Saturday, 18 January 2020 13:30

“ህወኃት የሽንፈት ፖለቲካ እያካሄደ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   • *ህወኃትና ብልጽግና ሽኩቻቸውን ለህዝብ ማውረድ የለባቸውም
           • *በትግራይ የምርጫ ሳይሆን የጦርነት ቅስቀሳ እየተደረገ ነው
           • *ከምርጫው በፊት ሁነኛ ድርድር ማካሄድ ያስፈልጋል
           • *ህወኃት ፌደራሊስት ነኝ የማለት ሞራል የለውም


          የቀድሞ የህወኃት መስራችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማሱ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ በመጪው ነሐሴ ወር ይደረጋል ስለተባለው አገራዊ ምርጫ፣ በብልጽግና ፓርቲና በህወኃት መካከል ስለተፈጠረው አለመግባባት፣ ከምርጫው በፊት ሊደረጉ ስለሚገባቸው ቅድመ ዝግጅቶች እንዲሁም በትግራይ ምን ዓይነት ምርጫ እንደሚጠብቁ አብራርተዋል - በቃለ ምልልሳቸው

          የመጪው አገራዊ ምርጫ ሂደትና ውጤት  ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?
ምርጫው ምን ሊመስል ይችላል ለሚለው ጥያቄ፤ የተለያዩ ሁኔታዎችን ማየት ያስፈልጋል:: ምርጫ ስንል፤ ነፃ፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡ ይሄ የምርጫ መመዘኛ፣ ሀገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ተፈፃሚነት ይኖረዋል ወይ? የሚለው የኔም ጥያቄ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ህገ መንግስቱ፣ ምርጫ በየአምስቱ አመቱ መካሄድ አለበት ይላል፡፡ እነዚህን ሁለት ሁኔታዎች የግድ ማስታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ለኔ ለምርጫ ምቹ ሁኔታ አለ ወይ? ቢባል፣ የለም ነው መልሱ፡፡ ኢህአዴግ በሀገሪቱ ህግና ሥርዓት ማስከበር ካልቻለ ቄሮ፣ ፋኖ፣ ኤጀቶ ወዘተ-- በሚል በየቦታው የተደራጀ አካል የጐለበተበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይሄ ሁኔታ ከምርጫው ጋር በተያያዘ፣ በመንግስት ላይ ሙሉ እምነትን ለማሳደር አያስችልም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አሁንም ድረስ ያዝ ለቀቅ የሚያደርጉ ግጭቶች አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዴት ያለ ምርጫ ነው ልናደርግ የምንችለው? ይሄ ለኔ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችስ በፈለጉበት ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት ይችላሉ ወይ? በአንዳንድ አካባቢዎች እኮ ተንቀሳቅሰው አባሎቻቸውን ማደራጀት አልቻሉም፡፡ ለምሣሌ “አረና” በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ተንቀሳቅሶ መስራት አልቻለም፡፡ ሌሎችም ፓርቲዎች ተመሳሳይ ችግር እንደገጠማቸው ይነገራል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ውጤታማ ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው የሚችለው?
ምርጫው በነሐሴ እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡ ምርጫው እርስዎ በገለጹት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከተካሄደ ውጤቱ ምን ይሆናል?
ምርጫ ቦርድ ከኛ የተለየ ግምገማ ኖሮት፣ ምርጫውን ማካሄድ ከቻለ አስገራሚ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ “ፍትሃዊ፣ ነፃና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ማድረግ እችላለሁ” ብሎ ከተማመነ እኛም እንደግፈዋለን፡፡ ነገር ግን ሁኔታው እንደዚያ አይደለም፡፡ የሌላውን አካባቢ ትተን እንኳ በትግራይ ያለውን ብንመለከት፣ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ በትግራይ እንደውም የምርጫ ሳይሆን የጦርነት ቅስቀሳ ነው እየታየ ያለው፡፡ በዚህ ሁኔታ ምን አይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው? አሁን’ኮ በህወኃት እየተቀነቀነ ያለው የድሮ የጦርነት ቅስቀሳ ዘፈን ነው፡፡ በጦርነት ቅስቀሳ መሃል ምን አይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው? ሃይል ያለው ገብቶ ይወዳደርበት ከተባለ፣ ያው ከዚህ በፊት የተለመደው ምርጫና ውጤቱ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ምርጫው በጐ ውጤት ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡ ግጭቶችን ያሰፋል የሚል ስጋት ነው ያለኝ፡፡   
“መድረክ” ለምርጫው እያደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል? የአቶ ጃዋር መሐመድ በኦፌኮ በኩል መድረክን መቀላቀላቸውስ  ምን አንድምታ ይኖረዋል?
እኛ በመድረክ በኩል ለምርጫው በቂ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ በምርጫውም ብቁ ተወዳዳሪ እንሆናለን፡፡ ለዚያም ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ከአቶ ጃዋር ጋር በተያያዘ በመድረክ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች ማንን በአባልነት እንደሚመለምሉ የራሳቸው ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ እንኳን ጃዋር ሌላውም በመድረኩ ውስጥ ባለ አንደኛው የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን ይችላል፡፡ የመድረክን አላማና ግብ ተቀብሏል ማለት ነው፡፡ ለድርጅቱ ህገ ደንብና ፕሮግራም ተገዢ ሆኗል ማለት ነው፡፡ መድረክ ደግሞ የቀድሞ ፕሮግራሙንና ደንቡን አልለወጠም፡፡
የመድረክ ፕሮግራምና ደንብ ደግሞ አንድ ግለሰብ በመቀላቀሉ አይለወጥም፤ ያ ግለሰብም የማስለወጥ አቅም አይኖረውም፡፡ እኛ እንደውም የጃዋርን ወደ መድረክ መምጣት በበጐ ነው የምናየው፡፡ ጃዋር መምጣቱ እንደ አንድ ተጨማሪ አቅም ነው የሚሆነን እንጂ የሱ መምጣት የመድረኩን አላማና ግብ አያዛንፍም፡፡ እንደ ጃዋር ያሉ ሰዎች እንደውም በሀገሪቱ ህጋዊ እውቅና ባላቸው ድርጅቶች ውስጥ አባል ሆነው ቢታገሉ ለሀገሪቱ ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ መድረክ ስለ ኢትዮጵያም፣ ስለ ዲሞክራሲም፣ ስለ መሬትም ስለ ሌላውም ያለው ፕሮግራምና አስተሳሰብ አልተቀየረም፡፡
ህወኃት፤ ከኢህአዴግ ድርጅቶች ተነጥሎ ብቻውን መቆሙና መስመሬን አልተውም ማለቱን እንዴት አዩት?
ህወኃት ያው እንደተለመደው የራሱን አቋም ነው የያዘው፡፡ ይሄን አቋም ለምን ያዝክ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ህወኃት እንደ ፖለቲካ አቅጣጫ ወይም ርዕዮተ አለም አድርጐ የወሰደው አብዮታዊ ዲሞክራሲን ነው፡፡ ይሄን እንደ ሃይማኖት ወስዶ “ይሄን ያልተቀበለ ከሃዲ ነው፤ አጥፊ ነው” የሚል አቋም ወስዷል፡፡ ይሄ ደግሞ አደገኛ የአፈና አቋም ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ሌሎችን በጠላትነት ፈርጆ የሚያጠፋ አተያይ ነው፡፡ ህወኃትን ከዲሞክራሲ ጋር የሚያጣላውም፤ ይሄው ጽኑ መስመሬ የሚለው ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ “ከእኔ ጋር የነበሩ መስመሬን ትተው ክደውኛል” የሚለውም በዚህ ግትርና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አቋም ነው፡፡ ፓርቲዎቹ የተለያዩት በአቋም እንጂ በመካካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ህወኃት መስመሬ የሚለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣እንዲህ አይነቱን ነገር በክህደት ነው የሚፈርጀው፡፡ በአጠቃላይ መስመሬ የሚለው አቅጣጫ ፍረጃ ይበዛዋል:: ከአዲስ አስተሳሰብ ጋር አብሮ የሚለወጥ መስመርም አይደለም፡፡   
ህወኃት መስመሬን አፀናለሁ ብሏል፤ አሁን በትግራይ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ያው እንደ ድሮው ነው አሁንም የቀጠለው:: የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ለውጥ አስተሳሰብ ነው:: አስተሳሰብ ካልተለወጠ ሌላ ምን ለውጥ ሊኖር ይችላል? የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፤ ለፖሊሲና ለአተያይ ለውጦች መነሻ የሚሆነው:: ህወኃት ደግሞ አስተሳሰቤን አልለውጥም ካለ፣ ፖለቲካውም እንደ ድሮው በአፈና ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነቱም ይቀጥላል፣ እኛን ማግለሉም እንዲሁ፡፡ ብልሹ አሠራሮችም ይቀጥላሉ፡፡ ሁሉም ነገር በነበረበት ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ አቶ መለስ እኮ ከ10 አመት በፊት በመቀሌ ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተናገሩትን፣ በየቀኑ በሚዲያቸው እየደጋገሙት ነው፡፡ “ባንዳ”፣ “አገር ሻጭ” እያሉ እኛን መፈረጁ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በአጠቃላይ ህወኃት በትግራይ እያካሄደ ያለው የሽንፈት ፖለቲካ ነው፡፡ ህዝቡን ለመቀስቀስ ያለመው፣ በድሮው የትጥቅ ትግል ስነ ልቦና ነው፡፡
የህወኃትና ብልጽግና ፓርቲ ቅራኔ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል?
በመጀመሪያ በየቦታው ለሚከሰቱ ግጭቶችና መፈናቀሎች ሁሉ ህወኃትን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ የራሱ ድርሻ ቢኖረውም በየአካባቢው ያሉ ልሂቃንም ድርሻቸው የጐላ ነው፡፡ ህወኃትና ብልጽግና ግን የስልጣን ሽኩቻ ነው ያላቸው፡፡ ሁለቱም ይሄን ሽኩቻቸውን በግላቸው ነው መወጣት ያለባቸው፤ወደ ህዝቡ ፈጽሞ ማውረድ የለባቸውም፡፡ በርግጥ አንድ ፓርቲ ከሌላው ተለይቶ የመውጣት መብቱ መከበር አለበት፡፡ ከዚህ አልፎ ግን ህዝብን ተገን አድርጐ የሚደረግ ነገር፣ አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የፓርቲን ጉዳይ ከህዝብ ጋር መቀላቀል ወይም  ወደ ህዝብ ለማውረድ መሞከር መጥፎ ውጤት ይኖረዋል፡፡ የትግራይ ህዝብንና ህወኃትን አንድ አድርጐ የመመልከት ችግር፣ በህወኃትም በብልጽግናም በኩል ይስተዋላል፡፡ ይሄን የአስተሳሰብ ህጸጽ ማረም ያስፈልጋል፡፡
ህወኃት “የፌደራሊስት ኃይሎች ፎረም” የሚል አደረጃጀት ፈጥሯል፡፡ ፎረሙ የህወኃትን ሃይልና አቅም የሚያጎለብትለት ይመስልዎታል?
ይሄ ፎረም የደካማዎች ስብስብ ነው፡፡ ህወኃት “የፌደራሊስት ሃይሎችን አሰባስቤ እንደገና ወደ ስልጣን እመለሳለሁ” በሚል አልሞ የፈጠረው ደካማ ስትራቴጂ ነው፡፡ በጠራው ስብሰባም ላይ አቅም ያላቸው ፓርቲዎች አልተሰበሰቡም፡፡ ብዙዎቹ ጠንካራ ፓርቲዎች ጥሪ ተደርጎላቸው አልተቀበሉትም፡፡ ለምሳሌ በመድረክ ውስጥ ያሉ ሌሎች ፓርቲዎች ሲጠሩ፣ አረና አልተጠራም ነበር፡፡ ሌሎች የተጠሩ የመድረክ ድርጅቶችም ተገቢውን መልስ በመስጠት፣ራሳቸውን ከሂደቱ አግልለዋል:: ህወኃት በጠራው ጉባኤ ላይ  የተሳተፉት ደካማዎቹ ናቸው፡፡ እነዚያ ደግሞ ከአሁን በፊትም ዝም ብለው ያለ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ ዓይነት ናቸው፡፡ ለነገሩ ህወኃት ፌደራሊስት ነኝ የማለት ሞራልም የለውም፡፡ ዲሞክራሲ አልባ ፌደራሊዝም እኮ ነው ሲያራምድ የቆየው:: የፌደራሊዝም መሠረቱ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ፌደራሊዝሙ ዲሞክራሲያዊ ባለመሆኑ እኮ ነው ለግጭት፣ ለተቃውሞና ለብጥብጥ የተዳረግነው፡፡ ከዚህ በኋላ ፌደራሊዝምን ያለ ዲሞክራሲ ማሰብ አይቻልም፡፡ በመሠረቱ፣ ህወኃቶች እናድነዋለን የሚሉትን ፌደራሊዝም የሚቃወም፣ ተጽእኖ ፈጣሪ፣ የፖለቲካ ድርጅት እስካሁን አላየሁም፡፡  
መጪው ምርጫ በተለይ በትግራይ ምን መልክ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
በትግራይ የፖለቲካ ምህዳሩ የሚስተካከል ካልሆነ፣ መጪው ምርጫ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን አጠናክሮ የሚያስቀጥል እንጂ አሳታፊ አይሆንም፡፡ በአሁኑ ወቅት ለዲሞክራሲ መሠረት የሚሆኑ አነስተኛ ነገሮች እንኳ የሉም፡፡ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ፣ ሚዲያ የሚባሉት ሁሉ የሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በትግራይ የሚካሄድ ምርጫ፤ ጉልበት ያለው የሚያሸንፍበት ነው የሚሆነው፡፡ ህወኃት ከዚህ በፊት በነበረው የአፈና ስልት ምርጫውን ሙሉ ለሙሉ ብቻውን ሮጦ፣ ብቻውን ሊያሸንፍ ይችላል፤ ነገር ግን እንደ ቀድሞው ለረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የሚችል አይመስለኝም፡፡ አሁን ዘመኑ ተለውጧል፤ ህዝብ መብቱን መጠየቅ እየተለማመደ ነው:: ስለዚህ አፈና ጊዜያዊ ውጤት እንጂ ዘላቂ ዋስትና አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል፤በአጭር ጊዜ ውስጥ የህወኃት የቆየ ባህርይና አቋም ተለውጦ፣ ነጻ ምርጫ ይካሄዳል የሚል ተስፋ ግን የለኝም፡፡
ከምርጫው በፊት የግድ መደረግ አለበት ብለው የሚያስቧቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ከባለድርሻዎች ጋር ቁጭ ብሎ “ምርጫውን እንዴት ነው ማካሄድ ያለብን” ብሎ መደራደር ያስፈልጋል፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ያለ ድርድር ነው እየተደረገ ያለው፡፡ ይሄ ሌሎችን አግላይ የሆነ አካሄድ ለውጥ አያመጣም፡፡ ስለዚህ በምርጫ ቦርዱ አወቃቀር፣ በህግ ማዕቀፎችና አሠራሮች ላይ ከምርጫው በፊት ባለችው ጥቂት ጊዜም ቢሆን ሁነኛ ድርድር ማድረግ ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ግን በርካቶች ቅሬታቸውን ይዘው የሚሳተፉበት፣ ከተሳተፉ በኋላም የማይተማመኑበት ምርጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መደራደር አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡      


Read 2004 times