Saturday, 30 November 2019 12:19

‹‹በጨቋኝ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ምርጫ ማካሄድ ከባድ ነው››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

      “ኢትዮጵያ የማንን ቀለም ትያዝ?.. የማንን ድምጽ ታስተጋባ?...የማንን ዘፈን ትዝፈን? ...የማንን መንፈስ ታጓራ?...ማንንስ ትምሰል …?”

           በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጥልቀት ያለው ትንተና በመስጠት የሚታወቁት ዶ/ር መንግስቱ አሰፋ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ሰሞኑን በነበራቸው ቆይታ፣ በግጭትና አለመረጋጋት፣ በኢሕአዴግ ውህደትና በአገራዊ ምርጫ፣ በአክራሪ ብሔርተኝነትና በጥላቻ ተረክ እንዲሁም በፖለቲካ ባህል ዙሪያ በስፋትና በጥልቀት ተነጋግረዋል፡፡ እነሆ፡-


             የለውጥ ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በአገሪቱ ላይ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
በመሠረቱ ለውጥ ተብሎ የሚከናወነው ነገር ፖለቲካል ሊበራላይዜሽን ነው፡፡ የፖለቲካ ነፃነት (ሊበራላይዜሽን) ደግሞ ማህበረሰብ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ የሀገራችንን ሁኔታ ስንመለከት፤ በአብዛኛው ጠንካራ ሀገረ መንግስት ነው ያለው፡፡ ማህበረሰቡ በአንፃሩ በጣም የሠለጠነ (የተማረ) የምንለው አይደለም:: ብዙ እንቅስቃሴም አያደርግም፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከራሱ ክበብ ውጪ 50 ኪ.ሜትር በላይ ያልተጓዘ ማህበረሰብ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ብዙም እርስ በእርሱ የተዋኃደ ማህበረሰብ አይደለም፡፡ አብሮ ያኖረው ጠንካራ ሀገረ መንግስት መኖሩ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ይሄ ማህበረሰብ ብዙ ስራ አጥ ወጣት ያሉት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ ባለበት ሁኔታ በፍጥነት ፖለቲካው ነፃ (ሊበራላይዝ) ሲደረግ የሚያጋጥም ነገር ነው፤ አሁን የምናየው፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ተለይቶ የተፈጠረ ወይም የታየ ነገር አይደለም፡፡ የፖለቲካ ነፃነት (ሊበራላይዜሽን) ምልክቱ እየታየ የመጣው በኔ እይታ፣ ባለፉት 10 ወራት ገደማ ነው፡፡ ለኔ አሁንም የሚታየኝ የለውጥ ምልክቶች ናቸው፡፡
ይሄን ለምን አልክ ካልከኝ… ይሄ ህዝብ ለዘመናት ታፍኖ የቆየ፣ ነፃነትን የተነፈገ፣ የመወያየት ባህሉንም እድሉንም ያላገኘ ህዝብ ነው፡፡ ይሄ የተዘጋበት ክዳን፣ አሁን ከላዩ ላይ ሲከፈት ሚዲያው ነፃ ይሆናል:: ብዙ የራሣቸው ምኞትና ፍላጐት ያላቸው አካላት፣ ሃሳባቸውን ያለ ገደብ ወደ ሜዳው ይዘው ይፈሳሉ፡፡ ስለዚህ ጫጫታው… ግጭቱ ከዚህ የመጣ ነው የሚል ምልከታ ነው ያለኝ::  በቅርብ እንኳ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያለውን እንቅስቃሴ በማነፃፀሪያነት ማየት እንችላለን፡፡ በእነዚህ ሀገራት እ.ኤ.አ ከ2011 ወዲህ ወደ ሊበራል የሚጠጋ አስተሳሰብ ያላቸው አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች በአንድ ጐራ፣ በሌላ ጐራ ደግሞ የሃይማኖት ወግ አጥባቂነት የሚያጠቃቸው የፖለቲካ ቡድኖች አሉ፡፡ በሌላ ጐራ ደግሞ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስልጣናቸውንና ጥቅማቸውን መነጠቅ የማይፈልጉ ልሂቃን ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሃል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የስራ አጥነትና ያልተመጣጠነ የኢኮኖሚ ገቢ የተንሰራፋበት ማህበረሰብ ነበር፡፡ በሌላ በኩል፤ በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ያለውን፣ በኛም ሀገር እናያለን፡፡ አብዛኛው ህዝብ መሬቱን በአግባቡ መጠቀም አልቻለም፤አምራች አይደለም፡፡ 20 በመቶ የሚሆነው ወጣት ስራ አጥ ነው፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ ሲከሰት የነበረውን ግጭትም ስንመለከት፣ ይሄን ነገር ወደ ሃይማኖትና ብሔር ግጭት የማሸሽ ጥረት ተደርጓል፡፡ በእኛም ሃገር የእነዚህ አይነት ክስተቶች ፍንጭ እያየን ነው፡፡
ነገር ግን እንዲህ ያሉ ነገሮች በሚያስነሱት አቧራ ራሳችንን ሳናጨልም፣ ወደፊት የሚታየውን ጥሩ ተስፋ አሻግረን እየተመለከትን፣ በየጊዜው ጉድለታችንን እየቀነስንና እንከኖችን እያረምን ብንጓዝ ጥሩ ቦታ እንደርሳለን፡፡ ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲ የማሸጋገር ነገር ቀላል አይደለም:: በአንድ ወይም በሁለት አመት አይመጣም፡፡ በአንድ በኩል ከስር ከመሠረቱ ችግርን መፍታት ይጠይቃል፡፡ ይሄ ማለት የስራ ፈጠራ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማምጣት ማለት ነው፡፡ ይሄ ከ10 እና 15 አመት በላይ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል፤ በማህበረሰባችን በጦርነት መሸነፍ እንጂ በሃሳብ መሸነፍ ወይም ማሸነፍ አልተለመደም፡፡ እንደ ጀግንነት አይታይም፡፡ ይሄን የማህበረሰቡን የባህል ውርስ ያነገበ ልሂቃን፤ ውይይትን ሲለማመድ፣ በሃሳብ መሸነፍ ማሸነፍን ሲለማመድ እያየነው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው ጩኸት ሁሉ የዚህ ሂደት ውጤት ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ የለውጡ መሪዎች በሚገባ ታይቷቸው፣ በትክክል ይዘውት መጓዝ አለባቸው፡፡ የልሂቁ መቻቻል ማጣት የፖለቲካ ውይይት ልምምድ ውጤት መሆኑን መገንዘብም ያስፈልጋል፡፡ የለውጥ ሃይሉ፤ ሀገረ መንግስቱ በሃይል የተመሠረተ እንደመሆኑ፣ ልሂቃኑ ህዝብን በዚህ ያለፈ ታሪክ ዙሪያ እያሰባሰቡ መሆኑን ተረድቶ፣ ‹‹ምን ያህል በጥበብ ያስኬደዋል›› የሚለው ነው - ቀጣዩ ጥያቄ:: ትልቁን መዳረሻ ግብ አይቶ፤ ይሄን ለውጥ ማስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ አሁን በሚታዩት ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚተኮር ከሆነ ግን የትም አይደረስም፡፡
የአገራችን የግጭትና አለመረጋጋት ዋና ተዋንያን እነማን ናቸው?
የኛ ሀገር የፖለቲካ ባህል የተገነባው በሴራ ነው፡፡ ሌላው ላይ ጐል በማስቆጠር ስኬቱን የሚለካ የፖለቲካ ባህል ነው ያለን፡፡ በመፈረጅ፣ በማጥቃት፣ በማጥላላት ነው ፖለቲካችን የሚታወቀው፡፡ በሌላ በኩል፤ ያልተማረ፣ በአግባቡ ያልሠለጠነ ማህበረሰብ፣ እንዲሁም በቀላሉ ስሜት ኮርኩሮ ለማንቀሳቀስ ቀላል የሆነ ስራ አጥ የወጣት ሃይል አለ፡፡ ይሄ ወጣት ባለፉት ዘመናት፣ የጥላቻ ትምህርቶችን ሲማርና ሲሰማ ነው የከረመው፡፡ ይሄ ሁሉ የግጭት ተዋናይ የመሆን እድል አለው፡፡ ነገር ግን ለውጡን የሚመራው አካል፣ ይሄ ችግር በሚገባ ገብቶታል ወይ? የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ:: እኔ፤ ‹‹ተጠያቂው ይሄ አካል ነው›› ለማለት ብቸገርም፣ ፖለቲካችን ስልጡን አለመሆኑ ግን አንዱ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሣሌ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን ያየነው ስድድብ ነው፣ መጠላላት ነው፤ ከነጠላቸው፣ ከድርቆሻቸው፣ ከስንቃቸው ጋር ተሸክመውት የሄዱትን ባህል ነው ያየነው፡፡ ስለዚህ እዚያም ሄደው ይሳደባሉ፤ ይፈርጃሉ፡፡ እዚያ የተፈጠረው የዚሁ የሀገር ቤቱ ነፀብራቅ ነው ማለት ነው፡፡ በሰለጠነ አገር ላይ የሚኖሩት እየተሳደቡ ‹እደበድብሃለሁ… አነጥፍሃለሁ› የሚል ዛቻ ከዛቱ፣ እዚህ ያለውም ቢዝትና ድንጋይ ቢያነሳ ብዙም አይደንቀኝም፡፡ ዋናው ተጠያቂው፤ የፖለቲካ ባህላችን ነው፡፡ በዚህ መሃል ግን ከሚገባው በላይ ሄደው ነገሩን ሲለጥጡ የነበሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱ አንዳንድ ጊዜ ተው ቢባሉ፣ በህግም ቢገሩ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ነጥዬ፣ እገሌ ነው ዋና ተጠያቂው ማለት አልችልም፡፡ አጠቃላይ የፖለቲካ ባህላችን ብልሽት ነው፣ በሁሉም ላይ የሚንፀባረቀው፡፡ ስለዚህ በሂደት ይሄን የፖለቲካ ባህል በተሻለውና በሠለጠነው እየቀየሩ፣ እየተለማመዱ መሄድ ነው… ከገባንበት አዘቅጥ ሊያወጣን የሚችለው፡፡
አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዴት ይገልጹታል?
እየውልህ… የድሃ ሀገር ፖለቲካ ልክ እንደ ቁስል ነው፡፡ ቁስል የሚሰበስበው ቆሻሻን ነው፣ ባክቴሪያን፣ ዝንብን ነው፡፡ የድሃ ሃገር ፖለቲካም እነዚህን ሰዎች ነው የሚሰበስበው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢውን፣ በአቋራጭ ሃብት ፈላጊውን፣ በጥላቻ፣ በዘመቻ ማሸነፍ የሚሻውን ነው የሚሰበስበው፡፡ የሃሳብ ድሃውን… የነጠፈውን ነው በብዛት የሚሰበስበው፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ አሻጋሪ ሀሳብ ከማምጣት ይልቅ የሚጠቀሙት፣ ለእነሱ ማሸነፍ ብቻ የሚመቻቸውን ቀላሉን ታክቲክ ነው። እነዚህ አካላት አሁን እየተጠቀሙ ያሉት በቀላሉ የወጣቶችን ቀልብ የሚገዛውን ነገር  ነው፡፡ ለዚህ ነው ከአሻጋሪ ሀሳብ ይልቅ ስሜት ገዝፎ የምናየው፡፡
በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ምንድን ነው?
ኢትዮጵያን የሚያድናት ውይይትና የሰከነ ንግግር ብቻ ነው፡፡ አንዳንዴ ደስ የማይሉ የውይይት አይነቶች ቢሆኑም መለመድ አለባቸው፡፡ ማዶና ማዶ ሆኖ፣ በራሳቸው ዙሪያ የሚመስላቸውን እያቧደኑ፣ ገንዘብ እያሰባሰቡ መቀጠል የትም አያደርስም፡፡ አንዱ ሌላኛውን በማብሸቅ፣ በመሳደብ፣ በማንጓጠጥ፣ ‹እኛ እና እነሱ› እየተባባልን ባለንበት ሁኔታ…ብዙ ርቀት መጓዝ አንችልም፡፡ የአንዱ ስኬት ለአንዱ ውድቀት እየሆነ ከቀጠለ ጥሩ አይደለም:: ይሄን ወደ መስመር ለማስገባት በአንድ መልኩ መንግስት አቋሙን በግልጽ መናገር አለበት:: የሚሰራቸውንና የማይሰራቸውን ነገሮች በዝርዝር መግለጽ ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ ለውጡን እያስተዳደረ ያለው መንግስት፤ የሕዝብ ግንኙነት ችግር አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ ቀይ መስመር ብሎ ያስቀመጣቸው ሲታለፉ እንደማይታገስ በተግባር ማሳየት ይኖርበታል:: አሁን ያለንበት የፖለቲካ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው በሚል ሰበብ፣ግልጽ ወንጀል መሸፈን የለበትም:: ወንጀልና ፖለቲካ መለየት አለበት፡፡ መታገስ ሌላ ነገር ነው፤ የሕግ የበላይነት ሌላ ነገር ነው:: እነዚህ ጉዳዮች መለየት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል፤ የለውጥ ሂደቱ በራሱ አካታች መሆን አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነ በሚቀጥሉት 6 ወራት የሚኖረው የፖለቲካ ክርክር፤ሕገ መንግስቱንና የፌደራል ስርአቱን የማዳንና የማፍረስ ጉዳይ ላይ ነው የሚሆነው፡፡ ይሄ አላስፈላጊ የሆነ ውዝግብ ነው ሊያመጣ የሚችለው፡፡ ስለዚህ ሁሉን አካታች እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ለአካታችነት የሚከፈለው ዋጋም ቢከፈል ጥሩ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ ብሄራዊ ውይይት ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ የቱኒዚያ ሽግግር የተሳካው በአንድ ጊዜ አይደለም፡፡  ከሁለት ጊዜያት በላይ ብሄራዊ ውይይት ተደርጎ ነው፡፡ እነሱ እንኳን የማንነትና የሃይማኖት ጥያቄ ሳይኖራቸው፣ ከአንድም ሁለቴ ተቀምጠው መወያየት ነበራቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ ከዚህም በላይ ተደጋጋሚ ውይይቶች ያስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ነገር ዝም ብሎ ተከድኖ ይብሰል የምንለው አይደለም፡፡ ተነጋግረን ተማምነን፣ ዘግተን መሄድ ነው ያለብን፡፡ ምክንያቱም ችግሩ የማንነት ፍለጋም ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ፍለጋ በአንድ በኩል አለ፣ ብሄራዊ ማንነት ፍለጋ ደግሞ በሌላ በኩል አለ፡፡ ስለዚህ ለእንዲህ ያለው ችግር ወደ መፍትሄ የሚወስደው፣ ብሔራዊ ውይይትና መግባባት ነው፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ ሊግባቡ የሚችሉት በዚህ መንገድ ስንሄድ ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መበላሸት ዋነኛ ምክንያቱ፣በአማራና በኦሮሞ ልሂቃን መካከል ያለው ችግር ነው የሚሉ አንዳንድ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
የሁለቱ ልሂቃን አለመግባባት፣ የአገሪቱን እጣ ፈንታ በመወሰን በኩል ድርሻው ምን ያህል ነው? እኔ ከዚህ በፊት በዚህ ጉዳይ በተከታታይ ስጽፍ፣ ሚዲያ ላይም ስናገር ነበር፡፡ አንድ ኖርማን ዌንዋይን የሚባል ምሁር አለ፡፡ ይሄ ሰውዬ ‹‹Negotating Nationalism›› ይላል:: በአማርኛ (ህብረ ብሄራዊ ማህበረሰብ ውስጥ አቻቻይ ሁኔታ መፍጠር) ልንለው እችላለን:: ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ  (Multinational) ነች ከተባለ፣ በአገረ መንግስቱ ውስጥ ብዙ ብሄሮች አሉ ማለት ነው፡፡ ሃገረ መንግስቱን እንደ አካል ብንመለከት፣ በውስጡ ያሉ ብሄሮች ደግሞ ንኡስ አካላት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ በአንድ ግዙፍ አካል ውስጥ ብዙ መናፍስት አሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ብዙ መናፈስት አንዳንዴ ሊጋጩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የብሄር ግንባታ ነበር፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ብሄር ግንባታን ማየት እንችላለን፡፡ የአማራ ብሄር ግንባታ አለ:: እነዚህ የብሄር ግንባታ ፕሮጀክቶች ደግሞ ሊጋጩ ይችላሉ። እነዚህ በብሄር ግንባታ ውስጥ ያሉ አካላት፣ ኢትዮጵያ በምትባለው አገር ስያሜ… ቅርጽ ሊጋጩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የማንን ቀለም ትያዝ? የማንን ድምጽ ታስተጋባ? ማንን ትምሰል? የማንን ልብስ ትልበስ? የማንን ዘፈን ትዝፈን? የማንንስ መንፈስ ታጓራ?... ሁሉም የራሱ መናፍስት ነው ያለው፡፡ ስለዚህ አሁን ጥያቄው፤ ኢትዮጵያ የማንን መናፍስት ታጓራ የሚለው ነው? የማንን ቀለም ታድምቅ?… የኦነግን፣ ኦዴፓን፣ አዴፓን፣ አብንን ወዘተ -- ሁሉም ግን የሚፈልጉት… ኢትዮጵያ በማን መልክ ትመራ የሚለውን ነው፡፡ ደራሲ ሃብታሙ አለባቸው ምን ይላል… አሜሪካን ከተመለከትን… አሜሪካ እንደ አገር የፖለቲካ ፎርም አላት። ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ሁሉም ተከባብሮ የሚኖርባት፣ ሁሉም መብቱ የተከበረባት አገር ናት፡፡ የአሜሪካ አገረ መንግስት ይዘቱ ግን ወንድ ነው፣ ፕሮቴስታንት ነው፣ ነጭ ነው፣ ስለዚህ በአንድ ፎርም ውስጥ ብዙ ይዘቶች አሉ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የማን ይዘት… የማን ድምፀት ይኑራት… የሚለው ነው አወዛጋቢው:: ህወሃት በጋራ ከተገፋ በኋላ አሁን እየተገፋፉ ያሉት ሁለቱ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ይሄ መገፋፋት ደግሞ አገርን ሊያፈርስም ሊያስቀጥልም ይችላል፡፡ እንዴት ነው ሊያስቀጥል የሚችለው ከተባለ -- እነዚህ ሁለት አካላት በተለይ በኢኮኖሚያዊ ትስስር ተስማምተው መሄድ አለባቸው፡፡ በፖለቲካ ትስስር መቼውንም መስማማት ስለማይችሉ በኢኮኖሚያዊ ትስስር ላይ ተስማምተው… ሌላውን በዝምታ ሊያልፉት ይገባል፡፡ ዝም የሚባለውን ነገር ምናልባት አንዱ ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስት ሊያነሳ ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህን ድምጸቶች እንዳይረብሹ ለመቀነስ አስቀድሜ እንዳልኩት ለውጡን አካታች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ድምጸቶቹ እንዳይጋጩ ለማድረግ አካታችነቱ ወሳኝ ነው። ስለዚህ ጠንካራ አገረ መንግስት መስርቶ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ማጠናከሩ ነው በተሻለ የሚያሸጋግረው፡፡ ይሄ ካልሆነ ሌላው አማራጭ ፌደሬሽኑን በጠንካራ ሕግ ማስከበር ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ስትገነባ የሚቀንሱ ውጥረቶች ናቸው፡፡
የኢሕአዴግን ውህደት በተመለከተ አስተያየትዎ ምንድን ነው? በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዴት ይገለጻል?
የኢሕአዴግና አጋሮቹ መዋሃድ ትልቅ የፖለቲካ አቅጣጫ ለውጥ ነው፡፡ ወዴት ይሄዳል ከተባለ፤ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ትልቅ የፖለቲካ አቅጣጫ ለውጥ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በ1983 ዓ.ም የተለወጠው አገዛዝ አይደለም፤ የአገረ መንግስቱ ቅርጽ ነው የተለወጠው:: አገረ መንግስቱ ሬደሬት ነው የተደረገው:: ስልጣን ነው የተከፋፈለው፣ ፖሊሲ ነው የተቀየረው:: አጠቃላይ ነገር ነው የተለወጠው፡፡ ስለዚህ ስርአቱ በራሱ ዜማና ቅላጼ ልሂቃን ፈጥሯል፣ ማህበረሰብ ቀርጿል፡፡ ቢሮክራሲ ፈጥሯል፣ በሱ ዜማና ቅላጼ አብዛኛውን ሰው ቀርጿል:: ከሱ በተቃራኒ በፍጥነት ከሱ ጡንቻ ስር ፈልቅቆ መውጣት ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ አሁን የተደረገውም ውህደት ከዚህ አንጻር፣ ትልቅ ተፈልቅቆ የመውጣት እርምጃ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ግን ትልቅ ትዕግስትና የበሰለ ስሌት ያስፈልጋል። እርምጃው ትልቅና የኢትዮጵያን ቀጣይ እድል ማለትም አምባገነናዊ ወይስ ዴሞክራሲያዊ የሚለውን የሚወስን ነው፡፡
ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ አሁንም ሁለት የፖለቲካ ጎራዎች ተፋጠዋል፡፡ እርስዎ ከየትኛው ወገን ነዎት---?
እውነቱን ለመናገር ቀጣዩ ምርጫ ከባድ ነው:: ለዚህ ነው የለውጡን ሂደት፣ ሁሉን አካታች ይሁን የምለው፡፡ ይሄ ሲሆን ‹‹በመጀመሪያ ‹ኢትዮጵያ› ላይ እንስማማ›› የሚለውን መነጋገር ይቻላል፡፡ ‹‹ምርጫ አድርገን ስልጣን እንቀራመት ወይስ ባለው ሥርዓት ጠንካራ የአገረ መንግስት ስርአት እየገነባን፣ ዴሞክራሲን አጎልብተን ወደ ምርጫ እንግባ?›› የሚለውን ለመነጋገርም ሂደቱ አካታች ቢሆን ጥሩ ነው፡፡  አሁን ያለው ሁኔታ በራሱ ለምርጫ የተስተካከለ ነው ብዬ አላስብም፡፡ በዚያ ላይ የፖለቲካ ምህዳሩ በራሱ… በተለያዩ ነገሮች የተመረዘ፣ በጣም ጨቋኝ የሆነ ምህዳር ነው፡፡ ሰው ለመንቀሳቀስ የሚቸገርበት፣ ከአንዱ ወደ አንዱ መሄድ የከበደበት፣ የግድያ ሙከራ የሚያሰጋበት፣ የጦር መሳሪያ እንደ ልብ የሚፈስበት፣ የሰው እንቅስቃሴን ከስጋት ለመከላከል ያልተቻለበት --- ሁኔታና ጊዜ ላይ ነን፡፡ በዚህ ጊዜ ‹ምርጫ ይካሄድ› የሚለው ነገር ለኔ አዋጭ አይደለም፡፡ እንደ አገር ሲታሰብ ነገሩ ከባድ ነው። የምርጫ ሂደትና ከምርጫ በኋላ የሚከሰቱ ቀውሶች፤ አንዳንዶቹ ተፈጥሯዊ ቢሆኑም ይሄ ጨቋኝ የፖለቲካ ምህዳር ተጨምሮበት፣ ነገሩን ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ነው የማስበው፡፡ ከዚህ አንጻር፤ እኔ የምርጫን ጉዳይ፣ አደገኛ ፕሮጀክት አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ ዋጋ የሚያስከፍለን አይነት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ሆኖም ምርጫው ይደረግ፣ አይደረግ በሚለው ላይ መናገር አልችልም። እንዲሁ ግን የሚታየኝን ስጋት ነው ለመግለጽ የሞከርኩት:: እንደኔ ብሄራዊ ውይይት ተደርጎ፣ በጨዋታው ሕግ ከተስማሙ በኋላ ወደ ምርጫው ቢገባ እመርጣለሁ፡፡    


Read 4527 times