Print this page
Saturday, 30 November 2019 12:18

ወላጆች ለልጆቻቸው ሊያደርጉት የሚገባ…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(3 votes)

    የወላጆች ኃላፊነት ሲባል ልጆችን በመንከባከብ ረገድ የወላጆችን መብታቸውን እና ኃላፊነ ታቸውን እንዲሁም ህጻናቱን በሚመለከት አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ማለትም የትኛው ትምህርት ቤት እንደሚማሩ፤የት መኖር እንዳለባቸውና እምነታቸው ምን መሆን እንዳለበት መወሰን የሚችሉ ናቸው፡፡ አንዳድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት…
ህጻኑ የህክምና ክትትል አለው ወይንስ የለውም የሚለውን በኃላፊነት መልስ መሰጠት የሚችሉ ናቸው፡፡
ክትባቶችን በትክክል እንዲወስድ ማድረግ የወላጆች ግዴታ ነው፡፡
ህጻኑ የህክምና ክትትል ማድረግ የሚገባው ከሆነ ወላጅ የሆኑ ሰዎች ፕሮግራሙን ሳያዛቡ ልጁን ወደሕክምና ተቋም መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የልጁ ስም ምን መባል እንዳለበትና የትውልድ ጊዜውን በአግባቡ መመዝገብ ወላጆች የሆኑ ሰዎች ግዴታ ነው፡፡
ህጻኑ በአንዳንድ ምክንያት ከአገር መውጣት ቢያስፈልገው ይሁን ወይንም አይሁን በማለት መስማማት ወይም መወሰን የመሳሰሉት ነገሮች የወላጅ ግዴታዎች ናቸው፡፡ ይላል Gingerbread 11 July 2018 በድረገጹ ለንባብ እንዳበቃው፡፡ ይህ መረጃ እንደሚገልጸው ወላጆች ምናልባት አብረው ሊኖሩም ላይኖሩም ስለሚችሉ በአብዛኛው ህጻኑ የሚኖርበት ወላጆች ድርሻን ከላይ የተመለከቱት እና ሌሎች ወሳኝ ነገሮች ነገር ግን ልጁ የትም ይኑር የት አብሮ የማይኖረው ወላጅ ደግሞ ልጁን በማሳደግ ረገድ እንደ ኤኮኖሚ ማሟላት፤ የልጁን ስነልቡና እንዳይጎዳ ለማድረግ የሚያስችሉ ነገሮን በቅርብ ሆኖ በመከታተል እንዲሁም በትምህርቱ ረገድ ማድረግ የሚገባውን ነገር በማሟላት ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡  
ጋብቻ ሲፈጸም በመጀመሪያ የሚታየው የወንድየውና የሴትየዋ በፍቅር መጣመር ወይንም በቤተሰብ ደረጃ የእከሌ ልጅ የእከሌ ልጅ በሚል ዘር ተቆጥሮ የሚፈጸም እንጂ ልጅ ቢወለድ በምን መንገድ ማደግ አለበት የሚለው እሳቤ በምንም መንገድ አስቀድሞ አይነሳም፡፡ እሱ እንግዲህ ኑሮው ይስመር እንጂ ሲደርስ ይታሰብበታል ተብሎ ወደጎን የሚተው ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከሴትና ከወንድ ግንኙነት ቀጥሎ የሚገኘው ይህ የተፈጥሮ ሀብት(ልጅ) በብቃት ማደግ እንደሚገባው የሁሉም እምነት ነው፡፡ የሚወለደውን ልጅ ጥንዶች በፍቅሩ አለም ኑሮአቸውን ሲጀምሩ በቅድሚያ የሚያዩት የእነሱን መጣጣም ሊሆን ይችላል:: ከዚያ በሁዋላ ግን የማይቀረው ነገር ልጅ መውለድ ነው:: በእርግጥ ልጅ መውለድ አልፎ አልፎ የማይሳካም እንኩዋን ቢሆን በአብዛኛው ግን ከሴትና ወንድ ግንኙነት ቀጥሎ የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ሀብት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡
በአገር ደረጃ በየቤቱ የሚወለዱ ልጆች ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ተደርገው እንዲያድጉ የሁሉም ምኞት ነው፡፡ ሕብረተሰብ የሚፈልገው ሓላፊነትን የሚረከብ ትውልድ ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ያሉ ልጆችን እንዴት ማሳደግ ይቻላል ተብሎ ሲፈተሸ ምስጢሩ የሚገኘው ከቤት ውስጥ ነው፡፡ በፍቅር ተገናኝተው ቤታቸውን የመሰረቱ ባልና ሚስት የፍቅራቸው ውጤት የሆኑትን ልጆች የሚያሳድጉበት መንገድ የተስተካከለ መሆን አለበት፡፡
ባልና ሚስት ሊያደርጉት ከሚገባቸው መካከል እንዴት እንደሚፋቀሩ እና እንደሚከባበሩ እንደሚተጋገዙ ለልጆቻቸው ምሳሌ መሆን አንዱ ነው፡፡  
ንብረትን በማስተዳደር በኩል ባልና ሚስት ተግባብተው እንደሚተጋገዙ እና ተወያይተው እንደሚወስኑ ለልጆቸው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል::
ባልና ሚስት ህብረተሰብ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ በጎ እና ቀና መሆኑን በተግባር ለልጆቻቸው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኑሮአቸውን በመደገፍ ረገድ ታታሪዎች መሆናቸውን ባልና ሚስት ለልጆቻቸው ማሳየት ይገባቸዋል፡፡
ባልና ሚስት በመከባበር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ መባባልን እንዲሁም ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግና በቅርብ ክትትል ማድረግ ልጆችን በግልጽ ማወያየትን በተመለከተ ጠንክረው ሊሰሩ እና ለልጆቻቸውም በጎ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባልና ሚስት ከአልኮሆል እና ሌሎች ሱስ አስያዥ እጾች ነጻ በሆነ መንገድ ልጆቻቸውን ማሳደግ ጠበቅባቸዋል፡፡
አለበለዚያ በሆነ ባልሆነው የሚነታረኩ እና በልጆቻቸው ፊት ጥላቻን የሚያሳዩ፤ በጎ ያልሆነ ባህርይን የሚያሳዩ ከሆነ ልጆቹ ነጻ አእምሮ የሌላቸው….እነሱም ሲያድጉ ልክ በእናት አባታቸው ቤት ያዩትን ነገር ለመፈጸም የተዘጋጁ… ምናልባትም ትክክለኛው አኑዋኑዋር አባት ልጆቹን ሳይረዳ ሚስት ደግሞ ከስር ከስር እያለች የጉልበት ስራም ይሁን ሌላውን ልጆችዋን የሚመለከተውን ሁሉ የመወጣት ግዴታ እንዳለባት ወይም ሚስት ያለውን ንብረትዋን ወደጎን በመተው ልጆችዋንም ዞር ብላ ሳታይ ከባልዋ ጋርም ምንም መከባበር በሌለበት ስሜት የምትኖር ከሆነ ያንን እንደ ትክክለኛ ምሳሌ አድርገው ሊቀበሉትና እነሱም ኑሮ ሲጀምሩ ያዩትን ለመተግበር የሚዘጋጁ ሊሆኑ ይችላሉ:: እንደዚህ አይነት ልጆች ከሆነ የምናፈራው ሐላፊነትን በትክክል ሊወጣ የሚችል ልጅ ለአገር ለወገን አስረከብን ማለት ያስቸግረናል ይላሉ Dr.Maha Al-Hujailan (king Khaled university hospital) ከሪያድ፡፡
ልጅ ሲወለድ ሊደረግ የሚገባው ዝግጅት ይላሉ ዶ/ር ማሃ አል-ሁጃይላን፤
ለሕጻኑ ለራሱ የሚሆን መኝታ ቤት ሊዘጋጅለት ይገባል፡፡ ይህ በራስ የመተማመን ብቃቱን ያጎለብትለታል፡፡
ከሕጻኑ ጋር የቅርብ ግንኙት ማድረግና አብሮ መኖር፣ የፍቅርን ትርጉም ምን እንደሆነ ይረዳል::
ሕጻኑ መጠበቅና መንከባከብ፣ ኃላፊነት ምን እንደሆነ ይገነዘባል፡፡
ሕጻኑ በተጊው ስነስርአት ይዞ እንዲያድግ መርዳት፣
ሕጻኑ የት ቢማር ይሻላል የሚለውን በመመካር መወሰንና ማመቻቸት፣ባልና ሚስት በእኩልነት ውሳኔ እንደሚወስኑ ሊያይበት ይችላል፡፡
የሕጻኑን ሓይማኖት በተመለከተ በተገቢው ሁኔታ ማስተካከል፣
ሕጻኑ የህክምና እርዳታ የሚያሻው ቢሆን እናትና አባት በጋራ መመካከርና መስማማት፣
የህጻኑ ስም ለውጥ ቢያስፈልገው  እናትና አባቱ በጋራ መወሰን፣
ለሕጻኑ ንብረቶች እናትና አባት በጋራ ሓላፊነት መውሰድ፣ ተጠያቂ መሆን፣
አስፈላጊ ከሆነ ሕጻኑን በተለይ የሚከታተል የሚያስጠና ሰው በመመካር መቅጠር፣
ስለህጻናትም ሆነ ስለማንኛውም ሕጻናት ሊያውቁት ይገባል ስለተባለ ነገር ልጁን በግልጽ ማናገር፣ መምከር፣ ማሳወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ሕጻኑ ግልጽነትን ይማራል፡፡
ባልና ሚስት ተጋብተው የሚኖሩ ከሆነና ልጅ ከወለዱ ወይንም በጋራ ተስማምተው በጉዲፈቻ ልጅ ሊያሳድጉ ከወሰዱ ሁለቱም እኩል የሆነ ድርሻ እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት አብረው የማይኖሩ ከሆነ እና የተወለደው ልጅ ከእናቱ ጋር ብቻ ወይም ከአባቱ ጋር ብቻ የሚኖር ከሆነ አብረው የማይኖሩ እናት ወይንም አባት ልጁን ሲያድግ የመከታተል ተገቢውን ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን በቅርብ በመከታተልና በመተጋገዝ በአንድነት በፍቅር የማሳደጋቸው ኃላፊነት ተፈጥሮአዊ እና ግዴታ ነው ብለው ማመን አለባቸው:: አባቶች እና እናቶች የልጆችን አመጋገብ፣ ጤንነት፣ ትምህርት፣ እድገት፣ አለባበስ፣ ጽዳት፣ ባጠቃላይ ሁሉንም ነገሮች መፈጸም እንዳለባቸው ማመን አለባቸው:: ወላጆች ለልጆቻቸው ትኩረት መስጠት ያለባቸው በቤት ውስጥ ብቻም ሳይሆን  ልጆቹ ከቤታቸው ውጪ መዝናናት እንዳለበቸው ወይንም የተለያዩ እስፖርታዊ ተሳትፎዎች አቅማቸው እንደሚፈቅደው ቢደረግላቸው ተገቢ መሆኑን ወላጆች አምነው ልጆቹ ሳይጠይቁ ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል፡፡
ወላጆች ትምህርትን በተመለከተ የልጆቻቸውን ደብተር የሚያዩ፤ የሚያስጠኑ፣ ንጽህናቸውንም በተመለከተ እሚከታተሉ እሚያጸዱ፣ በትምህርት ቤታቸው የሚመገቡዋቸውን ምግቦች  የመሳሰሉትን ሁሉ በተገቢው መንገድ በመተባበር መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው የቅርብ እረዳት፣ ችግራቸውን ፈትሾ መረዳት እና መፍትሔውንም ማግኘት፣ ለልጆቹ ተገቢውን የሕይወት ምስጢር ማስረዳትና እንዴት መጉዋዝ እንዳለባቸው ማማከር፣ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወላጆች እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለልጆቻቸው የሚያሟሉ ከሆነ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ሊባል ይችላል፡፡


Read 11592 times