Saturday, 23 November 2019 12:32

የኢህአፓ አዲሷ ሊቀ መንበር ስለ ፓርቲያቸው--

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   - የመጀመሪያ ግባችን ምርጫ ማሸነፍ ሳይሆን አገር ማረጋጋት ነው
           - ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሉ እንደግፋለን
           - ከዚህ በኋላ አሃዳዊት ኢትዮጵያ መቼም አትፈጠርም
           - አሁን በኢትዮጵያ ልክ ያልሆነው ነገር እየበዛ ነው

          ወ/ሮ ቆንጂት ብርሃነ ይባላሉ፡፡ ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነው በፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩት፡፡ የ1960ዎቹ አብዮት ጠንሳሽና ተዋናይ የነበረው የ“ያ ትውልድ” አባል ናቸው፡፡ በትምህርታቸው “ሰቃይ” ከሚባሉት ተማሪዎች አንዷ የነበሩት ወ/ሮ ቆንጂት፤ ህልማቸው የሳይንስ ፕሮፌሰር መሆን ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ለህብረተሰብ ተኮር ዘመቻዎች ቅድሚያ መስጠት ስለነበረባቸው፣ እንዳለሙት በትምህርታቸው መግፋት አልቻሉም፡፡
በአዲስ አበባ ንግድ ስራ ኮሌጅ የጀመሩትን የሴክሬቴሪያል ሳይንስ ትምህርት በእድገት በህብረት ዘመቻ ምክንያት ማቋረጣቸውን ተከትሎ፣ ፖለቲካን የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አደረጉት፡፡ በወቅቱ የፓርቲ አባል ባይሆኑም ቅሉ፣ ወጣት ሴቶችን በፖለቲካ በማንቃትና በማታገል በትጋት መንቀሳቀሳቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ኢህአፓ በህቡዕ ባቋቋማቸው የጥናት ክበቦች አማካኝነት የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምን ጥንቅቅ አድርገው ያጠኑት ወ/ሮ ቆንጂት፤ የኢህአፓ ወጣቶች ሊግ አባል በመሆንም ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡ ወጣቶች እየታደኑ ‹ኢህአፓ ናችሁ› ተብለው ወህኒ በሚታጎሩበትና በሚገደሉበት ወቅት እሣቸውም ከእስር አላመለጡም፡፡ በ1970 ዓ.ም ለ11 ወራት በታሠሩባቸው ጊዜያት ግርፋትና ከፍተኛ ማሰቃየት እንደተፈፀመባቸው ይገልጻሉ፡፡
 ከእስር በተፈቱ ጊዜ አብዛኞቹ የኢህአፓ ታጋዮች አንድም ተገድለዋል፤ አሊያም ተሰድደው ነበር፡፡ በዚህ ተስፋ ቆርጠው ፊታቸውን ወደ ትምህርት አዞሩ - ቤተሰባቸውን ለማስደሰት፡፡ በድጋሚ ማትሪክ ተፈትነው  ዩኒቨርስቲ በመግባትም ኢኮኖሚክስ ማጥናት ጀመሩ፡፡ የሁለተኛ አመት ተማሪ እያሉ ግን ችግር ገጠማቸው፡፡ ከኢህአፓ ጋር በተያያዘ ታስሮ የነበረው ወንድማቸው መገደሉን ተከትሎ፣ ሃዘን ውስጥ በመግባታቸው ውጤታቸው ተበላሽቶ ትምህርታቸውን አቋረጡ፡፡ ከዚያም ትዳር መስርተው ልጅ ወለዱ፡፡ ትምህርቱን ግን ትተው አልተውትም:: ያቋረጡትን የኢኮኖሚክስ ትምህርት በመቀጠል ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ፣ በአራት ዓመት መጨረስ የነበረባቸውን ትምህርት፣ በሰባት ዓመት አጠናቀው ድግሪያቸውን ወሰዱ::     
‹‹ኢሕአፓ በተሰራበት አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ የተነሳ በወጣቱ ትውልድ ውስጥ በማይገባ መልኩ ተስሏል›› የሚሉት ፖለቲከኛዋ ወ/ሮ ቆንጅት፤ ይሄን አመለካከት ለመቀየርና ለማስተካከል በማሰብ ሁለት መጻሕፍትን ለንባብ ማብቃታቸውን ይናገራሉ:: የመጀመሪያው በ2002 ዓ.ም ያወጡት ‹‹ምርኮኛ›› የተሠኘ ስለ ኢሕአፓና ታጋዮቹ የሚተርክ ልቦለድ መጽሐፍ ሲሆን ሌላው የኢሕአፓን የትግል መንገዶች የሚተርክ ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› የሚል ልቦለድ ነው፡፡ እኒህ መጻህፍት የፓርቲውን ገጽታ ከማደስም ባሻገር ለዓመታት ከተለዩዋቸው የኢሕአፓ የቀድሞ አመራሮች ጋር ዳግም አገናኝቷቸዋል፡፡ እንዴት? የታሪኩ ባለቤት ያብራራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በቅርቡ የኢህአፓ ሊቀመንበር ሆነው ከተመረጡት ጎምቱ ፖለቲከኛ ወ/ሮ ቆንጅት ብርሃነ ጋር በፓርቲው እንቅስቃሴ፣ ዓላማና ራዕይ ዙሪያ   ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡

                ከኢሕአፓ ጋር በድጋሚ ግንኙነት የፈጠሩት እንዴት ነው?
‹‹ምርኮኛ›› የተሰኘ መጽሐፌ መውጣቱን ተከትሎ፣ አሜሪካ በሄድኩበት ወቅት ከበርካታ የኢሕአፓ ታጋዮች ጋር ተገናኘን፡፡ ኢሕአፓ በአሜሪካ ቢሮ እንዳለው አየሁ፡፡ ይሄ በጣም ገረመኝ፡፡ ኢሕአፓን በዚያ መልኩ አገኘዋለሁ ብዬ አላስብኩም ነበር፡፡ በኋላም ግንኙነታችን እየጠበቀ ሄደ፡፡ እኔም አሜሪካ መመላለስ ጀመርኩ፡፡ በ2010 ዓ.ም ወደ አሜሪካ በድጋሚ በሄድኩበት አጋጣሚ፣ ጠ/ሚኒስትር  ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሜሪካን አገር መጡ፡፡ በወቅቱ ወደ አገራችሁ ግቡ የሚለው ቃላቸው ልቤን በጣም ኮረኮረው፡፡ ወዲያው ወደ ማውቃቸው የኢሕአፓ ሰዎች ጋ  እየደወልኩ ‹‹ለምንድን ነው የማትገቡት?›› እያልኩ መጨቅጨቅ ጀመርኩ:: ከዚያ ኢሕአፓ ካሉት ሁለት ቡድኖች በአቶ መርሻ ዮሴፍ የሚመራው፣ ጥሪውን ተቀብሎ ወደ አገር ቤት ገባ፡፡ ሌላኛው አውሮፓ ያለው ቡድን አልገባም፡፡ ኢሕአፓ ወደ አገር ቤት መግባቱን ሳውቅ፣ እኔም ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ አገኘኋቸው፡፡ ለስብሰባ ብቻ የመጣሁት ሴትዮ፣ አደራጅ ኮሚቴ ውስጥ ገብቼ እዚሁ ቀረሁ፡፡ እንግዲህ በእንዲህ ያለ መንገድ ነው ከኢሕአፓ ጋር በድጋሚ የተገናኘሁት፡፡
ኢሕአፓ ራሱን በማደራጀት በኩል በምን እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል?
ትልቁ ስንሰራው የነበረው የማደራጀት ስራ ነው፡፡ በአዲስ አበባና ሌሎች አራት ክልሎች ማለትም ደቡብ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ድሬዳዋ ላይ የማደራጀት ስራ ሰርተናል፡፡ በበርካታ አካባቢዎችም አባሎቻችንን አግኝተን እየሰራን ነው፡፡ ይሄን ስናደርግ ፈተናዎች አልገጠሙንም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ እንደ ኦሮሚያ ባለው አካባቢ፣ እንደ ልብ ገብተን፣ ልብ የሚሞላ ነገር መስራት አልቻልንም፡፡ ነገር ግን ያሰብነውን ያህል ባይሆንም፣ ለኛ እንደ መደራጀት በቂ ስራ ሰርተናል፡፡ በአማራ ክልል ትልቅ ሥራ ሰርተናል፤ ደቡብ ላይ ከሁሉም በተሻለ ተሳክቶልናል፡፡ የቀድሞ የኢሕአፓ አባላት ከየቦታው አለን ብለው በመውጣታቸው ነው ይሄን ስራ መሥራት የቻልነው፡፡ በአማራ ክልል፤ የቀድሞ የኢሕአፓ ሰራዊት አባላት፣ ‹‹እኛ ኢሕአፓ ነን›› ብለው እንደገና ራሳቸውን አደራጅተዋል። ኢሕአፓቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ በየቦታው እጅግ በጣም ብዙ አባላት እየተሰባሰቡ ነው፡፡ የኢሕአፓን የህብረ ብሄር አደረጃጀት ብዙዎች እንደሚደግፉ በየመድረኩ አረጋግጠውልናል፤ ቢሮዎችም ከፍተናል፡፡ አንዱ ቢሮ ደሴ ላይ ነው፣ ሌላው ጎንደር ነው፣ ሌላው ጎጃም ነው፡፡ ደቡብ ላይ ቢሮ ለመክፈት ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ከጠቅላላ ጉባኤዎች በኋላ እንከፍታለን፡፡ በኦሮሚያ ሻሸመኔ፣ ባሌ አርሲ አካባቢም እንንቀሳቀሳለን፤ ቢሮ ለመክፈትም ፍላጎት አለን፡፡ አባሎቻችን ራሳቸውን እያደራጁ ነው፡፡ ወጣቶችም አባል እየሆኑ ነው፡፡ ለምርጫ ቦርድም እንድንመዘገብ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተን ጥያቄ አቅርበናል፡፡  
10 ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ችላችኋል?
የተቀራረበ ቁጥር ያለው ፊርማ አሰባስበናል:: ያው 10 ሺህ ፊርማ ለማስፈረም ከአዲስ አበባ ውጪ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ለዚያ ደግሞ ሁኔታዎች እየፈቀዱልን አይደለም እንጂ የቀረውን ጥቂት ቁጥር ማሟላት አይቸግረንም:: በዚህ ጉዳይ ከምርጫ ቦርድ ጋር መልካም ግንኙነት ነው ያለን። አሁን  ጉባኤያችንን እንድናካሂድም ከምርጫ ቦርድ ተፈቅዶልናል:: በቀጣይ እንግዲህ በአዲሱ ሕግ መሰረት፣ ጉባኤያችንን ለማካሄድ ነው እየሰራን ያለነው፡፡
እርስዎ ከጉባኤው በፊት እንዴት የፓርቲው ሊቀ መንበር ሆኑ?
ወደ ኢሕአፓ በድጋሚ የገባሁት የዛሬ አመት ነው፡፡ በእርግጥ በሰፋፊ ጉዳዮች ላይ ሰርቻለሁ፤ ልምዱም እውቀቱም አለኝ:: አቅም እንዳለኝ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ግን ኢሕአፓን የሚያክል ድርጅት ለመምራት መመረጤ እድለኛ ያደርገኛል፡፡ ኢሕአፓ የበሰለ የፖለቲካ እውቀት ባላቸው ሰዎች ነው ሲመራ የነበረው:: እናም ወደ አመራር በዚህ ብስለት ልክ ብንመጣ ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁኔታዎች ለዚያ አልተመቹም:: ፓርቲው የአገር ውስጥ አመራሮች ይፈልግ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ነው የተመረጥኩት:: የቀድሞው ሊቀ መንበራችን የዜግነት ጉዳይ አለባቸው፡፡ ለዚያ ነው እኔ ወደ ሊቀመንበርነቱ የመጣሁት፡፡ በእርግጥ እነ አቶ መርሻ ወደ አገር ሲመጡ፣ ተወዳድረው የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ በሚል አይደለም፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ ኢሕአፓን ለማስተላለፍ ነው፡፡ ኢሕአፓ በጠንካራ ትውልድ ተገንብቶ፣ በተለይ ላለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያዊነት ላይ የተሰራውን የተዛባ ትርክት የሚቀይር የፖለቲካ ፓርቲ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ በተለይ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወግን ፓርቲ እንዲሆን  እንሻለን፡፡
ከቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ጋር ተያይዞ ኢሕአፓ በአሉታዊ መንገድ ነው የተሳለው:: ይሄ ፈተና አይሆንባችሁም? እንዴትስ ነው  የምትወጡት?
እየተወጣነው ነው፤ ተወጥተነዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን መጥፎ ምስሉን በአንድ ጊዜ ማጥፋት አይቻልም፡፡ እኔም ስራዬን ሁሉ ትቼ የመጣሁት፣ የዚህን ድርጅት ገጽታ ለማስተካከል ነው፡፡ አሁን ሙሉ ስራዬ ኢህአፓ ብቻ ነው፡፡ እኔም በዚህ ድርጅት ውስጥ ሆኜ ራሱ፣ ቀይ አርማ ያለበት ነገር ሳይ፣ ዛሬም እደነግጣለሁ:: እኔ ብዙ ነገሮችን ሰብሬ የመጣሁትን ሴትዮ፣ በውስጤ የተፈጠረው ጠባሳ እንዲህ የሚያደርገኝ ከሆነ፣ ምንም ሳይሰብር ቤቱ የተቀመጠውን ደግሞ እንዴት እንደሚያደርገው ይገባኛል፡፡ ፍርሃት አለ፡፡ ይሄ በጣም ይገባኛል:: ነገር ግን በነጭ ሽብርና ቀይ ሽብር ዙሪያ የነበረውን ጋግርት በመጽሐፎቻችን የገለጥነው ይመስለኛል፡፡ ብዙ መጻህፍት በዚያ ትውልድ እውነቶች ዙሪያ ተጽፈዋል፡፡ እንደው ማወቅ አልፈልግም የማይል ሰው ካልሆነ በስተቀር ብዙ ነገሮችን አጥርተናል የሚል እምነት አለኝ:: እንዲያም ሆኖ የተገደለውም የገደለውም ዛሬ በህይወት አሉ፡፡ ህወኃቶችም ከኢህአፓ ጋር ባላቸው ጠላትነት ምክንያት የማይሽር የጥላቻ ጠባሳ ጥለውበታል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ህወኃት ያለበትን ሁኔታ ስናይ ደግሞ በሠፈሩት ቁና መሠፈር አይነት እየሆነ ነው፡፡
ይሄን የሥነ ልቦና ችግር ለመቅረፍ ምን ስትራቴጂ ነድፋችኋል?
ርዕዮተ አለማዊ የሆነ ትምህርትን በመስጠት፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በማጽናት፣ በሰለጠነ መንገድ የመወያየት ባህልን ለማዳበር እንሰራለን፡፡ የሀገር አንድነትን በመስበክ፣ ለኢትዮጵያ ምን ይበጃታል የሚለውን በእውቀት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲና ፕሮግራም በማጋራት፤ ለወጣቶች ቂምና ቁርሾን ሳይሆን እውነታውን በመንገር፣ ከዚህ በኋላ የሚያሻግረንን መልካም አስተሳሰብ በተለያዩ መንገዶች በመስበክ እንንቀሳቀሳለን:: ፓርቲው ብዙ ሰነዶች ነው ያሉት፡፡ በእነዚያ ላይ ተመስርተን በሰለጠነ መንገድ እንነጋገራለን:: ህዝቡን በሠላማዊ መንገድ ሁሉ እንቀርባለን:: ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሃሳባችንን በሚገባ እናጋራለን፡፡
እንደ ኢህአፓ ያሉ ድርጅቶች አሃዳዊያን ናቸው በሚል ይተቻሉ፡፡ እናንተ የትኛውን የሀገረ መንግስት አወቃቀር ነው የምትከተሉት?
እኔ አንድ ግርም የሚለኝ ነገር አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት የትኛው ሃይል ነው ኢትዮጵያ ውስጥ አሃዳዊነትን ማምጣት የሚችለው? ለመሆኑ አሃዳዊነትን ኢትዮጵያ ውስጥ ማምጣት ይቻላል? እንዴት ይቻላል? ወይስ አሃዳዊነት አልገባን ይሆን? ብዙዎች ይሄን ሲናገሩ፣ የአሃዳዊነት ትርጉሙ ያልገባቸው ነው የሚመስለኝ፡፡ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የፌደራላዊ ስርአትን የመሠለ አወቃቀር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሀገር ብቻ ነው መሆን የምትችለው:: ግን ጥያቄው ምን አይነት ፌደራሊዝም? የሚለው ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግስት በህወኃት መሪነት ያመጣው ፌደራሊዝም፣ ዘርና ቋንቋ ላይ የተመሠረተ፣ የመለያየት ፌደራሊዝም ነው፡፡ የእርስ በእርስ ጥርጣሬን በመርጨት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ በመጥፎ ትርክት የተሞላ ፌደራሊዝም ነው፡፡ በዚያው ልክ የተቋቋሙት ክልሎችም ራሣቸውን በራሣቸው በትክክል ያስተዳድሩ ነበር ወይ? የሚለውም ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ በአንድ ድርጅት የበላይነት የቆመ መንግስት ነው የነበረው፡፡ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊው ዘርፎች ህወኃት ብቻ የበላይ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ይሄ የእውነት ፌደራሊዝም ነበር ወይ? የሚለውን ጥያቄ በትልቁ እንድናነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የጠራ ሰው፣ እንደ ትምክህተኛ እየተፈረጀ ነው የተኖረው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ብጥብጥ እኮ በዘር ጉዳይ ነው፤ ያውም በጥላቻ የታጨቀ:: ይሄን የፈጠረው እስካሁን የነበርንበት ሥርዓት ነው፡፡ እኛ ከዚህ የተለየ ፌደራሊዝም ነው የምንከተለው፡፡
ምን አይነት? ጂኦግራፊን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም፣ አሁን ባለው ሁኔታ መተግበር ይቻላል?
ብዙ ትግል ይጠይቃል፡፡ በመጀመሪያ ሰውን እንደ ሰውነቱ ብቻ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የኛ ፌደራሊዝም ሰውን እንደ ሰውነቱ የሚቀበል፤ በቋንቋና በዘር ሳይሆን ብዙ ነገሮችን ያካተተ ነው የሚሆነው፡፡ ታሪክን፣ ስነልቦናን፣ ማህበራዊ ትስስርን፣ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን፣ መግባቢያ የሚሆን ቋንቋን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ሁሉ በውስጡ የያዘ ጂኦግራፊያዊ ፌደራሊዝም ነው የምንተገብረው፡፡ ይሄ ሁሉ የሚሆነው ግን ከህዝቡ ጋር በሚደረግ ምክክር ነው፡፡ አሃዳዊት ኢትዮጵያ ግን መቼም አትፈጠርም፡፡
ርዕዮተ አለማችሁ ምንድን ነው?
ድሮ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ነበር፡፡ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ግን ሶሻል ዲሞክራሲን ነው ርዕዮተ አለሙ ያደረገው፡፡ ለወደፊትም በዚህ ርዕዮተ አለም ይቀጥላል፡፡
የኢህአፓ ራዕይና ግብ ምንድን ነው?
የፓርቲ የመጀመሪያው ግብ መንግስት መሆን ነው፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን የኢህአፓ ግብ ምርጫ ማሸነፍና መንግስት መሆን አይደለም:: እንደኛ ቀጣዩ ምርጫ ቢራዘም እንመርጣለን፡፡ እውነተኛ ሠላምና መረጋጋትን ተከትሎ፣ ምርጫ እንዲካሄድ ነው ፍላጐታችን፡፡ ሁሉም ፓርቲ በመላ አገሪቱ በነፃነትና በእኩልነት ተንቀሳቅሶ፣ ህዝብ አደራጅቶና ቀስቅሶ  ምርጫው ቢካሄድ ይመረጣል፡፡ ምርጫው ርቱዕና ፍትሃዊ የሚሆነው ያኔ ነው፡፡ አሁን ዘረኝነት ጣራ በረገጠበት ሁኔታ፣ ገና ለገና ‹ህብረ ብሔር ድርጅት ነኝ› ሲባል በጦር ሊወጋ የሚከጅል አካል በተፈጠረበት ሀገር፣ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው? በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን ማድረግ የበለጠ ሀገራዊ መረጋጋትን ማበላሸት ነው ብለን እናምናለን፡፡
መንግስት የግድ መደረግ አለበት ካለ ግን እንሳተፋለን፡፡ ቅድም እንዳልኩት በምርጫ ማሸነፍ የመጀመሪያ ግባችን አይደለም፡፡ የኛ የመጀመሪያ ግብ አገር ማረጋጋት፣ ይሄ ሂደት እንዳይቆም እንዳይጨናገፍ ማገዝ መርዳት ነው:: የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዳይዘጋ ተግተን እንሠራለን፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳን ለሚሠራ ሁሉ ድጋፋችንን ያለ ስስት እንሠጣለን፡፡  
በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አመራር ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?
ዶ/ር ዐቢይ ባመጣው መልካም እድል እኮ ነው እኛም የመጣነው፡፡ ለዚያ እውቅና መስጠት አለብን፡፡ በጣም ጥሩ ጅምር ጀምረዋል፡፡ እሣቸውና አብረዋቸው ያሉ አመራሮች፣ ስለ ኢትዮጵያ የሚሉት ነገር በጣም ጥሩ ነው፡፡ እንደ ፓርቲ፣ ልክ ያልሆነውን ልክ አይደለም፣ ልክ የሆነውን ልክ ነው እያልን ነው የምንቀጥለው:: አሁን ግን ልክ ያልሆነው ነገር እየበዛ ነው፡፡ ይሄን ለማረቅና ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረግ ጥረትን እንደግፋለን፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ልክ አይደለም፡፡ የህግ የበላይነት የለም:: መንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን መቻል አለበት፡፡ ይሄን ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡     


Read 2766 times