Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 30 June 2012 10:50

“…የእኔኑ ነጥቆ ነው እንጂ!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ባልና ሚስት ስለኑሮ ውጣ ውረዳቸው ይወያያሉ፡፡ ባል በጣም ጉረኛ ነው፡፡ ሚስት በጣም ትሁት ናት፡፡

ባል ሠፈር-መንደሩ ጀግና እንዲለው “ለሰው ሁሉ ይሄን ጀብዱ ሰርቼ፣ ከእገሌ ተጣልቼ ልክ አስገብቼው፣ እገሌና እገሌ ተጣልተው አስታርቄያቸው፣ የዕድር ሊቀመንበር ጠፍቶ እኔን መርጠውኝ” እያለ ጉራውን ይቸረችራል! ሚስት፤ “ይህ ሁሉ ጉራ አይጠቅምህም! ወይ ልብ ግዛ አሊያ ጉራ አትንዛ!” ባል፤ “ጉራ አይደለም! እንዲያውም በቅርቡ ጠብ የሚፈልገኝ አንድ ሰው አለ፡፡

እንዴት እንደማቀምሰው አሳይሻለሁ!  የሰው ልክ አያውቅም ይሄ የሰው ትንሽ!” ሚስት፤ “ልብም ቢኖርህ፣ ጀግንነትም ቢኖርህ ሳታወራው፣ ሳትጮህ መሥራት አትችልም?” ባል፤

“ሌላ ምርጫ የለም - አጋጨዋለሁ ብያለሁ አጋጨዋለሁ!” ሚስት፤ “ከነጭራሹ ባትጣላስ? እሺ?” ባል፤ “ምን?! እንደዛ ተናግሮኝ? ዝም ካልኩት ሬሣ ነኝ ማለት ነው!”

በነጋታው ባል ወደ ሥራ ይሄዳል፡፡

ሚስት ቤት ናት እንደተለመደው፡፡ ማታ ግድም ባል ደም በደም ሆኖ ስብርብር ባለ አረማመድ ወደ ቤት ይመጣል፡፡

ሚስት፤ “በሞትኩት! ምን ሆነህ መጣህ?”

ባል፤ “ያ ጠላቴ አሳቻ ቦታ አገኘኝ”

ሚስት፤ “እና ደበደበህ?”

ባል፤ “አይ ተደባደብን!”

ሚስት፤ ጠጋ ብላ ፊቱን እያያችው፤ “እንዴ! እንዴ! እንዴ! ስንት ቦታ ነው የተፈነከትከው፡፡ ይሄ መቼም ቦቅስ አይደለም! ጠላትህ ዱላ ይዞ ነበር እንዴ?”

ባል፤ “አዬ! ደሞ ይሄንን ያህል ወንድነት! የታባቱ ዱላ ይዞ ያውቃል?! የኔኑ ነጥቆ ነው እንጂ!” አላት፡፡

***

በባዶ ሜዳ ጉራ ከመንዛት ይሠውረን! የጠላትን ነገር ከማጣጣል ይሰውረን! ከሁሉም በላይ ግን የገዛ ዱላችንን ነጥቆ፣ በራሳችን ዱላ ከሚቀጠቅጠን ባላንጣ ይከልልልን! ይህ ባላንጣ የማህበር መሪ፣ የፓርቲ ኃላፊ፣ የተቃዋሚ ተጠሪ፣ የቢሮ አለቃ ወይም ማንኛውም ሹም ቢሆን እንኳ ወይ ዱላችንን አጥብቆ መያዝ፣ ወይ ቀድሞ መሠንዘር ወይ ሌላ አማራጭ ይዞ መገኘት ዋና ነገር ነው! ይህ ሲባል ግን የሼክስፒርን አባባል ሳንዘነጋ ነው፡-

“… ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም

አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ - ይቅደም”

ዕውነት ነው!! ሁሌ ወደጠብ ከማምራት፤ መቻቻልን፣ መታገሥን፣ ግማሽ ና ግማሽ እመጣለሁን፣ ማወቅ ትልቅ ነገር ነው! በዕውነት ካሸነፍከኝ ተሸንፌአለሁ፣ ካላሸነፍከኝ አልተሸነፍኩም ማለትን እንድፈር!! ከተሸነፍንበት ተነስተን፤ አርመን፣ በአዲስ ጉልበት መንቀሳቀስን፣ ምንጊዜም ለመማርም ሆነ ለመማማር ዝግጁ መሆንንና ግንዛቤን በአመርቂ ሁኔታ ማዳበርን መካን አለብን!

ስለ ዲሞክራሲ ብለን በምንታገልበት መድረክ ላይ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ ቢያጋጥመን በርግገን፣ የዲሞክራሲ ያለህ ብለን ከአገር መበርገግ በጎ አይደለም! ኢ-ፕሬሳዊ ሁኔታ ቢያጋጥመንም ፕሬስ ካገር ጠፋ ብለን መሰደድ የለብንም! ስለማካተት (accommodation) እና ማዋሃድ (assimilation) ማሰብ ጥንካሬ ነው! ፍትሕ ባጣን ቁጥር ኢፍትሐዊ ሁኔታ ተፈጥሯልና የህግ ነገር በአፍንጫዬ ይውጣ ማለት የህግ ግንዛቤያችንን ደብዛ ማጥፋት ነው!! እዚህም እዚያም ሙስና ተዘወተረ፤ ዘረፋ ናጠጠ፣ የሀሰት ዶክመንት ታተመ ብሎ በቃ፣ ሀቀኝነት ገደል ገብቷል ማለት ሐሞት ማጣት  ነው! አማራጩን ማስላትና ትግሉን ማትባት ብቻ ነው ዘዴው!

“አትሩጥ አንጋጥ” ይላል አበሻ - Haste makes waste ነው በፈረንጅኛ፡፡ ለልማትም፣ ለምርጫም፣ ለድልም አለመቸኮል ታላቁ የሀገራችን ትምህርት ነው! ፓርቲዎች ቸኩለው ፈርሰዋል! ማህበራት ተጣድፈው ተፈረካክሰዋል! ድርጅቶች ሲራወጡ ተጣድፈው እርስ በርስ ተቋስለው ወድቀዋል! ምኑ ቅጡ! ሁሉን በአንድ ጀንበር እንሥራ የማለትን በሽታ ማከም አለብን!

የማንማታበትን ዱላ ይዘን ስንዞር መነጠቅ እንዳለ አንርሳ! በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት ዓይነት ፀፀት የአገር አባዜ ነው! ወይ ዱላህን አጥብቀህ ያዝ፣ አልያም የዱላን ነገር እርግፍ አድርገህ ተወው! አለበለዚያ ”ደሞ ይሄን ያህል ወድነት የእኔኑ ነጥቆ ነው እንጂ!” እያልን መሳቂያ ከመሆን አንድንም!!

 

 

Read 3748 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 10:52