Print this page
Saturday, 16 November 2019 13:01

አዲስ ጐጆ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   እንደ ወትሮው የቢሮ ሥራ ጨርሶ፣ ታክሲ ተራ ረዥም ሠልፉን ታግሶ፣ ሠፈር ሲደርስ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ቤት ጐራ ብሎ፣ ፌቨን የምትወደውን ጠቃጠቆ ሙዝ ፍለጋ፣ አንድ ሁለት ቤት ረገጠና አገኘ፡፡ ሙዙን አስመዝኖ ወደ ቤቱ በእግሩ ሲያቀጥን፣ አንድ ሁለቴ ስልኳን ሞክሮ እምቢ አለው፡፡ ያቺን በቅመም ያበደች ሻይዋን መጠጣት ፈልጐ ነበር፡፡
በርግጠኝነት በዚያ ሰዓት ፌቨን እቤት መድረስ አለባት፡፡ እሱ ከሲኤምሲ ተነስቶ አየር ጤና እስኪደርስ፣ እሷ ካራቆሬ ቤቷ መድረሷ የተለመደ ነው፡፡ ምናልባት ብሎ ቴክስት አደረገላት፡፡
“አንቺ ቅመም፣ ያንን የቅመም ሻይሽን አጠጪኝ፤ እየመጣሁ ነው፡፡”
መልስ አልሰጠቺውም፡፡
ቤት ሲደርስ ቁልፍ ነው፡፡ ቁልፉን ሰደደና ከፈተው፡፡ ቤቷ ዝብርቅርቅ ብሏል፡፡ የፌቨን ሻይ የለም፡፡ ምሥልቅልቅ ያለ ነገር ተፈጥሯል፡፡ እጁ እግሩ፣ ወገቡ… መላው ሰውነቱ የተቆራረጠ፣ ወይም እንደ ባቢሎን ግንብ የፈራረሰ መሰለው፡፡
ሶፋዎቹ መካከል ያለችው ጠረጴዛ ላይ በነጭ ወረቀት የተፃፈ ደብዳቤ ላይ፣ ንፋስ እንዳይወስደው የቴሌቪዥኑ ሪሞት ተቀምጧል፡፡ ብድግ አድርጐ አነበበው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ወለሉ ላይ ባፍጢሙ ተደፋ፡፡ እንደ ሕፃን ልጅ ተንሰቀሰቀ፡፡
“እኔ ምን በደልኩሽ ታዲያ?”
አሁን ያንን ሁሉ ድካሙን ረስቶ፣ አክስቱ ጐረቤት ወዳለው ፍፁም ቤት ለመሄድ ተነሳ፡፡
ፌቨንን ያገኛት እዚያ ሠፈር፣ አክስቱ ቤት በሚሄድበት ጊዜ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ሳንቲም ሲያስፈልገው፣ ወይም ጥሩ ምግብ ሲያምረው፣ የእናቱ እህት ቤት ይሄዳል፡፡ አንዳንዴ ጓደኞቹንም ይዞ ይሄድ ነበር፡፡ አክስቱ በኑሮ ከእናቱ በጣም ትሻላለች፡፡ እናቱ ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ልጆቻቸውን ማሳደግ መከራ ሆኖባቸው ነበር፡፡
የአክስቱን ቤት ይወደዋል፡፡ ለሚበላው ምግብና አንዳንዴ ለሚሰጠው ብር ብቻ ሳይሆን ፌቨንንም ያገኛት እዚያው ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሲሄድ እርሷም ብቅ ስትል ተገናኙና ጐጆ ለመቀለስ በቁ፡፡
የእርሷ የልጅነት ጓደኛ፣ እንጀራ ፍለጋ ወጥቶ ዲላ የምትባል ከተማ ከሰመጠ በኋላ ፌቨን የራሷን ሕይወት ጀመረች፡፡ ይህንንም በስልክና በፌስቡክ ተነጋገሩ፡፡ ትዳር ከያዘች በኋላ ሁሉም ነገር አበቃ፡፡
ታክሲ ውስጥ ሲገባ፣ ሂሣብ ሲከፍልም ነፍሱን አያውቅም፡፡ ታክሲው ሲሄድ እንደ መጀመሪያ ተሣፋሪ ፎቁ፣ ዛፉ… ምናምኑ ሁሉ አብሮት የሚሄድ እስኪመስለው ግር አለው፡፡ እንባውን ውጦት እንጂ ቢዘረግፈው ደስ ባለው፡፡
የቀድሞ ፍቅረኛዋን እስኪያገኘው ድረስ ቸኩሏል፡፡ ከሥራ ተመልሶ ቤት እንደሚሆን ገምቷል፡፡ የቤቱን በር ቆልፎት እንደሆነ እንኳ አላወቀም፡፡ ምናልባት ቁልፉን በሩ ላይ ለክቶት መጥቶ ይሆናል፡፡ “የራሱ ጉዳይ” አለ፡፡ ከዚህ ስቃይ መሞት ባንድ ጣዕሙ ይሻላል፡፡
ታክሲው ገሰገሰ፣ ሙዚቃው ነደደ፤ ልቡ ልትፈነዳ ነው፡፡
ሲያገኘው ምን ሊፈጠር እንደሚችል፣ ምን ማድረግና እንዴት እንደሚያደርግ ገና የሰከነ ዕቅድ የለውም፡፡ የሚንቀሳቀሰው በደመ ነፍስ ነበር፡፡
ቀድሞ አክስቱ ቤት እንደማይገባ ወስኗል፡፡ እርሷም ግን መስማቷ እንደማይቀር ያውቀዋል፡፡
ባላንጣው በር ላይ ሲደርስ በሩን አንኳኳ፡፡ አልተከፈተም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሠራተኛዋ መጣችና ተመለሰች፡፡
አሁንም አንኳኳ፡፡
መጥታ ከፈተችለት፡፡
“ሰለሞን የለም?” አላት፡፡
“አለ” ስትለው፣ ሳያስፈቅዳት ገባ፡፡
ምናልባት አብሯት ሄዷል የሚል ፍርሀት ነበረው፡፡ ትንሽ ቀለል አለው፡፡
ሲገባ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ቴሌቪዥን እያየ ነው፡፡
ተወርውሮ ወደቀበት፡፡
ሠራተኛዋ እየሮጠች የፍስሃ አክስት ቤት ሄደች፡፡
ሳሎኑ ላይ እንደወደቀ የአክስቱ ድምጽ ይሰማዋል፡፡ በሩን በርግደው ገብተው፤ “ምንድነው?...ምንድነው?” አሉ፤ እየጮኹ፡፡
ፍሰሃ ያለቅሳል፡፡
“ያለ ፌቨን መኖር አልችልም፤ እባክህ፣ እባክህ መልሳት… እባክህ መልሳት” ይላል፡፡
አክስቱ ግራ በመጋባት “እግር ላይ መውደቅ ምን አመጣው? የገዛ ሚስትህን ከየት ነው የሚመልስልህ?”
ፍሰሃ ከወደቀበት ተነስቶ፣ “አክስቴ… ጥላኝ ሄዳለች”
“ታዲያ እርሱ ምናገባው?”
“በእርሱ ምክንያት ነው፤ ከርሱ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ከኔ ጋር በዚህ ሁኔታ መኖሩ ህሊናዋን ስላሰቃየው ጥላኝ ሄደች፡፡ ፌቪ ስስ ናት… ፌቪ ንፁህ ናት፡፡››
“ሂድ! የምን ንጽህና ነው? ንፁህ ከሆነች ሁለት አልጋ ምንድነው?”
ደግሞስ ለምን ጥርግ አትልም!”
“አክስቴ… ተዪኝ!”
“ለካ እንዲህ አልጫ ነህና!...ድንቄም የኛ ኢንጂነር!”
“…ዕውቀትና ሥልጣን፣ በፍቅር ፊት የሚያለቅስ ሻማ ነው፡፡”
“የራስህ ጉዳይ ነው! አሁን ይልቅ ተነስና ውጣ!”
“እባክህ ወንድሜ… ካለችበት አሥመጣልኝ!”
“እርሱ አስመጥቶልህ ሚስቴ ናት ብለህ አቅፈሃት ልተኛ?!”
“አዎ፤ እሾኋን እረስቼ አበባዋን አሸታለሁ፤ አክስቴ ተዪኝ!”
በሩን በሀይል ዘግታው ወጣች፡፡
“ለዚያች ለናትህ እነግርልሃለሁ፡፡ አሁን እርሷ አንተን ወለደች!? አንበሳ ድመት ይወልዳል?”
መልስ አልሰጣትም፡፡
እናቱ ነጠላቸውን አንጠልጥለው ታክሲ ሲሳፈሩ፣ ትንሹ ልጃቸው በድንጋጤ ተከትሏቸው ወጣ፡፡ እንደዚህ ሲበሽቁ አይቷቸው አያውቅም፡፡ ፊታቸው የጭራቅ ፊት መስሏል፡፡
“እውነት አንቺ ልደትዬ ካለሽ.. እውነት ከልጅነቴ ጀምሮ አንቺን የሙጢኝ ብዬ እንደሆነ”…
“እማዬ…እማ!”
“ዞር በልልኝ አልጫ! የአልጫ ዘር!”
መለስ አለና ቀስ ብሎ ተከተላቸው፡፡ ታክሲ ውስጥ ሲገቡ፣ እርሱም ተከትሎ ገባ፡፡
ልደታ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ‹‹ወራጅ›› አለ ብለው ሲወርዱ አብሯቸው ወረደ፡፡
ከዚየም ቀስ እያለ ተከተላቸው፡፡ እየፈጠኑ ሄደው አንድ ጥግ ተንበረከኩ፡፡ ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ይሰማል፡፡
“ያን ጀግና - አብዮትን በወለድኩበት ማህፀን… ይህንን አልጫ ወለድኩ! ላገሩ ጦር ሜዳ የሞተውን አንበሳ በወለድኩበት፣ ለሴት ብሎ የባላንጣውን ጫማ የሚስም አልጫ ሰጠሽኝ! ምነው ይሄ ድፍት ብሎ… ያኛው እንደ ጌታ ከሞት ቢነሳልኝ? ምን ብዬ ልኑር?...አሁን እንዴት ልኑር?›› ስቅስቅ እያሉ አለቀሱ፡፡
…“እባክህ አንተ መድሃኔዓለም… ገላግለኝ!..እባክህ “በቃሽ” በለኝ፡፡ አሁን በዕድሬ ሰዎች መካከል… በተከበርኩበት ሠፈር… በዚህ ውርደት እንዴት እኖራለሁ? ሀገር ለቅቄ እንዳልሄድ… ይሄ ራሱን ያልቻለ ልጅ አለ…››
ፀሎታቸውን ጨርሰው ቀና ሲሉ፣ ስልካቸው አቃጨለ፡፡
“ሄሎ?”
“እመት”
“ነገሩ ተበላሸ”…
“ምንድን ነው?”
“ልጅቷ ራሷን አጥፍታለች!”
“ተገላገልና! ስሙን አጨቅይታ ሞተች?...ባለጌ!”
“ተዪ እንርሱ አይባልም!”
“አዋርዳኝ ሞተቻ! ምናለ ዝም ብላ ብትሞት?”
“ጨዋ ስለሆነች አይደል ራሷን የገደለች!”
“ጨዋማ መጀመሪያ ሁለት ከንፈር አያምረውም!”
“ተዪ በቃ!”
ስልኩን ዘጉትና ከደጀ ሠላሙ ቀጥ ብለው ወጡ፡፡
ትንሽ እንደቆዩ አሁንም ስልካቸው ጮኸ፡፡
“ልጅቷ ተርፋለች፣ ልጅሽ ሆስፒታል ገብቷል!”
“ይደፋ! ድብን ይበል!...አሰዳቢ!”

Read 3104 times
Administrator

Latest from Administrator