Saturday, 16 November 2019 12:15

“ምርጫውን ማካሄድ ቀውስ እንደማይፈጥር በገለልተኛ ተቋማት መጠናት አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

     · ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መሪ ላያመጣ ይችላል
                · የኦሮሞ ብሔርተኝነት ለኢትዮጵያ ፈጽሞ ስጋት አይሆንም
                · ኢህአዴግ ከቀድሞ ስርአቶች የበለጠ አሃዳዊ ነበር
                · የብሔር ግጭት የሚባል በኢትዮጵያ ውስጥ የለም

          ዶ/ር ብርሃኑ መገርሣ ሌንጂሶ ይባላሉ:: የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በሶስዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በሶስዮሎጂ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል:: የዶክትሬት ድግሪያቸውን ከኔዘርላንድ ራድቡድ ዩኒቨርሲቲ በሶስዮሎጂ ወስደዋል፡፡ ለሰባት አመታትም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሶስዮሎጂ
አስተምረዋል፡፡ በርካታ ማህበረሰብ ተኮር ጥናቶችና ምርምሮችን ያካሄዱት ምሁሩ፤ በምርምር ስራዎቻቸው ሁለት ሽልማቶችን እንዳገኙ ይናገራሉ፡፡ የጥናት ጽሑፎቻቸውም በዓለማቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ ታትመውላቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጥናትና ምርምር ሥራ ላይ የተሰማሩት ዶ/ር ብርሃኑ፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ እየተከታተሉ በተለየ ዕይታ በመተንተን ይታወቃሉ፡፡ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣
በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በየጊዜው ስለሚቀሰቀሱ ግጭቶች፣ ስለ ለውጡና ፈተናዎቹ፣ ስለ ኢህአዴግ ውህደት፣ ስለ መጪው ምርጫና ሌሎችም --- በጥልቀት አብራርተዋል፡፡ እነሆ፡-

           የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገልፁታል?
ይህቺ ሀገር በጦርነት፣ በጉልበት፣ በወረራ… የተመሠረተች ናት፡፡ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ መጥተው ነው ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ በብዙ ለውጥ ውስጥ ብናልፍም፣ ችግሮቻችን ዛሬም አብረውን አሉ፡፡ ለውጡ ኢትዮጵያ የአሁኑን ቅርጽ ከያዘችበት 150 አመታት ወዲህ ከመጡ ዘገምተኛ ለውጦች አንዱ ነው፡፡ በዚህ የአንድ አመት ተኩል ለውጥ፣ ከነበርንበት አንጻር መሻሻሎች መጥተዋል፡፡ ነገር ግን ይሄን መሻሻል ለማምጣት ብዙ እንቅፋቶችና ችግሮች ይገጥማሉ፤ እየገጠሙም ነው፡፡
የእነዚህ እንቅፋቶች ምንጭ  ይታወቃል?
በአንድ በኩል፤ ከቀድሞ ስርአት ተጠቃሚ የነበሩ አካላት፣ ለውጡን ወደ ኋላ ለመጐተት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በማህበረሰብ ደረጃም ህገ ወጥነትንና ሌብነትን በማስወገድ በኩል ቸልተኝነት ይታያል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ውስጥም ቢሆን ቢያንስ በስነልቦና ደረጃ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምራት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት… ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊነት የሚያሰፍን ሥርአት ለመገንባት… የተሰነቀው ህልምና ራዕይ ወደፊት እየተራመደ ነው፡፡ እንደ ማህበረሰብም እየተለወጥን ነው፤ ተፈጥሯዊም ስለሆነ እየተለወጥን እንቀጥላለን፡፡ የለውጥ አመራሩ ብቻ የሆነን ነገር ጨብጦ የሚመራ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ አመራሩ በራሱ ገና ትግል ውስጥ ነው፤ ከራሱ ጋር ጭምር፡፡ አንዳንድ ጊዜ በፓርቲዎቹ ውስጥ ያለው አለመግባባት… ከሀገሪቷ ችግርም ይበልጣል፡፡ የለውጥ አመራር የሚባሉት ሁሉን ነገር ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው እየተጓዙ አይደለም፤ ገና ለመቆጣጠር እየተጣጣሩ ነው፡፡
የዚያኑ ያህል የለውጥ ሂደቱን ለማኮላሸት የሚጥሩ ወገኖች ደግሞ አሉ፡፡ የለውጥ ሃይሉ ከእነዚህም ጋር ሌላ ግብግብ አለበት፡፡ በእርግጥ እንዲህ አይነቱ ለውጥ፤ የተረጋጋ የሰጥቶ መቀበል ድርድርን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቀውና የተለመደው አብዮታዊ ለውጥ ነው፤ ስር ነቀል ለውጥ፡፡ ሁሉን አጥፍቶና ነቃቅሎ ከአዲስ መጀመር፡፡ ይሄ ግን አክሣሪ ነው፡፡ አብዮታዊ ለውጥ የሚያደርግ መሪ፤ ብዙ ውጣ ውረድና መከራ አይገጥመውም:: ተቀናቃኞቹን በሙሉ ቀድሞ ስለሚያጠፋ የሚፈታተነው አይኖርም፡፡ ነገር ግን ሃገሪቷን ከዜሮ የመጀመር ፈተና ይገጥመዋል፡፡ አሁን እየተካሄደ ባለው የለውጥ አይነት (ሪፎርም) ግን የሚፈታተንህን አትነቅልም - አታጠፋም:: በዚህም የተነሳ ፈተናው የሪፎርም መሪው ላይ ነው የሚያርፈው፡፡ ሀገሪቷን ግን ወደ ዜሮ አይመልሳትም፡፡ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአብዮት ወጥተን ወደ ሪፎርም (ለውጥ) በመግባታችን ብቻ አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምደናል፡፡ ይሄ ሊሠመርበት ይገባል፡፡
አሁን ፈተና የሆነው በዚህ ሂደት በሪፎርም ሃይሉና የቀድሞውን ስርአት ማስጠበቅ በሚፈልጉ ወገኖች መካከል የሚደረገው ሽኩቻ ነው፡፡ አሁን ለኢትዮጵያ ትልቁ ፈተናዋ ይሄ ነው:: እንደውም የቀድሞውን ስርአት ለማስጠበቅ የሚጥረው ቡድን፣ ከሪፎርሙ ቡድን የበለጠ አቅምና ጉልበት አለው፡፡ በገንዘብ፣ በትስስር፣ በፖለቲካ ሴራ … ከፍተኛ ጉልበት አለው:: ስለዚህ የለውጥ አመራሩን የገጠመው ከባድ ፈተና ነው ማለት ይቻላል፡፡  
ከዚህ ፈተና ያለ ብዙ ኪሳራና ጥፋት እንዴት መውጣት ይቻላል ይላሉ?
አሁን የሚያስፈልገው የሰጥቶ መቀበል የድርድር መድረክ ነወ፡፡ የድርድር መድረኩ ደግሞ በዋናነት የሚጠቅመው ለገዢው ፓርቲ ነበር፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለንበት ችግር ምንጩ ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ እነሱ በሚገባ ድርድር ማድረግ ነበረባቸው፡፡ ተደራድረውም የደረሱበትን ለሕዝቡ በግልጽ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን በሁለቱ ቡድኖች መካከል ግልጽ ውድድር እየተደረገ ነው፡፡ የውድድሩ ሜዳ ደግሞ ህዝቡ ነው፡፡ ህዝቡ የለውጥ ሃይሉ የገጠመውን ፈተና በትክክል ተረድቶ፣ ከጎኑ ካልቆመ  አስቸጋሪ ነው፡፡ ነቅሎ የመትከል አብዮት ቀርቶ፣ ሪፎርም አድርጐ መጓዝ ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝቦ፣ በሃሳብ ብቻ የመደራደርን ባህል  ቢያበረታታ… ለውጡ ጤናማ  ይሆን ነበር፡፡
ችግሩ ከህዝቡ ሳይሆን ከፖለቲካ ልሂቃኑ ነው--- ሲሉ የሚሞግቱ ወገኖች  አሉ… ይስማማሉ? --
በእርግጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የልሂቃኑ ፖለቲካ ነው፡፡ ስለ ህዝብም… ስለ ሀገርም… ስለ ሎጂክም… የማይጨነቁ ልሂቃን የሚፈነጩበት መድረክ ሆኗል፡፡ ዞሮ  ዞሮ በጣም የተማረ፣ ዲሞክራቲክ የሆነ ልሂቅ ቢመጣ--የህዝብ ተሣትፎና ድጋፍ ከሌለ፣ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ላይ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ተጽእኖ የሚያሳድርበት ካልሆን፣ ልሂቁ ወደ እውነተኛ ድርድር አይገባም፡፡ ለምሣሌ የአሜሪካ ዲሞክራትና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች፣ የመጨረሻ የእርስ በእርስ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግን የአሜሪካን ህዝብ ስለሚፈሩት፣ የግዳቸውን የአገራቸውን ህግ እያከበሩ፣ ይዳኛሉ፡፡ ራሳቸውን ከሀገር በታች አድርገው ነው የሚኖሩት፡፡ የአሜሪካ ህዝብ ጥንካሬ፣ ዱርዬ የሆኑትን የአሜሪካ ሁለት ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፣ ወደ ጨዋነት መስመር ማስገባት መቻሉ ነው፡፡ የኛ ህዝብ ንቃተ ህሊና ግን ገና ነው፡፡ ህዝቡ ንቃተ ህሊናውን በሚገባ አዳብሮ እስካልተንቀሳቀሰ ድረስ የእነዚህ ልሂቃን መጫወቻ መሆኑ አይቀርም፡፡ ልሂቃኑም ቢሆኑ ምናልባት ይበልጥ ምክንያታዊ እየሆኑ ቢመጡ ነው የሚበጃቸው፡፡ አሁን እኮ ብዙ ነገር የሚመራው በስሜት ነው፤ ምክንያታዊነት የለም፡፡
የእርስ በርስ ግጭቶች በየጊዜው መከሰት ሌላው የለውጡ ፈተና ነው፡፡ ግጭቶችን እንዴት በዘላቂነት መፍታት ይቻላል?
እነዚህን ግጭቶች እኔ እንደ ፖለቲካ መሣሪያ ነው የማያቸው፡፡ ምንጫቸውም የሁለቱ ቡድኖች ሽኩቻ ነው፡፡ አንዱ ሃይል ‹‹እኛ ነበርን ትክክል፤ አሁን ያለው የለውጥ አመራር ትክክል አይደለም›› የሚለውን ለማሳየት የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ ግጭት ነው፡፡ ስለዚህ ግጭትን ያበረታታሉ፤ ስፖንሰር እያደረጉ የለውጡ ሃይል በሁሉም አቅጣጫ እንዲዳከም ያደርጋሉ፡፡ ጊዜውንም በየቦታው የሚነሳውን እሣት በማጥፋት እንዲጨርስ ይፈልጋሉ፡፡ ይሄን ሲያደርጉ አንደኛ ተቀናቃኛቸው እየተዳከመላቸው ይሄዳል:: ባይዳከም እንኳ ወደ እነሱ ትኩረት ላያደርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ትኩረቱን ለመበታተን እንደ ስትራቴጂ ይጠቀሙበታል፡፡ አሁን ያለውን ግጭት፣ የብሔር ግጭት ነው የሚሉ አሉ:: እኔ በዚህ አልስማማም፡፡ ጉዳዩ የብሔር ግጭት አይደለም፡፡ ሲጀመር በብሔር ግጭት አልስማማም፡፡ የብሔር ግጭት የሚባል ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ተፈጥሮም አያውቅም:: በታሪክም የለም፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው፣ ነገሩን የብሔር ግጭት ብሎ የመሰየምና የመለጠጥ እንጂ የብሔር ግጭት እዚህ አገር የለም፡፡ ሊኖርም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጠራ የብሔር መስመርም የለም፡፡ ኦሮሞ ሆኖ ክርስቲያን፣ አማራ ሆኖ ክርስቲያን አለ ወይም ኦሮሞ ሆኖ መስሊም፣ አማራ ሆኖ ሙስሊም አለ፡፡ በዚህ መሃል ሁለቱም ማንነት ያላቸው ደግሞ አሉ፡፡ ስለዚህ በግልጽ የተሰመረ ለግጭት የሚጋብዝ ሰበብ የለም፡፡ ነገር ግን የብሔር ጉዳይም ሆነ የሃይማኖት----እንደ ፖለቲካ መሣሪያ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ግጭት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡
በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ሽኩቻ እንዴት ነው የሚቋጨው ይላሉ?
ይሄን ማስቆም የሚቻለው አንዱ ሃይል በበላይነት ሌላኛውን ማሸነፍ ሲችል ብቻ ነው:: የድሮውን ሥርዓት እናስቀጥላለን በሚሉትና በለውጥ አመራሩ መካከል የሚካሄደው ሽኩቻ የብዙ ነገሮች ምንጭ ነው፡፡ ስለዚህ ነገሮች ሁሉ የጠራ መስመር እንዲይዙ ከተፈለገ፣ አንዱ ሃይል ሌላኛውን በግልጽ በበላይነት ማሸነፍ አለበት፡፡ ቢቻል በሃሳብና በድርድር ማሸነፍ ይመረጣል፡፡ በሃሳብና በድርድር ማሸነፍ ካልቻለ ግን  ሃይል በእጁ ያለው መንግስት፣ ችግሮች የሚፈጥረውን ቡድን፣ በህግ መቆጣጠር አለበት፤ ያ ሲሆን ነው ነገሮች መስመራቸውን የሚይዙት፡፡ ለምሣሌ ተማሪዎች ለምን ይጋጫሉ? ለትምህርት ነው የሚሄዱት፡፡ ዋና ስራቸውን ትተው እንዲህ አይነት ነገር ውስጥ የሚሳተፉት፣ ከጀርባቸው የሚልካቸው አካል ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ አካል ከዚህ ጥፋት እንዲገታ  ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን በሰከነ መንገድ አለመነጋገራቸው፣ አለመከባበራቸው፣ መፈራረጃቸው ወዘተ-- ፖለቲካውን አበላሽቶታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ----
ለብልሽቱ አስተዋጽኦ ማድረጉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የኛ ልሂቃን አንዳንዴ ከማህበረሰቡ ተቃራኒ ናቸው፡፡ ከብዙኃኑ የተሻለ እሣቤ የሌላቸው ሰዎች፣ በሆነ አቋራጭ ይመጡና እገሌን የምወክል ልሂቅ ነኝ ብለው ይቀመጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የህዝቡን ፍላጐት ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ፣ ህዝቡን የሚጠቅም ነገር ሳይመረምሩ፣ ራሳቸው የፈለጉትን… አንዳንዴም ከግል ቂማቸው የሚመነጩ ነገሮችን ወደ ህዝቡ ሲረጩ እንመለከታለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልሂቅ ሳይሆኑ በአቋራጭ ልሂቅ የሆኑ ሰዎች፣ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ሲፈጥሩ ኖረዋል፡፡
ፖለቲካው ተወጥሮ እንዲኖር ያደረጉት የልሂቃን ተብዬዎቹ ጫፍና ጫፍ የረገጠ አካሄድ ነው፡፡ ማህበራዊ መግባባት ለመፍጠር ጥረት አያደርጉም፡፡ ለምሣሌ አፄ ሚኒልክ ማህበራዊ መግባባት ላይ መስራት ይችሉ ነበር፤ አልሠሩም፣ አፄ ኃይለሥላሴም፣ መንግስቱ ሃይለማርያምም አልሠሩም፡፡ መለስ ዜናዊም ይሄን መስራት ይችሉ ነበር፤ እሣቸወም አልሠሩም፡፡ እንደውም ሥልጣናቸውን ህዝቡን ለመከፋፈል ተጠቅመውበታል፡፡ አቶ ኃይለማርያምም ይሄን ማድረግ አልቻሉም፡፡ አሁን የመጣው አመራር ምናልባት ተስፋ ያለው ይመስላል፡፡ ነገሮችን ከዚህ በፊት በማይታወቅ የተለየ መንገድ… በመጽሐፍ ላይ ነቅሶ በማውጣት… ‹‹የራሳችንን ችግሮች በራሳችን እንፍታ›› ማለት የቻለ አመራር ነው፡፡ ህዝቡ እንዲሁም ሁላችንም ችግሩ የጋራችን መሆኑን ተገንዝበን፣ የህዝብን ትስስር ለማጠናከር በትጋት መሥራት አለብን ብዬ  አምናለሁ፡፡
ልሂቃኑ ግን አሁንም ለዚህ ዝግጁ አይደሉም:: በተለይ የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ዝግጁ አይደሉም፡፡ የትግራይ ልሂቃን በበኩላቸው፤ የሁለቱን ሽኩቻ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፤ መሀል ላይ በመጫወት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂ ነው፡፡ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቃን ስትራቴጂ የሚመነጨው ከኦሮሞና አማራ ልሂቃን ድክመት ነው፡፡ በዋናነት ግን ተጠያቂዎቹ የሁለቱ ብሔር ልሂቃን ናቸው፡፡ የኦሮሞ ልሂቃን ሁሉንም ነገር መካድ የለባቸውም:: በኢትዮጵያ አገረ መንግስት ምስረታ ላይ የተሳተፉ ኦሮሞዎች አሉ፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፡፡ ምናልባትም በብዛት ኦሮሞዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የአማራ ልሂቃንም ዝም ብለው የሌለን ነገር መጠየቃቸውን፣ ‹የኔ ብቻ ነው› ማለታቸውን ማቆም አለባቸው፡፡ የኦሮማራ ትስስርም ልሂቃኑን ወደ መሀል የሚያመጣና በምክንያታዊነት እንዲነጋገሩ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ ንግግር ነው ልዩነቶችን ወደ መሀል አምጥቶ ማስታረቅ የሚችለው፡፡
በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ወደ ውህደት አመራለሁ እያለ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ውህደት ላይ አስተያየትዎ ምንድን ነው?
እኔ የኢህአዴግን ውህደት የምረዳበት መንገድ፣ ምናልባት ከኢሕአዴግ አላማ ጋር ሊቃረን ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፤ ነገር ግን ከሰሞኑ የውህደቱ መሃንዲሶች ከሚሰጡት ማብራሪያ የተረዳሁት፤ ኢሕአዴግ መሰረታዊ ችግር ያለበት ግንባር ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ ደግሞ አመሰራረቱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ  የተመሰረተው በህወኃት ጭንቅላት ውስጥ ነው፡፡ ህወኃት የመገንጠል አላማውን ቀይሮ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ለማስተዳደር በወሰነ ጊዜ የክልሎች ፓርቲ ማቋቋምና የእነዚህ ፓርቲዎችን ግንባር የመመስረት አካሄድን ነበር የተከተለው፡፡ በዚያ ሂደት ነው ከሱ ጋር ግንባር የመሰረቱ ሶስት ፓርቲዎች የተፈጠሩት፡፡ ግንባሩ ሲመሰረት ግን ከዘጠኙ የሃገረ መንግስት መስራች (በሕገ መንግስቱ አረዳድ መሰረት) ክልሎች አምስቱን ያገለለ ነበር፡፡ ነገር ግን ስሙ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ነው የሚለው፡፡ ሕዝባዊ አልነበረም:: የኢትዮጵያን ሕዝቦች በሙሉ አይወክልም፡፡ ምክንያቱም በአምስቱ ክልሎች ውስጥ ያሉ 17 ያህል ብሔር ብሔረሰቦችን ያገለለ ነበር፡፡ እነሱን አግልሎ በእነሱ ላይ ሲወስን ነው የኖረው፡፡ ትክክለኛ የፌዴራሊዝም መንገድን አይከተልም ነበር፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን ነጥቆ በእነሱ ላይ ይወስን ነበር:: ይሄ በፌዴራሊዝም መርህ ትክክል አይደለም:: ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ይቋቋም ከተባለ፣ መጀመሪያ ይሄ አካሄድ መፍረስ አለበት፡፡ ሁለተኛ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ይላል፤ ነገር ግን በተግባር ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ በምንከተለው የውክልና ዴሞክራሲ፣ ሕዝቦች ባላቸው የሕዝብ ቁጥር ልክ ነው የሚወከሉት:: ኢሕአዴግ ግን የ6 ሚሊዮን የትግራይንና የ40 ሚሊዮን የኦሮሚያን ሕዝብ በእኩል ቁጥር ነው የሚወክለው፡፡ ስለዚህ የውክልና ዴሞክራሲን ያፈረሰ አሰራር ነው፡፡ ፍትሃዊ አይደለም፡፡ ይሄ ኢ- ፍትሃዊነት መፍረስ አለበት፡፡ ሶስተኛ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ፤ ህወኃት የሚፈልገውን ውሳኔ ብቻ እየወሰነ ያስፈጽም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በጣም አሃዳዊ መንግስት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ቀድሞ ከነበረው ሥርዓት ሁሉ የበለጠ አሃዳዊ ነበር፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት አሃዳዊነት ነው ተፈጻሚ የነበረው። አሁን ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ፣ እንደገና ፌዴራሊዝሙ መጠናከር አለበት፡፡ ሕዝቦች እውነተኛ ራስን በራስ ማስተዳደር ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ እውነተኛ ፌዴራሊዝም መኖር አለበት፡፡ ሁሉም ክልሎች እኩል በአገራቸው ጉዳይ እየወሰኑ፣ በዚያው ልክ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አለባቸው፡፡ እንደውም ኢሕአዴግ እነዚህን አምስት ክልሎች - መሪ ድርጅቶቻቸውን እስከ ዛሬ አግልሎ በር ላይ በማስቀመጡ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ የአንድ ብሄር ልሂቅ ብቻ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ውሳኔ የሚሰጥበትን አካሄድም ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት አለበት፡፡
እነዚህን ለማድረግ ደግሞ አሁን ያለው ኢሕአዴግ ቅርጽ መለወጥ አለበት ማለት ነው። ሲለወጥ ሁሉንም ክልሎች ያቅፋል፣ የበለጠ ዴሞክራሲያዊ… ፌደራላዊ ስርዓት መገንባት ያስችላል፡፡ አሁን ኢሕአዴግ እኮ የለም፡፡ ኢሕአዴግ የፈረሰው ታህሳስ 2010 ዓ.ም ኦህዴድ እና ህወኃት ሲጣሉ ነው፡፡ አሁን የሚመሰረተው አዲስ ፓርቲ፣ የተሻለች ፌደራላዊት ኢትዮጵያን የሚፈጥር ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ ውህደት የሚለው ቃል ብዙም አይስማማኝም፡፡ ውህደት የሚለው ስያሜ ችግር ፈጣሪ ነው። አሃዳዊነት ነው የሚለው ቅሬታ የሚመነጨው ከዚህ ከስያሜ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ከላይ የገለጽኳቸውን ተግባራዊ ያድርግ እንጂ የፈለጉትን ስያሜ ቢሰጡት ግድ የለኝም። ሕዝቡም የፓርቲና የመንግስትን ጉዳይ በሚገባ ለይቶ ማየት አለበት፡፡ ሁለቱ አንድ ሊሆኑ አይገባም፡፡ እስከ ዛሬ ከፍተኛ የጎራ መደበላለቅ ነበር። በነገራችን ላይ ጉዳዩ የማይመለከታቸው ወገኖች በኢሕአዴግ ውህደት ላይ ከሚገባው በላይ አስተያየት ሲሰጡ እሰማለሁ፡፡ ኢሕአዴግ ከፈለገ ቢዋሃድ፣ ቢቀናጅ፣ ቢፈርስ… እኛ ምን አገባን? የኢሕአዴግ ውህደት ስጋት ውስጥ የከተተው ሰው፣ ሌላ ፓርቲ ማቋቋም ነው እንጂ ውጪ ቆሞ ‹‹እኔ በምፈልገው መንገድ ተንቀሳቀስ… አትዋሃድ›› ማለት ተገቢ አይደለም። አንዳንዴ በፓርቲ ጉዳይ የማያገባን ውስጥ መግባት ትክክል አይደለም፡፡  
በአሁኑ አካሄድ የቀጣይ ምርጫ እጣ ፈንታ ምን ይመስልዎታል?
እኔ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቄ በሰጠሁት ማብራሪያ፤ ‹‹ምርጫ አያስፈልግም የሚሉ ምሁራን መጥተዋል” ተብሎ ተወርቶብኛል፡፡ የኔ ሃሳብ ግን እንደዚያ አልነበረም። በእኔ ግንዛቤ፤ ምርጫን የሁሉ ነገር መፍትሄ አድርጎ ማየት ስህተት ነው። ምርጫ ለማድረግ በመጀመሪያ የምርጫ ባህል ያስፈልገናል፡፡ ዴሞክራሲን ለማምጣት የዴሞክራሲ ባህል ልምምድ ያስፈልጋል፡፡ ጥሩ ሰራተኛ ለመሆን የሰራተኛነት ልምምድ ያስፈልጋል፡፡ በኛ አገር ሁኔታ፤ ብዙዎች ምርጫን የሁሉ ነገር መፍትሄ… አልፋና ኦሜጋ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ምርጫ የቀውስ መንስኤም ሊሆን ይችላል፡፡ አሜሪካን አገር ትራምፕ እንዲመረጥ ያደረገው፤ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው። ያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ግን ዴሞክራት መሪ ያመጣል ማለት አይደለም:: ሕዝቡ በምክንያት ሳይሆን በስሜት የሚነዳ ከሆነ፣ ስሜታዊ የሆነ ሰው ነው የሚመረጠው፡፡ በስሜት የተሞላ ሕዝብ ባለበት አገር… በፖለቲካ ሳይንስ የተራቀቀ፣  ይህቺን አገር በፖሊሲ በ3 ወር ‹ሰማይ አደርሳታለሁ› የሚል እጩ ተወዳዳሪን… ማንም አይመርጠውም፡፡ ምርጫ የሚሰጠው ውጤት… የወቅቱ ስሜት፣ ባህል --- የሚፈቅደውን ነው፡፡ ለዚህ ነው… ምርጫ ላይ ብቻ መንጠልጠል አያዋጣም። ነባራዊ ሁኔታው ምንድነው ነው? ለምርጫ የሚቀርቡት ሰዎች እነማን ይሆናሉ?-- የሚለውን መፈተሽ ያስፈልጋል የምለው፡፡
እኔ  በምርጫ ጉዳይ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በበርካታ አገራት ሰርቻለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ቅድመ ጥናት ይደረጋል። በዚያ ቅድመ ጥናት፣ ውጤቱ ምን ሊመስል እንደሚችል ትንበያ ማስቀመጥ ይቻላል። በኛ አገር ሁኔታም ከመረጋጋት አንጻር ከምርጫው በፊትና በኋላ የሚመጡ ተጨማሪ አለመረጋጋቶችን፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ መሸከም ትችላለች ወይ? የሚለውን መመለስ ይገባል፡፡ እኔ እንደ ግለሰብ፤ አትችልም ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ እዚህ አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ይሄን በሚገባ ማጤን አለባቸው፡፡ ሁለተኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበስ ፓርቲ አለ ወይ? አንዳንዱ መሬት ላይ እየሠራሁ ነው ይላል፡፡ ለምን ፊት ለፊት አይሠራም? ስራውን ለምን እየገለጠ አይሠራም? ስለዚህ እኔ፣ አማራጭ  በሌለበት ነው ወደ ምርጫ ልንሄድ እየተዘጋጀን ያለነው፣ የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሌላ በኩል፣ ገለልተኛ ድርጅቶች መጥተው፣ ሀገሪቱ ምን ያህል ለምርጫው ዝግጁ ነች? የሚለውን ቢያጠኑ ይመረጣል:: ምርጫው ቢካሄድ ምን ውጤት ይዞ ይመጣል? ምርጫው ቢካሄድ ማን ሊያሸንፍ ይችላል… የሚለው ሁሉ ቀድሞ ቢጠና የተሻለ ይሆናል:: ይሄ ሲሆን ቢያንስ ሳይንሳዊ አካሄድ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ትንሽ ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡  ከምርጫ በኋላ በሚኖረው ሁኔታ የሚተዳደሩበትን ህግ ከወዲሁ ተፎካካሪ ሃይላቱ ተነጋግረው ቢፈራረሙ ጥሩ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በደፈናው “በቀጣዩ ግንቦት ምርጫ መደረግ አለበት” ማለት… ‹‹እኔ ምን አገባኝ… ስልጣኔን ብቻ ነው የምፈልገው፣ ከፈለገ ህዝቡ ይጥፋ›› የሚል አይነት ይመስለኛል፡፡ እኛ በቂ የሆነ ዝግጅት ማድረግ አለብን፡፡ የግድ ነው፡፡ እስካሁን ግን ዝግጅቱ  የለም ባይ ነኝ፡፡
የኦሮሞ ብሔርተኝነት የመጨረሻ መዳረሻው ምንድነው? ጽንፈኝነትስ?
እኔ ራሴን እንደ ኦሮሞ ብሔርተኛ ነው የማየው፡፡ የብሔርተኛና ብሔርተኝነት አተረጓጐሜ ግን ብዙዎቹ ከሚያዩበት መንገድ ምናልባት ይለይ ይሆናል፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት፣ በኦሮሞ ማንነት ወይም ኦሮሙማ የሚባለው ማለትም --- የኦሮሞ ማህበረሰብ ለረዥም ጊዜ ያከማቸውን እውቀት፣ ለራሱ መተዳደርና ከሌሎች ጋር ተማክሮ ለመኖር በቂ ማንነት ነው ብሎ የሚነሳ ነው፡፡ ይሄን ማንነት እንከባከበዋለሁ፤ አሳድገዋለሁ፡፡ ይሄን ማንነት ሊያጠቃ የሚመጣ ካለ ደግሞ እከላከለዋለሁ:: ለኔ የብሔርተኝነት ጽንሰ ሃሳብ ይሄ ነው፡፡ የአማራንም ብሔርተኝነት የሚፈታተን ቢመጣ እከላከላለሁ ማለት ነው፡፡ የትግራይንም እንዲሁ፡፡ ምክንያቱም ‹‹በአንተ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ›› በሚለው መርህ ነው የምመራው፡፡ ብሔርተኝነቱ ለየብሔሩ የሚሰጡት ጥቅም አለ፡፡ እነሱ መጠበቅ አለባቸው ማለት ነው እንጂ ‹‹የኔ ብቻ ነው የተሻለ… የኔ የበላይ ነው›› ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጋር አይገናኝም፡፡ የራስህን ትጠብቃለህ፤ ሌሎችም ከተበደሉ ለእነሱም ትታገላለህ ማለት ነው፡፡
የኦሮሞ ብሔርተኝነት የተገነባው ከማንነቱ ላይ ከዚህ ቀደም ከሚሰነዘሩ ጥቃቶች በመነሳት ነው፡፡ አሁን የመጣው የአማራ ብሔርተኝነትም ከዚሁ ጽንሰ ሃሳብ መነሻ ነው:: ከዚህ ሃሳብ ተነስተን ስንመለከተው፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ምንም ጽንፈኝነት የሌለው ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች አጣመው ለጽንፈኝነት አይጠቀሙበትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የኦሮሞ ብሔርተኝነት በፍፁም ለኢትዮጵያ ስጋት አይሆንም፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት አካሄድ፣ ኢትዮጵያ የእኩልነት ሃገር እንድትሆን ነው፡፡ ሁሉም ብሔሮች በዚህች ሃገር ውስጥ እኩል እንዲታዩ የሚታገል ብሔርተኝነት እንጂ ለኢትዮጵያ ህልውና የሚያሰጋ አይደለም፡፡

Read 2569 times