Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 23 June 2012 07:59

“ማንነትህን ስታውቅ እውነተኛ ፍላጎትህን ታውቃለህ”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ትልቁ ነገር፤ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመግባት ከባድ አይደለም፡፡ ታሪካችንና ማንነታችንን እንድናውቅ የሚያግዙ ብዙ ድንቅ ስራዎች ትተውልን አልፈዋል፡ የኋለኛው ከሌለ አይኖርም የፊተኛው እንደተባለው ነው፡ ያ የማንነታችን ጉዞ የቱ ጋ እንደተቋረጠ አውቀን፤ የኋለኛ መነሻችንን አይተን የወደፊቱን ማስተካከል እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡

“ጥቁር ሰው” የሚለው ዘፈን ላይ የተጠቀሱ ጀግኖች አሉ፡፡ ሌሎችስ ለምን አልተጠቀሱም?

ዘፈን በባህሪው፣ በተወሰነ የደቂቃ ገደብ ውስጥ ተጠናቅቆ ማለቅ አለበት፡፡ ማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ዘርዝሮ ለማስረዳት ትንታኔውን ሰብስቦ፤ ራስ ራስ የሚላቸውን ነገሮች በምጣኔ አስቀምጦ በተቀመጠለት ጊዜ ማለቅ አለበት፡፡ ብዙ ትንታኔ የመስጠት ስልጣንህ (ፈቃድህ) የተገደበ ይሆናል፡ በተመጠነው ጊዜ ሃሳቡን ለመግለፅ የሚያስፈልጉትን ዋነኛ ናቸው የሚላቸውን በመንፈሱ ይመርጣል፡፡ ከመምረጥ በተጨማሪ አመዛዝኖ የማመጣጠን ስራም ይጠብቀዋል - የአድዋ ጀግንነት የተለያዩ ብሄረሰቦች የተሰባሰቡበት ስለሆነ፤ ይህንን ለማንፀባረቅ ማመጣጠን ይኖራል፡፡ እነዚህን ሁሉ አስማምተህ ማስኬድ ያለብህ በተመጠነ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የምትጠቅሳቸው ነገሮች የተወሰኑ ይሆናሉ፡፡ ሙሉውን ታሪክ፣ ሁሉንም ጀግኖች መጥቀስ አትችልም፡፡ ግን የሙሉውን ታሪክ የሁሉንም ጀግኖች መንፈስ የሚያሳዩ ነገሮችን መርጠህ ትጠቀማለህ፡፡ በዚህ ምክንያት፤ በስም ሳይጠቀሱ የሚያልፉ እልፍ ጀግኖች፤ እልፍ ገድሎች ይኖራሉ፡፡ የዘፈኑ ሀሳብና ስሜት በትክክል ሲዋሃድ ግን ሁሉንም ጀግኖችና ጀብዶች እንደማየት ነው፡፡

ዘፈን፤ ሁሉንም የሚዘረዝር የታሪክ መፅሃፍ አይደለም፡፡ ነገር ግን፤ በተመጠነ ጊዜ፣ በተመረጡ ባህርያት፣ የታላቁ ታሪክ መንፈስ የሚገለጥበት ነው፡፡

የተወሰኑ ጀግኖችን በማሳየት ሁሉንም ጀግኖች እንድናደንቅና እንድናከብር የሚያደርግ መንፈስ ማለት ነው?

ምልክት ከሌለ፤ የህይወት ጉዞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሞዴል፣ ሮል ሞዴል፣ የሚባለው አይነት ነው፡፡ የጀግንነት አቅጣጫ የሚያሳይ ምልክት፣ የጀግንነትን ትንታኔ የሚዘረዝር ሳይሆን ጀግንነትን በአካል፣ በህይወት በእውን የሚያሳይ ማለት ነው፡ ፍቅርን ወይም ቅንነትን እየተነተነ የሚዘረዝር ሳይሆን፤ ፍቅርን ወይ ቅንነትን ህይወት አላብሶ የሚያሳይ … ይህንን ማለቴ ነው ምልክት ማለቴ፡፡ በህፃንነት ጊዜ በምዕራባዊያን ፊልሞች ውስጥ የጀግና ገፀ ባህርያትን ስናይ፣ ውስጣችን የሚነሸጠውና ጀግና ለመሆን የምንመኘው፤ ፊልሙ ውስጥ የጀግንነት ምልክት ስለምናይ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የአገራችንን ጀግኖች በምስል ለማየት፤ ምልክትነታቸውን ለማየት ብዙ እድል አላገኘንም፡፡ የአድዋን ጀግኖች በምስል በፊልም ለማየት እድል እናገኛለን፡፡ በተለይ ደግሞ ለታዳጊዎች ጥሩ እድል ነው፡ ምልክቶችን ከራሳቸው ጋር አዋህደው መጓዝ ይችላሉ፡፡ ምልክቶች ሃይልና አቅም ይሆኑሃል፡

ለአንድ ክሊፕ ከ400ሺ ብር በላይ ወጪ ለማድረግ ፍቃደኛ የሆንከው እንዴት ነው?

ዘፈኑ በተፈጥሮው ከምስል - ከፊልም ጋር በውህደት ሲቀርብ ከፍተኛ ሃይል እንዲኖረው ታስቦ የተሰራ ነው፡፡ የመጀመሪያ ሃሳቤ፤ የጥንት ምስሎችን በማሰባሰብ ክሊፕ ለመስራት ነበር፡ ነገር ግን በዚሁ ስራ ያገኘኋቸው ታምራት እና ተስፋዬ፤ ስራውን በፍቅር የመስራት ስሜታቸው ማረከኝ፡ እያንዳንዱ ትዕይንት ምን እንደሚመስል  በንድፍ፣ በስእል ሰርተው ሲያሳዩኝ የእውነት ተግባባን፡፡ ዘፈኑ ከምስል ጋር ለመዋሃድ የተፈጠረ ነው፡፡ ክሊፑ ደግሞ ትልቅ ስራ ነው፡፡ አሳታሚው አዲካም በዚህ ሃሳብ ተስማምቶ ስራው ተጀመረ፡፡ ብዙ ሰውን የሚያረካ ስራ መሆኑ ያስደስታል፡ የክሊፑን ስራ የመሩትና የተሳተፉ በሙሉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

አፍሪካዊነት …

ሁሉም በየራሱ ልዩ የሚሆንበት ባህርይና ገፅታ አለው፡፡ የሚያመሳስሉና የጋራ የሆኑ ማንነቶች አሉ፡፡ በዚህም አፍሪካዊ ነን፡፡ ይሄ የማይለወጥ እውነት ነው፡ የአፍሪካዊነት ስሜትም የእውነት ነው፡ የየራሳችን የሆኑ ማንነቶችና ታሪኮችም አሉ፡፡ ልዩ የኢትዮጵያዊነት ስሜት አለኝ፡ ይሄም የማይለወጥ እውነት ነው፡፡ በስሜት ብቻም ሳይሆን የእምነትና የታሪክ አዋቂዎች የሚነግሩን፣ የሚያስተምሩን ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዳለን አውቃለሁ፡፡ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን፤ ከመላው አለም ልዩ ነን የሚያስብል ማንነት አለን፡፡ ለምሳሌ፤ ከኖህ በኋላ ያለውን ታሪክ የሚያወሱ መፃህፍትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኖህ ልጆች ሴም፣ ካም እና ያፌት ናቸው በሚል ይነሳና፤ እነዚህ ህዝቦች የሴም ልጆች፣ እነዚያ የካም፣ እነዚህኞቹ ደግሞ የያፌት ልጆች በማለት ይተነትናሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን የሁሉም … ማለት የሴም፣ የካም እና የያፌት ልጅነትን የያዙ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ንቡረዕድ ኤርሚያስ በፃፉት መፅሃፍ፤ የዩቶር ታሪክ በማሳያነት ተጠቅሷል፡፡ የመጀመሪያውን መልከፀዲቅ ይሉታል፡፡

በአጠቃላይ ከባህልና ከታሪክ አንፃር ኢትዮጵያ ልዩ ማንነት የያዘች አገር ነች የሚያስብል የስሜትና የሃሳብ እውነቶች አሉ፡ በዚያው ልክ ደግሞ፣ አፍሪካ ውስጥ የምንገኝ ሁሉ አፍሪካዊ ነን፡፡ ከአይነት አይነት ይኖራል፡፡ ግን የጋራችን አፍሪካዊ ማንነታችን እውነት ነው - የአንድ ጉዞ መንፈሶች፡፡

እንዲያው የአፍሪካ ፀሃይ ብንል አይሻልም?

የአፍሪካ ፀሃይ ብትላትም አፍሪካዊነቷን እየገለፅክ ነው፡፡ የአለም ፀሃይ እንደሆነች ሲነገርስ አልሰማህም? የአለም ፀሃይ ብንላት፤ የአለም አካልነቷን እየገለፅን ነው፡፡ የአባይ ውሃ ከገነት የመነጨ እንደሆነ በቅዱስ መፅሃፍ ተጠቅሷል፡፡ አዳምና ሔዋን የኖሩበት ገነት ነው፡፡ የሰው ዘር መገኛ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ምስራቅ ማለት እንደሆነ፤ ምስራቅ ማለት ደግሞ የብርሃን መውጫ፤ የህይወት መጀመሪያ እንደማለት መሆኑን እነዚህንና ሌሎች ጠቋሚ ነገሮች ስታይ፤ ኢትዮጵያ ልዩ ስፍራ እንዳላት ይሰማሃል፡፡ የህዝቡ ጥንታዊነትና የስልጣኔ ቀዳሚ ታሪኳም ይህንን የሚደግፍ ነው፡፡ ፊተኞች ኋለኞች ይሆናሉ እንደሚባለው ሆኖ፤ በኢትዮጵያ የሚታይ ይመስለኛል፡፡

“ጥቁር ሰው”፣ “አፍሪካዊ ማንነት” ብዬ የዘፈንኩት ከእውነተኛ የራሴ ስሜት በመነሳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልዩ ማንነትም እውነተኛ ስሜቴ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልዩ ማንነት ይሰማኛል የምለው፤ እንዲሁ በምኞትና በውድድር መንፈስ ከሌሎች አገሮች የገዘፈ ነገር ለኢትዮጵያ ለመስጠት አይደለም፡ እውነተኛውን ስሜቴን ለመግለፅ ነው፡ ልዩ ኢትዮጵያዊ ማንነታችንም እውነት ነው፡፡ አፍሪካዊ ማንነታችን እውነት ነው፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያዊነት አፍሪካዊነት ነው፡ አፍሪካዊነት ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡

ይሄ ደግሞ ምን ማለት ነው? የሚያምታታ የገጣሚ አባባል ነው ወይስ የምር?

አዲስ ነገር አልጨመርኩበትም፡፡ አፍሪካን ለማስተባበር የጣርንበት ታሪክ አለን፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ነፃነት በአርያነት በማየት፤ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጋር ተቀራራቢ የሆኑ ሰንደቅ አላማዎች መለያቸው አድርገዋል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያዊነት የአፍሪካ ማንነት አልሆነም ትላለህ? የአድዋ ድል የአፍሪካ ድል ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡ አፍሪካዊያን እንደራሳቸው ድል ቆጥረው ኢትዮጵያዊነትን ማንነታቸው አድርገውታል፡፡

እሺ ይሁንና ኢትዮጵያዊነት በበጎ መልኩ የሌሎች አፍሪካዊያን ማንነትም ሆኗል እንበል፡ግን እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥስ? ኢትዮጵያዊ ማንነት ሲደበዝዝ አይታይህም? እንዲያው የአድዋውን ድልና ነፃነት ተወው፡፡ እነዚያ አስደናቂ የስልጣኔ ውጤቶች … ፋሲለደስ እና ላሊበላ፤ የአክሱም ሃውልትና የሃገረ … ዛሬ’ኮ ብዙም ስሜት አይሰጡንም፡፡ ካስደነቁን እንኳ፤ በተፈጥሮ እንደበቀሉ አስገራሚ ወፍ ዘራሽ ትንግርቶች አድርገን ነው የምናያቸው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ማንነት ጋር አናያይዛቸውም፡ ኢትዮጵያዊነት፤ እነዚያን ድንቅ ስራዎች የመስራት አላማና ጥበብ እንደሆነ አይገባንም፡፡

ከማንነታችን ጋራ ተራርቀናል፤ ተጣልተናል፡፡ ራሳችንን ለመሆን አልፈቀድንም፡ የሌሎችን ማንነት በተውሶ ለመልበስና ለመምሰል እንባዝናለን፡፡

የራስህን ማንነት ስትዘነጋና ራስን መሆን ስትተው፤ የሌሎችን ማንነት ለመልበስና ለመምሰል ትደክማለህ፡፡ ከተሞቻችንን አታይም? የመጠጥና የሻይ ቤት፣ የምግብ ቤትና የሆቴል ስያሜዎች ተመልከት፡፡ ይህንን ነው ያተረፍነው፡፡ ከማንነታችን ምን ያህል እንደራቅን ያሳያል፡፡ ማንነትህን ስታውቅ ነው እውነተኛ ፍላጎትህን የምታውቀው፡፡ ራስን መግዛት ማለት ይሄ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን መገዛት ይሆናል፡፡ ለዚያውም በጦርነት ግዴታ ሆኖብህ የመገዛት መከራ ሳይሆን በፈቃደኛነት የመገዛት ውርደት ነው፡፡ የሚያሳዝን የሚያስቆጭ ጉዞ ነው፡፡

ስለ ፍቅር በሚለው ዘፈን የመጣንበት መንገድ ያሳዝናል እንዳልከው ነው?

ትልቁ ነገር፤ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመግባት ከባድ አይደለም፡፡ ታሪካችንና ማንነታችንን እንድናውቅ የሚያግዙ ብዙ ድንቅ ስራዎች ትተውልን አልፈዋል፡ የኋለኛው ከሌለ አይኖርም የፊተኛው እንደተባለው ነው፡ ያ የማንነታችን ጉዞ የቱ ጋ እንደተቋረጠ አውቀን፤ የኋለኛ መነሻችንን አይተን የወደፊቱን ማስተካከል እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ የድሮውን መነሻ ስናውቅ፤ አኩሪ ማንነታችንን እንይዛለን፤ አርአያነታቸውን እንከተላለን፡፡ ቀድሞ የተፈፀሙ ስህተቶችም እንዳይደገሙ እናደርጋለን፡፡  ማንነትህን ስትይዝ፤ ከሌሎች አገሮችም ብዙ ትምህርት ልትቀስም ትችላለህ፡ አኳኋናቸውንና የአነጋገር ቅላፄያቸውን እየቃረምን፣ የውሸት እነሱን ለመምሰል ስንባዝን ጊዜ አናጠፋም፡፡ እውነተኛ ማንነት ሲኖረን፤ የሌሎችን መልካም ጎን ማየትና እውቀት መቅሰም ትችላለህ፡፡የራሳችንን ማንነት ለማነፅ እንጠቀምበታለን፡፡በነፃነት፣በፍቅር፣በኩራትናበስልጣኔ ትኖራለህ - ራስህን ትገዛለህ፡፡ ማንነትህን ከጣልክ ግን፤በፍቃደኝነት ተገዥ ትሆናለህ፡፡ ድሮ’ኮ፤ ቅን ገዢዎች ከሁሉም በፊት በወረራ የህዝቡን ባህልና ማንነት ለማጥፋት ሲጣጣሩ የነበሩት፤ ተገዢ እንዲሆኑላቸው ነው፡፡

ይህን የምለው ለመፍረድ አይደለም፡ ለመክሰስና ለመውቀስ አይደለም፡ እንዲያውም፤ በአገራችን መወጋገዝና መወቃቀስ መብዛቱ ጥሩ አይደለም፡፡ የመጠን ልዩነት እንጂ፣ ሁላችንም የተለያዩ ስህተቶችና ጥፋቶች ፈፅመናል፡፡ በምንፈፅመው ስህተት ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲዘነጋ እናደርጋለን፡ ማንነታችን ስለተዘነገ ደግሞ ስህተት እንፈፅማለን፡፡ አንዱ ሰው ላይ ወይም ሌላው ላይ ለመፍረድ ስልጣን የለንም፡፡

የመጠጥ ቤቱን ስም በአገር ቋንቋና ትርጉም ስላልሰየመ፤ ልጁን የአገር ቋንቋ ስላላስተማረ፤ በአገሩ ተስፋ ቆርጦ ለስደት ስለተጓዘ … በደፈናው መፍረድ ትክክል አይሆንም፡ አቅጣጫ የሚያስቱ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ይልቅስ፤ እንዲህ ስደትን ለመምረጥ ወይም የአገርን ቋንቋ ቸል ለማለት የምንፈቅድበት ደረጃ ላይ መድረሳችን ያሳዝናል፡፡

ውጭ ለትምህርት ሄዶ እዚያው መቅረት እንደትንግርት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር፡፡ ግን በትምህርት ብሎ ሄዶ መቅረት ተለመደ፡፡ በምኞት አሜሪካንና አውሮፓን መናፈቅ የብዙ ሰው ህልም አልነበረም፡፡ ግን ሆነ፡፡ ከዚያ ሃብታም ወደሚባሉ የአረብ አገራት መጓዝ መጣ፡፡ ይሄም ተለመደ፡፡ አሁን ግን፤ በቀውስ ወደ ሚታመሱ አገራት ሳይቀር … በሶማሊያ ወደ የመን ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይጓዛሉ፡፡ በታንዛኒያ ሦስት ሺ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ታሰሩ ሲባል ትሰማለህ፡፡ በሞዛንቢክ፣ በማሊ ስንት ሺህ ኢትዮጵያውያን እንደታሰሩ ታስባለህ፡፡ ይሄ ነገር መጨረሻው የት ነው? እዚህ ሃገር ምን አይነት ስህተት ቢፈጠር ነው የሚል ስሜት …

ያስጨንቃል፤ ውስጥን ያሳምማል፡ ኑሮ የቸገረው ሰው፤ ልቡ ወደ ውጭ ቢማትር፤ እግሩ ለስደት ቢነሳ፤ ማናችንም ልንፈርድበት ስልጣን የለንም፡፡ ሌላ አሳዛኝ ነገር አለ፡ ብዙ ያየንበት ያ የተጓዝነው መንገድ፤ እንዲህ ያሳዝናል፡፡

በስደት ሄደው የሚጥሩ እውቀትና ሞያ፣ ጥሩ የስልጣኔ መንፈስና አቅጣጫ ለመያዝ የሚጣጣሩ አሉ፡፡ ከአገር መለየት ውስጣቸውን ቢያጎድልባቸውም፤ ራሳቸውን ጠብቀው ባጋጠማቸው እድል ሁሉ ነፍሳቸውን ይገነባሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር፤ በስደት አገር ሄደህ፤ እዚያ ከምታገኘው ባህል ጥሩውን ሳትይዝ፣ ከአገርህ ባህልም ጥሩውን ጥለህ፣ እርስ በርስ ለመተባበር አለመፈለግ፣ በፍቅር አለመተያየት ነው፡፡

ሩቅ ቦታ ሩቅ አገር ሄደህ ስትገናኝ፤ እዚህ ሩቅ ስትለው የነበረ ሰው እዚያ ቅርብ ሆኖ ሊሰማህ ይገባል፡፡ ከአንድ አገር በስደት ሄደህ፣ በስደት አገር የባሰ የመራራቅ ስሜት ስታይ ያሳዝናል፡፡

እዚህ’ኮ፣ ሲሆን ሲሆን በእውነተኛ ፍቅር፣ ቢያንስ ቢያንስ በጨዋነትና በይሉኝታ አብሮ የመኖር ባህል ይኖራል፡፡ በስደት አገር ይሉኝታዋም ስትጠፋ ማየት ያስቆጫል፡፡

ከጥንት ታሪክም ብትጠቅስ፣ ያለፉት መቶ አመታት ውስጥም፣ ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ለሚመጡ ስደተኞች መጠለያ ነበረች፡ ከአርመን፣ ከየመንና ከሌሎች አገራትም ማለት ነው፡፡

ዛሬ፤ እንደዚያ አይደለንም፡፡ በሌላም በኩል ብታስበው፤ በቀድሞ ዘመን የነበረው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የጥራት ደረጃው ከፍ ያለ ነበር፡፡

አስደናቂዎቹ የፋሲለደስ፣ የላሊበላና የአክሱም ስራዎችን ማለቴ አይደለም፡፡ ያ ሌላ ነው፣ ሚስጥሩን ለማየት ገና አልጀመርንም፡ ግን የዛሬ 50 አመት 40 አመት መለስ ብለን የቅርብ ታሪክ እንኳ ብናይ ያስደንቃል፡፡ ከሙያዊና ጥበባዊ ስራዎች ጀምሮ እስከ ከተማ እስከ ንግድ አሰራር ድረስ የተፃፈው ልዩ ነው፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሃር ድረስ ያለውን ድንቅ የከተማ አሰራር ተመልከት፡ የህንፃዎቹ ብትል የመንገዱ ጥራትና ሞገስ ልዩ ነው፡፡

በየሙያው የነበሩ ሰዎች ለሙያው ከነበራቸው ፍቅርና ክብር ጋር የስራዎቻቸው ጥራት ያስደንቃል፡፡ በኛ ሙያ በሙዚቃ መስክ ብታይ፤ ጥላሁን ገሰሰ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ማህሙድ አህመድ … በድምፃዊያን ብቻ ሳይሆን በሙዚቀኞችም የኦርኬስትራዎች ደረጃ ያስገርማል፡፡

በስዕል ጥበብ እንደ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ የመሳሰሉ አርቲስቶች፣ ስነ ፅሁፍም እንደ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ከበደ ሚካኤል፣ ሃዲስ አለማየሁ፣ መንግስቱ ለማ … በህክምናም ከፍተኛ እውቀትና ሙያ የያዙ ሃኪሞች፤ በንግድ ዘርፍም በጊዜያቸው አዲስ የጥራት ደረጃ የፈጠሩ እንደ በቀለ ሞላ የመሳሰሉ ትልልቅ ሰዎች ነበሩ፡ እነዚያን ሁሉ አዋቂዎችና ባለሙያዎች ማፍራት የቻለ ማህበረሰብ፤ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡ የሩቁን ታሪክ ካየህማ አስቸጋሪ ነው፡፡ የአክሱም፣ የፋሲለደስ፣ የላሊበላ … እነዚያን ድንቅ ስራዎች በዚያ በጥንት ዘመን ሊሰሩ የሚችሉ ባለሙያዎችንና አዊቂዎችን ያፈራ ማህበረሰብ ምን አይነት ማንነት የያዘ እንደሆነ ሲታሰብ …ጉዞው ተቋርጦ ሰፊ ክፍተት እንደተፈጠረ ያሳያል፡፡

የእነዚያ ድንቅ ስራዎችን ትርጉም መመርመርና ማወቅ ከተነሳን ደግሞ ክፍተቱ በጣም ይሰፋል፡ ይሄኛው ድንጋይ እንዲህ ተጠርቦ እንዲያ ተበጅቶ ማለት ብቻ አይደለም መመራመር፡ በዚያ የጥንት ዘመን፤ የድንቅ ስራ ሃሳቦችን በውስጣቸው ፈጥረው፤ ሃሳባቸው በመራቸው መንገድ ለመጓዝ የደፈሩና በአዲስ የጥራት ደረጃ ለመስራት የበቁ ሰዎች ናቸው፡ ምን አይነት ማንነት የያዘ አገርና ህዝብ ነው እንዲህ አይነት ሰዎች የሚኖሩት? ብዙ የሚያመራምሩ ጥያቄዎች አሉ፡፡

አስደናቂዎቹን ስራዎች እንድ ግዑዝ ቅርስ፣ የቱሪስት ፌርማታ ከማድረግ ያለፈ ነገር ካላከናወንን ስራዎቹን ገና አላየናቸውም ማለት ነው፡፡ አስደናቂዋቹ ስራዎች የማንነታችን ጉዞ የቱ ጋ አቅጣጫውን ስቶ እንደተቋረጠ ለማወቅ፤ ልንመራመርባቸው ይገባል፡፡ ይህች አገር ምን ያህል የሊቃውንት፣ የአዋቂዎችና የባለሙያዎች አገር እንደነበረች ማወቅ አለብን፡ ትልቅነታቸውን ካላወቅን፣ ትልቅ መሆን አንችልም፡፡

አገራችን የራሷ ፊደል እና ፅሁፍ ያላት መሆኗን እንደ ተራ ነገር የምንቆጥር ከሆነ፤ ወደ ተራራዉ አንወጣም፡፡ አቡጊዳ … የፊደል መጀመሪያ የሆነው አዳም፣ አልፋ፣ አብ፣ አባት የሚሉ ቃላት ውስጥ የምናገኘው የአጋጣሚ ጉዳይ እንዳልሆነ የቋንቋ አዋቂዎች ያስረዱናል፡፡ እንደ ሳምንቱ ቀናት ሁሉ፤ እያንዳንዱ ፊደል በሰባት ድምፆች ይዘረዘራል፡፡ ከ”አ” እስከ “ኦ”፡ ከአልፋ እስከ ኦሜጋ፡፡

የሁሉም አህጉሮች ስያሜ በ”አ” ድምፅ የሚጀምር ነው፡፡ ከሰባቱ የሳምንት ቀናት፤ ከሰባቱ አህጉሮች፣ ከሰባቱ ፊደሎች፣ እና ከሰባቱ የሰው ባህርያት ጋር ግንኙነት እንዳለው ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ሁሉም ነገር ከአፈር፣ ከውሃ፣ ከእሳት፣ ወይም ከነፋስ ባህርያት ጋር የተያያዙ ናቸው ይባላል፡ የሰው ግን ከእነዚህ በተጨማሪ የህያውነት በተጨማሪም፤ የማወቅ፣ የማሰብ፣ የመቀኘት፣ በሙዚቃ የመጠበብ ባህርይ አለው - ነባቢት ይሉታል፡፡ መለኮትን ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ባህርያት አሉት ተብሎ ነው “ሰብ” ተብሎ የተሰየመው፡፡ ቤተሰብ እንል የለ? ሰብ፤ ሰባት ከሚለው ቁጥር ጋር የተገናኘ እንደሆነ ያስረዳሉ ሊቃውንት፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ የራሱ ታሪክ ያለው ፊደል አላት፡፡ ይህንን የፈጠሩና ያሳደጉ ሊቃውንትና አዋቂዎች ነበሯት፡፡ ኢትዮጵያ የድንቅ ሚስጥር አገር ነች፡፡ ካለፈው ትውልድ የተረከቡትን ድንቅ ስራ አክብረው፤ በተራቸው የላቀ ድንቅ ስራ የሚሰሩ ነበሩ ኢትዮጵያውያን፡ ያ ጉዞ የቱ ጋ እንደተቋረጠ አውቀን ወደ ፊት መራመድ እንችላለን፡፡ ከማንነታችን መነሻ ተነጥለን ወዴት መሄድ እንችላለን? ሌላው አማራጭኮ ሌሎችን ለመምሰል መባዘን ነው፡፡ ማንነትን ማጣትና ተገዢ መሆን ነው፡፡

“ስለ ፍቅር” በሚል አንድ ዘፈን ዙሪያ ይሄን ሁሉ ተነጋግረንም አላለቀም፡፡ በዘፈኑ መግቢያ ለየት ያለ ዜማና ግጥም አለ፡፡ ምን እያልክ ነው የምትዘፍነው? ዲጂኖ …

ዘፈኑን እንዴት እንደሰራሁት ልንገርሃ፡ አብዛኛውን ግጥም የፃፍኩት አዲስ አበባ ነው፡ መዚቃውን ጥሩ አድርጎ የተቀናበረው አዋሳ ነው - በሚካኤል ሃይሉ፡፡ እንግዲህ፤ እያንዳንዱ ቀን፣ አገር፣ አካባቢ … የየራሳቸው ድባቦች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በዛፎች ልምላሜ አረንጓዴ የለበሰ አካባቢ ይኖራል፡፡ ከልምላሜውና ከነፋሻማነት የተያያዘ መንፈስን የሚያድስ ድባብ ይኖረዋል፡፡ ከቅዝቃዜና ጥላ ጋር የተያያዘ ድባብም ሊኖረው ይችላል፡፡ ወደ የትኛው ድባብ ታዘነብላለህ?  የማየት አቅምህ፣ የመንፈስህ ቅኝትና ምርጫህ ይወስኑታል፡፡ ለአንዱ ያልታየው ውበት ለሌላው ይታየዋል፡ ግን አስበህ አስልተህ አይደለም ከአካባቢው ድባብ ጋር የምትያያዘው፡፡ ከስሜት ጋር ነው የሚዋሃደው፡፡ ዘፈኑ ውስጥ የደቡብ ድባብ ልጨምርበት ብዬ አስልቼ አልወሰንኩም፡፡ አዋሳ ውስጥ የደቡብ ድባብ ከዘፈኑ ስሜት ጋር ተዋሃደ፡፡

ስለ ፍቅር ሲባል ስለፀብ ካወራን ከሚለው ዘፈንና ስሜት ጋር፤ ድንገት ዲጂኖ …

ዲጂኖ ጫና ኦታ

ኦታ ጫና ኦሬ

ኦሬ አ አሃ ሃሃ …

ትርጉሙ ምንድነው ብትለኝ፣ የቃል ትርጉም ሳይሆን የስሜት ትርጉም ነው፡፡ የፍቅር ረሃብ፣ የፍቅር ጥሪ፣ የፍቅር ሃይል ነው፡ የድምፅ የዜማ የትርጉም ነው፡፡ የደቡብ ድባብ የተጎናፀፈ የፍቅር መንፈስ ነው፡፡

በአልበምህ ከተካተቱት ዘፈኖች መካከል በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ እያለህ የፃፍካቸው አሉ?

ሁለት ናቸው፡፡ “ህልም አይደገምም” የሚለው ዘፈን፤ ከተወሰኑ ማስተካከያዎች በስተቀር በእስር ቤት የተፃፈ ነው - ግጥሙን ማለቴ ነው፡፡ ዜማው ቀደም ሲል በቴዲማክ የተሰራ ነው፡፡ በኢንስትሩመንታል የተጫወተው ነው፤ የተወሰነ ክፍል ጨምሬበት ነው የተጫወትኩት፡፡ ግጥሙ ግን ከሞላ ጎደል በእስር ቤት ውስጥ ያለቀ ነው፡፡

ከእስር ቤት ህይወት ጋር ግንኙነት አለው?

ህልም በእስር ቤት ውስጥ ውድ ነው፡፡ ህልም ውስጥ ያለ ነፃነት … ልክ ስትተኛ ከእስር ትፈታለህ፡፡ ጠዋት ስትነቃ ትታሰራለህ፡፡

ሌላኛው ዘፈንስ?

“ፊዮሪና” የሚለው ዘፈን ነው፡፡ ግጥምና ዜማው ቃሊቲ ውስጥ የተሰራ ነው፡፡

ከአልበም ቀጥሎ የሚመጣው ኮንሰርት ነው …

በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገራችን ከተሞች፤ በውጭ አገራትም ኮንሰርት ለማቅረብ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ የመጀመሪያው ኮንሰርት አዲስ አበባ ቢሆን ደስ ይለኛል፡ በእርግጥ፤ የክረምት ወራት የዝናቡ ሁኔታ ለኮንሰርት ያስቸግራል፡፡ ተመልካቾች መቸገር ስለማይኖርባቸው ምናልባት መስከረም ክረምት እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ የግድ ሊሆንብኝ ይችላል፡ የተወሰኑ አገራት ውስጥ ኮንሰርት አሳይቼ የአዲስ አበባውን በተሟላ ዝግጅት አቀርባለሁ ማለት ነው፡፡

በድሬዳዋ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በመቀሌ፣ በአዋሳ እና ሃረር፣ ጋምቤላና አፋር በሌሎች ከተሞችም የኮንሰርት ጉዞ ይኖረናል፡፡ ወደ ፍቅር የሚል ስያሜ ልንሰጠው አስበናል፡፡ ኮንሰርቱን ከመጀመራችን በፊት ከአቡጊዳ ጋር ሰፊ የዝግጅት ጊዜ ይኖረናል፡፡

አቡጊዳ ባንድ ከአሜሪካ መጥቶ፣ ለሁለት ወር ያህል ልምምድ እናደርጋለን፡፡ ጥንቅቅ ያለ ኮንሰርት እንዲሆን ነው የፈለግነው፡፡

የአቡጊዳ ባንድ ስንት አባላት አሉት?

አምስት የመዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችን፤ ሁለት አጃቢ ድምፃዊያንን የያዘ ነው፡፡ የአዲሱ አልበም ዘፈኖች፤ ብዙ ህብረ ዜማ ስላላቸው፤ ሁለት አጃቢ ድምፃዊያን ለመጨመር አስበናል፡ በአጠቃላይ አቀራረባችን ከቀድሞው የተሻለ መሆን አለበት፡፡

የጥቁር ሰው ክሊፕ በአሰራሩ ከቀድሞ ክሊፖች የተለየና የተሻለ ነው፡፡ ኮንሰርቱም እንደዚያ ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ የአልበሙ ተቀባይነት ከቀድሞዎቹ የላቀ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ትክክል ነው?

ስለ አልበሙ ተቀባይነት … እኔን ከምትጠይቀኝ፤ አንተን ብጠይቅህ አይሻልም? እንዴት አየኸው?

/ይቀጥላል/

 

 

ማ’ድን ቆፋሪዎች

ሁለት ሆነው ሔዱ

በጠቆረው ሰማይ

በጨረቃ ብርሃን

በኮከብ ተመርተው

አገሩን ቀየውን ወደ ኋላ ትተው

አድማሱን አሻግረው

በሀሳብ እያዩ

ካደጉበት አምባ

ከመንጋው ተለዩ

ሄዱ፡፡

-

ማድን ቆፋሪዎች በጉድጓድ ውስጥ ያሉ

ባልማዝና ሰንፔር በንቁ ያጌጣሉ

እዛ ሕይወት ቀሏል በማለት ገምተው

ካገር ተሰደዱ በማለዳ ነቅተው፡፡

-

የበረሀው መንገድ ጊንጥ እባብ ያለበት

እሬትና ቁልቋል አልፎ አልፎ በቅሎበት

ንፋሱ እያፏጨ

አሸዋ እየረጨ

ወቅት የማያበርደው የበረሀው ሀጋይ

በተቆላ አሸዋ በጨቀነ ፀሀይ

እየለበለበ አቅም ሲነሳቸው

ተስፋ እየቆረጡ

ተስፋ እየቀጠሉ

ሲወድቁ ሲነሱ

ኑቢያ ሱዳኖች ያያት እርስት ወርሰው

ከተቀመጡበት ጠረፍ አገር ደርሰው

በዚያ ድንኳን ሰሩ

ሆነው እንደቦታው መስለው እንዳገሩ

ጥቂት የማይባል ብዙ ግዜም ኑሩ

ወራት ተፈራርቀው

ሆኖ ብዙ በጋ አልፎ ብዙ ክረምት

እልሕ ባስጨረሰ ድካምና ጥረት

ባሕር ለመሻገር አንድ እድል አጊኝተው

ለወደብ ጠባቂ ትንሽ ገንዘብ ሰጥተው

ከቃጫኝ መርከብ ላይ ከታችኛው ክፍል ያንዱን ቋሚ ይዘው

በውሀ ላይ መንገድ ብዙ ለሊትና ብዙ ቀን ተጉዘው

ፈረንጆች ካሉበት አንድ ወደብ ደረሱ

ፓሪስ!

-

ፓሪስ ቫንዛሊዜ የጐዳናው መብራት

ያስፓልቱ ንቅሳት

የዛፉ ከመከም እያስደነቃቸው ጥቂት እንደቆዩ

ወደ ቀኝ ቢያዩ ምንም አልማዝ የለም

ወደ ግራ ቢያዩ ምንም አልማዝ የለም

ወደ ግራ ቢያዩ ምንም እንቁ የለም

እንኳን መአድኑ ማዕዱም ጠፋና

ያገር ልጆች ባክነው በፓሪስ ጐዳና

የማታ የማታ ግራ ሲገባቸው

ለጊዜው አሉና ጨለማው ተገፎ እስኪሆን ብርሃን

ድስትና ብርጭቆ እያጠቡ ሰሀን

የስደትን ኑሮ አንድ አሉ ጀመሩ

እንደሰሙት ሳይሆን እንዳዩት ሊኖሩ

-

እዚ በሀገር ቤት

ወንድማማች ሄደው ብዙ ዘመን አልፎ

የብዙ መስከረም አደይ አበባ ረግፎ

ታናናሾች አድገው ታሪክ ሲጠይቁ

ባሕር ማዶ ያሉ ወንድም እንዳሏቸው ጠንቅቀው አወቁ

-

ከውጭ የተላከው ግድግዳ ላይ ያለው ባለከለር ፎቶ

ከፓሪስ የመጣው ጐረቤት ሚቀባው የናታቸው ሽቶ

ትልልቅ ቁልፍ ያለው ያባታቸው ካፖርት ከዑል የተሰራ

የሚሞላ ሰአት ከራስኔ ሚቀመጥ በደውል ሚጣራ

እነዚህን እና ከውጭ የመጡትን ሌሎችንም ነገር

አይተው ሲደነቁ በፈረንጆች አገር

-

“ማድነ ቆፋሪዎች በዙሪያው በዚያ ያሉ

ባለማዝና ስንፔር በንቁ ያጌጣሉ

እዛ ሕይወት ቀሏል በማለት ገምተው

ታናናሾች ሄዱ በማለዳ ነቅተው፡፡”

-

ግና!!

ማድን ቆፋሪዎች በሰው አገር ያሉ

አልማዝና ሰንፔር እንቁ ቢያወጡም

ጌቶቻቸው እንጂ እነሱ አያጌጡም

ታላላቆች ሄደው የላኩት ደብዳቤም ይህንን ግልፅ አርጐ ስለማይናገር

ታናናሾች አድገው መኖር ይመኛሉ ተሰደው ሰው አገር

ብቻ እንዲ እንዲህ እያሉ

ትውልድ ሐረግ ስበው

በታላቅ ከተሞች በረጃጅም ፎቆች በጥላው ተከበው

ታላላቆች ሄደው ዛሬም ይልካሉ

ባለ ከለር ፎቶ

ፓሪስ ሻኔል ሽቶ

ባርኔጣና ካፖርት

አልፎ አልፎም ትንሽ ብር ደላርና ሊሬ

ከዚ እየተጫነ ሽሮና በርበሬ

2001 ዓ.ም

ቃሊቲ

ቴዎድሮስ ካሳሁን

 

 

Read 12620 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:36