Print this page
Monday, 03 February 2020 12:04

በመንገድ ላይ ለሚያጋጥሙ የመኪና ብልሽቶች መፍትሄ የሚሰጥ ድርጅት ሥራ ጀመረ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

     በመንገድ ላይ ለሚያጋጥሙ የተለያዩ ድንገተኛ የመኪና ብልሽቶች መፍትሄ የሚሰጥ ድርጅት ሥራ ጀመረ፡፡ ድርጅቱ ለሚሰጠው አገልግሎት በዓመት አንድ ጊዜ አነስተኛ ክፍያ እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡
‹‹ከች ሮድ ሳይድ ኢመርጀንሲ ሰርቪስ›› የተባለው ይኸው ድርጅት፤ መኪኖች በቀላል ብልሽቶች ሳቢያ መንገድ ላይ እየቆሙ የአሽከርካሪውንም ሆነ የሌሎች የመንገዱ ተጠቃሚ አሽከርካሪዎችን ጊዜ ከማጥፋት እንዲቆጠቡ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል፡፡ በድርጅቱ ከሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል የጎማ መቀየር፣ የባትሪ ችግር አነስተኛ ብልሽቶች፣ በመኪና ውስጥ የሚረሱ ቁልፎች፣ የነዳጅ ማለቅ እንዲሁም መኪናው ከባድ ችግር አጋጥሞት መንገድ ላይ ሲቆም በመኪና መጎተቻ ወደሚፈልግበት ጋራዥ የማድረስ ሥራ እንደሚገኙበት የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን የሻው ወንድሜነህ ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ ትናንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት የትራፊክ ፍሰቱን በእጅጉ እያበላሹ  ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል በመንገድ ላይ በብልሽት ሳቢያ የሚቆሙ መኪኖች ዋንኞቹ ሲሆኑ ይህም ለትራፊክ አደጋዎችና ለአላስፈላጊ መጨናነቅ እያጋለጠ ይገኛል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ሥራ የገባው ‹‹ከች ሮዳሳያድ ኢመርጀንሲ ሰርቪስ››፤ የስልክ ጥሪ በተደረገለት በጥቂት ደቂቃ ውስጥ በሞተር ሳይክል በሚንቀሳቀሱና በሙያው በሰለጠኑ ባለሙያዎች ከሥፍራው በመድረስ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡ ለዚህ አገልግሎት ደንበኞች የሚከፍሉት ለኮድ 2 የቤት መኪኖች 995 ብር አመታዊ የአባልነት ክፍያ እንዲሁም ለድርጅቶች የኮድ 3 እና የመንግሥት የኮድ 4 መኪኖች ደግሞ 1500 ብር አመታዊ ክፍያ ነው ተብሏል፡፡
ተሽከርካሪው ነዳጅ ጨርሶ በሚቆምበት ወቅት ማደያ ድረስ ሊወስደው የሚችል ከ5-10 ሊትር የሚደርስ ነዳጅ እንደሚቀርብለትና አሽከርካሪው የነዳጁን ዋጋ ብቻ በመክፈል አገልግሎቱን እንደሚያገኝም አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ ለሥራ ያሰማራቸው ባለሙያዎች በሙያው በሚገባ የሰለጠኑና በሥነ ምግባር የታነፁ ናቸው ያሉት አቶ ዘሪሁን፤ ሥራውን ለመጀመር ረዥም ጊዜ የወሰደብን ምክንያትም ሠራተኞቻችንን በሙያውና በሥነ ምግባር የታነፁ የማድረግ ሥራ ነበር ብለዋል፡፡


Read 2371 times