን ባረጋ በሴቶች ገንዘቤ ዲባባ፤ በምርጥ እግር ኳስ ተጨዋች ዘርፍ በሴቶች አብዱልከሪም መሃመድ እና በሴቶች ሰናይት ቦጋለ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ የህይወት ዘመን ተሸላሚ የነበሩት ደግሞ የአትሌቲክሱ አንጋፋ አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ ነበሩ፡፡

Read 935 times