Saturday, 25 January 2020 12:09

በ40ኛው የለንደን ማራቶን

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   ቀነኒሳና ኪፕቾጌ ለአምስተኛ ጊዜ በማራቶን ይፋለማሉ፡፡
          የዓለም ሪከርድ ሊሻሻል ይችላል፡፡

            የዓለም የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኬንያዊው ኤለውድ ኪፕቾጌ እና በማራቶን ሁለተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት የያዘው ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በሩጫ ዘመናቸው ለአምስተኛ ጊዜ በማራቶን ውድድር ሊፋለሙ ነው፡፡ ሁለቱ የዓለማችን የረጅም ርቀት የምንግዜም ምርጥ ሯጮች ከ56 ቀናት በኋላ የሚገናኙት በ40ኛው የለንደን ማራቶን ሲሆን፤ የዓለምን ትኩረት የሳበው የማራቶን ሪከርድ ሊሻሻል እንደሚችል ሁለቱም እምነት ስላላቸው እና  ከቶኪዮ ኦሎምፒክ በፊት አስደናቂው የአትሌቲክስ መድረክ ሊሆን እንደሚችል በመገለፁ ነው፡፡
በ40ኛው የለንደን ማራቶን ላይ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ለአምስተኛ ጊዜ በማሸነፍ አዲስ ታሪክ ለመስራት ማሰቡን ሲናገር፤ ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ በ2004 እና በ2005 እኤአ ላይ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር ካስመዘገባቸው የዓለም ክብረወሰኖች በኋላ ሶስተኛውን የዓለም ሪከርድ በማራቶን ለማስመዝገብ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡
‹‹ወደ ለንደን ማራቶን መመለሴ ከፍተኛ ጉጉት ፈጥሮብኛል፡፡ ያልጨረስኩት ስራ እንዳለ ነው የሚሰማኝ፡፡  የዓለማችን ምርጥ ማራቶን በመሆኑ ከማሸነፍ እፈልጋለሁ›› ሲል የተናገረው ቀነኒሳ ከኤሊውድ ኪፕቾጌ ጋር መፈጣጡን አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት ‹‹ከኤሊውድ ጋር መገናኘትን ስጠባበቀው ነበር፡፡ በሩጫ ዘመናችን ትልልቅ ፍልሚያዎች ነበሩን፡፡ በትራክ፤ በአገር አቋራጭ እና በጎዳና ላይ ሩጫዎች ብዙ ተወዳድረናል፡፡ ልዩ አትሌት ነው፡፡ በሩጫ ዘመኑ ያገኛቸው ስኬቶችም አከብራቸዋለሁ፡፡›› ብሏል፡፡
የዓለም ማራቶን ሪከርድ የሚሰበርበትን እድል አስመልክቶ አትሌቲክስ ዊክሊ በፃፈው ሀተታ ገብ እንደምችል ያረጋገጥኩበት ነው:: በለንደን ማራቶን ካሸነፍኩ እና ሪከርድ ካስመዘገብኩ ድርብ ደስታ ይፈጥርልኛል:: ለንደን የዓለማችን ምርጥ የማራቶን መድረክ ነው፡፡ ስለዚህም ህልሜ እንዲሆን እፈልጋለሁ..›› ማለቱን አውስቷል፡፡
ሁለቱ አትሌቶች በማራቶን ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በ2014 እ.ኤ.አ ላይ በቺካጐ ማራቶን የነበረ ሲሆን ኪፕቾጌ ሲያሸንፍ ቀነኒሳ በአራተኛ ደረጃ ነበር የጨረሰው፡፡ ከዚያ በኋላ በሌሎች 3 የማራቶን ውድድሮች ተገናኝተው ሁሉንም በድል የተወጣው ኪፕቾጌ ነበር፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በበርሊን የዓለም ማራቶን ሪከርድ ያስመዘገበውና በ2019 እኤአ ደግሞ  በልዩ ሁኔታ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች በመግባት የመጀመሪያው አትሌት ለመሆን የበቃው ኤሊውድ ኪፕቾጌ  እንደ ሌተስ ራን ትንተና ከለንደን ተሳትፎው በኋላ የሩጫ ዘመኑን ሊያበቃ ይችላል፡፡  
በሌላ በኩል የ37 ዓመቱ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በለንደን የሚያስመዘግበው ውጤት እስከ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ስኬት ሊያነሳሳው እንደሚችል ነው የተገለፀው፡፡ ራኒንግ ዎርልድ የተባለው መጽሔት በሰራው ዘገባ ደግሞ ሁለቱ የዓለማችን የረጅም ርቀት ምርጥ አትሌቶች በሩጫ ዘመናቸው ለመጨረሻ ጊዜ የሚገናኙበት የውድድር መድረክ 40ኛው የለንደን ማራቶን መሆኑን ነው፡፡ ራኒንግ ዎርልድ የሁለቱን ምርጥ የማራቶን ሯጮች መገናኘት በተነተነበት ዘገባው ቀነኒሳ ኪፕቾጌን እንደሚያሸንፍ ርእሱ አድርጐታል፡፡
በሩጫ ዘመኑ  11 የማራቶን ውድድሮችን ያደረገው አትሌት ቀነኒሳ በ7 ውድድሮች ርቀቱን የጨረሰ ሲሆን አራት ማራቶኖችን አቋርጦ መውጣቱ ይታወቃል፡፡ በ2016 እና በ2019 እ.ኤ.አ በበርሊን ማራቶን ሲያሸንፍ ያስመዘገባቸው ምርጥ ሰዓቶች ግን የኪፕቾጌን ክብረወሰን ሊሰብር እንደሚችል ግምት አሰጥቶታል፡፡
ራነረስ ዎርልድ በ40ኛው የለንደን ማራቶን ቀነኒሳ ሊያሸንፍ ይችላል በሚል ርእስል ባቀረበው ፅሁፍ በዘረዘራቸው ምክንያቶች በማራቶኑ 2 ማይሎች እስኪቀሩ ተያይዘው ከሮጡ ቀነኒሳ በፈጣን አጨራረስ ሊቀድም እንደሚችል፤ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለመስበር በሚችልባቸው ሁለት ፈጣን ሰዓቶች መቃረቡንና ኪፕቾጌ ከያዘው ክብረወሰን በ2 ሰኮንዶች ብቻ የሚፈጥንበት ልምድ መያዙንና ይህንም በአንድ ውድድር ሊቀይረው እንደሚችል፤ በትራክና በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ሲገናኙ ብዙዎችን በማሸነፍ ቀነኒሳ ብልጫ ያለው መሆኑ የሚያስገኘው ሞራል እና ኪፕቾጌ የማራቶን ዘመኑ መጨረሻ ላይ መገኘቱን ጠቃቅሷቸዋል፡፡
በ2018 እ.ኤ.አ ላይ በበርሊን ማራቶን ኤሊውድ ኪፕቾጌ ማራቶንን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ39 ሰኮንዶች በመሮጥ  የዓለም ማራቶን ሪከርድን እንዳስመዘገበና ባለፈው ጥቅምት ደግሞ በኦስትሪያ ቪዬና ከናይኪ ጋር በያዘው ልዩ ፕሮጀክት በከፍተኛ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ድጋፍ
1፡59.40 በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ከ2 ሰዓት የበታች የገባ የመጀመሪያው ሰው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ቀነኒሳ በበኩሉ በ2019 የበርሊን ማራቶን ላይ 20 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ በማሸነፍ በማራቶን የዓለማችን ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል፡፡
በሩጫ ዘመኑ 13 የማራቶን ውድድሮችን በመሮጥ 12 ጊዜ ያሸነፈው ኪፕቾጌ፤ ባለፉት 6 ዓመታት  10 ማራቶኖችን አከታትሎ  ከማሸነፉም በላይ፤ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ መጎናፀፍና የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡
ከእነዚህ የማራቶን ድሎቹ መካከል በ2014 እኤአ የቺካጎ ማራቶንን፤  በ2015፣ በ2016፣ በ2018 እና በ2019 እኤአ የለንደን ማራቶንን ለአራት ጊዜያት፤ በ2015፣ በ2017፣ በ2018 እኤአ የበርሊን ማራቶንን ለሶስት ጊዜያት ማሸነፉ ከፍተኛ ስኬት ማግኘቱን ያመለክታል::
ኪፕቾጌ በማራቶን ውድድሮች ይህን የመሰለ የባልይነት ቢኖረውም በትራክ እና የአገር አቋራጭ ውድድሮች  ከቀነኒሳ በቀለ ጋር በምንም መልኩ የሚፎካከርበት ውጤት አላስመዘገበም:: በ5ሺ ሜትር 12፡46 እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 26፡49 ምርጥ ሰዓቶቹ ናቸው፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር በ2003 እኤአ የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በኦሎምፒክ በ2004 እና በ2008 እኤአ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን ነው ያገኘው፡፡
ከኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ላይ የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊነጥቅ እንደሚችልና ምናልባትም ማራቶንን የተጋነነ የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሳይኖር ከ2 ሰዓት በታች ሊገባ እንደሚችል የሚወሳለት  አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በትራክ እና የአገር አቋራጭ ውድድሮች ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ግን የሚፎካከር የለም፡፡  
ከ40ኛው የለንደን ማራቶን በፊት ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ በረጅም ርቀት በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር፤ በአገር አቋራጭ እና በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች 24 ጊዜ ተገናኝተው 15 ጊዜ ቀነኒሳ ሲያሸንፍ ኪፕቾጌ 9 ጊዜ ድል ቀንቶታል፡፡ ቀነኒሳ ሶስት የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያዎች 16 የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎች እና ሁለት የዓለም ሪከርዶች ሲያስመዘብ፤ ኪፕቾጌ 1 የወርቅ ሜዳልያ በኦሎምፒክና 1 የወርቅ ሜዳልያ በዓለም ሻምፒዮና  ብቻ ነው ያስመዘገበው፡፡
በአጠቃላይ ሁለቱ አትሌቶች በኦሎምፒክ እና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 5 ጊዜ ተገናኝተው በ4ቱ ያሸነፈው ቀነኒሳ ነው፡፡


Read 898 times