Saturday, 09 November 2019 12:01

ፕ/ር መረራ - በግጭቱ፣ በለውጡና በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

    • ፖለቲካው አቅጣጫውን ስቷል፤ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መመለስ ይገባል
                      • የብሔራዊ መግባባት ሂደት መዘግየቱ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው
                      • ለውጡ መሬት የሚረግጠው ህዝቡ በመረጠው ሲመራ ነው

          ከሰሞኑ በኦሮሚያ ግጭት ተፈጥሮ ብዙ ሕይወት ሲጠፋና ንብረት ሲወድም፣ አንጋፋው ፖለቲከኛና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በአገር ውስጥ እንዳልነበሩ ይናገራሉ፡፡ ግጭቱን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ በስማቸው የወጣው መግለጫ የእሳቸው አለመሆኑን የገለፁት ፕ/ር መረራ፤ በግጭቱ ዙሪያ አሁን ከአዲስ አድማስ ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ ውጭ የሰጡት መግለጫ እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በግጭቱ፣ በለውጡና በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ከፕ/ር መረራ ጉዲና ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡


              በኦሮሚያ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በተፈጠረው ነገር በእጅጉ አዝኛለሁ፡፡ በወቅቱ ሀገር ውስጥ አልነበርኩም፡፡ ባለሁበት ቦታ ሆኜ ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች ‹‹ፕ/ር መረራ ይሄን አለ›› ተብሎ ሲሰራጩ የነበሩ ነገሮች በሙሉ የእኔ አይደሉም:: እኔ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ አልሰጠሁም፡፡ ምናልባት ሰዎች እሱ ሊናገር የሚችለው እንዲህ ነው በሚል ያወጡት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን ያንን አላልኩም:: እንዲያም ሆኖ የተፈጠረው ችግር መፈጠር ያልነበረበት አሳዛኝ ነገር ነው፡፡
እንደ  ፖለቲከኛ፣ ችግሩ የተከሰተበትን ሁኔታ ገምግመዋል?
ይሄ በየሰበቡ ህይወት እየጠፋ ያለበትን ሁኔታ መሻገር እንዳልቻልን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ችግሩ ፖለቲካችንን ባለማሰልጠናችን የመጣ ነው፡፡ የብሔራዊ መግባባት ሂደትና ሌሎች ፖለቲካዊ እርምጃዎች መዘግየታቸው፣ የሰው ሕይወት እያስከፈለን ነው፡፡ የፖለቲካ ልሂቃን የምንባለውም ለህዝቡ ችግር መፍትሄ ለማምጣት በቂ ጥረት አላደረግንም፡፡ የሕዝቡን ጥያቄዎች በትክክል ለመፍታትና ወደ ብሔራዊ መግባባት ለመድረስ  በንቃት መንቀሳቀስ ይገባናል፡፡
ብዙዎች አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ በማህበራዊ ሚዲያ የለቀቀውን መልዕክት ተከትሎ ግጭቱ መከሰቱን ያምናሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምልከታ ምንድን ነው?
ጃዋር ያስተላለፈው መልዕክት ምናልባት ገፊ ምክንያት ወይም መነሻ ሊሆን ይችላል:: ግን ዋናው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ መሠረታዊ ችግሩ ነው፡፡ ይኸውም  ለውጡን ወደፊት ለማስኬድ እየተከተልነው ያለው መንገድ ነው፡፡
ፖለቲካውን ለለውጡ በሚሆን መንገድ አላዘመንንም፡፡ ለውጡን ወደፊት በሚያራምድ መንገድ እያስኬድነው አይደለም:: ለምሣሌ ህዝብ ከለውጡ ሲጠብቅ የነበረውን ምን ያህል አግኝቷል? የህዝቡ ጥያቄና የፖለቲካው አለመዘመን በፈጠሩት ውጥረት የተከሰተ ችግር ነው፡፡ በተወጣጠሩ ብዙ ነገሮች ሳቢያ የፈነዳ ክስተት አድርጐ መውሰድ ይቻላል፡፡ ‹‹ጃዋር እንዲህ አድርጓል፤ እንዲህ ብሏል›› የሚለው ብቻውን ችግሩን በምልዐት አያሳይም፡፡ ህዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዞ መቀመጡን፣ ወጣቶች ስራ አጥ መሆናቸውን እንዲሁም ሌሎች ችግሮች እንዳሉ… አብሮ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከጃዋር በፊትም ሆነ ከጃዋር በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ ሲታገል ነበር:: ስለዚህ ችግሮችን በሙሉ ከጃዋር ጋር ብቻ ማያያዝ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የችግሩን መነሻ ሳይሆን የችግሩን ስረ መሠረትና ስፋት መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡
የተፈጠረውን ችግር ምን ብለው ይገልፁታል? ተቃውሞ ነው? ግጭት ነው? የፖለቲካ ጥያቄ ነው? ወይስ --- ?
ህዝቡ በተወሰነ ደረጃ ወደ ግጭት መግባቱ የማይካድ ነው፡፡ ግን ዋናው ጉዳይ በኢትዮጵያም ሆነ በኦሮሚያ ክልል፣ ፖለቲከኞች የህዝብን አጀንዳ ወይም ጥያቄ ይዘው ህዝብ ወደሚፈልገው ደረጃ ማሻገር አልቻሉም:: ከዚህ አንጻር ህዝቡ ያለውን ጥያቄና ቅሬታ ነው በተቃውሞ ያቀረበው ማለት እንችላለን፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ግጭት ሊኖር ይችላል፡፡ ግጭቱ ግን መነሻ እንጂ ዋናውን ችግር የሚያሳይ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ዋናው ጉዳይ ‹‹የኢትዮጵያ ልሂቃን በሽታችን ምንድን ነው? ከዚህ በሽታ እንዴትና በምን እንፈወስ?›› የሚለውን እስካሁን አለመጠየቃችን ነው፡፡ የኦሮሞም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ ልሂቃን ወደምንፈልገው ብሔራዊ መግባባት ሊወስዱን አልቻሉም፡፡ ትልቁ ችግር ይሄ ነው፡፡ አገሪቱ በተወሰነ ደረጃ ወደፊት መራመድ የምትችለው፣ ቆርጠንና ወስነን ወደ ብሔራዊ መግባባት ስንገባ ነው፡፡ ህዝቡም ተረጋግቶና ከለውጡ የሚጠብቀውን አውቆ፣ ከለውጡ ጐን የሚሠለፈው፣ የፖለቲካ ልሂቃኑ ያላቸውን ጫፍ የረገጠ ቅራኔ መፍታት ስንችል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በፊት የፖለቲካ ሃይሎች ‹‹የሀገሪቱ መሠረታዊ የፖለቲካ ችግር ምንድን ነው? እንዴት እንፍታው? ከማንስ ምን ይጠበቃል? እስካሁን ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ያልተቻለው ለምንድን ነው? እንዴትስ መፍጠር እንችላለን?›› በሚሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው፣ አንድ ውሣኔ ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ በትንንሽ ገፊ መነሻ ምክንያቶች ላይ ብቻ አተኩረን ‹በእገሌ ምክንያት እንደዚህ ሆነ፣ እንዲህ ተፈጠረ›› በሚል ብቻ የምንወጣው ችግር አይደለም የተጋፈጥነው፡፡
ዘላቂ ውጤት የሚያስገኘው የሀገሪቱ መሠረታዊ ችግሮች ላይ ተነጋግሮ፣ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ነው፡፡ ይሄን ካላደረግን ግን የኢህአፓና መኢሶን ዘመን እንደ ቀልድ ተመልሶ የሚመጣበት ሁኔታ ሊፈጠር ሁሉ ይችላል፡፡ ፖለቲካችን አቅጣጫውን ስቷል፤ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መመለሱ ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይመስለኛል፡፡
“የኦሮሞ የፖለቲካ ሃይሎች ጥላ” የሚል ስብስብ ፈጥራችኋል፡፡ ስብስቡ ከተፈጠረ በኋላ ያከናወናችሁት ሥራ  አለ?
አዎ ስብስቡ ተፈጥሯል፡፡ እኛም ተስፋ አድርገን ገብተንበታል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በቂ የሆነ በተለይም አሁን የሚታዩትን ችግሮች ሊቀለብስ የሚችል ሥራ እየሠራን አይደለም:: ፖለቲካችንን ወደ ቀና አቅጣጫ ለመመለስ እየሠራን እንዳልሆነ ከሰሞኑ የተፈጠረው ችግር ማሳያ ነው፡፡ በፖለቲካው ረገድ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የበለጠ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ስብስብ የኦሮሚያንም ሆነ የሀገሪቱን ችግሮች በፍጥነት ተወያይቶ  መፍታት አለበት፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተጀመረ ነገር የለም፡፡ በፍጥነት ወደ ስራ ገብቶ፣ ውዝፍ የቤት ስራውን መስራት ይገባዋል፡፡
ለውጡ ከፍተኛ የመቀልበስ አደጋ ተጋርጦበታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
እርግጥ ነው ከእንደዚህ አይነቱ ስጋት አሁንም አላመለጠም፡፡ እኛ ገና አቶ ኃይለማርያም ከስልጣን ሊለቁ ሲሉ፣ ለውጡን ለማገዝ 16 ነጥቦችን ለይተን፣ ለመንግስት አቅርበን ነበር:: ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮና የብሔራዊ አንድነት መንግስት ተመስርቶ ለውጡ ቢመራ እንደሚሻል ነግረናቸዋል፡፡ የዲሞክራሲ ተቋማትም ሆነ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት በዚህ መልኩ እየተመሩ፣ ማሻሻያና ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል ብለን ነበር፡፡ ነገር ግን ሃሳባችን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ አሁን ለውጡ እየተካሄደ ያለው ብሔራዊ መግባባት ሳይፈጠር ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ወደ ብሔራዊ መግባባት መግባት አለብን፡፡ የብሔራዊ መግባባት ሂደት መዘግየቱ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ለምሣሌ ምርጫ ቦርድ አዳዲስ ሕጎች አዘጋጅቷል፤ ነገር ግን ብሔራዊ መግባባት ባለመፍጠራችን፣ ህጐቹ የመረሩ ቅሬታዎችን እያስተናገዱ ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ቢቀድም ኖሮ፣ ይሄን ያህል ቅሬታ አይፈጠርም ነበር፡፡
አሁን ባለው አካሄድ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ጥረት ማድረግ አለባቸው:: ህዝቡንም ወደ ብሔራዊ መግባባት መምራት ይገባቸዋል፡፡ ይሄ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ምናልባት ሃቀኛ ድርድር በማድረግና ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር፣ ወደተሻለ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሻገር እንችላለን፡፡ ያኔ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ አሁን ያለው ችግር ተባብሶ፣ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ልንገባም እንችላለን፡፡ በስክነት ካልተጓዝን ይሄ የማይሆንበት ምክንያት የለም:: አዝማሚያውም ታይቷል፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ከቀጠልን ሀገሪቷ ልትበታተንም ትችላለች:: ሩዋንዳ ላይ እልቂት የተፈጠረው እኮ ፈጣሪ ሩዋንዳን ስለማይወዳት አይደለም፡፡ ሰዎች ባለመስከናቸው ነው፡፡ እኛም ካልሰከንን ዕጣ ፈንታችን ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አይነቱ ችግር ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፤ ከዚህ ቀደም ተፈጥሮ ያውቃል፡፡ ለኢትዮጵያዊነትም ሆነ ለብሔር ብሔረሰቦች መብት እታገላለሁ የሚሉ ሃይሎች፣ በሰከነ ሁኔታ መጓዝ ካልቻሉ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች፤ ‹‹ያለን አንድ ሀገር ነው፤ ይህን ሃገር ወደተሻለ ስርአት ማሻገር አለብን›› የሚል መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ ይሄን ሲያደርጉም ከራሳቸው ህዝብ ወይም ወገን ወጥተው ማሰብ አለባቸው:: አሁን እኮ ሁሉም የየራሱን ህዝብ ይዞ ነው ወደ ፖለቲካ ጨዋታው የገባው፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ ካልሰከነ፣ በመጨረሻ የዘራነውን ነው የምናጭደው፡፡
በዚህ ሁኔታ ቀጣዩን ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ብሔራዊ መግባባት ላይ ከደረስን ምርጫው የተሳካ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ብሔራዊ መግባባት ሳንፈጥር ወደ ምርጫው ከገባን ግን አስቀድሜ እንዳልኩት፣ የዘራነውን የምናጭድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሁሉም የቤት ሥራውን ከወዲሁ ከሰራ ግን ምርጫው የተሳካ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን ሁሉም የየራሱን ሕልም ብቻ ይዞ ፈረስ ግልቢያ ውስጥ ከገባ፣ በሃገር ደረጃ ትልቅ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ምርጫውን ማዘግየቱም የትም አያደርስም፡፡ የሕዝቡ አንዱ ጥያቄ፤ ‹‹እኔ በመረጥኩት ልመራ” የሚል ነው፡፡ ለውጡ መሬት የሚረግጠው ሕዝቡ በመረጠው ብቻ መመራት ሲጀምር ነው፡፡ ለዚህ እንግዲህ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡
በቀረው ጊዜ  ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮ፣ ምርጫውን ለማድረግ  ይቻላል?
ሃገርን የሚያስተዳድሩትም ሆኑ ፖለቲከኞች፣ ከየራሳቸው ህልም በመውጣት፣ ‹‹ምን እናድርግ?›› በሚል ተመካክረው በፍጥነት ወደ ሥራ ከገቡ፣ ያለው ጊዜ አሁንም በቂ ነው፤ አልረፈደም ግን ፍጥነትንና ጥራትን በእኩል ደረጃ ይጠይቃል፡፡
አገሪቱን ከጥፋት ለመታደግ ብሔራዊ መግባባት ከመፍጠር ባሻገር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
በማህበረሰብ ደረጃ ትላልቅ ባለድርሻ አካላት ከሚባሉት ጋር ቁጭ ብሎ መደራደር ያስፈልጋል፡፡  በአንድ ወገን ብቻ የሚደረገው ነገር የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ይሄ በፍጥነት መስተካከል አለበት፡፡ አገሪቱን ወደ ብሄራዊ መግባባት ለማስገባትም በቅድሚያ በመሰረታዊ ጉዳዩ ላይ መደራደር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ብሔራዊ መግባባት፣ በመቀጠልም ወደ ምርጫ መግባት ይቻላል፡፡

Read 3237 times