Print this page
Saturday, 16 November 2019 11:50

መዘናጋት ያስከተለው አደጋ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

                  - በየዓመቱ 13 ሺህ ዜጎች በኤችአይቪ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጣሉ
                 - አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የስርጭቱ መጠን 4.5 በመቶ ደርሷል
                 - ከአራት ሴተኛ አዳሪዎች አንዷ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሟ ውስጥ ይገኛል
                    
              በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤድስ በሽታ የወረርሽኝ ስጋት ማንዣበቡ የተገለፀ ሲሆን አዲስ አበባ ውስጥ የስርጭቱ መጠን 4.5 ደርሷል ተብሏል፡፡ በአሁን ሁኔታው ከቀጠለም አገሪቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የበሽታው ወረርሽኝ ሊከሰትባት እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት፣ ከኤድስ ኸልዝ ኬር ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር፣ ለሚዲያ ባለሙያዎች ሰሞኑን ለበሽታው ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ጉብኝት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የዝዋዩን ሼር ኢትዮጵያ የአበባ ልማትና የወንጂ ስኳር ፋብሪካ /ወንጂ ሆስፒታልን ማዕከል ባደረገው በዚህ ጉብኝት፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ለበሽታው ከፍተኛ ተጋላጭነት ካላቸው ሠራተኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኘውን የ70 ዓመቷን ወ/ሮ በርነሽ አማረን ያገኘኋቸው በዚሁ የዝዋዩ የሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ውስጥ ነበር፡፡ ተወልደው ካደጉበትና የልጅነት ሕይወታቸውን ካሳለፉበት ወሎ ላስታ ተነስተው፣ ወደ አዲስ አበባ የመጡት ገና የአስራ አንድ ዓመት ልጅ ሳሉ ነበር፡፡ ለዘመድ ጥየቃ ወደ ላስታ ያቀኑትን አንዲት ዘመዳቸውን ተከትለው አዲስ አበባ ገቡ:: ‹‹እኔ አስተምራታለሁ›› ብለው ያመጧቸው ዘመዳቸው፣ እንደ ቃላቸው ታዳጊዋን በርነሽን ለማስተማር አልተቻላቸውም፡፡ በርነሽ የአዲስ አበባን ምድር በረገጡ በአመታቸው፣ አሳዳጊ ዘመዳቸው ሞቱባቸው፡፡ ሃዘኑ ለበርነሽ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ የተሻለ ነገን ፈልገው ቤተሰቦቻቸውን ጥለው፣ ተስፋ አድርገው የመጡባቸውን አሳዳጊያቸውን በሞት ማጣታቸው የከፋ ሃዘን ውስጥ ከተቻቸው፡፡ የአዲስ አበባ ሕይወትና የኑሮው ውጣ ውረድ እንኳንስ ለአስራ ሁለት ዓመት ልጅ ቀርቶ፣ ለአዋቂውም ፈታኝ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ታዳጊዋ በርነሽም ኑሮን ለማሸነፍ የገቡበት ትግል ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው መመለስ ደግሞ ፈጽሞ አልፈለጉም:: ‹‹አገር ምን ይለኛል? ገና አንድ ዓመት እንኳን በቅጡ ሳልደፍን ብመለስ ምን እባላለሁ?›› በሚል ይሉኝታ ላለመመለስ ወሰኑ፡፡ የታዳጊዋ ቀጣይ ሕይወት ያሳሰባቸው የበርነሽ ዘመድ ጎረቤቶች፣ በርነሽን ትዳር ለማስያዝ በማሰብ ያማክሯቸዋል፡፡ በርነሽ ሃሳቡን ለመቀበል አላመነቱም፡፡ ምርጫ አጥተው ነበርና… የአስራ ሦስት ዓመቷ ታዳጊ፣ የ35 አመቱን ጎልማሳ አግብተው ትዳር መሠረቱ:: ባለቤታቸውን ተከትለውም ዝዋይ ገቡ። ትዳር በያዙ በአንድ ዓመት ከሦስት ወራቸው ፀነሱ። ሰውነታቸው በደንብ ያልጠነከረና ያልጠና በመሆኑ፣ እርግዝናው ከባድ ፈተና ሆነባቸው:: ባልጠና አካላቸው የተፀነሰው ልጅ፣ ለወ/ሮ በርነሽ ሕይወት ሥጋት ደቀነ፡፡ በዘጠነኛ ወራቸውም በኩየራ ሆስፒታል በኦፕሬሽን ተገላገሉ፡፡ ሆኖም ፅንሱ ባጋጠመው ውስብስብ ችግር ምክንያት በሕይወት ለመወለድ አልታደለም፡፡ የእሳቸውም ጤንነት አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ ከሳምንታት ሕክምና በኋላ ሆስፒታሉን ለቀው ወጡ፡፡ በወሊድ ሳቢያ ከገጠማቸው የጤና ችግር ግን ሙሉ በሙሉ አልዳኑም ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ትዳራቸው ፈረሰ፡፡
ወ/ሮ በርነሽ ሀዘን ተደራረበባቸው፡። ወይ ከጤናቸው ወይ ከትዳራቸው አሊያም ከልጃቸው ሳይሆኑ ሁሉንም አጥተው፣ ባዶ እጃቸውን መቅረታቸው በእጅጉ ያበሳጫቸው ነበር፡፡ በጎረቤት ማፅናናትና አይዞሽ ባይነት በርትተው፣ የመጀመሪያ ትዳራቸውን በፈቱ በስድስተኛ ዓመታቸው ሁለተኛ ትዳር መሰረቱ:: እኚህኛው የትዳር አጋራቸው ጥሩ ስነ ምግባር ያላቸው አናፂ ነበሩ፡፡  የወ/ሮ በርነሽ ዕድሜም 23 ዓመት ደርሷል፡፡ የትዳር አጋራቸው ደግሞ የ48 ዓመት ጎልማሳ ነበሩ። የሁለቱ ጥንዶች ትዳር በልጅ ተባረከ፡፡ ወ/ሮ በርነሽ ተረጋግተው በሰላም መኖር ጀመሩ፡፡ በትዳራቸውም ደስተኛ ሆኑ፡፡ ባለቤታቸውን በተቻላቸው ሁሉ በማገዝ፣ የስስት ልጃቸውን ለማሳደግ ይታትሩ ጀመር:: ደስታቸው ግን ለረዥም ጊዜ አልዘለቀም፡፡ ልጃቸው ገና የአንደኛ ዓመት የልደት ሻማዋን ሳትለኩስ፣ ባለቤታቸው በስራ ላይ እያሉ ከፎቅ ላይ ወድቀው ሕይወታቸው አለፈ፡፡ በወ/ሮ በርነሽ ሕይወት ላይ ከባድ መከራ ወደቀባቸው:: በሁሉ ነገር ተስፋ ቆረጡ። ‹‹ደስታ ለእኔ አልተፈጠረም፤ ከዚህ በኋላ በቃኝ፤ ልጄን ማሳደግ ብቻ ነው የምፈልገው›› ሲሉ ወሰኑ፡፡
የወ/ሮ በርነሽ የብቸኝነት ኑሮ ከጥቂት ዓመታት አልዘለለም፡፡ ‹‹እስከ መቼ ለብቻሽ ትኖሪያለሽ? ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ነውና ትዳር መያዝ አለብሽ›› የሚል መካሪ በዛባቸው። ጎረቤቶታቸው እንደምንም አሳምነው ትዳር አስያዟአቸው፡፡ ወ/ሮ በርነሽ ግን በዚህ ትዳር እምብዛም ደስተኛ አልነበሩም:: ደስታና ጤና እየራቃቸው ሄደ፡፡ ይባስ ብሎ ባለቤታቸው ከቀን ወደ ቀን እየከሱና በሽታም እየተደጋገመባቸው ሄደ፡፡ ሁኔታው ለወ/ሮ በርነሽ ጥርጣሬን ፈጠረባቸው፡፡ ‹‹ይሄ ሰውዬ ምናልባት ኤችአይቪ የሚባለው በሽታ ይኖርበት ይሆን እንዴ?›› ሲሉ በጥርጣቄ የታሸመ ጥያቄ ለራሳቸው አቀረቡ፡፡ ተመርምረው እርግጡን ለማወቅ ወሰኑ፡፡ በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ለመሄድ ቀጠሮ አላበዙም፡፡ ፍላጎታቸው ተመርምረው ራሳቸውን ማወቅና ብቸኛ አንድ ልጃቸውን መታደግ ነበር፡፡ ‹‹ራሴን ማወቅ እፈልጋለሁና መርምሩኝ›› አሉ። የሚመጣውን ውጤት በፀጋ ለመቀበል መወሰናቸውንም ተናገሩ፡፡
የምርመራው ውጤት የወ/ሮ በርነሽ አማረን በቫይረሱ መያዝ የሚያረጋግጥ ሆነ፡፡ እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ውጤቱ ከባድ ድንጋጤ ላይ ጣላቸው፡፡ ለጎረቤቶቻቸው ‹‹ልጄን አደራ፤ እኔ ቫይረሱ አለብሽ ተብያለሁ›› ሲሉ ተናገሩ:: ጎረቤቶች ሁኔታው ቢያስደነግጣቸውም ወ/ሮ በርነሽን ሊያስደንግጧቸው አልፈለጉም:: ‹‹አይዞሽ ራስሽን ጠብቀሽ መኖርና ልጅሽን ማሳደግ ትችያለሽ›› አሏቸው፡። በዚህ ተፅናኑ:: አካባቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ሄደው በድጋሚ ከተመረመሩ በኋላ የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት መውሰድ ጀመሩ፡፡ ወ/ሮ በርነሽ ዛሬ የሰባ ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከቫይረሱ ጋር መኖር ከጀመሩ ከ14 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡። የአብራካቸው ክፋይ የሆነችው ብቸኛዋ አንድ ልጃቸው ዛሬ ትዳር ይዛና ልጅ ወልዳ ወ/ሮ ብርነሽን አያት አድርጋቸዋለች፡፡ እሳቸውም ዝዋይ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ውስጥ ተቀጥረው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በዝዋይ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሼር ኢትዮጵያ የአበባ እርሻ ልማት ውስጥ ከሚገኙት 18 ሺሕ ሰራተኞች መካከል ወደ አምስት ሺ የሚጠጉት መመርመራቸውንና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የተገኘባቸው የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት እንዲጀምሩ መደረጋቸውን የእርሻ ልማቱ የሥራ ኃላፊዎች ነግረውናል፡፡
የእርሻ ልማቱ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የተለየ እንክብካቤና ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ቢናገርም፤ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኘው ወገኖች የተባለው ሃሰት መሆኑንና ምንም የተለየ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው ተናግረዋል፡፡
ኤችአይቪ ኤድስ በአገራችን እያስከተለ ለሚገኘው ጥፋት ዋንኛ ሰበቡ የመንግስት፣ የመገናኛ ብዙኃንና የሕብረተሰቡ ልክ ያጣ መዘናጋት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በሽታውን ለመከላከል ሁሉም ከፍተኛ ርብርብ በማድረጉ ለመቆጣጠር በመቻሉ ችግሩ መቀነሱ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ሁኔታው በዛው መጠን ሊቀጥል ባለመቻሉ የበሽታው ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሄድ በአሁኑ ወቅት አገራዊ የስርጭቱ መጠን 0. 9 በመቶ ሊደርስ ችሏል፡፡ በከተማችን አዲስ አበባ ደግሞ ስርጭቱ 4.5 በመቶ ደርሷል፡። በአገራችን በየዓመቱ 13 ሺህ ዜጎች በኤችአይቪ ኤድስ ሳቢያ ሕይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን 13 ሺህ አዳዲስ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ይያዛሉ፡። ከ600ሺ በላይ ሰዎችም ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ::
በአዲስ አበባ ከተማ በወሲብ ንግድ ስራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙት ወገኖቻችን መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ወይም ከአራት ሴት አንዷ በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት፣ ከኤድስ ኸልዝ ኬር ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ ጋር በትብብር ያዘጋጀውና ሰሞኑን የተካሄደው የተጋላጭ አካባቢዎች ጉብኝት፣ ቀጣይ ጉዞውን ያደረገው ወደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ/ወንጂ ሆስፒታል ነበር፡፡ በሆስፒታሉ የART ክሊኒክ ሰራተኛ የሆነችው ታጫውት አስራት፣ ቫይረሱ በደሟ ውስጥ እንደሚገኝ ያወቀችው በ1997 ዓ.ም ነበር፡፡ ለበሽታው ያጋለጣትን አጋጣሚ ፈጽሞ አትዘነጋውም፡፡ የጉርምስና ዕድሜ ሲጀማምራት ለቤተሰቦቿ መታዘዝንና ምክራቸውን መስማት አልዋጥልሽ ይላታል፡፡ አፍላው የወጣትነት ዕድሜዋ፣ የቤተሰቦቿ ምክር፣ አንገፍጋፊ ጭቅጭቅ ሆነባት፡፡ ‹‹ከዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ ለምን ጥየላቸው አልሄድም›› በማለት በወቅቱ ልቧ ከከጀለው ወጣት ጋር ትዳር ልትመሰርት የቤተሰቦቿን ቤት ጥላ ወጣች፡፡ የተጣደፈችለት ትዳር አልበረከተም፡፡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ከባሏ ተለያየች፡፡ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት መመለሱ የማይታሰብ ሆነባት፡፡ ራሷን አሸንፋ ለመኖር ያስችለኛል ያለችውን ሥራ ለመስራት በመወሰን የትውልድ አካባቢዋን ጥላ መተሃራ ገባች፡፡ በመተሃራም የሴተኛ አዳሪነት ኑሮ ጀመረች፡፡ ቤተሰቦቿን መለስ ቀለስ እያለች ትጠይቅ ነበር፡፡ እናት የልጃቸውን ሁኔታ በትኩረት ማጤናቸው አልቀረም፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰውነቷ መመንመን ያሳሰባቸው እናቷ፤ ልጃቸውን ‹‹እስቲ ልጄ ተመርመሪ›› አሏት፤ የእናቷ እንዲህ ማለት አስደነገጣትና ልትመረመር ወስና ጤና ጣቢያ ሄደች፡፡
እናት የፈሩት ደረሰ፡፡ ልጃቸው ቫይረሱ በደሟ ውስጥ መኖሩ ተነገራት፡፡ ውጤቱን ለቤተሰቦቿ ለመንገር ግን ድፍረት አጣች፡፡ አድሎና መገለል ያደርስብኛል ስትል ፈራች:: ስለዚህም ምርመራው ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን እንዳረጋገጠላት ተናገረች። ይህ ምላሿ ግን ቤተሰቦቿን በተለይም እናቷ አላሳመናቸውም:: ‹‹በሽታው ቢኖርብሽም ምንም አትሆኚም፤ ራስሽን ከጠበቅሽ መኖር ትችያለሽ›› እያሉ ያግባቧት ጀመር፡፡ ይህ ሁኔታም ታጫውትን እጅግ አበረታት ቫይረሱ በደሟ ውስጥ እንዳለ ለእናቷ ነገረቻቸው፡፡
‹‹እናቴ ጀግና ናት፤ የመኖሬ ምክንያት ብርታትና ጥንካሬዬ ናት፡፡ በወቅቱ ስለ በሽታው የነበራት ግንዛቤ ከእኛ የተሻለ ነበር›› ትላለች። ታጫውት ዛሬ በወንጂ ሆስፒታል ውስጥ ለኤችአይቪ ኤድስ ምርመራና ክትትል የሚመጡ ወገኖችን ከእሷ ሕይወት ተሞክሮ በመነሳት የምክር አገልግሎት ትሰጣለች፡፡ በዚሁ ሆስፒታል ውስጥ የኤአርቲ ክሊኒክ አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር ኤደን አበባ እንደሚናገሩት፤ ሆስፒታሉ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት መስጠት የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለአንድ ሺ አንድ መቶ ሰዎች መድሃኒቱን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ሆስፒታሉ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝ ወገኖች ከሚያደርገው የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት እደላ በተጨማሪ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምርመራ አገልግሎት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ፣ ጧሪ የሌላቸውን አዛውንቶችና በበሽታው ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን የመደገፍ ሥራ ይሰራል፡፡ ለዚህም ሆስፒታሉ ፋብሪካው ካሉት 3000 ቋሚ ሰራተኞች መካከል ፍቃደኛ ከሆኑት 825 ሰራተኞች ደመወዝ 0.5 መዋጮ ይሰበሰብና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዲደርስ ያደርጋል፡፡
ቦታው፣ ለቫይረሱ እጅግ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በስፋት የሚገኙበት እንደመሆኑ መጠን የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር እየተከናወነ ያለው ተግባር እምብዛም አመርቂ አይደለም፡፡ በየዓመቱ ከአንድ ሺ በላይ ወጣቶች ለአገዳ ቆረጣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አካባቢው የሚተሙ ሲሆን ለእነዚህ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጥና የኮንዶም ስርጭት እንደሚሰራ ሲስተር ኤደን ተናግረዋል፡፡
የዚህ ጉብኝት አጋር የሆነው ኤድስ ኸልዝ ኬር ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ፣ የፕሪቬንሽን ፕሮግራምና የአፍሪካ ዩኒየን አድቮከሲ ላይዘን ማናጀር አቶ ሄኖክ መለሰ እንደሚናገሩት፤ በሽታው በአገራችን በርካታ እህት ወንድሞቻችንን ያሳጣን ሲሆን በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ያለው መዘናጋት የበሽታው ስርጭት እንዲጨምር በማድረግ ላይ ይገኛል›› ብለዋል፡፡
በኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ላይ አተኩሮ የሚሰራው ኤድስ ኸልዝ ኬር ፋውንዴሽን በኮንዶም ስርጭት፣ በኤችአይቪ ኤድስ ምክርና ምርመራ አገልግሎት፣ ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኙ ወገኖች ነፃ የመድሃኒትና የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ስራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ በራሱ ሁለት ክሊኒኮችና ድጋፍ በሚያደርግባቸው የመንግስት ጤና ጣቢያዎች እየሰጠ የሚገኘውን ነፃ የምርመራና የሕክምና አገልግሎት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የማስፋፋት ዕቅድ እንዳለው የድርጅቱ የአድቮኮሲ ላይዘን ማናጀሩ አቶ ሔኖክ መለሰ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2020 ታሳካዋለች ተብሎ ዕቅድ የተያዘለትና ‹‹ሶስቱ ዘጠናዎች›› እየተባሉ የሚጠቀሱትን ግቦች እውን ለማድረግ የምትችልባቸው ዕድሎች አጠራጣሪ እንደሆኑ በርካቶች ይገልጻሉ። በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የምትገኝበት የ0.9 የስርጭት መጠን ለወረርሺኝ እጅግ የተቃረበ ቁጥር በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡


Read 3603 times