Print this page
Saturday, 23 November 2019 12:02

ፍቅር እውር … አሉ?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

   በማህበራዊ፣ በመንፈሳዊ ወይም በህጋዊ መንገድ  በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መካከል ጥምረት ሲፈጠር ትዳር ተመሰረተ ይባላል፡፡ ይህ ጥምረት ጋብቻ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የጋብቻው ስነስርአት በተለያዩ ሁኔታዎች ማለትም የፊርማ ስነስርአት እንዲሁም መብል መጠጥ ተዘጋጅቶ ወዳጅ ዘመድ ሲጋበዝ ደግሞ ሰርግ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ስርአት ያለፉ ግለሰቦች በህግ ትዳራቸውን እንደፈጸሙ ይታመናል፡፡ በእርግጥ የሰርጉ ስነስርአት እንደየሀገሩ፣ እንደየባህሉ፣እንደ የግለሰቦቹ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል፡፡
 ------////------
እኔና ጉዋደኛዬ በወልድያ በአንድ መንደር አብረን እየተደባደብን አድገን አብረን ተምረናል፡፡ የመፋቀርን ትርጉም በውል ሳናውቀው ነገር ግን ውስጣችን የሚነግረንን ነገር እያዳመጥን የታዳጊነት ዘመናችንን ስንጨርስ ጉዋደኛዬ ቀድሞኝ ከምንኖርበት ራቅ ብሎ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ለትምህርት ሄደ፡፡ መፋቀር የሚለውን ትርጉም ሁለታችንም ያወቅነው ያን ግዜ ይመስለኛል፡፡ እሱም ትምህርቱን ከማጥናት ይልቅ ለእኔ የፍቅር ደብዳቤ ሲጽፍ፤ ፖስታ ቤት ሄዶ ሲልክ፤ ገንዘብ ሳይኖረው ደግሞ መኪና ተራ ሄዶ ደብዳቤውን መላክ ትልቅ ስራው ነበር፡፡ እኔም መማሬን ትቼ ደብዳቤ መጠበቅ፤ ሲደርሰኝ እያለቀስኩ ማንበብ፤ በሕልም ሆነ በእውነቱ በመንፈሴ እሱን መመልከት ብቻ ሆነ ስራዬ:: በአንድ ወቅት እንዲያው ብድግ ብዬ ከአባቴ ሳንቲም ሰርቄ እሩቁን መንገድ አቋርጬ ልሄድ ስል አጎቴ ያዘኝ:: በሁዋላም ከቤቱ ወስዶኝ ምን እንደከፋኝ ሲመረምረኝ አጎቴ ዘመናዊ ሰው ስለነበር ደፍሬ ነገርኩት፡፡ በቃ…እኔ ፈልጌው ሳገኘው ይዤሽ እሄዳለሁ እንጂ እንዲች ብለሽ እግርሽን እንዳታነሽ ብሎ አስጠንቅቆኝ ወደቤት ተመለስኩ፡፡ ከዚያ በሁዋላ በአጎቴ ጣልቃ ገብነት እኔና ጉዋደኛዬ ጉዳያችን ግልጽ ወጥቶ …እሱም ከዩኒቨርሲቲ መጥቶ ቃል ማሰሪያ አደረገልኝ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ሶስት አመት ተምሮ ሲመረቅ ወዲያው ወደትዳር ገባን፡፡ አይ የእነዚህ ልጆች ኑሮ…እንዲያው ምን ይመስል ይሆን በሚል የወደፊቱን ለማየት ሁሉሰው ጉዋጉዋ፡፡ነገር ግን አንድ ልጅ እንደወለድን ሁሉነገር እየተበላሸ መጣ፡፡አልቀረም ወንድ ልጅ ደግመን ወለድን፡፡
ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ሆነ፡፡ ተሰለቻቸን፡፡ ያ…ብን አድርጎ ሊያጠፋን የነበረ ፍቅር አብረን መኖር ስንጀምር አምስት አመት እንኩዋን ሊያቆየን አልቻለም፡፡ ነጋ ጠባ ሽምግልና ሆነ፡፡ እኔ በእሱ ፍቅር ስከንፍ ትምህርቴን እየወደቅሁ አስረኛን ክፍል እንኩዋን ሳልሸገር ነበር የቀረሁት፡፡ ስለዚህ እራሴን ለመርዳት አልቻልኩም፡፡ እሱም ለካስ ሌላ ወዶ ኖሮ…እርግፍ አድርጎ አባቴ ላይ ጥሎኝ እብስ አለ፡፡ እንግዲህ ይህን ምን ትሉታላችሁ? ለካስ መፋቀር ማለት ስሜት የሚገዛው ዝም ብሎ መጉዋተት ማለት ነው፡፡ የተፋቀረ ሁሉ በትዳር አብሮ ይዘልቃል ማለት አይቻልም፡፡ በእርግጥ እድለኞቹ ይዘልቁ ይሆናል፡፡ ፍቅር እውር ነው አሉ?
ስናፍቅሽ ይርጋ ከደሴ
ስናፍቅሽ እንደገለጸችው ዛሬ የሰላሳ አመት እድሜ ያላት እናት ናት፡፡ ገና በልጅነትዋ ያፈቀረችው ሰው ሁለት ልጅ አስወልዶአት ኑሮውን ግን መጋራት ስላልፈለገ ተለያየተዋል፡፡ ይህም የሚያሳየን ‹‹ፍቅር መኖሩ ብቻ ትዳርን ለመምራት በቂ አይሆንም›› የተባለውን የባለሙያዎች ምክር ነው፡፡
ትዳር አንዱ ለአንዱ ደጋፊ፣ ግልጽ፣ አፍቃሪ፣ ታማኝ፣ ኑሮንና ቤተሰብን ጨምሮ  የሚመለከተውን ሓላፊነት እንደሚወጣ ቃል የሚገባቡበት የኑሮ ኮንትራት ነው:: ትዳር ማለት ሁለት የማይተዋወቁ ሰዎች፣ ከተለያዩ ቤተሰቦች የተገኙ፣ በተለያየ የአኑዋኑዋር ልማድ ያደጉ ሰዎች በፍቅርም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ተገናኝተውና ተፈቃቅደው በአንድነት ለመኖር የሚወስኑበት ትልቅ ማህበራዊ ተቋም ሲሆን እነዚህ የትዳር አጋሮች አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በሃሳብ የተለያዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቀድመው ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ የትዳር ጥበቡ ሁለት የተለያየ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ልዩነታቸውን ተቀብለው አንዳቸው የአንዳቸውን ስሜት ተረድተው በመግባባት ሊኖሩ የሚችሉበት መሆኑ ነው፡፡
ትዳር ሲፈጸም የተጋቡት ጥንዶች ላይ መብትና ግዴታዎችን ይጥላል ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ  የተወሰኑትን ለመግለጽ ያህል፡-
ባል ወይም ሚስት አንዳቸው የሌላውን ዕዳ በሀላፊነት የመጋራት፣
ባል ወይም ሚስት ላይ ህመም ቢከሰት የማስታመም፣
ባል ወይም ሚስት ሀዘን ቢገጥማቸው የማስተዛዘን፣
ባል ወይም ሚስት አንዳቸው ያላቸውን ጉዳይ ሌላው የመከታተልና የመቆጣጠር፣  
ልጆችን በተገቢው ሁኔታ ውጤታም አድርጎ ለማሳደግ ሲባል በጋራ ንብረቶችን የማፍራትና የመቆጣጠር ሀላፊነት፣
ከባል ወይም ከሚስት ቤተሰቦች ጋር ግንኙነትን ማዳበር እና ዝምድናን መፍጠር የተወሰኑት ናቸው፡፡
እነዚህ መብትና ግዴታዎች እንደ የህብረተሰቡ ሁኔታ እና በህብረተሰብ ውስጥ ባሉት ቡድኖች ወይንም ግለሰቦች እንደሚያገኘው ተቀባይነት ሊለያይ ይችላል:: ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚመክሩት ማንኛቸውም ወጣቶች ትዳር የመመስረት ፍላጎት ሲያድርባቸው የሚመሩት ባላቸው ስሜት በመገፋት ሊሆን ስለሚችል ግራ ቀኙን እንዲመለከቱ በሚመለከታቸው አካላት በቤተሰባቸው ጭምር ልምድን መቅሰም፤ ትምህርትን መውሰድ፤ እንደሚገባቸውና በሚሰጣቸው መስፈርት መሰረት የሚወዱትን ሰው መመዘን ካቃታቸው ጊዜ ወስደው እንዲያዩ ማድረግ ይመከራል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ትዳር አንዴ ከተመሰረተ በሁዋላ በቀላሉ እንዲፈርስ የማይደረግ ጠንካራ ተቋም መሆኑን ተጋቢዎች እንዲረዱት ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ፡-
በጋራ የሚያፈሩዋቸው ልጆች
የሁለቱ ጥንዶች ቤተሰቦች ጉዋደኞች
ተጋቢወዎችን በማሳደግን በመንከባከብ ለወግ ማእረግ በማቃት ጭምር የተሳተፉ የአካባቢ፤ የዘመድ አዝማድ፤ የጎረቤት፤ እድር፤ ማህበር፤ የማህበራዊ ተቋማት፤
የመሳሰሉት ሁሉ ሊጎዱ እንደሚችሉ መገንዘብ ይገባል፡፡
ጥሩ ትዳር ማለት ምንም እንከን የሌለው ማለት አይደለም፡፡
ግጭት የጥንዶችን ግንኙነት የሚሰብር ሳይሆን ጥንዶችን አጅግ የሚያጠነክር ሁኔታ ነው::
ትዳር ማለት አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜዎች የሚፈተን እና ከባድ በሆኑ ትምህርቶች የተሞላ፤ ሁሉም በየግሉ የሚገባበት ታላቅ የሆነ የህይወት ክፍል ነው፡፡ እነዚያ አስቸጋሪ የሆኑት ጊዜዎች እና ትምህርቶች ህይወት ከትዳር ጉዋደኛ ጋር እንድትቀጥል እና ኑሮውም ሲጀመር ከነበረው የፍቅር ደረጃ እጅግ የጠለቀ እና የጠነከረ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ትዳር መሆን ያለበት እንደሚወራለት በፍቅር በታወረ ልብ ብቻ ተጎትተው  የሚገቡበት ሳይሆን አንዱ ላንዱ ባለው ፍቅር፣ ታማኝነት፣ አሳቢነት ተሳስቦ የሚመሰረት የህይወት ምዕራፍ ነው፡፡ የትዳር ጉዞ ግን  ሁሌ አልጋ ባልጋ አለመሆኑን የሞከሩትም ሆኑ ያልሞከሩት የሚመሰክሩት ነው፡፡
ጥሩ የሆኑ የትዳር ጊዜዎች ጠቃሚ እንደሆኑ ባይካድም ጥሩ ያልሆኑ የትዳር ጊዜዎችም ሥለራሳችን፣ ስለትዳር አጋራችን እና ስለፍቅር ተፈጥሮአዊ ሁኔታ እጅግ አድርገው የሚያስተምሩበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡
ትዳር ስንመሰርት ትክክለኛ ነው ብለን ያመንንበትን ሰው እስከመረጥን ድረስ ያ ሰው ሁሌ ደስተኛ ሊያደርገን አንደሚችል ልናስብ እንችላለን፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ የሰርጋችን እለት ኬኩን ቆርሰን ስንጎራረስ… የሻምፓኝ ብርጭቆ ስናጋጭ… በሙሽራዬ ሙዚቃ ቯልስ ስንደንስ… እስከመቼም ቢሆን አለመግባባት ሊከሰት እንደማይችል አርገን ልንደመድም እንችላለን፡፡ የገባነውን ቃል ኪዳን መተግበር የምንጀምረው ብስጭት፣ ጎልቶ የሚታይ ብቸኝነት፣ ሐዘን እና ሌሎች  አሳዛኝ የህይወት ምዕራፎች ሲከሰቱ እንደሆነም እናምናለን፡፡ በዚህ አስተሳሰባችንም በመኖር ታሪክ ውስጥ የመጨረሻውን ደረጃ እንደረገጥን አስበን ይሆናል፡፡ ነገር ግን ትዳር ማለት የኑሮ መጨረሻ ሳይሆን በደስታ እና በአስቸጋሪ  የህይወት ክፍሎች የተሞላ ነው፡፡
ምንም እንኳን የትዳር አጋራችን ጥሩ ሰው ቢሆንም/ብትሆንም ከእያንዳንዷ ደቂቃ እና ቀን የተወሰነውን ጊዜ በሱ/በሷ ሁኔታ ደስተኛ የማንሆንበት ጊዜ መኖሩን እንደርስበታለን:: ታዲያ በሁኔታዎች ስንከፋ በመጀመሪያ ደረጃ  ምን አስቸኩሎኝ አገባሁ? በቃ ትዳር ማለት ይኼው ነው እንዴ? ብለን እራሳችንን የምንጠይቅባቸው ጊዜያቶች ይመጣሉ፡፡ ትዳር አንዳንድ ጊዜ ከመልካም ነገር የራቀ …ነገር ግን ከገመትነው በላይ ደግሞ ታላቅ ዋጋ ያለው የህይወታችን ታላቅ ምዕራፍ መሆኑን ግን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህ በትዳር ላይ ሆነን የሚገጥሙንን አለመግባባቶች ሁሉ በእርጋታ መፍታትና ኑሮው እንዲደረጅ እንዲጠነክር የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባን መዘንጋት አይገባም፡፡ Yolanda Gault Caviness በ“Redbook” magazine እንደጠቁሙት፡፡

Read 13532 times