Print this page
Saturday, 28 December 2019 13:56

አንዱን ሁኑ፤ ሙቅ ወይ ቀዝቃዛ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 የደቀ መዝሙርነት ካባ የለበሰ አንድ ሰው ሁልጊዜ ማለዳ በቅርብ ወደሚገኝ አንድ መናፈሻ ይሄድና የዛፎቹን አበቦች ይመለምላል። እጅና ዓይኖቹ አበቦቹን ሲያገኙ ይስገበገባሉ፡፡ አጠገቡ ያገኘውን አበባ  በሙሉ ይቀጥፋል፡፡ አበቦቹን የሚፈልጋቸው ለአንድ የሞተ ምስል፣ ከድንጋይ ለተቀረፀ ምስል ሊያቀርባቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ለማለዳው ፀሐይ የተጋለጡት አበቦች ያምራሉ። ሲቀጥፋቸው ደግሞ በሃይል እየመነጨቀ ነው፤ ርጋታ አይታይበትም፡፡ ለሚያመልከው ጣኦት፣ ለሞተ የድንጋይ ምስሉ ብዙ አበባ ይፈልጋል፡፡
በአንድ በሌላ ቀን የተወሰኑ ወጣት ልጆች አበባ ሲቀጥፉ ተመለከትኩ። እነዚህኞቹ አበቦቹን የፈለጓቸው ለጣዖታቸው አይደለም መሰል ያለ ርህራሄ እየቀነጠሱ ይጥሏቸዋል። እናንተስ እንዲህ አድርጋችሁ አታውቁም? ግን ለምንድነው የምታደርጉት? በመንገዳችሁ ያገኛችሁትን ቀንበጥ እየቀነጠሳችሁ ወዲያ ትጥላላችሁ፡፡ እንዲህ አይነት ሃሳብ የለሽ ተግባር እንደምትፈጽሙ አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? በእድሜ የገፉ ሰዎችም ይህን ይፈጽማሉ:: እነሱም ውስጣዊ ጭካኔያቸውን፣ ለህያው ነገሮች ያላቸውን ንቀት የሚገልጡበት የራሳቸው መንገድ አላቸው። ስለ ርህራሄ ያወራሉ፤ የሚሰሩት ነገር በሙሉ ግን አፍራሽ ነው፡፡
አንድ፣ ሁለት አበባ ቀንጥሳችሁ ፀጉራችሁ ላይ ብትሰኩ ወይም ለምትወዱት ሰው ብታበረክቱ ምንም ላይባል ይችላል። ዝም ብሎ ቀነጣጥሶ መጣሉን ግን ምን አመጣው? ትላልቅ ሰዎች ምኞታቸው ያስከፋል፤ በጦርነት ይገዳደላሉ፤ በገንዘብ ይጠፋፋሉ። የተደበቀ ተግባራቸውን የሚገልጡበት የተለያየ መንገድ አላቸው፡፡ ወጣቶች ደግሞ የእነሱን ፈለግ እየተከተሉ ነው፡፡
ወጣቶችም ሆንን ሽማግሌዎች የርህራሄ ስሜት የለንም፡፡ ለምን? ፍቅርን ስለማናውቅ ነው?
ቀላል ፍቅር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ውስብስቡ የወሲብ ፍቅር ወይም የእግዚአብሄር ፍቅር ሳይሆን ፍቅር ብቻ - ለስላሳ መሆን፤ በሁሉም ነገር ለስላሳ አቀራረብን መጠቀም:: ወላጆቻችሁ በጣም ስራ ስለሚበዛባቸው ቤት ውስጥ ይህን ቀላል ፍቅር አታገኙትም፤ በቤታችሁ ይህን እውነተኛ ፍቅር፣ ለስላሴ ስለማታገኙ እዚህ ስትመጡ ይህን ስሜት አልባነታችሁን ይዛችሁ ነው፡፡ ይህን ስሜት ንኩነት እንዴት ማምጣት አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ የደንብ እገዳ ሲኖርባችሁ ትፈራላችሁ፡፡ ሰዎችን፣ እንስሳትን፣ አበቦችን እንዳትጎዱ የሚያደርጋችሁን ስሜት ንኩነት እንዴት ህያው ማድረግ ይቻላል?
በዚህ ሁሉ ነገር ተማርካችኋል? መማረክም አለባችሁ፡፡ ስሜት እንዲኖራችሁ ፍላጎት ካላደረባችሁ ሙት ናችሁ - አብዛኞቹ ሰዎችም እንዲህ ናቸው። በቀን ሶስት ጊዜ ቢበሉም፣ ልጆች ቢያፈሩም፣ መኪና ቢያሽከረክሩም፣ ምርጥ ልብሶች ቢለብሱም እንደ ሙት ናቸው፡፡
ስሜት ንኩ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? ለነገሮች ርህራሄ ማሳደር ነው፡፡ የሚሰቃዩ እንስሳትን መታደግ፣ በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ሰዎች እንዳይጎዱ ከመንገድ ላይ ድንጋይና ምስማሮችን ማንሳት ነው፡፡ ለሰዎች፣ ለአዕዋፋት፣ ለአበቦች፣ ለዛፎች መራራት ነው፤ የእናንተ ስለሆኑ ሳይሆን የነገሮችን ድንቅ ውበት በንቃት ስለተመለከታችሁ ብቻ። ይህን ስሜታዊነት እንዴት ማምጣት ይቻላል?
ጥልቅ ስሜት ሲኖራችሁ አበቦችን አትቀጥፉም፣ ነገሮችን የማጥፋት ሰዎችን የመጉዳት ፍላጎት አይኖራችሁም፤ እውነተኛ አክብሮትና ፍቅር ይኖራችኋል፡፡ በሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ዋነኛው ፍቅር ነው፡። ፍቅር ስንል ምን ማለታችን ነው? አንድን ሰው የምታፈቅሩት በምላሹ ፍቅር ሽታችሁ ከሆነ በእርግጠኝነት ይህ ፍቅር አይደለም:: ማፍቀር ማለት በምላሹ ምንም ሳይጠይቁ በልዩ የፍቅር ስሜት ውስጥ መሆን ነው፡፡ በጣም ጎበዞች ልትሆኑ፣ ፈተናዎቻችሁን በሙሉ ልታልፉ፣ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝታችሁ ትልቅ ቦታ ልትይዙ ትችላላችሁ፡፡ ይህ ስሜታዊነት፣ ይህ የፍቅር ስሜት ከሌላችሁ ግን ልባችሁ ባዶ ይሆናል፣ ህይወታችሁን በሙሉ ትሰቃያላችሁ፡፡
ስለዚህም ልብ በዚህ የፍቅር ስሜት መሞላት አለበት፡፡ ልባችሁ በፍቅር ሲሞላ አታጠፉም፣ ርህራሄ የለሽ አትሆኑም፣ ጦርነቶች አይኖሩም:: ደስተኞች ትሆናላችሁ፡፡ ይህ ፍቅር  እንዴት እውን ሊሆን ይችላል? ፍቅር ከአስተማሪው፣ ከመምህሩ መጀመር እንዳለበት እርግጥ ነው። መምህሩ ስለ ሂሳብ፣ ስለ ጆግራፊ ወይም ስለ ታሪክ መረጃ ከሚሰጣችሁ ይልቅ በልቡ ይህን የፍቅር ስሜት አሳድሮ ስለ ፍቅር ቢናገር፣ ከመንገድ ላይ ድንጋይ ቢያነሳና በሰራተኛው ላይ የስራ ጫና ባይደራርብ፣ ሲናገር፣ ሲሰራ፣ ሲጫወት፣ ሲመገብ፣ ከእናንተ ጋር ሲሆንም ሆነ ብቻውን፤ይህ ስሜት ተሰምቶት --- ስሜቱንም የሚገልጽ ከሆነ እናንተም ፍቅር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ፡፡
ንፁህ ቆዳ፣ ቆንጆ ፊት ሊኖራችሁ ይችላል፤ የሚያምር ልብስ ልትለብሱ ወይም ታላቅ አትሌት ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ በልባችሁ ፍቅር ከሌለ ግን ከሚገባው በላይ አስቀያሚዎች ናችሁ፡፡ ስታፈቅሩ ፊታችሁ ጨፍጋጋ ይሁንም ቆንጆ ያበራል። በህይወት እንደ ፍቅር ያለ ምንም የለም፡፡ ስለ ፍቅር ማውራት፣ ስሜቱን መጎናፀፍ፣ መንከባከብ፣ እንደ ሃብት መያዝ አስፈላጊ ነው:: አለበለዚያ ይጠፋል - ምክንያቱም ዓለም በጣም ጨካኝ ነው፡፡
በወጣትነታችሁ የፍቅር ስሜት ከሌላችሁ፣ ሰዎችን፣ እንስሶችን፣ አበቦችን በፍቅር ካልተመለከታችሁ በዕድሜ ከፍ ስትሉ ሕይወታችሁን ባዶ ሆኖ ታገኙታላችሁ፤ ብቸኞች ትሆናላችሁ፤ ፍርሃት ጥላውን ያጠላባችኋል፡፡ ልባችሁ በዚህ ልዩ የፍቅር ስሜት በተሞላ ጊዜ ጥልቀቱን፣ ደስታውን፣ ፍንደቃውን በተጎናፀፋችሁ ቅጽበት ዓለም ተለውጣ ትታያችኋለች፡፡       
ምንጭ፡- (በተስፋሁን ምትኩ ከተተረጎመው “ውስጣዊን ማንነት ማወቅ” መጽሐፍ የተወሰደ፤1999 ዓ.ም)

Read 3392 times
Administrator

Latest from Administrator