Saturday, 16 November 2019 11:42

October-20-አለም አቀፉ የአጥንት መሳሳት ቀን

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

 በየአመቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ኦክቶቨር 20/ አለም አቀፍ የአጥንት መሳሳት ቀን (world osteoporosis day) ስለሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ቀኑን በሚመለከት ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሚሆኑ መረጃዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ተላልፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል  በዘንሮው አለም አቀፍ የአጥንት መሳሳት ቀን ምክንያት www.worldosteoporosisday.org የተባለው ድረገጽ እና International  osteoporosise foundation ለንባብ ያሉትን እኛም ለአንባቢ ብለናል፡፡
እንደመረጃዎቹ እማኝነት (Osteoporesis) ወይም የአጥንት መሳሳት ማለት የአጥንት መጠን ማነስና አጥንትን የሚደግፉ አካሎች የቅንጅታቸው መሰባበር የሚያመጣው ችግር ነው፡፡ አጥንት በተፈጥሮው በሚኒራል የተገነባ ሲሆን የእራሱ ውፍረትም አለው:: ያ ውፍረት (Bone Mass) ወይም ደግሞ የአጥንቱ፤ የአካሉ መጠን ወይንም ክብደት ሊባል ይችላል፡፡ መጠኑ የሚለካውም በሚይዛቸው ካልሺየም በመሳሰሉ የተለያዩ ሚኒራሎች ነው፡፡ እነዚህ ሚኒራሎች ይህንን ነገር መስራት ካቆሙ አጥንቱ በቀላሉ ሊሰበር እና ችግርን መቋቋም ሊያቅተው ይችላል፡፡
(Osteoporesis) የአጥንት መሳሳት ችግር በአብዛኛው ከ50 አመት አድሜ በላይ የሚከሰት ሲሆን በዚህ የእድሜ ክልልም (40%) አርባ በመቶ የሚሆኑ ሴቶች እንዲሁም (13%) አስራ ሶስት በመቶ ያህል ወንዶች ህመሙ ያጋጥማቸዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪካ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢራን በአለም አቀፍ ከሚገኙ የአጥንት መሳሳት ታማሚዎች 0.85 በመቶ አንዲሁም ከመካከለኛው ምስራቅ ታማሚዎች ደግሞ 12.4 በመቶ የሚሆነውን እንደምትይዝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሳኡዲ አረብያ ደግሞ እድሜያቸው 50 አመት ከደረሱ ሰዎች ወደ 8‚768 የሚሆኑት በዚሁ በአጥንት መሳሳት ችግር የሚሰቃዩ ናቸው፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የሕመሙ ተጠቂዎች ምን ያህል እንደሆኑ ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ባይገኝም በአጠቃላይ በአለም ደረጃ እንደሚገመተው ከሆነ በአጥንት መሳሳት ከሚደርስ የጤና መታወክ ጋር በተያያዘ የህክምና ክትትል የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር በቀጣዮቹ ሀምሳ አመታት በእጥፍ ያድጋል የሚል ስጋት አለ::
የምትመለከቱት የአጽም ስእል በመጀመሪያ ያለውን አቋምና አጥንት እየሳሳ ሲሄድ እየጎበጠ እንደሚሄድ የሚያሳይ ነው፡፡
የአጥንት መሳሳት ችግር ሲባል መረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት በተለይ ሶስት አካባቢዎች ለችግሩ የተጋለጡ መሆናቸው ይታያል፡፡
አንደኛው የጀርባ አጥንት አከርካሪ የሚባለው ነው ፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የቅልጥም አጥንት ነው፡፡ ይሄ የጭን አጥንትን የሚጨምር ነው፡፡ ምክንያቱም የሚገናኙበት ቦታ አንገት አለው፡፡ እንዲያውም የቅልጥም አንገት ይባላል፡፡
ሶስተኛው የአጥንት መሳሳት የሚደርስበት ደግሞ የእጃችን መዳፍና እጃችን የሚገናኝበት ቦታ ነው… ሰአት ጌጣጌጥ የምናስርበት ቦታ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሶስት ቦታዎች  ከጠቅላላው የሰውነታችን ክፍሎች የበለጠ ለአጥንት መሳሳት የሚጋለጡ ናቸው፡፡
የአጥንት መሳሳት ችግር እድሜ ከመግፋቱ አስቀድሞም ይከሰታል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ በቤተሰብ የሚተላለፍ መሆኑ ነው፡፡
በዘር አፈጣጠር አጥንቱ ሲሰራ ትክክል እንዳይሰራ ሆኖ የሚፈጠርበት አጋጣሚ አለ፡፡
ሲጋራ ማጨስ፤ አልኮል በብዛት መጠጣት፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለዚህ ሕመም ከሚያጋልጡ ምክንያቶች የተወሰኑት ናቸው፡፡
ሌላው ቀጭን ሰውነት ነው፡፡ ቀጭን ሰውነት ማለት በክብደት ወይንም በኪሎ ያነሰ ማለት ነው፡፡ አጥንት ክብደትን የሚሸከመው ዋና ክፍል በመሆኑ ያ ክብደት  አጥንትን ሁል ጊዜ እንዲጠነክር ይረዳዋል፡፡ ምክንያቱም እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት አጥንት ስራ እያሰራ ነው ማለት ነው፡፡ ክብደቱ አጥንትን በተዘዋዋሪ መንገድ ስፖርት እያሰራ ስለሚሆን ወፍራም ሰዎች አጥንታቸውን ብዙ ስፖርት ያሰራሉ ቀጭን ሰዎች ደግሞ አጥንታቸው የሚሸከመው መጠነኛ ጉልበት ስለሆነ አጥንቱ የሚፈልገውን ያህል ክብደት ስለሚያገኝ ጠንካራ አይሆንም:: እንደሚፈለገው አያሰሩትም፡፡ አጥንት በደንብ ካልሰራ ደግሞ ብዙ ሚኒራል በውስጡ እንዲከማች አያደርግም ይሄ የተፈጥሮ ሕግ ስለሆነ ነው፡፡
ምግብ ካልሽየም ያነሰው ከሆነ እድሜ ከሀምሳ አመት በታች ቢሆንም እንኩዋን ለአጥንት መሳሳት ምክንያት ይሆናል፡፡ ከጸሐይ ብርሃን ማነስ የሚመጡ ችግሮችም አሉ፡፡ ማንኛውም ሰው በቀን ለተወሰነ ሰአት (ከ20-30 ደቂቃ) ሰውነቱን ለጸሐይ ብርሃን ማጋለጥ አለበት፡፡ ይህ በተለይም በህጻንነት እድሜ ሊታለፍ የማይገባው ቁምነገር ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክተቱት መጀመሪያ ላይ በእድገት ላይ ያለው ሰው የሚኖረው የአጥንት መጠን እስከ እድሜ ልክ ድረስ ያገለግለዋል፡፡ ስለዚህ ታዳጊ ትውልድን ፀሐይ ማሞቅ፤አመጋገብን ማስተካከል የሁዋላ ሁዋላ የሚደርሰውን የአጥንት መሳሳት ችግር ያስቀራል::
ሴቶች በተለይም የወር አበባቸው ከእድሜያቸው ቀደም ብሎ ከአርባ አምስት አመት በፊት ካቋረጠ ለአጥንት መሳሳት ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
ለአጥንት መሳሳት መንስኤ ከሚሆኑት መካከል ለተለያዩ ህመሞች የሚወሰዱ መድሃኒቶችም ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ… ለአስም በሽታ… ለተለያዩ አለርጂ  በሽታ የሚሰጡ እና እነዚያን መድሀኒቶች ለረጅም ጊዜ መውሰድ  አጥንትን ሊያሳሳ ይችላል፡፡
የሚጥል በሽታ መድሀኒቶች… ደም እንዳይረጋ መከላከያ መድሀኒቶች የመሳሰሉትን መውሰድ አጥንትን ያሳሳል፡፡ ሌሎች ደግሞ ለምሳሌ የደም ካንሰር …የመሳሰሉት የደም ችግሮች ከንጥረ ነገር ጋር የተያያዙ ስለሆነ ለአጥንት መሳሳት ችግር ሊያጋልጡ ይችላሉ::
ከላይ የተጠቀሱትና ሌሎችም ችግሮች ዋና ስራቸው ሰውነት ለአጥንት ግንባታ የሚያስፈልገውን ንጥረ ነገር በሰአቱ እንዳያገኝ መከልከል ነው፡፡ መድሀኒቶቹ ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች ጋር ይቀራረባሉ፡፡ የጨጉዋራ የአንጀት የመሳሰሉት ችግሮች ምግቡን መመገብ ቢቻልም እንኩዋን እነዚያ ንጥረ ነገሮች ተስተካክለው ወደ ደም እንዳይገቡ ይከላከላቸዋል፡፡ ስለዚህ ባጠቃላይ የንጥረ ነገሮቹ ማነስ የአጥንት መሳሳት ችግርን ስለሚያመጣ አስቀድሞ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
የአጥንት መሳሳት ችግርን አስቀድሞውኑ ለመከላከል በአመጋገብ ካልሺየምን ማዘውተር ይጠቅማል፡፡ በማንኛውም እድሜ ጤናማ እና ጠንካራ አጥንትን ይዞ ለመገኘት ባማካይ አንድ ኪሎግራም ካልሺየም ማለትም 99% የሚሆን ካልሺየም በአጥንት ውስጥ እንዲገኝ ይመከራል፡፡ አጥንት በደም ውስጥ ሊገኝ የሚገባውን የካልሺየም መጠን ማጠራቀሚያም ሆኖ የሚያገለግል የሰውነት ክፍል ነው፡፡ ይህ በደም ውስጥ የሚገኝ የካልሺየም መጠን ጤናማ ለሆነ የነርቭ ስርአት መኖር እና ለጡንቻዎች ጤናማ ተግባር ያግዛል፡፡ ሰውነት የሚፈልገውን ካልሺየም በትክክል ካላገኘ በአጥንት ውስጥ ያለውን ካልሺየም በራሱ ጊዜ ይጠቀማል፡፡ የዚህ አካሄድ ምን ያህል አጥንትን እንደሚጎዳ መገመት ባይቻልም ግን እየዋለ እያደረ ለአጥንት መሳሳት ሕመም ይዳርጋል፡፡ ካልሺየምና ቫይታሚን ዲ እጅ ለእጅ ተያይዘው ስራቸውን የሚሰሩ ሲሆን እነዚህ ሁለት ንጥረ ነገሮች አጥንትን ሁልጊዜ ጤናማ እንዲሆን የሚያግዙ እና አዲስ እንዲሆን የሚረዱ ናቸው፡፡  
ካልሲየም ከሚገኙባቸው ምግቦች መካከል፤
የከብት ውጤቶች ወተት፤ እርጎ እና አይብ ከፍተኛ የሆነ ካልሲየም የሚገኝባቸው ምግቦች ናቸው::
እንደ ብሮኮሊ ያሉ ቅጠላ ቅጠሎች እንደ ሰርዲን የመሳሰሉ የአሳ ዝርያዎች ካልሲየም ስላላቸው መመገብ ይጠቅማል፡፡  

Read 12629 times