Saturday, 23 June 2012 07:25

አበባ አረጋዊ በስዊድን ተፈልጋ ነበር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የማነ ፀጋዬ በፌደሬሽኑ ምርጫ ተከፍቷል

በ1500 ሜትር በለንደን ኦሎምፒክ ለወርቅ ሜዳልያ ከተጠበቁ አትሌቶች እንዷ የሆነችውን አትሌት አበባ አረጋዊን ዜግነት በማስቀየር ለስዊድን ለማሰለፍ የተደረገው ሙከራ ከወር በፊት መክሸፉ ታወቀ፡፡ በዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ በ1500ሜ በ10 ነጥብ አንደኛ ሆና የምትመራው አበባ መሮጥ የምትፈልገው ለኢትዮጵያ ነው ሲል ባለቤቷ የሆነው የማራቶን ሯጭ የማነ ፀጋዬ  ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡ ከወር በፊት አትሌት አበባ አረጋዊ ለስዊድን ኦሎምፒክ ቡድን ዜግነቷን በመቀየር እንድትወዳደር በአገሪቱ ሚዲያዎች የነበረው ከፍተኛ ግፊትና ተስፋ ሳይሳካ የቀረው ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ሁኔታ ያስቀመጠው የግዜ ገደብ በማለቁ መሆኑን ሺት የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣና ኤስቪቲ ስፖርት የተባለ የቴሌቭዥን ጣቢያ አውስተዋል፡፡

አበባ አረጋዊ በስዊድን የመኖርያ ፍቃድ ቢኖራትም ፖስፖርት ግን የላትም፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ለኦሎምፒክ ቡድን ይምረጣት አይምረጣት ባይታወቅም ለስዊድን ኦሎምፒክ ተስፋ ትሆናለች በማለት ራኒንግ ኒውስ የተባለ ድረገፅ ከዘገበ በኋላ ሁኔታውን  የስዊድን መገናኛ ብዙሓናት ከወር በፊት ሲያራግቡ ሰንብተዋል፡፡

ከመጋቢት 2009 እኤአ ወዲህ በስዊድን ነዋሪ የሆነችው አበባ አረጋዊ በዚያ አገር ለሚገኘው ሃመርቢ የተባለ ክለብ ስትወዳደር ቆይታለች፡፡  ከወር በፊት ቲቪ4 የተባለ አንድ የስዊድን ሚዲያ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ያወጣው አዲስ ዜግነትን የመቀየር ደንብ መሰረት በዜግነቷ ኢትዮጵያዊ የሆነችው አትሌት አበባ  ለስዊድን የምትወዳደርብት እድል በመኖሩ ይታሰብበት ብሎ  ግፊት አድርጓል ፡፡ በዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ደንብ መሰረት አንድ ስፖርተኛ ከትውልድ አገሩ ውጭ በሚኖርበት አዲስ አገር ሶስት ዓመት ሲኖር ከቆየ ለዚሁ አገር ዜግነቱን ቀይሮ በዓለም አቀፍ ውድድር መሳተፍ እንደሚችል  በወቅቱ ያወራው ቲቪ4 አበባ አረጋዊ ለስዊድን በኦሎምፒክ ተስፋነቷ በመታየት ዜግነቷን እንድትቀይር ጥረት እንዲደረግ ቀስቅሶ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም የስዊድን አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ቅድሚያ ትኩረታችን አበባ ናት፡፡ ያለችበት አቋም  በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ልትወስድበት የሚያስችል ነው፡፡ ለምን አገር በኦሎምፒክ ትሰለፋለች የሚለው አያሳስበንም ብለው  በወቅቱ መናገራቸውንም አንድ ዘገባ አመልክቷል፡፡

አትሌት አበባ አረጋዊ እስከዛሬ ወደ አገሯ የመመለስ እቅድ እንዳላት የነገረን አትሌት የማነ ፀጋዬ በስዊድን የኦሎምፒክ ቡድን ዜግነቷን ቀይራ እንድትሰለፍ ስለተፈጠረው ፍላጎት ብዙ ባላውቅም ምናልባትም ዘንድሮ ካላት ውጤታማነት በመነሳት የተደረገ ሙከራ ሳይሆን እንደማይቀር ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡

አበባ አረጋዊ በዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ ውድድር ሮም ላይ በ1500 ሜትር ስታሸንፍ የገባችበት 3 ደቂቃ ከ56.54 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ  ከስድስት ዓመታት በኋላ  በርቀቱ ፈጣን ሰዓት ሆኖ የተመዘገበ ነው፡፡በመካከለኛ ርቀት ዘንድሮ ብቅ ካሉ የዓለማችን ምርጥ አትሌቶች ግንባር ቀደም የሆነችው አትሌቷ በዚህ የ1500ሜ ሰዓቷ የኢትዮጵያን ሪኮርድ ጨብጣለች፡፡

የ21 ዓመቷ አበባ አረጋዊ ከ3 ዓመት በፊት በ800 ሜትር የኢትዮጵያ ሻምፒዮን በመሆን ከወጣች በኋላ   ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመግባት በአውሮፓ በርካታ ውድደሮችን ማድረግ የጀመረች ስትሆን ከ3 ዓመት በፊት በአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች፡፡ የውድድር መደቧን ከአጭር ርቀት ወደ መካከለኛ ርቀት የ1500 ሜትር ተሳትፎ ከ2 ዓመት በፊት የቀየረችው አትሌቷ በዚሁ ጊዜ በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች መሳተፍ የጀመረች ሲሆን በ2011 እኤአ ላይ በገጠማት ጉዳት ዓመቱን ያለውድድር አሳልፋለች፡፡ ዘንድሮ ከጉዳቷ አገግማ ወደ ዓለም አቀፍ ውድድሮች   በዳይመንድ ሊግ በ1500 ሜትር ተሳታፊ ከሆኑ አትሌቶች ተርታ ገብታ ወደ ውድድር ተመለሰች፡፡ በዳይመንድ ሊጉ መጀመርያ በሻንጋይ የግራንድ ፕሪ ውድድር በገንዘቤ ዲባባ ተቀድማ ሁለተኛ ብትወጣም ከዚያ በኋላ በሮምና ቢስሌት የተደረጉ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮችን አሸነፈች፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ላይም ለኢትዮጵያ በ1500 የወርቅ ሜዳልያ ድል ተስፋ የፈጠረች ድንቅ አትሌትም ሆነች፡፡

በተያያዘ በኢትዮጵያ የለንደን ኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን የአትሌቲክስ ፈደሬሽንን የምርጫ ደንብ በመተላለፍ ሳይመረጥ የቀረው አትሌት የማነ ፀጋዬ ፌደሬሽኑ እኔን ላለመምረጥ የተከተለው መመርያ አያሳምነኝም በሚል ተቃውሞውን ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በለንደን ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው በማራቶን የሚወዳደሩ አትሌቶችን መርጦ በይፋ ያሳወቀው ከወር በፊት ነበር፡፡ በውድድር ዘመኑ የሮተርዳም ማራቶንን ሲያሸንፍ ከዱባይ ማራቶን አሸናፊው አየለ አብሽሮ ቀጥሎ የዓመቱን ሁለተኛውን ፈጣን የማራቶን ሰዓት ያስመዘገበው አትሌት የማነ ፀጋዬ  በኦሎምፒክ የማራቶን ቡድኑ ሳይካተት የቀረው በምርጫው ወቅት ያለፌደሬሽኑ ፍቃድ በሁለት ማራቶን ውድድሮች በመሳተፉ ነው፡፡ የማነ ፀጋዬ የሮተርዳም ማራቶንን ያሸነፈው በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ48 ሰኮንዶች ነበር፡፡ በዱባይ ማራቶን ስሳተፍ 10ኛ ደረጃ ባገኝም የግሌን ምርጥ ሰዓት አስመዝግቤ ነበር ያለው አትሌቱ  ኦሎምፒኩ 119 ቀን ሲቀረው ሰዓቴን አሻሽዬ ለኦሎምፒክ ተሳትፎ ለመብቃት በያዝኩት ዓላማ በሮተርዳም ማራቶን ተካፍዬ ውድድሩን በማሸነፍና በታሪክ 3ኛ ፈጣን ሰዓትን በማስመዝገብ ተሳክቶልኝ ነበር ይላል፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ግን  ከኦሎምፒክ የማራቶን ቡድኑ ውጭ ሲያደረገኝ የሰጠው ምክንያት አላሳመነኝም በማለት ለስፖርት አድማስ የተናገረው አትሌት የማነ ፌደሬሽኑን ለምን እንዳልመረጠኝ ጠይቄ የሰጠኝ ምላሽ በውስጥ አሰራራችን የኦሎምፒክ የማራቶን ቡድኑን ለመምረጥ ያወጣነውን ደንብ በመተላለፍህ ያለኝ አልተዋጠልኝም ብሏል፡፡  ፌደሬሽኑ በምርጫው ወቅታዊ ብቃትን፤ ጤንነትን፤ ልምምድን በብቃት ማከናወንና ማሸነፍን በመከተል አትሌቶችን እንደሚመርጥና ከኦሎምፒክ በፊት በማራቶን ውድድር ለመሳተፍ ባወጣው የ90 ቀናት ገደብ ከመድረሱ 29 ቀናት ቀደም ብሎ ባደረግኩት ውድድር የኦሎምፒክ የተሳትፎ እድሌን ያበላሸ ውሳኔ ማሳለፉ አበሳጭቶኛል  ብሏል፡፡

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በኦሎምፒክ ቡድኑ ምርጫ ላይ በሚከተለው አሰራር ግልፅነት ይጎለዋል ያለው አትሌት የማነ በአጓጉል ደንብና የአድልኦ አሰራር የአትሌትን የረጅም ጊዜ ህልም እንዴት ሊጨናግፍ እንደሚችል ህዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ ብሎ ተናግሯል፡፡ ማንም አትሌት አስፈላጊውን ውጤት ይዞ እና ተገቢውን ሚኒማ አሟልቶ ከኦሎምፒክ መድረክ መቅረት የለበትም ያለው አትሌቱ በእንዲህ አይነት ውሳኔዎች በመማረር አትሌቶች ሌሎች አማራጮችን ለመከተል እንዳይገደዱ ስጋት አለኝ ብሎ የሁላችንም ፍላጎት በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ የትውልድ አገራችንን በመወከል  ታሪክ ለመስራት መሆኑን በማሰብ ፍትሃዊ የምርጫ ሂደት እንዲኖር በሚል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የ26 ዓመቱ አትሌት የማነ ፀጋዬ በጎዳና ላይ ሩጫ በተለይ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን የውድድር መደቦች የሚሳተፍ ነው፡፡ በ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርሊን ላይ በማራቶን 4ኛ ደረጃ ያገኘበትን ውጤትም አስመዝግቧል፡፡

 

 

Read 16599 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 10:48