Saturday, 09 November 2019 12:51

የአንድ ቀን ውሎ

Written by  ደ.በ
Rate this item
(5 votes)

   ቱምቻ፤ ተፈሪ ኬላ ከተማ ላይ የታወቀ ደላላ ነው፡፡ ወደ ዲላ፣ ይርጋለምና አዲስ አበባ የሚመላለሱትን መኪኖች ያስተናግዳል፡፡ አንዳንዴ እያስቆመ ተሳፋሪ እንዲጭኑ ያደርግና ገንዘብ ይቀበላል፡፡ በዚያ መስመር የሚያልፍ የሕዝብ ማመላለሻ ሰራተኛ ሆኖ ቱምቻን የማያውቅ የለም፡፡ አዳዲሶቹ ከመላመዳቸው በፊት ቢጣሉትም የኋላ ኋላ ወዳጅ ሆነው ቁጭ ይላሉ፡፡
ቱምቻ ተደባድቦ አያሸንፍም፤ ምላሱ ነው ሀይለኛ፡፡ በፀብ ሰዓት ቀድሞ ትልቅ ድንጋይ ይዞ ይመጣል፡፡ ከተደባደበ ግን አፍንጫው ወዲያው ስለሚደማ፣ ደሙን ለመከላከል ሲል ከፀቡ ሜዳ ይወጣል፡፡
ሲጃራም ከእጁ አይለይም፤ ሁልጊዜ እንዳጨሰ ነው፡፡ እዚያው መኪና ተራ ከሚገኙ ጠጅ ቤቶች ጎራ ብሎ ጠጁን ይጠጣል፡። መኪና ሲመጣ ብድግ ብሎ ሲወጣ ‹‹ሂሳብ አምጣ!›› የሚለው የጠጅ ቤት አሳላፊ የለም፡፡ ተመልሶ ቤተኛ ስለሆነ ዝም ይሉታል፡፡
‹‹ዛሬ ደግሞ ምን አይነት ቀን ነው?›› አለ፤ ትልልቅና ደም የመሰሉ አይኖቹን ጎልጉሎ፡፡
‹‹ምን ሆንክ?››
‹‹ሥራም የለም! አየሩም ደስ አይልም!››
‹‹አንዳንዴ እንደዚያ - ነው!›› አለው ጓደኛው ሻንቆ አበጀ፡፡
ሻንቆ ትክክለኛ ስሙ ነው፡፡ ባልጩት የመሰለ ጥቁር ነው፡፡
‹‹ነይ እስቲ ድገሚኝ!›› አለና የብርሌዋን አንገት፣ በሁለት ጣቶቹ መካከል አስገብቶ አንጠለጠለ፡፡
‹‹ዛሬ እኔ ነኝ የምጋብዝህ!›› አለው ሻንቆ፡፡
‹‹እኔንም ጋብዘኝ!›› አለች አስተናጋጇ፡፡
‹‹አንቺንማ አልጋብዝሽም፤ ብጋብዝም ቢረዳን ነው፡፡ አንቺ ወደ ኩሽና ምግብ ሳዝዝ ነው የምጋብዝሽ! የጠጁ ጌታ የት ሄዶ ነው?!
‹‹ምሳ ሊበላ ገብቷል!››
ቱምች ቀና ብሎ አያትና ፈገግ አለ፡፡
‹‹ይቺ ልጅ ንግግር ለመደች! በፊት ዝምተኛ ነበረች፡፡ ይኸው ጋብዘኝ ሁሉ ማለት ጀመረች፡፡›› አለ ሻንቆ፤ ረጅም አንገቱን አስግጎ ወደ ባንኮኒው እስክትሄድ እያያት፡፡
ቱምች ጠጁን ደጋገመና መኪና ሲመጣ ተወርውሮ ወጣ፡፡
‹‹እነዚህ የይርጋለም ሎንቺኖች አስቸግረዋል… ገንዘብ ሳይሰጡ መሄድ ጀምረዋል!›› እያለ ማጉተምተም፡፡
‹‹ወንዶ - ይርጋለም - ሰንተርያ!›› ይላል ረዳቱ፡፡
ቱምችም ጠራለት፡፡ ከዚያም ከረዳቱ ጋር ተቃቀፈው ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡
ሻንቆ ጠጁን እየደጋገመ ሲጠጣ፣ ሰውነቱ ሲሞቀው ታወቀው፡፡ ቱምች አንዴ ለሥራ እየወጣ ሌላ ጊዜ ጠጁን እየተጎነጨ ውሎውን ፈጸመ፡፡
ሻንቆ ከሚስቱ ጋር ተጣልቶ ብቻውን ከሆነ ቆይቷል፡፡ የቤቱ ደጃፍ በሳር የተወረረው እርሷ፣ ከሄደች በኋላ ነው፡፡
ለወትሮ አኩርፋ ብትሄድም፣ ከወር በላይ ቆይታ አታውቅም፤ አሁን ግን ያለፈው ሀሙስ ሶስት ወራት ደፈነች፡፡ ስለዚህ ሻንቆ በጠጅና በካቲካላ ልቡን ጥርቅም አድርጎ ካልዘጋ፣ ብቸኝነቱን አይችለውም፡፡
ቢሆንም ግን ቅር ቅር ይለዋል፡፡ ለምን ሆድ እንደባሳት ያውቃል፡፡ እንደዚህ ቆርጣና ጨክና የቀረችው ልጅ ባለመውለዷ ነው፡፡ በዚያ ላይ የእርሱ ቤተሰቦች ‹‹በቅሎ አግብተህ!›› እያሉ የሚጨቀጭቁትን ሳትሰማ አልቀረችም፡፡ ግን ምን ያድርግ? እርሱ እግዚአብሄር አይደል… ሃናን ከፍነና ትችት ያስጣሉ አምላክ.. አንድ ቀን ያስባታል ብሎ ያምን ነበር፡፡ እቴነሽ ግን በቃ ቆረጠች፡፡ ሀኪም ቤት ተመላለሰች፤ ቤተስኪያን ሄዳ ፈጣሪን ደጅ ጠናች፤ ሲያቅታት አመረረች፡፡
‹‹እስቲ ጨምርልኝ ቢረዳ!››
‹‹ዛሬ ትንሽ አልበዛብህም?››
‹‹ተወው ባክህ! ነገር ሲበዛ ብዙ ጠጅ ያስፈልገዋል!››
‹‹እኔ ገበያዬ ቢሆንም፣ ቢበቃህ ደስ ይለኛል:: ከዛሬው ገበያ ያንተ መኖር ይበልጥብኛል! ገበያዬ አንተ ነህ!››
ፈገግ ብሎ የብርሌዋን አንገት አነቀ፡። ከዚያም ጭልጥ አድርጎ ጠጣው፡፡ ሰዓቱ ሲገፋ ለመሄድ ተንቀሳቀሰ፡፡ እያንገዳገደው ነው፡፡ እስከ ዛሬ እንዲህ አድርጎት አያውቅም። ቢረዳ በአይኑ ተከተለውና አዘነለት፡፡
‹‹ባለቤቱ ጥላው ሄዳ ልቡ ተሰበረ››
‹‹ለዚያ ነው እንዴ? አለች አበበች››
‹‹አዎ! ያሳዝናል!››
‹‹ከእኔ ጋር መሳፈጥም ጀምሯል፣ መሸሻ ሊያደርገኝ ነዋ! ቱምች እንዳያውቅ ነው የፈራሁት፡፡ ይሄ ደም የለበሰ አይኑ እንዲያውም ዛሬ ያስፈራል፡፡››
‹‹አይመስለኝም›› አለ ቢረዳ፤ ‹‹ልጁ ተጫዋች ነው፡፡ አንቺ ደሞ ሴት አጥቶ ብለሽ ነው?... እንዲያው ከሀዘኑ ለመውጣት… ለመጫወት ብሎ ነው…?››
‹‹እንዳፍህ ይሁንለት!››
‹‹ባይሆንለትስ?››
‹‹ችግር ውስጥ ይገባላ!… የሰው ሰው መንካት…›› ብላ ሳቀች፡፡
ቱምች በተራው በጣም ሰክሮ መጣ፡፡ ከማን ጋር እንደተጣላ ባይታወቅም አፍንጫው ደምቶ ታጥቦታል፡፡ ቀጭን ሰውነቱ ላይ ወፍራም ሹራብ ለብሶ ሲጋራውን ያጨሳል፡፡
‹‹እስቲ የሚበላ ነገር አምጪ!››
አበበች ፈጥና ሄዳ አመጣችለት፡፡ ምን እንደሚወድ ታውቃለች፡፡ ቀይ ወጥ ካለ፣ ሌላ ምርጫ የለውም፡፡
ቀይ ወጡን ይዛለት ከተፍ አለች፡፡
‹‹ደ’ሞ በዚህ ልታቃጥይኝ ነው?››
‹‹ሌላ በምን ተቃጥለሃል?››
‹‹ባንቺ ነዋ!››
‹‹‘ጫን ያለው መጣ’… አለች ሴትየዋ!››
አጎንብሶ አንዴ ጎረሰና… ለእርሷም ሊያጎርሳት ሲል
‹‹አታብዛው … አታብዛው አለችው››
አሳንሶ ጠቀለለና አጎረሳት፡፡
ቤቱ ከከተማው ዳር ነው፡፡ ወደ ጅጌሳ ወንዝ አካባቢ፡፡ ቁልቁለት ላይ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሳይመሽ ነበር የሚገባው፡፡
‹‹ዛሬ አመሸህ? አበበች ናት››
‹‹ዶሮ አደረግሺኝ እንዴ?...›› አለ ኮስተር ብሎ፡፡
ጎኑ ላይ ሁልጊዜ የሚታጠቃት ጩቤ አለች:: በጃኬትና በሹራብ ይሸፍናታል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት አንድ የመኪና ረዳት ወግቶ፣ ስድስት ወር ታስሮ ወጥቷል፡፡
እጁን ሊታጠብ ሲወጣ ወደ መታጠቢያው መንገድ ላይ አገኛትና እቅፍ አድርጎ ሳማት አበበችን፡፡
‹‹እትዬ እንዳይመጡ!›› ብላ ተግደረደረች፡፡
ሂሳብ ከፍሎ ሲወጣ አሳዘናት፡፡ የባከነ ሰው ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ያገኛል፡፡ ገንዘቡ ግን ከሲጋራና ከመጠጥ አያልፍም፡፡ አዘቦትና ዐውዳ መት አያውቅም፡፡ ቢሮው መጠጥ ቤት፣ እንጀራው መጠጥ ቤት!
በአይኗ ተከተለችው፡፡
ምሽት ላይ ገበያው ሲደራ… ቢረዳን ልታግዘው አንድ ማንቆርቆሪያ ያዘች፡፡ ጠጅ እየቀዳችም… ምግብ እያስተናገደችም ቆየች፡፡
በጦፈው ገበያ መሃል… ቢረዳ አንድ ሰው የሆነ ወሬ ሹክ አለውና ማንቆርቆሪያውን ቁጭ አድርጎ፣ ጭንቅላቱን በድንጋጤ ያዘ፡፡ የሰማውን ማመን አቃተው፡፡
‹‹አይ የኬላ አድባር! አይ ቅዱስ ባለወልድ! ምን ታሰማኛለህ?›› አበበች ቀስ ብላ ተጠጋችው:: መልስ አልሰጣትም፡፡
‹‹በስመ አብ ወልድ!... በስመ አብ ወልድ!››
‹‹ምንድነው?›› ጮክ ብላ ጠየቀችው፡፡
‹‹ቱ!... ቱምች ሻንቆን ገደለው!›› የሚል ቃል ከአፉ አመለጠው፤ የጠጅ ደንበኞች ሁሉ አይናቸውን አፈጠጡ!
‹‹ወይኔ… ወይኔ… የኔው ጣጣ ነው! ቱምች እኮ ይቀናል!›› አበበች በተራዋ ጭንቅላቷን ያዘች፡፡
አንድ ደንበኛ ሲያጨበጭብ፣ ቢረዳ ትልቁን ማንቆርቆሪያ ይዞ ሮጠ፡፡
‹‹ሻንቆ ሞተ!››    


Read 2947 times