Saturday, 11 January 2020 14:18

ለውጥ የሚሻው ፓርላሜንታዊ ሥርዓታችን

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

   የጽንሰ ሐሳብ ቅንፍ
በፓርላሜንታዊ የመንግሥት አወቃቀር፣ አስፈጻሚውና ሕግ አውጪው ልክ እንደ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት የሚለያዩበት ወሰን ስለሌላቸው፤ እርስ በርስ ተቀይጠው በጋራ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ የአስፈጻሚው አባላት፣በቀጥታ በሕዝብ አይመረጡም፡፡ በቅድሚያ፣በሕዝብ እንደራሴዎች  አማካኝነት  የአስፈጻሚው ቁንጮ ይሰየማል፡፡ የሕግ አስፈጻሚው አለቃ የሚሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር በበኩሉ፣ ካቢኔውን ያዋቅራል፡፡ የአስፈጻሚው ቁንጮ ሆኖ የሚሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል አብላጫ መቀመጫ ባለው አንድ ወይም ጥምር ፓርቲዎች አማካኝነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲው እስከመረጠው ድረስ እድሜ ልኩን ለመምራት የሚችልበት እድል አለው፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ልሂቃን፣ ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን በገደል የተከበበ እንደሆነ ይገልጹታል:: ሥርዓቱ፣ ለአምባገነናዊ አገዛዝ ያለው ተጋላጭነት ከፍተኛ ነው፡፡ በአፍሪቃ፣ ይህንን መንግሥታዊ አወቃቀር የሚከተሉት ሀገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በአንጻሩ፤ ሀገራችን እስካለንበት ዘመን ድረስ፤ በዚህ መንግሥታዊ ቅርጽ እየተዳደረች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የፓርላሜንታዊው ሥርዓት፣ ከዘውጌው ፌዴራሊዝሙ ባልተናነሰ ደረጃ፣ እንደ ሀገር ብዙ አጉድሎናል፡፡ መንግሥታዊው አወቃቀር፣ ለአምባገነናዊ አገዛዝ ምቹ አውድን እንደፈጠረ ዋቢ የሚሆነን፣ የሶሻሊስት ቅሪት የሆነው አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ተንሰራፍቶ የኖረበትን የአፈና ዘመን መለስ ብለን ስንቃኝ ነው፡፡
ሥርዓቱ፤ በነቢብ ህልውናቸው የተረጋገጠ፤ በገቢር ግን ተመጣጣኝ ሥልጣን የሌላቸው “ፓፔት” ቅርንጫፎችን ሊታቀፍ ይችላል:: ሥልጣን በአንድ ክሊክ፤ በጥቂት ግለሰቦች እጅ ተጠቃሎ የሚያዝበት እድሉ በእጅጉ የሰፋ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፤ ለዴሞክራሲዊ ሥርዓት እንደ ማእዘን ድንጋይ የሚቆጠረው የቁጥጥርና የሚዛን መርህ /checks and balance/ ውሃ ይበለዋል፡፡ ያለ ቁጥጥርና ሚዛን መርህ፤ በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች መካከል፣ የሥልጣን ክፍፍል የሚባል ነገር ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ በአልቦ የቁጥጥርና ሚዛን በሚዋጅ መንግሥት ውስጥ፤ የአንዱ ቅርንጫፍ ጉልበት ከልክ በላይ ፈርጥሞ፣ ሌሎችን ጭፍራ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ይህ ነባራዊ ሁኔታ፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመንን በትክክል የሚገልጽ ነው ቢባል፤ እውነታውን ማበል አይሆንም፡፡
ጥርስ አልባ የመንግሥት ቅርንጫፎች
ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፣ ሕግ አውጪው /House of Peoples’ Representatives/ በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርገውን ግብር ሲተገብር ነው የኖረው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት፣ ራሳቸውን እንደ ሕዝብ እንደራሴ ሳይሆን እንደ መንግሥት ሠራተኛ /civil servant/ ነበር የሚቆጥሩት:: እንደራሴዎቹ “ለህሊናቸውና ለመረጣቸው ሕዝብ ታማኝ መሆን አለባቸው” የሚለው የሕገ-መንግሥት አንቀጽ፤ ከተጻፈበት ቀለም የበለጠ ዋጋ አልነበረውም፡፡ የሕዝብን ትርታ ከማድመጥ ይልቅ፤ ለፓርቲያቸው ሕግና ደንብ ሎሌ ሆነው ኖረዋል፡፡ ፓርላሜንታዊው ሥርዓት ከላይ ወደ ታች፣ በአውራና ጭፍራ የግንኙነት መስመር በተጠረነፈ የፓርቲ አሠራር ሽባ ተደርጓል፡፡  
ሸንጎው የሞቀ ክርክር ጎብኝቶት አያውቅም:: የአስፈጻሚው ተቀጽላ ነበር፡፡ የአስፈጻሚውን ረቂቅ፣ ፓርላማው ውድቅ ለማድረግ የጀገነበትን አጋጣሚ አናስታውስም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ካቢኔያቸውን ለይስሙላ ተጠቅመው፣ የፈለጉትን አዋጅ፣ በዚሁ ፓርላማ ሲያጸድቁ እንደኖሩ ይታወቃል:: በሙስና የተጠረጠረ ግለሰብን ዋስትና የሚከለክለው ሕግ፣ በአንድ ጀምበር ተረቅቆ በፓርላማ የጸደቀበትን ክስተት፣ ለአብነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ ሕግ ተርጓሚውም ቢሆን ከፖለቲካ ውግንና ነጻ አልነበረም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነትና በፓርላማው አጽዳቂነት የሚዋቀር ነው፡፡ የእጩነት መለኪያ ሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባር ሳይሆን፣ ለሕወሓት/ኢሕአዴግ ያላቸው ታማኝነት ነበር፡፡
በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተደነገገው ፓርላሜንታዊው አወቃቀር፣ የመንግሥት ሥልጣን እንዲሽመደመድ፣ በአንጻሩ የፓርቲ ጉልበት እንዲፈረጥም ምቹ አውድን እንደፈጠረ፤ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሕወሓት ያሻውን የፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለማንበር፣ የተለያዩ መርህዎች ይከተል እንደነበረ “The Last Post-Cold War Socialist Federation: Ethnicity, Ideology and Democracy in Ethiopia” በሚለው የሶስተኛ ዲግሪ ሟማያ ጽሑፍ ላይ ተገልጿል፡፡ “ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱን ለፖለቲካ ፋይዳ ብቻ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ከዚህ ይልቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የልማታዊ መንግሥት መርህ፣ተከታታይና አሰልቺ የፓርቲ ግምገማ  ዋነኛ መሳሪያዎቹ ናቸው፡፡”
ሕወሓት ወሳኝ የሆኑ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን  ወደ ፓርላማ ማምጣት ሳያስፈልገው፤ የራሱን አጀንዳ ገቢራዊ የሚያደርግበት፣ ሌሎች አማራጮችን በሥራ አስፈጻሚው አማካኝነት በአቋራጭ ይጠቀም  ነበር፡፡ በዚህ ላይ ከፓርቲ ውግንና ያልጸዳው የደህንነቱና የመከላከያው አወቃቀር ሲታከልበት፤ የፓርላሜንታዊው ሥርዓት ለይስሙላ የተቀመጠ እንጂ ምንም አይነት ፋይዳ ያለው ሥራ ሲሰራ እንዳልኖረ ግልጽ ነው፡፡  
ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት ከመንግሥት ይልቅ፤ የፓርቲ አቅም በእጅጉ የፈረጠመበት ዘመን ነበር፡፡ ገዢው ፓርቲ፣ የፈለገውን አዋጅ ለማጽደቅ የፓርላማውን ፊት ማየት አይጠበቅበትም፡፡ በዴሞክራሲያዊ ማእከልነት መርህ የሚዘወረው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም፣ ሁሉን ነገር አቅልሎት ኖሯል፡፡ ለዚህም ነው፤ከለውጡ በኋላም ቢሆን፣ሕወሓት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደቆረበ የቀረው፡፡
አምባገነንነትን ለመከላከል ተመራጭ የሆነው ፕሬዝዳንታዊው ሥርዓት
ፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት ቅርጽ፣ ከፓርላሜንታዊ ሥርዓት ጋር ሲነጻጸር ብዙ ጥንካሬ አለው፡፡ ይህን የመንግሥት ሥርዓት የሚያንጹት ምክር ቤቶች፣ የራሳቸው ህልውና ያላቸው ሲሆን የሕግ አውጪው ምክር ቤት (legislative) እና ሕግ አስፈጻሚው (executive) በተመሳሳይ የምርጫ ቀመርና ወቅት የሚመሠረቱበት አካሄድ አይኖርም::  የአሜሪካን ርእሰ ብሔርና ርእሰ መንግሥት የሆነው ፕሬዝዳንቱና የተወካዮች ምክር ቤት (congress) አባላት በተለያየ የምርጫ ዘመን ነው በሕዝብ የሚመረጡት፡፡
የፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት በጣም የተረጋጋ መንግሥትን ለመፍጠር ተመራጭ ነው፡፡ ልክ እንደ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት በየጊዜው ጥምር መንግሥት እየመሠረቱ የመፍረስ አደጋ አይኖርም፡፡ ፕሬዝዳንቱ በሙስና፣ በወሲብ ቅሌት አልያም በሀገር የመክዳት ወንጀል ከተጠረጠረ “ኢምፒችመንት” በሚባለው አሰራር ብቻ፣ የሥልጣን ዘመኑ ከማክተሙ በፊት  ሊባረር ይችላል፡፡
ይህ ከሥልጣን የማባረሪያ መንገድ ግን ብዙ ፈታኝ የሆኑ አስተዳደራዊ ውጣ ውረዶችን ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ የሰሞኑን የትራምፕን ውዝግብ እዚህ ጋ መጥቀስ ይቻላል::
ሕግ አውጪውና ከአስፈጻሚው  ጋር ያለው ወሰን በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች እርስ በርስ መተዛዘል ሳይጠበቅባቸው፣ በራሳቸው ቆመው በሕገ መንግሥት የተሰጣቸውን ሥልጣን፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል በነጻነት መከወን ይችላሉ፡፡ የእኛን የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ብንወስድ፣ በአካል ሁለት በግብር ግን አንድ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በሁለቱም ምክር ቤት ያሉት ካድሬዎች በፓርቲ ማእከላዊነት ስም እግር ተወርች ተይዘዋል፡፡
ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት፣ ቅጣ ያጣ የፓርቲ አምባገንነት እንዳይሰፍን ልጓም ያበጃል:: የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ አወቃቀርን አብነት ብናደርግ፣ ይህንን ነጥብ በእጅጉ የሚያጠናክርልን ይሆናል፡፡ ሴኔቱ /የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ/ ከኮንግረሱ /ከሕግ አውጪው/ ጋር እኩል ሕግ የማውጣት ሚና አለው፡፡ ሁለቱ ምክር ቤቶች ከ 2/3 ድምጽ በላይ ወስነው ያሳለፉትን ረቂቅ፣ ፕሬዝዳንቱ ውሳኔውን የመሻር ስልጣኑን /ቪቶ ፓወርን/ መጠቀም አይችልም፡፡ ስለዚህ ሴኔቱ  ከኮንግረሱ ጋር ያለው የአግድሞሽ የሥልጣን ክፍፍል ጤናማ ነው፡፡
የእኛ የፌደሬሽን ምክር ቤት ግን፣ ሕገ መንግሥትን ከመተርጎምና በክልሎች መካከል የሚፈጠር ግጭትን ከመፍታት በዘለለ፤ ልክ እንደ አሜሪካው ሴኔት፣ የቁጥጥር ሥልጣን ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አይችልም:: ሕግ መንግሥቱን የመተርጎም ሥራም ቢሆን በአግባቡ ተፈጽሞ አያውቅም፡፡ ይኽ ሥልጣን፣ ለነጻ የሕግ አካል እንጂ የካድሬዎች መቀመጫ ለሆነው ለፌዴሬሽን ምክር  የሚሰጥበት አግባብ የለም፡፡
ካድሬ ሕግ ጥሶ፣ መልሶ ለካድሬ አቤቱታን ማቅረብ ወለፈንዲ ይሆናል:: አባቱ ዳኛ፣ ልጁ ቀማኛ እንደ ማለት ነው:: ሌላው፣ በፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ውስጥ ሁሉም ሕዝብ ይሁንታውን የሰጠው መሪ፣ በርእሰ መንግሥትነት መቀመጡ በአዎንታዊነት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡
ሕዳግ
ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት አምባገነናዊ አገዛዝ እንዳይሰፍን፣ በነጻ ምክር ቤቶች መካከል ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ከለላ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም የሕገ መንግሥቱ “ንቀለ-ተከላ” ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡት ዐቢይ ነጥቦች ውስጥ መንግሥታዊ አወቃቀሩ አንዱ መሆን አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ የተንጸባረቀው ሃሳብ የጸሃፊውን አመለካከት ብቻ የሚገልጽ ነው፡፡

Read 1689 times