Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 23 June 2012 06:58

“ልማት እንደ ምሥማር ከላይ ወደ ታች የሚመታ ሳይሆን እንደ እንጉዳይ ከመሬት የሚፈላ ነው” - የድሬዳዋ ገበሬ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የሀበሻ ጀብዱ” የሚለው መፅሐፍ ውስጥ የሚከተለው ታሪክ አለ፡፡ እነሆ:-

በጨርቅ ተራ ሁለት ገበያተኞች ይጨቃጨቃሉ፡፡ ጨርቁን የሚገዛው ሰውዬ እጅግ በጣም ረጅም ሲሆን ሻጩ ደግሞ በጣም አጭር ነው፡፡ እናም ገዢ በሚችለው መልኩ ክንዱን ዘርግቶ፣ ጣቶቹን ወጥሮ አስር ክንድ ለካና ምልክት አደረገ፡፡ ሻጩ ደግሞ በሚችለው ሁሉ ጣቶቹን ሳይወጥር እሱም አስር ክንድ ለካና እሱም ምልክት አደረገ፡፡ ሁለቱ በለኩት መካከል ከአንድ ክንድ የሚበልጥ ልዩነት መጣ፡፡ ገዢው ሻጩን፤ አውቆ ክንዱን ሳይወጥር ይለካል ሲል አመረረ፡፡ ሻጩ በምኒልክ እየማለ ሃቀኛ ነጋዴ መሆኑን እግዚአብሔርን ምስክርነት ጠራ፡፡ በዚህ መሃል ብዙ ወሬኛ ገበያተኞች ከበቧቸው፡፡ በነዚህ ወሬኞች ፊት ሁለቱም ደጋግመው ቢለኩም ልዩነቱ ተመሳሳይ ነበር፡፡ እናም መግባባት ባለመቻላቸው ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ዳኛ ፍለጋ መሄድ ብቻ ነበርና፣ ሸማቸውን አያይዘውና አቆላልፈው፣ ጐን ለጐን ግራና ቀኝ እጆቻቸውን በነጠላቸው ጫፎች ሸብ አድርገው አስረው፤ ከቋጠሩ በኋላ ወደ የገበያው ሸምጋይ ዳኛ በብዙ ወሬኞች ታጅበው ሄዱ፡፡

ብቸኛው የገበያዋ ፈላጭ ቆራጭ ዳኛ ከፍ ብላ ከተሰራች አንዲት ባለ ሁለት ቆርቆሮ መደብር ላይ ተኮፍሶ ተቀምጧል፡፡ የሚንጫጫውን ወሬኛ ፀጥ ካሰኘ በኋላ በትግስት ሁለቱንም ባለጉዳዮች አዳመጠ፡፡ ሁለቱም በእምየ ምኒልክ እየማሉና እግዜሩን ምስክርነት እየጠሩ ችግራቸውን ለዳኛው አስረዱ፡፡ ገዢም ሻጭም ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ እየጮሁ ዳኛውን ለማሳመን ሞከሩ፡፡ ዳኛው ሁለቱንም በትግስት ካዳመጠ እና ከቦ የሚያወራውን የገበያ ወሬኛ ዝም ካስባለ በኋላ፣ ወደ ሁለቱ ባለጉዳዮች እያየ መጀመሪያ ገዢውን አስር ክንድ እንዲለካና ምልክት እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ ወዲያው ሻጩንም አስር ክንድ እንዲለካና ምልክት እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ ሁለቱም ጨርቁን ለክተው ምልክት አድርገው እንደጨረሱ ዳኛው ጨርቁን ተቀብሎ፣ መጀመሪያ ገዢው ለክቶ ምልክት ያደረገበት ቦታ ላይ በመቀስ ቆረጠው፡፡ ወዲያው ቀጥሎ ሻጩ ለክቶ ምልክቶ ያደረገበት ቦታ ላይ በመቀስ ቆረጠው፡፡ ወዲያው ቀጥሎ ሻጩ ለክቶ ምልክት ያደረገበት ቦታ ላይ ቆረጠውና ሁለቱም እውነት አላቸው፣ እግዚአብሔር ያውቃል አለና ፍርዱን ሲሰጥ፣ በእምዬ ምኒልክ ሁለታችሁም እውነት አላችሁ፡፡ ግን እንዳትጣሉ፡፡ ገዢው በሻጩ አጭር ክንድ መስማማት ስላለበት፣ ነጋዴውም ከዚህ ትርፍ እንዳያገኝ ልዩነት ያመጣውን ጨርቅ ለዳኝነቱ ዋጋ ለራሱ አስቀርቶ ሁለቱን ባለጉዳዮች አሰናበታቸው፡፡

በዳኛው ፍርድ ሁሉም ተደስተዋል፡፡ ነጋዴው፣ ገዢው ሰውየ በሱ አጭር ክንድ የተለካ ጨርቅ በመግዛቱና በረጅሙ ክንድ ባለመጠቀሙ፣ ገዢው ደግሞ ነጋዴው ባለቺው አጭር ክንድ እየለካ ከፍ ያለ ትርፍ ባለማግኘቱ፣ ወሬኞችም ሳምንቱን ሙሉ የሚያወሩት ወሬ በማግኘታቸው፣ ዳኛውም ከጨርቋ በተጨማሪ ጥቂት ቤሳ ሳንቲሞች በመስራቱ፣ ብቻ ሁሉም ተደስተው ዳኝነቱ ተበተነ፡፡ የንጉሥ ሰሎሞንን ፍርድ የሚያስተካክል ፍርድ ይልዎታል ይኼ ነው፡፡

***

ህዝብ ዳኛውን አምኖና ተማምኖ ወደ ፍርድ የሚሄድበት ጊዜ ያስቀናል፡፡ በእርግጥ ከሳሽና ተከሳሽ ተቆራኝቶ ዳኛ ፍለጋ የሚሄድበት ዘመን ሩቅ ነበር፡፡ ሀሳቡ ግን ይገርማል፡፡ ጉዳዩን ወይም የአመለካከት ልዩነትን በህግ ለመዳኘት ህግ ያለውን እንቀበላለን ማለት የሚያስጐመጅ ነገር ነው፡፡ ዳኛ የፈረደውን ዝግጁ ሆኖ የሚቀበል አዕምሮ መልካም ፍትሕ ካገኘ፣ ሚዛናዊ ህይወቱን ለመምራት ፈቃደኛ ነው፡፡ የሰላም ፅንሰ ሀሳብ የገባው ነው፡፡ ችግሩ፤ የተቀመጠው ዳኛ የህግ የበላይነትን ተንተርሶ ቁራጭ ጨርቅ የሚወስድ ዳኛ ከሆነ፤ እውነተኛ ፍትሕ ቤቷ የለችም ማለት መሆኑ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ እንደ ዘመኑ ከሳሽም ተከሳሽም፤ ገዢም ሻጭም ያልኩት ተፈፅሟል - እኔ በምፈልገው መንገድ ተሳክቶልኛልና አሸንፌያለሁ - ብሎ ማመኑ ቢያንስ የዋህነት መሆኑን አንክድም፡፡ ጮሌ ዳኛና የዋህ ባለጉዳይ የፍርድ ሂደት ላይ የሚያደርሱት ተፅእኖ አሌ አይባልም፡፡ እንደየዘመኑ ምክንያታዊ አንድምታ (Logic) ስናየው፤

“ሁለት አንድ ዐይናዎች ተጋብተው፤ ሁለት ዐይን ያለው ልጅ ወለዱ፡፡ ምነው ቢሉ፤ አንዱን ከእናቱ አንዱን ከአባቱ” አይነት ሀሳብ በነገሰበት ዘመን፤ ፍርደ-ገምድልነት ቢኖር አይገርምም፡፡ የሚያስደነግጠውና የሚያሰጋው ፍርደ-ገምድልነት በዛሬው ዘመን ከታየ ነው፡፡ ምነው ቢሉ ህግ የዘመነበት፤ አዕምሮ የሰለጠነበት ዘመን ነውና ፍትሕ አንዱ የልማት እጅ ነው - የዲሞክራሲ አካል ነው፡፡ ፍትሕ ወገናዊነትን መዋጊያችን ነው! ይህ ከተጓደለ ትልቅ አቅም ያሳጣል! ትልቅ እጅ ይሰበራል! ትልቅ ህልም በአጭር ይቀጫል፡፡ የመልካም አስተዳደሩም፣ የኢኮኖሚ ግንባታውም፣ የፕሬሱም፣ የግልፅነቱም፣ የማነቆውም፣ የፖለቲካ ጉዘቱም፤ እናቱም አባቱም በህግ ካልታገዘ መሽመድመዱ ሥጋት ላይ የሚጥል ክፉ አባዜ ነው፡፡ የንግድ ህጉ ያለወገናዊነት መሥራት አለበት፡፡ መከላከያው ህጉ ነው፡፡ የዲሞክራሲ ዋንኛ ባህሪው የህዝብ ድጋፍና አለኝታነት ነው፡፡ የዚህ ዋንኛው አምድ ደግሞ ህግ ነው፡፡ ህግ መጣስን ለተለያየ አላማ ያዋሉ መንግሥታትን አይተናል፡፡ ያ እስኪጣራ ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ የዲሞክራሲ ሂደታዊ ባህሪው፤ ሽንፍላ እንደማጠብ አስቸጋሪ ነው፡፡ የህግ አፈፃፀም ከባህል ጋር ይወሳሰባል፡፡ በተለይ ዝግ ሆኖ የቆየ ህብረተሰብ ውስጥ ዲሞክራሲን ፍፁም በሆነ መልኩ ሥራ ላይ ማዋል በርግጥ ፈተና ነው፡፡

ምነው ቢሉ ህግ አውጪውም ሆነ አስፈፃሚውም ጭምር የመጡት ከዚያው ህ/ሰብ ነውና፡፡ ሥጋ ለሥጋ እንዲሉ መሞዳመዱ አሊያም እከክልኝ - ልከክልሁ ከህግ በላይ ይሆናል፡፡ “ዱቤ መጠየቅ ዝምድናን ማራቅ ነው” እንደሚለውና ኋላ ለዘመዱ ዱቤ እንደሚሰጠው ነጋዴ መሆኑ ነው! ሁሉም የዲሞክራሲ ትግል ረዥምና መራራ ገፅታ አለው፡፡ የተተለመደው አባባል“ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር” ነው፡፡ እንደዘመኑ ተፋላሚ አቅም ርዝመቱና መስዋዕትነቱም “ሲያዩት ያምር፣ ሲይዙት ይደናገር” የሚባልበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም፡፡ መስዋዕትነት ውስጡ ደም እንዳለበት ግን ያየ የቀመሰ ያቀዋል! “አይቶ ነው ገምቶ ነው መፍረድ፣ ይቸግር የለም ወይ ሬሳ መራመድ!” የሚለው ግጥም ያለዋዛ አልተገጠመም፡፡ ስለሆነም ያገራችንን ነገር ስናሰላ፣ እንለውጣታለን ብለንም ስናስብ፣ “የእለቱን ትተሽ የአመቱን” የሚለውን ተረት ልብ ማለት ያባት ነው! ፈረንጆች አንድን የሥርዓት አመሰራረት ሲያዩ፣ የሚጠይቁት ጥያቄ Is it Top-Bottom or Bottom – up? የሚል ነው፡፡ አወቃቀሩ ከላይ ወደታች ነው ከታች ወደላይ እንደማለት፡፡ ማዘዝ ቁልቁለት ነው እንደሚባለው መንግሥት፣ አለቃ፣ ሹም፣ የፖለቲካ ኃላፊ ከላይ ወደታች የሚያፈሰው ነው፣ ወይስ ከታች ከህዝቡ፣ ህዝቡም ቢሉ ተሳታፊውና የልማቱ ባለቤት፣ ከሥር ወደላይ የሚያወጣው እንቅስቃሴ ነው? ህብረተ-ሱታፌ (Social participation) የሌለበት ልማት አንድም በውጤቱ፣ አንድም ዘላቂ ባለቤት በማግኘቱ ረገድ አስጊ ነው፡፡ ለዚህ ነው የድሬዳዋ ገበሬ - “ልማት፤ እንደሚስማር ከላይ ወደታች የሚመታ ሳይሆን፤ እንደ እንጉዳይ ከመሬት የሚፈላ ነው” ያለው፤ ታላቅ ቁምነገር ነው የምንለው!!

 

 

 

 

 

 

Read 3824 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 07:14