Saturday, 02 November 2019 12:28

ገፍቶ፣ ገሸሽ…‘የፖለቲካችን ዲ.ኤን.ኤ.’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ….እንግዲህ ጨዋታም አይደል፡፡ አሁን፣ አሁን  ጊዜ ከራስ ጋር አሸናፊ የሌለበት ግብግብ ይገጥማል፡፡ ለማን? እንዴት? በምን ምክንያት? ምን ለማግኘት? ምን ለማትረፍ? አይነት ጥያቄዎች ይደረደራሉ…ሰሞኑንና ደጋግሞ  በሀገራችን እንደገጠመን፡፡
አስቸጋሪ ነው ይህ አይነት ጣጣ፣
ነገሩስ በእኔ ድንገት ቢመጣ
ሁሉ እየሳቀ እጆቹን ሊያወጣ
…ተብሎ ተዚሟል፡፡ ‘ነገሩ ድንገት ሲመጣ’ እጃቸውን የሚያወጡ ሰዎች ሀገሪቱን እየሞሏት ነው፡፡
የምር እኮ….እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በበፊት ጊዜ የሆነ ልጅ “ሂድና እንትናን በደንብ አድርገህ እርገጠው፣” ይባላል፡፡
“ታላቅ ወንድሙ ቢመጣስ?”
“አይዞህ፣ እኔ እዚህ ሆኜ እጠብቅሀለሁ፡፡”
እናላችሁ… አይዞህ የተባለው ሰው ይሄድና መቧቀስ ሲጀምር፣ የዛኛው ታላቅ ወንድም ብቅ ይልላችኋል! ልጅየውም ‘መመከያ’ ከጀርባ ስላስቀመጠ “አግዝልኝ፣” ለማለት ዘወር ሲል ወላ ሰው የለ፣ ወላ ወፍ የለ፣ ባዶ! እንዲህ ነው የእኛ ነገር…አይዞህ ብለን የባሰው ሲመጣ ገፍተን ወደ ጉድጓችን መግባት፡፡
“የሆነ የማይረሳ ወይም አጨቃጫቂ ነገር በመፍጠር አንተ ላይ ትኩረት እንዲደረግ አድርግ፡፡ የሆነ ትርምስ ፍጠር፣” ወይም… የወጣቶቹን አነጋገር ለመጠቀም… ‹‹ቀውጠው፣” አይነት ምክር ይመክራል፡፡ ለትርምሱ አሳማኝም ሆነ የማያሳምን ምክንያት አያስፈልገውም፡፡ ለምን ብሎ! ዓላማው ሀሳብን የተመረኮዘ አይደለማ! አላማው፣ ከመዝገበ ቃላት እየወጣች የምትመስል አነጋጋርን ለመጠቀም -  ‘አንድና አንድ’ ብቻ ነው፡፡ “ጨፍኑ፣ ላሞኛችሁ፣” የሚል ‘ላይትዌይት’ ፖለቲከኛ  ካልሞገተን በስተቀር ይቺን ዘዴ እየተጠቀሙባት ያሉት ብዙዎች ናቸው…አውቀውት ይሁን ሳያውቁት፡፡ በምንም ሁኔታ ከእይታ መጥፋት የማይፈልጉ፣ ከሚዲያ መጥፋት የማይሹ፣ ከሚዲያ መጥፋትን ‘ራስን እንደ ማጥፋት’ ከማየት የማይመለሱ ሰዎች በዝተዋል…የምር! ኧረ ባካችሁ ትንሽ ትንፋሽ ስጡን!
እኔ የምለው…‘ሂሮ’ በዛብን እኮ!:: ጌሾ ሳይወቅጥ “ከጠላው አካፍሉኝ” የሚል በዛብንሳ! ተዉ እንጂ…እይታችን በአሉታዊውም ይሁን በአዎንታዊ መልኩ “ትናንት” የምንለው እኮ ሁለት እንቁጣጣሽ እንኳን አልደፈነም፡፡ ‘ቆዳ ግልበጣው’ በጣም፣ እጅግ በጣም ፈጠነብንሳ! እንዴ ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ፣’ ቅብጥርስዮ ምናምን ብሎ ነገር እንኳን በሌለበት! እንደ ዳሌና ‘ብሬስት’ ‘አርቲፊሻል ቁመት’ የሚሉት ነገር በሌለበት፣ “የእኔማ ዘንካታ፣ የእኔማ መለሎ ብላችሁ ዝፈኑልኝ!” አይነት ነገር…አለ አይደል… “የቅሽምናዎች ሁሉ እናት፣” ነው፡፡ የእኛ ቢጤ ‘ሾርት’ መሆኑን የምናውቀው ሰው…(በፈረንጅ አፍ ሲሆን ‘መልክ’ እንዲሰጠው ነው!) በአንድ ጊዜ “አሜሪካዊው ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኮቤ ብራያንት ቢበልጠኝ በአንድ ወይም ሁለት ሴንቲ ሜትር ብቻ ነው፣” ወደ ማለት ሲገባ ጨዋታው ‘ተጭበርብሯል’ ማለት ነው:: (‘ተጭበርብሯል’ ተጠቃሚነቷ መቀጠሉ ስለማይቀር አንረሳት ለማለት ያህል - ነው)
ኮሚክ እኮ ነው…ትናንት… “ስማ የሰሞኑ አየር ክብድ አላለሀም!” ስትሉት “ተወኝ፣ ልጆቼን ላሳድግበት፣” ይል የነበረ ሁሉ… ፖለቲካው ምርቃናም፣ ጨብሲም የሆነበት ዛሬ ተነስቶ… “በሩስያኖች አሻጥር እንጂ የሌኒን ወራሽ ነኝ፣” ለማለት ሲዳዳው ማየት፣ ምናልባት ፈጣሪ… “በዚህ ሲገርማችሁ ይኑር…፣” ብሎ የላከልን ይሆናል ብሎ ማሰቡ ነው የሚሻለው…እንደዛ አይነት ሰዎች መአት እያመጡብን ነውና!
ስሙኝማ…ወላ ማጋነን፣ ወላ መለጠጥ፣ ወላ እየቀደዱ መስፋት በሌለበት… እውነትና አውነቷን ብቻ እንነጋገር ከተባባልን…አሁን፣ አሁን እኛ ዘንድ በጠራራ ፀሀይና በአደባባይ እየተፈጸሙ ያሉ የአሰቃቂነትን ጥግ ጥሰው የሄዱ ድርጊቶች… በየትኛውም የዓለም ከፍል አይታዩም እኮ! አይደለም መታየት ሆሊዉድ አንደዛ አይነት ድርጊቶች የሚታይባቸው ፊልም ቢሠራ ተመልካቹ “ልብ ወለድ ቢባልስ እንዲህ ነው እንዴ!” ብሎ ምድረ ኝሮዲዩሰር ሆዬ፤ የሶስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ኪሳራውን ይሸከማት ነበር፡፡ ለወሬ የማይመቹ፣ ሰቅጣጭ፣ የተቀረው ዓለም እኛ ላይ ያለውን ግራ መጋባት “ድሮም እኮ ሰዎቹ አልሰለጠኑም እንል ነበር፣” ወደ ማለት ውሳኔ የሚያሸጋግሩ ድርጊቶች በዝተዋል፡፡
የአመለካከት አለመጣጣም፣ የፖለቲካ ሚዲያችንም ችግር ላይ ነው… የህክምና ባለሙያዎች ‘ክሮኒክ’ እንደሚሉት አይነት የማስጠንቀቂያ ‘ቀይ መብራት’ እየተብልጨለጨበት ያለ ችግር፡፡ እኔ የምለው…አለ አይደል….ስለ ሚዲያ ሲወራ ሙያዊ ግዴታቸውን የሀገርና የመላውን ህዝብ ጥቅም ባስቀደመ መልኩ የሚሠሩትን “መስመራችሁን ሳትስቱ የሙያ ከፍታችሁን ጠብቃችሁ ቀጥሉ…” ማለት አሪፍ ነው፣ እንደዛ አይነት የሚዲያ ተቋማት አሉንና! በአብዛኛው ግን የሚዲያው ነገር አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የሚያሳዝነው ምን መሰላችሁ…ማናችንም ተነስተን እንደፈለገን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየለየን መዝለፍ፣ መስደብና መፎከር በእጅጉ ቀላል ሆኗል…አንዳንድ የሚዲያ ተቋማት አርቆ ማየት እየተሳናቸውና አንዳንዶቹ የሚዲያ ተቋማት ደግሞ የመቋቋማቸውን እውነተኛ ዓላማ እንቆቅልሽ በሚያስመስል መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ያስፈራል፡፡  
እግረ መንገዴን…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…አንድ ጸሀፊ ኢትጵያውያንና መላ አፍሪካውያንን ከአንዲት የአፈ ታሪክ ድመት አባባል ጋር ያመሳስላቸዋል፡፡ ድመቷ እንዲህ ብላለች ይባላል.…“ማንም ይምጣ ማንም፣ ብቻ ወተቴን አይቅርብኝ፡፡” እሷ ወተት አልቀረባትምና አጥንት የቀረበት ቦቢስ ምን ይበል?
እናላችሁ…ስድድብ በዛ! ዘለፋ በዛ! እንደመንደር ነገረኛ ወገብ ተይዞ መውረግረግ የሚመሰል ተራና የወረደ የቃላት መወራወር በዛ! እናላችሁ…በሀሳብ ሊሞላ ይገባ የነበረውን የአእምሮ ክፍል የስድብና የዘለፋ መዝገበ ቃላት አጨናነቀው፡፡  በአስራ ምናምንና በሀያ ምናምን ዓመታት ልፋት ተገኘ የተባለ እውቀት… “ሀምሳ ብር የነበረው አስራ አምስት ብር!” እየተባለ እንደሚጮህበት ፈላጊ ያጣ እቃ ሆነ፡፡
እንደገና ፖለቲካኛው ማን ምን እንደሆና፣ ማን ምን አላማ እንዳለው፣ ማን ካልተፋቀ እውነተኛ መልኩ የማይወጣ እንደሆነ… መለየቱ እየቸገረን ነው፡፡ ዛሬ መልአክ ለመሆን ክንፍ ብቻ የጎደለው ያደረግነው ሰው… የዛሬ ሳምንት የኦልድ ትራፎርድ ሜዳን አንድ ዙር ዞሮ የዲያብሎስን ጭራ እያወዛወዘ የሚመጣ ሲበዛብን ምን እናድርግ!
“እንደ አጭበርባሪ አትታይ፣ ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ አጭበርባሪ ሳይሆኑ መኖር አስቸጋሪ ቢሆንም፡፡ ትልቁ ብልጥነትህ መሆን ያለበት ብልጥነት የሚመስልብህን መሸፈን መቻል ነው፣” ይላል “ፎርቲ ኤይት ሎውስ ኦፍ ፓወር” የሚለው መጽሀፍ፡፡ የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… እሱን መጽሀፍ ስንቶቹ ፖለቲከኞች አንብበውት ይሆን! (“አንብበው ተረድተውት ይሆን!” ለማለት ተፈልጎ እንዳልሆነ ይሰመርበት…ምንም አንኳን ቃላትና ሀረጋትን ለሚፈልጉት አላማ እንዲመች አድርጎ እንደፈለጉ መተርጎሙ ወደ ‘አርትነት’ ደረጃ እያደገ ቢሆንም!)
እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ከአርባ ስምንቱ ህጎች በሁለቱ ብቻ ‘ኤክስፐርት’ የሆነ የሚመስል ይገጥማችኋል፣ አንዳንድ ጊዜ ገና አርዕስቱ ላይ ‹‹ፎርቲ ኤይት›› የምትለውን ሲያይ መብቱ አንደተነካ የሚቆጥር አይኖርም አይባልም፡፡ እሱ በፈረንጅ አፍ የሚያውወቃት ብቸኛዋ ቁጥር ‹‹ሰርቲ ናይን›› ነቻ! (ቂ…ቂ…ቂ…) እሷ ነገር ግን ‘ጎደሎ ቁጥር’ መሆኗ (ያውም በ‘እድለ ቢሱ’ አስራ ሦስት ቁጥር መካፈል የምትችል!) ድንገት ነው ወይስ ‘ስላቅ’ አለው! (እንደተጸፈበት ስሜት ሳይሆን እንደ እራሴ ስሜት እንደፈለግሁ የመተርጎም ሀገራዊ መብቴን ለመጠቀም ያህል ነው፡፡)  
“የወደቅህበትን ቦታ አትይ፣ የተደናቀፍክበትን እንጂ…” አለ የተባለው ማን እንደሆነ እንጃ፡፡ ግን፣ ማንም ይበለው ማንም አሪፍ አባባል ነው፡፤ እናለችሁ አሁን ላለንበት ችግር፣ አሁን አፈር እያቀምን ላለንበት ችግር የትና እንዴት እንደተደናቀፍን መለየቱ አሪፍ ይሆናል፡፡
ደግሞላችሁ መጽሀፉ ምን ይል መሰላችሁ…“ስልጣን የምትፈልግ ከሆነ ሀቀኝነቱን እርሳው:: አውነተኛ እቅዶችህን በመሸፈን ራስህን አብቃ!” ለመጨመር ያህል…“እንደምንም ብለህ አንተ ላይ ትኩረት እንዲደረግ አድርግ›› መጽሀፉ፡፡ በሰዉ መሀል አትሰወር፣” ይላል መጽሀፉ፡፡ ግዴላችሁም… እንደ ስነጽሁፍ ሰዎች አነጋገር ‘አድምቶ ማንበቡ’ ቢያዳግትም… አለ አይደል…ጫፍ፣ ጫፏን የሞካከሩ ሳይኖሩ አይቀሩም!
እንዲህም ሆኖ… ዘንድሮ በፖለቲካችን አካባቢ ከተሰበሰቡት ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ…
አስቸጋሪ ነው ይህ አይነት ጣጣ፣
ነገሩስ በእኔ ድንገት ቢመጣ
ሁሉ እየሳቀ አጆቹን ሊያወጣ
ገፍቶ፣ ገሸሽ…‘የፖለቲካችን ዲ.ኤን.ኤ.’ ነውና!
ደህና ሰንበቱልኝማ!


Read 2251 times