Print this page
Saturday, 28 December 2019 13:34

እጅህን ወደ ውሃው አስገባ፤ ወይ አሣ ይዘህ ትወጣለህ አሊያም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ

Written by 
Rate this item
(18 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ በጣም ብርቱ ሰው ነበረ፡፡ ይህ ሰው ሃሳቡን ማጋራት ይወዳል:: ምግቡንም ብቻውን መመገብ አይወድም፡፡ መወያየትና የመጣላትን አዲስ ሃሳብ ማንሳትና ማዳበር ያዘወትራል፡፡ ነጋ ጠባ አስተውሎቱን የማሳደግና ልባዊ የብስለት ፀጋን የማጐልበት፣ የመወያየት፣ ተስፋና ምኞትን የማለምለም፣ ብርቱ ታታሪነትን የማፍካትና አዲስ መንገድን አለመፍራት፣ ለለውጥ አለመሸማቀቅ፣ ሁልጊዜም የሃሳብ በርን የመክፈት ባህል ተገቢ የጉዞ ጥንካሬ አለው፡፡ ይህ ሰው አዘውትሮ “አዝማሪና ውሃ ሙላት” የሚለውን የከበደ ሚካኤልን ግጥም ይጠቅሰዋል፡፡ እንደሚከተለው፡-
አንድ ቀን አንድ ሰው ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር እያለ ጐርደድ
አንድ አዝማሪ አገኘ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ ድምፁን አሳምሮ
ምነው አቶ አዝማሪ ምን ትሠራለህ ብሎ ቢጠይቀው
ምን “ሁን ትላለህ”
አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ
አሁን ገና ሞኝ ሆንክ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩስ ባልከፋ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን እያሽካካ መገስገሱን ትቶ
እስኪ ተመልከተው ይህ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ
ተግሳጽም ለፀባይ ካልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ
መሄድ መሄድ አለኝ ጐዳና ጐዳና
አልግደረደርም ዘንድሮስ እንዳምና
እስቲ ላነሳሳው አንበርብር ጐሹን
በደሬ አደባባይ የወደቀውን
እሱስ ሆኖ አይደለም ታሪከ - ቅዱስ
መጽደቁንም እንጃ ያች ያንበርብር ነብስ
ሃዋርያው ሲናገር ወደምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ!!
ኧረ ስንቱ ስንቱ፣ ናቸው የሞቱቱ
ቀኝ እጃቸው አጥሮ ፊደል በማጣቱ
እናትሽን አትውደጅ ለ9 ወር ዕድሜ
ተሸክሜሻለሁ እስከዘላለሜ!
እንደ ዐይን እንደ ጆሮ፣ እንደ እግር እንደ እጅ
ወዳጅ ማለት አብሮ፣ ሲባክን ነው እንጂ
***
ሀገራችን ከልቧ ምሁር ትፈልጋለች፤ አለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” እንደሚባለው ይሆናል፡፡ አሊያም በከርሞ ሰው መንፈስ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን እንደሚለው፤
“ምኞቴ እንደ ጉም መንጥቃ
ተስፋዬ እንደ ጉድፍ ወድቃ
የወንድሜን ልጆች እንኳ ለርስታቸው ሳላበቃ
የእኔ ነገር በቃ በቃ!”
ምንም ይሁን ምንም፤ ከመሆን የማይቀር አንድ አንድ ጉዳይ፤ ከመፈፀም ወደ ኋላ አይልም፡፡ ሲሆን አይተን ዳኝነት ከመስጠት በስተቀር እነ ገዳይ የሚረፍዱ አያሌ ናቸው፡፡ ከበደ ሚካኤል እንዳሉት፤
“ሂደቱን ስንቆጥር፣
አለ አንዳንድ ነገር
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር”
ይህን የዓለም ዕውነት መካድ አይቻልም
ለውጡ ዐይናችን ሥር ነው ውሉ እንዲለመልም
አገር እንደ ኮረዳ አካል ያለ ፍቅር ከቶ አትጠናም
አንጀት ካልቆረጠ ግና
የአንጀት ጥሪው አይሰማም
ሳይበስል ፍሬው አይጠናም
መንገድ ሳይጀምሩት አያልቅ
ምኞት ዳር -ዳር አያፈራም
ፈተናው ለትዕግሥት ነው፤ ለማይሞት የቁም አበሳ
እንደ አዳኝ በማነጣጠር፣ እንደ ዕውር በዳበሳ
ለዳኝነት አትቸኩል፣ ለቀና መፍትሔው ሳሳ
ከሁለት ነገር አንድ ላለማጣት ልፋ፡፡
ተረታችን እንደሚለው፤
እጅህን ወደ ውሃው አስገባ
ወይ አሳ ይዘህ ትወጣለህ፡፡
አሊያም እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ፡፡   

Read 33302 times
Administrator

Latest from Administrator