Saturday, 21 December 2019 12:04

ወሲብ ለመፈጸም የአእምሮ ዝግጅትና የአካል ብቃት ያስፈልጋል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(8 votes)

  አንድ ጥያቄ አለኝ ያሉን የአምዱ ተከታተይ በስልካችን ደውለው ነው፡፡ ምን እንርዳዎ ስንላቸው …አደራችሁን ስሜን ንገረን እንዳትሉኝ የሚል ነበር መልሳቸው፡፡ መተዋወቅ ባይከፋም ለጉዳዩ ስንል ምርጫዎን እናከብራለን የሚል ነበር መልሳችን፡፡ ጉዳዩ እንደሚከተለው ነው፡፡
‹‹እኔና ባለቤቴ ከተጋባን ወደ አስራ አምስት አመት ሆኖናል፡፡ ሶስት ልጆችም አፍርተናል፡፡ ባለቤቴ ልጅ እንዳትወልድ ስትል ቋሚ የእርግዝና መከላከያ አሰርታለች፡፡ በእርግጥ ሳይንሱ በጣም ጥሩና ብዙዎችን የሚረዳ መሆኑን ባውቅም እኔ ግን  በጣም የሚቆጨኝ እርምጃ እንደወሰድን ይሰማኛል:: የዚህም ምክንያቱ ደግሞ እስዋ ህክምና ውን እንደወሰደች ብዙም ሳልቆይ እኔ ግንኙነት ማድረግ አቃተኝ፡፡ ለማን ልንገረው? እስዋ ጠልቼአት ፤ሌላ ሴት ጋ እየሄድኩ አድርጋ ትቆጥረኛለች፡፡ ለእስዋ ብነግራት ምንም አልገባትም፡፡ ሐኪም ጋ እንዳልሄድ አፈርኩ፡፡ ምን ትሉኛላችሁ…እስቲ ምክር ለግሱኝ የሚል ነበር የደወሉት ሰው መልእክት፡፡››
ከላይ ላነበባችሁት ጥያቄ መልስ የሚሆን የተጠና ነገር ስናፈላልግ የ ማዮ ክሊኒክን ጥናታዊ ስራ አግኝተን ወደአማርኛ መለስን፡፡ በተጨማሪም ከአሁን ቀደም ለዚህ እትም በዚሁ ርእሰ ጉዳይ መልስ እንዲሰጡን የጋበዝናቸው ዶ/ር ተሸመ ሽፈራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የስነአእምሮ ህክምና ባለሙያ ገልጸውት ከነበረው ላይ ተጨማሪ አድርገን ለንባብ ብለናል፡፡ ጠያቂያችንና ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ወንዶች ጠቃሚ ሀሳብ እንደሚያገኙበት እናምናለን::
ማዮ ክሊኒክ እንዳወጣው ዘገባ ወንዶች የወሲብ አካላቸው ወሲብ ለመፈጸም ከጊዜ ወደጊዜ  ችግር እየገጠመው ሲሄድ የግድ የዝግጁነት ወይንም ፍላጎት ማጣት ነው ተብሎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ ነገር ግን ሁኔታው ከእለት እለት ጭንቀት ማስከተሉ ስለማይቀር ይህ ደግሞ በራስ የመተማመንን ብቃት ከመቀነስ ባሻገር ከትዳር ጉዋደኛ ወይንም ከሴት ጉዋደኛ ጋር ለመገናኘት ችግር እንደሚፈጥር የታመነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወንዶች የብልት መቆም ችግር ሲገጥማቸው ችግሩ ከሌሎች የጤና ሁኔታዎችም ጋር ሊያያዝ የሚችል መሆኑን እና በተለይም ከልብ ጋር የሚገናኝ ሊሆን ስለ ሚችል በፍጥነት ሐኪምን ማናገር ጠቃሚ መሆኑን መረጃው ይጠቁማል፡፡
የማዮ ድረገጽ እንደሚያስነብበው በየደረጃው የሚያጋጥመው ችግር ከመጀመሪያውም የብልት መነሳት ችግር ወይንም ከተነሳ በሁዋላ መቆየት አለመቻል እንዲሁም ወሲብ ለመፈጸም አቅም ማጣት ሊሆን ይችላል፡፡ መረጃው እንደሚያስነብበው የወንዶች የወሲብ ድርጊት በቀጥታ ከአእ ምሮ ጋር የሚገናኝ ሲሆን ወሲብ ለመፈጸም የሆር ሞኖች መነቃቃት፤ የነርቭ እና የደም ስሮች በትክክል መስራት በአስፈላጊነታቸው ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡ ጭንቀትና የአእምሮ ሕመም ያለበት ወንድ አካሉ ለወሲብ ዝግጁ አይሆንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የአካልና የስነልቡና ጉዳዮችም ለወሲብ መነሳሳትን የሚያውኩበት ሁኔታ ይገጥማል፡፡ ለምሳሌም ይላል የማዮ ክሊኒክ መረጃ አንድ ሰው የአካል እንቅስቃሴው በጣም ዝቅተኛ ከሆነ የወሲብ ፍላጎት ምላሽም አዝጋሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት የሚፈጠረው ጭንቀት ወይንም መረበሽ ደግሞ የወሲብ ዝግጁነቱን ወደባሰ ሁኔታ ሊያወርደው ይችላል፡፡
ዶ/ር ተሸመ ሽፈራው በአንድ ወቅት ለዚህ እትም የገለጹትን እናስነብባችሁ፡፡
‹‹ወሲብና አእምሮ እጅግ በጣም ይገናኛሉ፡፡ምክንያቱም የአእምሮ ዝግጅት ከሌለ ሰዎች  በአካል ለወሲብ መዘጋጀታቸው ብቻ ወሲብን አመርቂ አያደርገውም፡፡ሰዎች በአእምሮ በሚዘጋጁበት ጊዜ አእምሮ የነርቭ ኬሚካሎችን ወደተለያዩ ቦታዎች በመላክ ሆርሞን አመንጪ እጢዎች እንዲ ዘጋጁ ያደርጋል፣ የደም ፍሰት ዝግጅት እንዲኖር ያደርጋል፣ የወሲብ አካላት መዘጋጀት እንዲኖር ያደርጋል:: ለምሳሌ እርጥበት እንዲኖር በሚያስፈልግበት ጊዜ እርጥበት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የወንድ ብልት ደግሞ እንዲነቃቃ እና እነዲነሳሳ  ካስፈለገ የሚያነሳሳውና የሚያነቃቃው ወደብልቱ የሚኖረው ከፍተኛ የሆነ የደም ፍሰት ነው፡፡ ያ የደም ፍሰት ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ አስፈላጊ ከሆነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ወደቦታው እንዲመለስ ለማደረግ ራሱን የቻለ የአእምሮ ዝግጅትና የአካል ብቃት ይጠይቃል፡፡ለምሳሌ ደም ስሮች ጤነኛ መሆናቸው፣ የነርቭ ስርጭቱ ትክክለኛና ጤነኛ መሆን፣ እነዚህ ሁሉ በስርአት ቢሰሩም እንኩዋን አእምሮ ሰውነት እንዲነሳሳ እና እንዲነቃቃ ትእዛዝ ካላስተላለፈ ስሜቱ እክል ሊገጥመው ይችላል፡፡ ስለዚህ አእምሮና ወሲብ እጅግ በጣም የተቆራኙ የሚሆኑበት ምክንያት አብዛኛዎቹ የነርቭ ኬሚካሎች የሚታዘዙት በዚህ መልክ ስለሆነ  ነወ፡፡››
ለግብረስጋ ግንኙነት የወንዶች ብልት ዝግጁ ከማይሆንባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት የሕመም እና ሌሎች ምክንያቶች ይገኙበታል፡፡ የወንዶች ብልት ለወሲብ እንዳይነቃቃ የሚያደርጉ አካላዊ ምክንያቶች የሚኖሩ ሲሆን ከዚያ ውጭ በውስጥ አካል ላይ በሚደርሱ የተለያዩ ሕመሞች ምክ ንያት ችግሩ ሊከሰት እንደሚችል የማዮ ክሊኒክ ለንባብ ብሎአል፡፡
የልብ ሕመም
የደም ስር መዘጋት
ከፍተኛ ኮለስትሮል
ከፍተኛ የደም ግፊት
የስኩዋር  ሕመም
ከፍተኛ ውፍረት
ፓርኪንሰንስ--- የነርቭ በሽታ
ለአንዳንድ ሕመሞች የሚታዘዙ መድሀኒቶች
የቶባኮ (ሲጋራ) ተጠቃሚ መሆን
አልኮሆል እና ተመሳሳይነት ያላቸው እጾች መጠቀም
የእንቅልፍ መዛባት
ለፕሮስቴት ካንሰር ወይንም እብጠት የሚሰጡ ሕክምናዎች
በብልት እና በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች የሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች
የደም ግፊት ሲጨምር፤ ወይንም ከፍተኛ ኢንሱሊን ፤ሰውነት በወገብ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሲወፍር እና ከፍተኛ የሆነ ኮለስትሮል ሲኖር የሚሰጡ ሕክምናዎች…ወዘተ ናቸው፡፡
ዶ/ር ተሸመ ከሰጡት ማብራሪያ ላይ ስለመፍትሔው እናስነብባችሁ፡፡
‹‹…ለወሲብ ስንፈት የሚደረጉ ህክምናዎች በጥንታውያኑ ግብጾች በግሪኮች እና ሮማኖች እንዴት እንደነበር የሚገልጹ ጽሁፎች አሉ፡፡ በዘመናዊው መንገድ ደግሞ የወሲብ ስንፈት በአካልም ሆነ በስነልቡና መንገድ እርዳታ የሚያሻው ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ በአካል ላይ ለሚደርስ ችግር እ.ኤአ. ከ1980 ዎቹ ጀምሮ በመርፌ የሚሰጥ መድሀኒት ስራ ላይ ውሎአል፡፡ይህም ለብልት ጥንካሬ የሚረዳ መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚገልጹት፡፡ ለዚህ አገልግሎት ይበልጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ፐሮስታግላንዲን ኢ አንድ (prostaglandin E1)የተሰኘ እንደሆነ ነው ፡፡በአነስተኛ ደረጃም በጥቅም ላይ የዋሉና የተለመዱት መድሃኒቶች ፓፓቭሪን እና ፔንቶላሚን (papaverine & phentolamine) የተሰኙት ሲሆኑ አንዳንዴ ደግሞ የእነዚህ የሶስቱ መድሃኒቶች ድብልቅም ከጥቅም ላይ ይውላል፡፡በየጊዜውም ሳይንስ ምርምር በማድረግ የሚገኙ አዳዲስ መድሀኒቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡››
ለዘመናዊው ዘዴ ወይንም ለቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በህክምናው አለም የሚሰጥ የፕላስቲክ ቀዶ ህምና ዘዴም ከጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በወንዶች ላይ የሚደርሰውን የወሲብ ስንፈትን ለመከላከል የተለያዩ የህምና እርዳታዎች ከመደረጋቸው በላይ ያለመድሀኒትም የስነልቡና ስልቶችን በመጠቀም የሚደረግ እርዳታ አለ፡፡
እ.ኤአ.በ1970ዎቹ ነበር የዊሊያም ማስተርስ እና ቪረጂኒ ሆንሰን ቡድን ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ባህሪያዊ ህክምና ችግሩ ለደረሰበት ወንድና ለጉዋደኛው እንዲሰጥ እቅዳቸውን ያቀረቡት፡፡ ይህም ጥንዶቹ ምንም እንኩዋን ወሲባዊ ግንኙነት ከማድረግ ለተወሰነ ጊዜ ቢታቀቡም ሌሎች ሁኔታዎችን ወይም አብሮ የመኖርን ትርጉም ወይንም ግንኙነታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት አብረው ለመኖር እንዲችሉ ያደርጋል ፡፡ ወንድየው የግብረስጋ ግንኙነት ለማድረግ በሚችልበት ማለትም በተወሰነ የጊዜ እርቀትም ወሲብ ለመፈጸም ቢችል ጉዋደኛው በትእግስት በመጠበቅ ያን ጊዜ ብቻ ግንኙነት በማድረግ ልትረዳው ትችላለች፡፡  
የማዮ ክሊኒክ ድረገጽ እንደሚመክረውም ችግሩ የደረሰባቸው ወንዶች ካለምንም ሐፍረት ወደሐኪማቸው መቅረብና ለትዳር ወይንም ለፍቅር ጉዋደኛቸውም ሁኔታውን ማስረዳት ይጠቅማቸዋል::


Read 16835 times