Print this page
Saturday, 09 November 2019 11:26

ከጋብቻ በፊት በወጣትነት እድሜ ወሲብ የመፈጸም ምክንያቶች

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

   ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ለሆነ ሕመም በተለይም ለስነተዋልዶ ጤና መታወክ የሚያደርስ ከዚያም አልፎ ለሞት ዋነኛ ምክንያት ተብሎ የሚጠቀስ እንዲሁም ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ባጠቃላይም ለወጣቱ መቅሰፍት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ጉዳትን የሚያስከትል ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት እትም ለንባብ ብለን የነበረው ወጣቶች ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንደሚ ፈጽሙ እና የዚያም ክፉ ጎን ምን እንደሆነ የሚመለከት ነበር፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ በተለያዩ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ በመሰናዶ እና በዩኒቨርሲቲዎች በተደረጉ ጥናቶች ወጣቶች በምን ምክንያት ከጋብቻ በፊት ለወሲብ ድርጊት እንደሚነሳሱ የሚያሳዩ ነጥቦችን ደግሞ በዚህ እትም እናስነብባችሁዋለን፡፡
በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በምትገኘው ወልድያ ከተማ ባሉ የመሰናዶ ትምህርት ተከ ታታዮችና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን የመሚመለከተው ጥናት እንደሚ ያሳየው ከጋብቻ በፊት ወሲብ ለመፈጸም ወጣቶቹን የሚያነሳሱዋቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው፡፡ እነዚህን ፈትሾ ለማውጣት ሲባል የታዩ ዋና ዋና ነገሮች ጾታን፤ የጋብቻን ሁኔታ፤ ትምህርት፤ የሀይማኖት ትምህርት መከታተል፤ የወላጅና የወጣቶች ግልጽ ውይይት፤ አልኮሆልን መጠጣት፤ ሲጋራን ማጤስ፤ ከትምህርት ቤት ፕሮግራም ጋር ያለው ግንኙነት፤ የአቻ ምክር ወይንም ጫና፤ የወሲብ ድርጊትን ለሚያሳዩ ቪድዮ ፊልሞች ወይንም ህትመቶች የመጋለጥን ሁኔታ ለመመ ልከት የተሞከረ ሲሆን በትክክልም ከጋብቻ በፊት በወጣትነት እድሜ ወሲብ ከመፈጸም ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው ነገሮች መሆናቸው ተረጋግጦአል፡፡  
ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ዙሪያ በወልድያ በተደረገው ጥናት የተገኘው ውጤት እንደሚ ከተለው ነው፡፡
የሃይማኖት ትምህርትን የማይከታተሉ ወጣቶች ከሚከታተሉት ሶስት እጥፍ ያህል ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ለወሲብ ድርጊት የተጋለጡ ናቸው፡፡
ወላጆቻቸው በቅርብ የማይከታተሉዋቸው ወጣቶች ከሚከታተሉዋቸው ይልቅ ሶስት እጅ በሚበልጥ ደረጃ ለወሲባው ድርጊቱ ካለእድሜያቸው የተጋለጡ ናቸው፡፡
የአቻ ወይንም የጉዋደኛ ግፊት ያለባቸው ወጣቶች የአቻ ግፊት ከሌለባቸው ልጆች ይበል ጡኑ በከፍተኛ ማለትም 90%  ያህል ለወሲብ የተጋለጡ ናቸው፡፡
ለወሲባዊ ድርጊት ቪድዮ ወይንም ስእሎች የተጋለጡት ልጆች ካልተጋለጡት በሶስት እጥፍ ያህል ለወሲብ ድርጊት ተጋልጠው ይገኛሉ ይላል በወልድያ የተደረገው ጥናት እንደሚ ያሳየው፡፡
ጥናቱ ጨምሮ እንደሚያስነብበውም ከ18 አመት በታች በሆነ እድሜ ልጃገረዶች ከወ ንዶች በበለጠ ሁኔታ ለወሲብ የሚነሳሱ ሆነው እንደሚገኙ በወልድያ በተደረገው ጥናት ብቻ ሳይሆን በኢ ትዮጵያ ማለትም EDHS 2016 በደሴ እና በደብረ ማርቆስ በተደረ ገው ጥናትም የተገኘ እውነታ ነው፡፡ ምናልባትም ለዚህ እንደምክንያት የሚወሰደው ሴት ልጆች በባህል  በልጅነታ ቸው ትዳር እንዲይዙ ስለሚፈለግ ከዚያ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል ባህርይ ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡  
ከወልድያ ጥናት የተገኘው ሌላው ነገር የእምነት ተቋማት የተለያዩ ምክሮችን …ማለትም ወሲብን ከጋብቻ በፊት መፈጸም አግባብ አለመሆኑን እንዲሁም ሱስ የሚያስይዙ እጾችን መጠ ቀም ተገቢ አለመሆኑን እና ከአንድ በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር ወሲብ መፈጸም ኃጢአት መሆኑን በማስተማር የወጣቶችን ሕይወት በመጠበቁ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ከጥናቱ ውጤት የተገኘው እውነታ ያስረዳል፡፡   
በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ጅማ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተደረገው ጥናት እንደሚያ ሳየው በወልድያም ሆነ በሌሎች ተመሳሳይ አካባቢዎች በተደረጉት ጥናቶች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ውጤት እንደተመዘገበ ያስረዳል:: እድሜያቸው ለጋብቻ ከመድረሱ አስቀድሞ ወሲብ የሚፈጽሙ ወጣቶች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን እና የወጣቶቹ ድርጊትም ለተለያዩ ጾታዊና የስነተዋልዶ ጤና ችግር እንደሚያጋልጣቸው ያስረዳል ፡፡
ወጣቶቹን ከሚደርስባቸው ችግር ለመጠበቅ በተቀናጀ መልክ ወጣቶቹ ሊገኙ እና ምክር ሊያገኙ የሚችሉባቸውን ፀረ ኤችአይቪ ክለቦች፤ የወላጆችን ንቃተ ሕሊና ለመጨመር ቅስቀሳ ማካሄድ የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲሁም ሌሎቸም አካላት ስለሁኔታው አሳሳቢነት የሚነጋገ ሩባቸው እና መፍትሔ የሚፈልጉባቸው መድረኮችን በተለይም ወላጅና ልጅ ከወሲብ ጋር በተያ ያዘ በምን መንገድ ሊወያዩ ወይንም ተግባብተው ጉዳዩን መስመር ሊያስይዙ ይችላሉ በሚል የሚነጋገሩባቸውን መድረኮች መፍጠር ጠቃሚ ነው የጅማው ጥናት እንደሚጠቁመው፡፡
በጅማ በተደረገው ጥናት እንደታየው ወደ 352 ተማሪዎች ለጥያቄው መልስ እንዲሰጡ በጥናቱ የተጋበዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 197 ወንዶችና 157 ሴት ወጣቶች ነበሩ፡፡ ጥናቱ በተ ደረገበት ወቅት 25% የሚሆኑት ወጣቶች ወሲብ ፈጽመዋል፡፡ ለዚህም እንደዋና ምክንያት የተጠቀሰው በፍቅር መውደቅ፤ የመኖሪያ ቤት አካባቢ፤ የእምነት ተቋማትን ትምህርት አለመከታ ተል፤ የእናቶች እና አባቶች ትምህርት አለመማር፤ ከጋብቻ በፊት እድሜያቸው ገና ህጻን እያለ ወሲብ እንዲፈጽሙ ከሚገፋፉ ሁኔታዎች መካከል ናቸው፡፡  
በኦሮሚያ ባሌ በተደረገው ጥናት እንደተገለጸው ለጥናቱ ከተመረጡት ወጣቶች ውስጥ ከጋብቻ በፊት ወሲብ የሚፈ ጽሙ መኖራቸውንና ከእነዚህም መካከል 47.7% የሚሆኑት ከአንድ በላይ የወሲብ ጉዋደኛ እንዳላቸው ተረጋግጦአል፡፡ በተጨማሪም 20.5% የሚሆኑት በወሲብ ስራ ንግድ ላይ ወይንም በሴተኛ አዳሪነት ስራ ከተሰማሩ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ታውቆአል፡፡
ሴት ልጆች ከጋብቻ በፊት ወሲብ በመፈጸማቸው ምክንያት እርግዝና ስለሚከሰት ትምህ ርታቸውን በማቋረጥ በወላጆቻቸው ላይ ጥገኛ በመሆን የወለዱትን ልጅ ለማሳደግ ይገደዳሉ፡፡ ለዚህም ችግር ከሚዳርጋቸው መካከል ሕጻናት ወይንም ወጣቶች ወደ ወሲብ ሲገፋፉ ምንም ጥንቃቄ ወይንም መከላከያ በሌለው መንገድ ወሲብ መፈጸም ስህተት መሆኑን ስለማይረዱ እና ስለሚያስደስታቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአለም ዙሪያ አሳሳቢና ትኩረትን የፈለገ ነው፡፡  
ወጣቶች ከጋብቻ በፊት ለወሲብ ድርጊት የሚገፋፉባቸው ምክንያቶች ተብለው የተጠቀሱት እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
የተማሪዎቹ የቤተሰብ ሁኔታ፤
ለጥናት ከተመረጡት ተማሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ የመለሱት መልስ እናት እና አባቶቻቸው በሕይወት እንደሚኖሩ እና ገቢያቸውም መካከለኛ እንዲሁም ሱስ የሚያስይዝ እጽን ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከግማሽ ትንሽ አለፍ የሚሉ ተማሪዎች ወላጆቻቸው ምንም ትምህርት ያልቀሰሙ መሆኑን እና የቀሩት ደግሞ ወላጆቻቸው ትምህርትን የቀሰሙ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ከወላጆችና ከጉዋደኞቻቸው
ጋር ያላቸው ግንኙነት፤
አብዛኞቹ ተማሪዎች ማለትም ወደ 75.8% እና 66.8% የሚሆኑት መልስ ሰጪዎች ከአባታቸው ወይንም ከእናታቸው ጋር ምንም ምክክር አድርገው እንደማያውቁ እና ወደ 50.3% የሚሆኑት ከጉዋደኞቻቸውም ጋር ተነጋግረው እንደማያውቁ ድብቅ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የኪስ ገንዘብ የሚላክላቸው ተማሪዎች(ወጣቶች)፤
በጥናቱ ከተካተቱት ወጣቶች መካከል ወደ 22.4% የሚሆኑት መላሾች የኪስ ገንዘብ ከወላጆቻቸው እንደሚሰጣቸውና በዚያም ገንዘብ ሱስ አስያዥ እጾችን፤ አልኮሆል መጠጣትን፤ እንዲሁም ጫት መቃም የመሳሰሉትን  እንደሚጠቀሙ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ከጋብቻ በፊት ወሲብ በመፈጸሙም ረገድ የኪስ ገንዘብ ከማይላክላቸው ልጆች እጥፍ ይበልጣሉ፡፡
የተማሪዎቹ ወሲባዊ ባህርይ፤
ወደ 17% የሚሆኑት ወጣቶች ይህ መረጃ ከመሰብሰቡ በፊት ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንደፈጸሙ የገለጹ ሲሆን የተማሪዎቹ መጠንም 46% ወንዶች እና 54% ሴቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያውን ወሲብ የፈጸሙበት እድሜም 15 ሲሆን ባጠቃላይም ከ13-20 ባለው ጊዜ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም መገመት የሚቻለው ሁሉም ከጋብቻ በፊት ወሲብ የፈጸሙ ወጣቶች እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ስለወሲብ መረጃ የሚያገኙበት እና ምንጩ፤
ወደ 75.1% የሚሆኑት መላሾች በተለይም ስለ ወሲባዊነትና ስነተዋልዶ ጤና መረጃዎችን የሚያገኙት ከቤተሰቦቻቸው እና ጉዋደኞቻቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባጠቃላይም ከጋብቻ በፊት በወጣትነት እድሜ የሚፈጸም የግብረስጋ ግንኙነት ወጣቶቹን ለተለ ያዩ አስከፊ ጉዳቶች ሊጥላቸው ስለሚችል ቤተሰብ ፤ህብረተሰብ፤ትምህርትቤቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በጉዳዩ ላይ ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ የሚረዱ ምክር አዘል ትምህርቶችን ለወጣቶቹ ቢያበረክቱ ይመረጣል፡፡


Read 12752 times