Saturday, 07 December 2019 12:14

ከዚህም፣ ከዚያም ‘ወከባ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የአንድ መስሪያ ቤት ሰዎች ናቸው፡፡ እና…በየወሩ ገንዘብ እያዋጡ የሆነ ቅዳሜ ቀን ጥሬ ሥጋቸው ላይ ይዘምታሉ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ በወር አንድ ቀን ቀበቶ ቀዳዳ ሊሰነጠቅ እስኪደርስ ድረስ የጥሬ ስጋ ‘አምሮታቸውን’ ይወጣሉ!
እኔ የምለው…እዚች ከተማ ውስጥ እግረኛ ሆኖ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሆነሳ! ጠቅላላ ‘ዱላ’ ሆነ እኮ! እስክትንገዳገዱ ድረስ የሚገፈትራችሁ፣ “ኳሷን ካጣሁ እግሩን አላጣም፣” በሚል እንደሚንሸራተት እግር ኳስ ተከላካይ እግራችሁ ላይ በአርባ አምስት ቁጥር ጫማ የሚቆመው፣ በተጨናነቀ መንገድ ላይ አምስት ሆነው ተደርድረው ማለፊያ የሚያሳጧችሁ…ምን አለፋችሁ ወዲህ ወዲያ ማለት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ (ይቺ ሌላ ሌላዋን ማለትም በአሎሎ ወርዋሪ ጉልበት  ‘እንትፍ’ እንደምንላት ነገር የመሳሰለችውን ነገርማ ዝም ማለቱ ይሻላል!) የምር እኮ… አለ አይደል … ሳይገፋፉ መተላለፍ እኮ የስልጣኔ፣ የከተሜነት የምናምን ጉዳይ ሳይሆን በቃ የሰው ፍጡር የመሆን ጉዳይ ነው፡፡ እኔ የምለው…ይሄ ‘ሙሉ ልብስ ግጥም ያደረገው’ (ሱፍ የሚባለው ነገር ጠፍቷል ብዬ ነው) ሁሉ ምነ ነካው!
ኮሚክ እኮ ነው…“ብታያት እኮ እንዴት የሰለጠነች መሰለችህ! ፓስታ ስትበላ እኮ ሹካ አያያዟ ፈረንጆቹን ታስንቃለች፡፡”  ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ... የ‘ስልጣኔ’ የብቃት ማረጋገጫ የሹካ አያያዝ ሲሆን አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ኑሮ አስቸጋሪ ሆኖ የለም እንዴ! አንዲት እንጀራ ብቻዋን ዘጠኝና አስር ብር ደርሳ የለም እንዴ! ታዲያ የአንዳንዶቻችን የ‘ሚድሴክሽን ዳያሜትር’ የሚለጠጠው በምን አይነት ተአምር ነው! ደግሞ ያንኑ  ‘ሰልፍ ሩል’ ያወጀ የሚመስል አካል (ቂ…ቂ…ቂ…) ልከ የሆነ ምናምን  አነፍናፊ -- አስቀድመን ሰውም ‘እየገፈተርንበት’ ነው፡፡ የፈለገ ጠርዝ ላይ ሁኑ፣ ወደ ጎን ለመንቀሳቀስ በማይመች ሁኔታ ላይ ሁኑ… መንገድ መልቀቅ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ፡፡ አካሄዳችን እኮ ልክ ፊት ፊት መንገድ የሚያስለቅቅ ሞተረኛ፣ ለምን አይመደብልኝም … የምንል ነው የሚመስለው፡፡
እናላችሁ… ትብብር ጠይቆም የሚኮሳተርባችሁ ሲበዛ፤ የሆነ የተበላሸ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
መንገድ ላይ እየሄዳችሁ እያለ ያስቆማችሁና “ሰዓት ስንት ነው?” ሲል ይጠይቃችኋል፡፡ አጠያየቁ ልክ “ራስህ ቀድመህ ሰዓቱን ለምን አልነገርከኝም!” የሚል ነው የሚመስለው፡፡
“ስምንት ሰዓት ከሀያ፡፡”
በአንድ ጊዜ ፊቱ ቅጭም ይላል፡፡ እሷዬዋ ሰባት ሰዓት ተኩል ነዋ ያለችዋ! እናላችሁ… እሱየው በራሱ ምክንያት ያረፈደ ሳይሆን እናንተ በፈቃዳችሁ ሰዓቱን ስምንት ሰዓት ከሀያ ያደረጋችሁት ያስመስሉታል፡፡
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እንደ ዘንድሮ የኑሮ መወደድ፣ ሱፐርሶኒክ ፍጥነት ጊዜ በኋላ… አለ አይደለም… “ክብደት ለመቀነስ የተመሰከረላቸው ሳይንሳዊ ዘዴዎች…” ምናምን ብሎ ነገር ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ኑሮ ራሱ ከበቂ በላይ ክብደት መቀነሻ ነዋ!
ስሙኝማ እግረ መንገድ.… “እከሌ እኮ ሀብታም ነው፣ አስር ሚሊዮን ብር አለው ይባላል፣” ሲባል በሳቅ የሚንፈራፈሩ ዜጎቻችን በዝተዋል ይባላል፡፡ “አስር ሚሊዮን ምን አላትና ነው!” ይባላል አሉ፡፡ “ጊዜ ደጉ” ነው ምናምን የሚል ዜማ ነበር አይደል፣ “እውነትም ጊዜ ደጉ” ያስብላል፡፡ “የእሳቸው ልጅ እኮ በወር አንድ ሺህ ብር ይዝቃል!” ማለት እዳር ላይ የቪአይፒ. ወንበር የሚያሰጥበት ዘመን አለፈና አሁን… “አስር ሚሊዮን ብር ምን አላት!” የሚባልበት ዘመን ተደረሰ! (እነእነትና ወዳጆቼ፣ እናንተ ዓለም ድሮ የረሳው አይነት ‘የዚህ ኢዝም’፣ ‘የዛ ኢዝም፣’ ነገር ስትነታረኩ፣ ህዝቤ በደፈጣ ውጊያ ዘዴ ብር እየሰበሰበሰ ይመስላል፡፡ “ይመስላል” የተባለው አትክልት ተራ ስንሄድ በኪሳችንም፣ በመቀነታችንም የማናገኘው ብር በየሰዉ ኪስ የሚበቅለው ‘ምን አይነት ማዳበሪያ’ እየተደረገለት እንደሆነ ግራ ስለሚገባን ነው፡፡)
አትክልትና ፍሬ የሥጋ ብልቶች
ሞልቷል በሀገራችን የምግብ አይነቶች
መባሉ ቀረና…አለ አይደል… “ጉልበት በዳገት ይለግማል…” እየተባለ በጎመን ላይ ‘ሙድ መያዝ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ቀረና፣ “ሂጂና ዶኬሽን አንደክድኪ!” ብሎ ሹሮን ጭርሱኑ ወደ ጤና ቡድንነት ማውርድ ቀረና፣ ይኸው ለቆሎ ቀድመን ሰልፍ ለመያዝ የምንጣደፍበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ አሀ…ቆሎ እኮ የቺስታነትን ጥግ ለማሳየት እንደ ማስረጃነት የምትቀርብ ነበረች!
አንድ አፍኛ ቆሎ ቁርጥም አደርግና
አንድ ጣሳ ውሀ ግጥም አደርግና
ተመስገን እላለሁ ኑሮ ተባለና
ተብሎም ነበር እኮ!
ድሮ የሰሃን ኤግዚቢሽን እናይባቸው የነበሩ ድግሶች እኮ፣ አሁን የሳህን ሰልፍ የለ፣ የጭልፋ መአት የለ፣ …ምን አለፋችሁ፣ ከሞላ ጎደል ‘ከምግብ የጸዳ ድግስ’ እየበዛ ነው፡፡ “ሆድ እንዳሳዩት ነው ስለሚባል…አለ አይደል…መጀመሪያውኑ ለሆድ ‘አለማሳየት’ ነው፡፡ አሀ፣ ልክ ነዋ…መጀመሪያ ላይ ስፔሻል ክትፎ ከ‘ፍሬንች ዋይን ጋር’ ከጋበዛችሁ በኋላ በሚቀጥለው ጊዜ አንዷ የቀበሌ ክበብ ቋንጣ ፍርፍር “ለሁለት ትበቃናለች” አይነት ‘ኦስቴሪቲ ሜዠር’ (ቂ…ቂ…ቂ…) የምትወስዱ መጀመሪያ ‘ለዚያኛው ሆድ’ ማን ክትፎና ፍሬንች ዋይን አሳዩ አላችሁ!
ነገርዬው… አለ አይደለም… “ኪስህ ነው የልብ ወዳጅህ፣” አይነት ነው፡፡ “ገንዘብ ከፍቅር አይበልጥም፣” ምናምን ብሎ ነገር ልብ ወለድ ውስጥም ለመክተት የሚያስቸግርበት ጊዜ ሆኗል፡፡ “ልብወለድ ከሚለው ዝም ብሎ አንደኛውን ‘ሳይንስ ፊክሽን’ ቢለው አይሻልም!” ሊባል ይችላል፡፡
ስሙኝማ...እግረ መንገድ፣ ዘንድሮ እኮ ዋናው ችግር ተጋብዞ የሚመጣው ዋነኛው እንግዳ ሳይሆን… ‘በሰብአዊ ተሳቢነት’ ተከትለውት የሚመጡት ናቸው፡፡ መጀመሪያ ነገር “ራስህን ችለህ ና” ተባለ እንጂ ማን አስከትለህ ና” አለው! እናላችሁ…ትው ቀዳዳ የሚበጅ ከሆነ የዋነኞቹ እንግዶች ሰይሆን ማን ቤት እንደመጡ እንኳን የማያውቁት ‘ሰብአዊ ተሳቢዎቹ’ ናቸው…በተለይ በዘንድሮ ፖለቲካ፡፡ በአንድ በኩል በቂ ባይሆንም የተቻለውን ያህል በንባብና በመሳሰለው የሆነ የፖለቲካ ስንቁን በመለስተኛ አግልግል የሸከፈና፣ በሌላ በኩል፣ በፖለቲካ ስብስብና በእቁብ ስብስብ መሀል ያለው ልዩነት በየወሩ የሚወጣው እጣ ብቻ የሚመስለውና ‘ለጠፍ ብሎ’ የገባው የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን ልብ በሉልኝማ፡፡
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን የሚል ነገር አለ መሰላችሁ፣ የሰው ልጅ ይበልጡኑ የሚደሰተው እሱ አንድ ነገር በማግኘቱ ሳይሆን ሌላው የሆነ ነገር በማጣቱ ነው’ የሚባል ነገር አለ፡፡ ይቺ ነገር ግን እኛ ዘንድ በርከት ከማለትም ያለፈች አትመስላችሁም?! ፖለቲካችን ውስጥ እኮ ‘ቀና ሲሉ ቅውር’ የበዛው…አለ አይደል… እሱዬው ለጥቁር ሱሪው ቀዳዳ ነጭ ጨርቅ በማስጣፉ እንኳን ‘ጄለስ’ የመሆን ነገራችን ስለሚከተለን ነው፡፡ ልክ ነዋ…እስቲ ነገሬ በሉና በ‘ቦተሊካው’ ሰፈር ጮክ ብሎ ከሚሳደበውና ለስለስ ብሎ ቁም ነገር ለመናገር ከሚሞክረው መሀል ያለውን ልዩነት እዩልኝማ! 
ስሙኝማ…እግረ መንገድ…‘ሴንስ ኦፍ ሂዩመር’ ምናምን የሚሉት እኮ…አለ አይደል…የትናንት ነገር እየሆነ ነው፡፡ መሳቀቅ እኮ ነው! ነገና ከነገ ወዲያ ደግሞ አንዱ ይነሳና “ባለፈው ምናምን ስርአት … ሀዝቡን ለማደነዘዝ በሚዲያ፣ ቀልድ እየለቀቁ፣ የሚል አክቲቪስት ሊመጣ ይችላል፡፡
የምር ግን አንዳንዴ ፈገግ ማለት ትጀምሩና መሀል ላይ ቀጥ ይላል…ጣጣ አለዋ! መንገዱን ተሻግሮ “እዛ ማዶ ያለው በእኔ ነው የሚስቀው…” ብሎ ሀገር ቀውጢ ሊያደርግ ይችላል! ዘንድሮ እኛ ዘንድ አይሆንም የሚባል ነገር የለም:: እናላችሁ…እዚህ ሀገር ችግሩና ‘ወከባው’ ከዚህም፣ ከዚያም ሆነብንና፣ ግራ ገብቶናል፤ ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2485 times