Saturday, 07 December 2019 12:23

አገር የማዳን ሩጫው ይሳካ ይሆን?

Written by 
Rate this item
(4 votes)


              “ዴስትኒ ኢትዮጵያ” በሚለው ቡድን ባለፈው ሳምንት ከስካይ ላይት ሆቴል በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሲተላለፍ የመመልከት ዕድል የገጠማቸው
ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው አዲስ ተስፋ ማቆጥቆጡን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በታች ጥቂት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ስሜታቸውን ለአዲስ አድማስ አጋርተዋል፡፡

             “እጅግ የተገረምኩበትና ለአገሬ ተስፋ የሰነቅኩበት መድረክ ነው
                     ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር)

            ዴስቲኒ ኢትዮጵያ የተባለው ቡድንና አጠቃላይ ሃሳቡ በእጅጉ የተደነቅኩበትና ለአገሬ ተስፋ የሰነቅኩበት ነው፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች ከጀርባ ስራቸውን በዝምታና በትጋት እየሰሩ ስለመሆናቸው ያየሁበትም ጭምር ነው፡፡ የዚህ የስልጠና ሞዴሉም ቢሆን፤ ለአገራችን ጠቃሚና በደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ በእጅጉ ውጤታማ የሆነ ነው፡፡  
ከምንም በላይ የኦነጉ ዳውድ ኢብሳና የአብኑ ዶ/ር ደሳለኝ ጐን ለጐን ተቀምጠው ሲወያዩና ሲነጋገሩ ማየት በራሱ በእጅጉ አስደሳች ነው፡፡ ይህ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡ ሁለቱ ሰዎች ማስመሰል የሌለበትና ተፈጥሯዊውን ውይይት ነው ያሳዩን፡፡ ይሄ እንደ አንድ ለአገሩ እንደሚያስብና ለአገሩ እንደሚጨነቅ ዜጋ ተስፋን የሚያጭርና የሚያስደስት ነው፡፡

_______________

                 “የአገሪቱ ትልቁ ችግር የልሂቃን አለመወያየት ነበር”
                      ጋዜጠኛ የኋላሸት ዘሪሁን

         ትልቁ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የልሂቃን ቁጭ ብሎ አለመነጋገር ነበር፡፡ አሁን ይሄ መጀመሩ በአገራችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ያስቀራል የሚል ትልቅ ተስፋ ስለሰነቅኩኝ፣ ጉዳዩን እጅግ በበጐ ጐኑ ተመልክቼዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጽንፍ ለጽንፍ ሆነው በጥላቻ ሲተያዩ የነበሩት ሁሉ ኢትዮጵያ በምትባል በአንዲት ትልቅ አገር ስር ተሰባስበው ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ውስጥ ለውስጥ ከ6 ወራት በላይ ሲመክሩ መቆየታቸው፣ በራሱ በአይነቱ የተለየና እሰየው የሚያስብል ነው፡፡
በዋነኝነት አሁን የተቀመጡት ስለ ፓርቲ ወይም ስለ ግለሰብ ጉዳይ ለመነጋገር ሳይሆን  ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔ ለመፈለግ መሆኑ ነው ይበልጥ አስደሳች የሚያደርገው፡፡
በተጨማሪም በዴሞክራሲ ግንባታና ሂደቱ ላይ አብረው መስራት እንዳለባቸው፣ በምንም መልኩ ሕዝብ እርስ በእርሱ መጫረስ እንደሌለበት፣ ችግሮች ሲከሰቱም በሰከነ መንገድ በውይይት መፈታት እንዳለበት ነው የተነጋገሩት:: በሌላ መልኩ ለአገር ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው በልዩነታቸው ላይ በቀጣይነት መወያየት እንዳለባቸው መነጋገራቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ይህንን ደግሞ የተወያዩት ለመጠፋፋትና ለመጨራረስ የሚፈላለጉ ቡድኖች መሆኑ የሚደንቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦነግና አብንን የሚመሩ ሰዎችን ተመልከቺ፡፡ ኦነግና አብንን ተይውና የዘውግ ፌዴራሊዝምንና የጂኦግራፊ ፌደራሊዝምን የሚከተሉ እጅግ ጫፍና ጫፍ ያሉ ወገኖች ጐን ለጐን ቁጭ ብለው መነጋገር መቻላቸው በአገሬ ላይ ተስፋ እንዳልቆርጥና ጭንቀቴ ቀለል እንዲል አድርጐኛል፡፡ በዚህ ረገድ ጉዳዩ በአይነቱም ለየት ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ አገር ባለው ልምድ እንደዚህ አይነት ነገር ይጀመርና በወሬ ያልቃል፡፡ ይሄኛውን ስናይ ግን ምንም እንኳን ሰሞኑን በይፋ በሚዲያ ይውጣ እንጂ ለረጅም ወራት (ለግማሽ ዓመት) ውስጥ ለውስጥ ሲሰራ ቆይቶ እዚህ መድረሱ ያስገርማል፡፡

____________________


                     “ፍቅር የነገሰበት፤ ጥላቻ የደቀቀበት መድረክ ነው”
                              ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን


           ትንሿን ኢትዮጵያን ነው በዚያ አዳራሽ የተመለከትኩት፡፡ ከምን አንጻር መሰለሽ? የሀሳብ ልዩነት ያላቸው፣ በባላንጣነት የሚተያዩ፣ አንድም ቀን ሳይቀራረቡ ማዶ ለማዶ ሆነው ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቧ የሚያቀነቅኑ ከጀርባቸው መዓት ተከታይ ያላቸው ሰዎች ናቸው አንድ ጣሪያ ስር ቁጭ ብለው ሲነጋገሩና ሲወያዩ የነበሩት፡፡ ይሄ እስካሁን ያልተሞከረ አካሄድ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ጅማሮ ነው፡፡ መድረኩ ፍቅር የነገሰበት ጥላቻ የደቀቀበት፤ በተቃርኖ ጎራ የነበሩ ሰዎች ለአገርና ለሕዝብ ክብር ያሳዩበት መድረክ ነው እላለሁ፡፡
ለምን ለስድስት ወር ይፋ አልሆነም ለሚለው ‹‹ግልጽነት ለዘላለም ይኑር›› የሚለው እሳቤ በኢትዮጵያዊያን ልብና ምድር መስፈን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምስጢር አድርገው ማቆየታቸውን አልስማማበትም፡፡ ምክንያቱም ለአገርና ለሕዝብ የሚደበቅ አንዳችም ነገር እንደማይኖር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል፡፡ አገርና ሕዝብ አብሮ ማወቅ፣ ሀሳቡን መደገፍና የማይጥም ነገርም ካለው መንቀፍ አለበት፡፡ ስለዚህ በድብብቆሽ ሳይሆን “ግልጽነት ለዘላለም ይኑር” በሚለው እሳቤ፣ ወደፊት መራመድ አለባቸው ይህንን የምለው ለምን መሰለሽ? ይፋ ቢሆንና በርካታ ሰው ቢነጋገርበት፣ የበለጠ የዳበረና ጠቃሚ ሀሳብ ለቡድኑ ግብአት መሆን ይችል ነበር ብዬ ስለማምን ነው፡፡  ዞሮ ዞሮ ሰዎች የሀሳብ ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና የአገር ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ተቀራርቦ ለመነጋገርና በአገር ዕጣ ፋንታ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ቁርጠኝነት ማሳየታቸው ራሱን የቻለ ስልጣኔ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ተቀራርበው ሲነጋገሩ፣ አፍ ለአፍ ገጥመው በወንድማማችነት መንፈስ ሲወያዩ የተሰማኝ ስሜት እውነተኛ ስሜት “ፍቅር ለዘላለም አይወድቅም፤ ደግሞሞ ፈጣሪ ሁሌም ኢትዮጵያን ይጠብቃታል” የሚለው ነው፡፡ ፈጣሪ ልጆቿንና ኢትዮጵያን ይታደጋታል የሚለው የምንጊዜም እምነቴ እንዳይሸረሸርና ይበልጥ እንዲፀና አድርጐልኛል፡፡ በዚያ አዳራሽ ውስጥ የነበሩት ሁሉም የአንዲት አገር የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፤ የተለየው ሀሳባቸው እንጂ አገራቸው ወንድማማችነታቸው አይደለም፡፡ በዚያ አዳራሽ ፍቅር፤ ወንድማማችነትና የሰለጠነ ንግግር ጐልቶ ተንፀባርቋል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጣይ ንጋት ለማመላከት መሞከራቸው ስልጣኔን ያሳያል፡፡ በእርግጠኝነት አመርቂ ውጤት ያመጣል የሚል እምነትም ተስፋም አሳድሮብኛል፡፡    

Read 4034 times