Saturday, 14 December 2019 12:30

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በቤተ መንግሥት

Written by  ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
Rate this item
(7 votes)

  በሐምሌ ወር መጨረሻ ይመስለኛል። ከአምስት ወራት በፊት። በምንይልክ ቤተ መንግሥት አዲስ በገነቡት ቢሯቸው ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን አገኘኋቸው።  አቅፈው ተቀበሉኝ። ‹‹የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ›› የሚለው መጽሐፌ  ኢትዮጵያዊነትን ለማዳበርና የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር እንደሚረዳ አበሰሩኝ። መጽሐፉንም የሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲያነቡት እንዳደፋፈሩና ከውስጡም እያወጡ ይጠቅሱ እንደነበር አወጉኝ። የእዛን ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአካል ከማግኘቴ በፊት ግን  ቤተ መንግሥቱን እንድጎበኝ እድል ሰጥተውኝ ነበር።
ከዶክተር ዐቢይ ጋራ በቢሯቸው ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ተነጋገርን። በመጨረሻ፣ ህዝብ ስለ እሳቸው አመራር የሚለውን አንዳንድ አስተያየት ባካፍላቸው ቅር ይላቸው እንደሆነ ጠየቅኋቸው። ቅር እንደማይላቸው ገለፁልኝ።  ‹‹ህዝብ፣ ለምን ወንጀለኞችን አያስሩም ይሉዎታል›› አልኳቸው። እሳቸውም፤  “አሁን ደግሞ ለምን አትፈታም ይሉኛል። ወንጀላቸው ተረጋግጦ ያሰርናቸው ሰዎች እሉ። ታዲያ እኔን ሁሉም ‹‹የእኔ ወገኖች ስለታሰሩ ፍታልኝ፣›› ይላል። የማንን ወገን ፈትቼ የማንን በእስር ላቆይ?  ጥፋተኛ ጥፋተኛ ነው፤” አሉኝ።
የተወዳጅነታቸው ማሽቆልቆል ስለ አሳሰበኝ፣ ተወዳጅነታቸው እንደ መጀመሪያው ጊዜ ከፍ እንዲል አንድ ሥራ ቢሠራ መልካም መሆኑን ባማክራቸው፣ “አንደኛ፤ አሁንም የሚወዱኝ ብዙ ሰዎች አሉ። ሁለተኛ፣ እኔ ህዝብ እንዲወደኝ ብዬ ምንም ነገር አላደርግም። ደግሞም እውነትና ትክክል ነው ያልኩትንም አቋም ለመወደድ ብዬ አልለውጥም። እርስዎን እንደ ምሳሌ ልውሰድዎት። እርስዎ ‹የኦሮሞ  እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ› ብለው የፃፉትን መጽሐፍ ከማሳተምዎ በፊት ዐያሌ ግጥሞችን፣ ተውኔቶችን፤ የተለያዩ መጣጥፎችን ጽፈው እንደነበር አውቃለሁ። ሆኖም ይህን ወሳኝና ሃቀኛ ታሪካዊ መጽሐፍ ለህትመት ከአበቁ በኋላ ተቃዋሚዎች ተነሱብዎት። መቼም መፅሐፉን የጻፉት እውነተኛነቱን አምነውበት ነው። ታዲያ በመጻህፉ ምክንያት ተቃዋሚዎች ስለተነሱብዎ ለመወደድ ብለው የመጽሐፉን ሃቀኝነት ይክዳሉ? የቆሙለትንስ እውነት  አውግዘው ያፈገፍጋሉ?›› አሉኝ፤ ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ እኔም “በፍፁም!” አልኳቸው። እሳቸውም፤ “እኔም እንደዛው ነኝ፣” ሲሉ በቆራጥነት የተሞላ ድምፃቸውን አሰሙኝ። 
በመሃላችን ጥቂት ፀጥታ ከሰፈነ በኋላ ንግግራቸውን በመቀጠል እንዲህ አሉ፤ “እኔ ሰውን በግፍ አልገድልም። ሰው መግደል ፀያፍ ነው። እግዚአብሄርም አይወደውም። ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ህዝብ አንድም ገንዘብ አልሰርቅም።  ደግሞ የመጣው ቢመጣ የእኔ መሪነት ዘመን ላይ ሲደርስ ኢትዮጵያ እንድትበጣጠስ አልፈቅድም። በዚህ ቀልድ የለም።”
ስለ ስልጣናቸው ደግሞ ዶክተር ዐቢይ እንዲህ አሉኝ፡- “የልቤን መሻት ብናገር… እኔ የምፈልግው ስልጣን ለቅቄ፣ ፖለቲካን ትቼ የምርምርና የሳይንስ መስኮች ላይ መሰማራት ነው። “መደመር” የሚባል መጽሐፍ ጽፌ ልጨርስ ነው። ይሄው ይመልከቱት። እኔን ለሚተካው መሪ አቅልዬለታለሁ። ይሄን መጽሐፍ እያነበበ በቀላሉ ኢትዮጵያን ሊመራ ይችላል።”
እኔም በዚህ ትርምስና ሁከት ውስጥ እንዴት ይህን መሰል መርሃ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሊጽፉ እንደቻሉ ተደነቅሁ። እራሳቸውና ትከሻቸው እጅግ ደንዳና መሆናቸውንም አስተዋልኩ።   
 በመጨረሻም ልሰናበታቸው ቆሜ ሳለሁ፤ እሳቸውም በትህትና ‹‹እባክዎን ይፀልዩልኝ›› አሉኝ። እኔም እሺ በማለት ልፀልይላቸው ቃል ገባሁ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋራ የተነጋገርነው በስፋት ነው። ሆኖም የህይወት ታሪኬን ልጽፍ ከበቃሁ የተረፈውን በሱ ውስጥ አካትተዋለሁ። የቤተ መንግሥት ጉብኝቴንም ዝርዝር እንዲሁ። ስለ ቤተመንግሥቱ በአጭሩ ለማለት ግን በዶክተር ዐቢይ ግንባታ እጅጉን ተደምሜአለሁ። ሊፈራርሱ የነበሩትን የዓፄ ምንይልክ እና የእፄ ኃይለሥላሴ ህንፃዎችን ነፍስ ዘርተውባቸዋል። የደርግና የኢሕአዴግ የቅልብ ጦሮች ሰፍረውበት፣ በቅራቅንቦ የተሞላውን ሥፍራ ሁሉ አፅድተው አበቦች ተክለውበታል። በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በግፍ ተገድለው ቅጥር ግቢው ውስጥ ተቀብረው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን አፅሞች አስቆፍረው አውጥተው በመቃብራቸው ቦታ ላይ ለምለም ሳሮች አብቅለውባቸዋል። ደርግና ኢሕአዴግ ዜጎችን አስረው ይገርፉባቸው የነበሩትን ምድር ቤቶች መዘክር አድርገዋቸዋል። 
ብርቅዬውን ጥቁር አንበሳ ጨምሮ ለተለያዩ የዱር እንስሳት መሰማሪያ ቦታ ተመድቦላቸዋል። ግቢው በጠቅላላ 42 ሄክታር ሲሆን ለህዝብ መዝናኛ በማሰብ “አንድነት መናፈሻ” የሚባል አዘጋጅተዋል። በዚህም ስያሜ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን የማያወላውል አቋም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ባህል የሚወክሉ ጎጆዎችም በመናፈሻው ውስጥ በየዐይነቱ ቁጭ ቁጭ ብለዋል። እነዚህን የቃኙ ሰዎች፣ ዋናዎቹን ብሄር ብሄረሰቦች ሄደው እንዲጎበኙ የሚጋብዙ ናቸው። በሺህ የሚቆጠሩ የጎብኚ መኪኖች ማቆሚያም አለ። በፊት የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጽህፈት ቤት የነበረውንም አስዘምነው፣ አሳድሰውና አሳምረው ከአፄ ኃይለ ሥላሴ እስከ እሳቸው ድረስ ኢትዮጵያን የመሩትን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ፎቶግራፎች (ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሳይቀሩ) በቅደም ተከተል ደርድረዋቸዋል።  ቤቱን በዘመናዊ የመገናኛ እቃዎች (ኮምፒውተሮችንና ኢንተርኔትን ጨምሮ) አደራጅተው፣ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የውጭ  አገር ርዕሰ ብሄሮች ማረፊያ አውለውታል። ለደህንነታቸውም ቢሆን ሆቴል ቤት እንዳይቆዩ በመትጋት። የሆስፒታል ኮሪዶር ይመስል የነበረውን ቀፋፊና ጨለማ የወረሰውን የደርግና ኢሕአዴግ ቢሮ ለመዘክርነት እዛው ትተው የእንግዳ መቀበያና የስብሰባ ክፍሎች ያሉት ብሩህና ለመንፈስ ደስ የሚል አዲስ ቢሮ ሠርተዋል። 
ቀድሞ በጦረኞች በብርቱ እየተጠበቀ ዜጎች ዘወር ብለው በሙሉ ዐይኖቻቸው ሊቃኙት የማይደፍሩት ቤተ መንግሥት ተውቦ፣ ዛሬ ለሁሉም ዜጎች ክፍት መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያስመሰግናቸዋል። በእንደዚህ ዐይነት ውጥረት ውስጥ ሆነው ይህን ሁሉ በአስራ ሁለት ወራት በቤተ መንግሥቱ ማከናውን ከቻሉ፣ በተረጋጋ አገርና ሕዝቦች መሃል ቆይተው ቢያስተዳድሩ፤ ምን ያህል ዕፁብ፣ ድንቅ ተግባራት በፈፀሙ ያሰኛል። እኛ ያልታደልን ሆነን ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከልባቸው እጅግ የሚያፈቅሩ፣ ብዙ ሊሠሩላት የሚሹና የሚችሉ ታላቅ መሪስ አግኝተን ነበር። የኢትዮጵያን የ4300 ዐመታት ታሪክ እኔ የአቅሜን ያህል መርምሬአለሁ። የነገሥታቱንም ታሪክ አንብቤአለሁ።  ዶክተር ዐቢይ እንደ አሉበት እንደኛ ዘመን ክፉና የተወሳሰበ ዘመን ውስጥ የኖሩ መሪዎች ግን አላጋጠሙኝም።  ለእኛ ግን ነገሮችን የሚያገናዝብና መልካም የሚያሳስብ ቅን ልቦና እግዚአብሄር ያድለን። 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ስለተቀበሉ በዚህ አጋጣሚ የተሰማኝን ፍስሀ ልገልጽላቸው እወዳለሁ። ሽልማቱ የኛ የኢትዮጵያውያን፣ የኤርትራውያንና የመላው አፍሪካውያን ነው። ሽልማቱን የተቀበሉ ዕለት ያደረጉትም ንግግር እጅግ መሳጭ ነበር። ወረቀት ሳይዙ ዘለግ ላለ ጊዜ  በተሳካለት እንግሊዝኛ፣ ያን የመሰለ ቁምነገር መናገራቸው ያስደንቃቸዋል። በሳቸው ምክንያት በሽልማት ሰጪዎቹ አፍ፣ ኢትዮጵያ እንደትወደስ ማስደረጋቸውም ያስመሰግናቸዋል። የኖቤል ሽልማቱን ስነስርዓት ያካሄዱት  ሴት ወይዘሮ፤ “ኢትዮጵያ የሰው ዘር ምንጭ ስለሆነች እኛም ኢትዮጵያዊያን ነን፣ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ተገዝታ የማታውቅ ሃገር ነች፤” ያሉት በእሳቸው ምክንያት ነው። እሳቸው ሽልማቱን ባያገኙ ኖሮ ሴትዮዋ ይህን ባላሉ ነበርና። ይህን ጽሑፍ ከመደምደሜ በፊት ለእሳቸውና ለቤተሰባቸው ረጅም ዕድሜና ጤንነት እመኝላቸዋለሁ። ኢትዮጵያም በሰላም፣ በፍቅርና አንድነት ለዘላለም እንድትኖር እፀልያለሁ።  

Read 4241 times