Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 30 June 2012 11:58

ያላስፈላጊ ቁጭት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ብዕሬን እንዳነሣ ያደረገኝ ሰኔ 9 ቀን 2004 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በነፃ አስተያየት አምዱ፣ “ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” በሚል ርዕስ ከዓለሙ ከድር የተፃፈው ጽሑፍ ነው፡፡ ጸሐፊው “እግዚአብሔር ይመስገን” ወይም “አላህ ይክበር” ወይም “በጌታ ኢየሱስ ኃይል” የሚል እምነታዊ ቃል እንደማይወጣቸው ብገነዘብም እንደምን ሰነበቱ? እላቸዋለሁ፡፡ እኔ ግን በእግዚአብሐር ቸርነት ጤናውንና ዕውቀቱን ሰጥቶኝ ይህችን አጭር የመልስ ጽሑፍ ለመስጠት በቅቻለሁ፡፡ ዓለሙ ከድር፣ ከጽሑፋቸው እንደተረዳሁት እርሳቸው የምንም ዓይነት እምነት ተከታይ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ተሣስቼ ከሆነ እታረማለሁ፡፡ ከስሕተት መማር ታላቅ ብልህነት መሆኑን አውቃለሁና፡፡ የምንም ዓይነት እምነት ተከታይ ያለመሆናቸውን ልነቅፍም አልችልም፡፡ እምነት አልባ የመሆን ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን አልጋፋም፡፡

ከራሳቸው የግል እምነት አልፈው የሌላውን የእምነት መብት ሊያንኳስሱ ወይም ሊንቁ የተነሡበትን ሐሳብ ግን ከመቃወም አልመለስም፡፡ ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሣሣኝም ይኸው ነው፡፡

እንደ ጽሑፋቸው አባባል “…ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት፣ ሱፊ ወይም ዋሃብያ መሆናቸውን በሚያውጅ መንገድ ይናገራሉ፡፡ ለዚህ ያደረሰኝ እግዚአብሔር ይመስገን፣ አላህ ይክበር፣ በወላዲት አምላክ እርዳታ፣ በጌታ ኢየሱስ ኃይል እናሸንፋለን የሚሉ ንግግሮችን ትሰማላችሁ፡፡ …” በማለት የተለያዩ የእምነት ተቋሞችንና የየእምነት ተከታዮችን መብት፣ አልፈው ተርፈውም የእግዚአብሔርን (የፈጣሪን) ክብር ለመንካት ወይም ለመዝለፍ ሞክረዋል፡፡ ለመሆኑ የራሳቸውን እምነት አልባ የመሆን መብት ማስከበር የሚችሉት የሌላውን እምነታ ተከታይ መብት አክብረው ሲገኙ ብቻ መሆኑን እንዴት ሊዘነጉት ቻሉ?

ሰው የእግዚአብሐር ፍጥረት መሆኑንና ለእያንዳንዱም የተለያየ ፀጋን የሚያድለው እግዚአብሔር ራሱ መሆኑን የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ሁሉ ያውቀዋል፣ ይገነዘበዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ እንደ የእምነት ሥርዓቱ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና ይሰጣል፡፡ ይህንን የማይቀበል ካለ እሱ ቁስ አካላዊ ወይም በሚታይ፣ በሚጨበጥና በሚዳሰስ ነገር ካልሆነ በቀር አላምንም የሚል አመለካከት ያለው ብቻ መሆን አለበት፡፡

ዓለሙ ከድርም በዚህ መነሻ ይመስለኛል የ”እግዚአብሔር”፣ የ”አላህ”፣ የ”ጌታ ኢየሱስ” ወዘተ… ስም ሲነሣ በመስማታቸው ባላስፈላጊ ቁጭት ተነሣስተው የጭቃ ጅራፋቸውን በአማኞች ላይ ያወረዱት፡፡

አማኞች ምንም ተባሉ ምንም እምነታቸውን አይተውትም፡፡ በእግዚአብሔር እንደተፈጠሩ፣ የታዋቂነት ክሕሎቱንም ከእግዚብሔር እንደተሰጣቸው ያምናሉ፡፡ ስለሆነም ታዋቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ከሊህቅ እስከ ደቂቅ ያሉት በሔዱበት፣ በሚሳተፉበት፣ ወይም በሚወከሉበት፤ በሚበሉበትና በሚጠጡበት፣ በመኝታና የመንቂያ ጊዜያት ሁሉ ሳይቀር እንደየእምነታቸው ሥርዓት የእግዚአብሔርን (የፈጣሪን) ስም መጥራት፣ ማመስገንና ማወደስ ዋነኛ ዓላማቸው ነው፡፡

አዎ! ዓለሙ ከድር ራሳቸው እንደጠቀሱት “…ለዚህ ያደረሰኝ እግዚአብሔር ይመስገን፤ አላህ ክበር፤ በወላዲት አምላክ እርዳታ፤ በጌታ ኢየሱስ ኃይል፣ …” እያሉ ለውጤት ያበቃቸውን አምላክ ማወደሳቸው ተገቢ እንጂ አስነዋሪ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃይማኖትንም መስበክ አይሆንም፡፡

የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክህሎት አዳብሮና አሻሽሎ ለውጤት ሲበቃ ያንን እንዲያደርግ የረዳውን አምላክ ቢያመሰግን ነውሩ ከምን ላይ ይሆን? እንደሃይማኖት ሰበካ አድርገው የቆጠሩት ፀሃፊው እንጂ በአማኞች መሐል ሰበካ ነው የተባለበት ጊዜ የለም፡፡

በጣም የሚገርመው ደግም በጽሑፋቸው ሃይማኖታችንና አማኞችን ከመንቀፍ አልፈው የእግዚአብሔርን ክብር በሚነካ መልኩ የሰነዘሩት ሐሳብ ነው፡፡ እጠቅሰዋለሁ፡፡ “…ለነገሩ በደፈናው፣ ያንን ወይም ይሄንን ሃይማኖት በማይገልጽ መንገድ ከፈጣሪ ጋር እናሸንፋለን፣ በፈጣሪ ኃይል አሸነፍን ብሎ አለቦታው ሃይማኖትን መስበክና ለሃይማኖት ምስክርነት መስጠትም ተገቢ አይደለም…” ይላሉ፡፡

ጥቅል አባባሉን ስንመለከተው ለምን የእግዚአብሔር ስም ይነሣል? ለምንስ አማኞች ለሃይማኖታቸው ክብርን ሞገስን ይሰጣሉ? እንደማለት ነው፡፡ የእርሳቸው የ”እግዚአብሔር የለም” እምነት እንኳን ለራሳቸው እውነት ሆኖ ሲከተሉትና ያንኑ ለመስበክ እየተፍጨረጨሩ አይደለምን? ታድያ! የእግዚአብሔር አማኞችን የሃይማኖት ምስክርነት ለምን ይጠሉታል?

ለመሆኑ ዓለሙ ከድር በዓለም ላይ አንቱ የተባሉ ሳይንቲስቶችና ፈላስፎች የእግዚአብሔርን ሕልውና ሲክዱ ኖረው በመጨረሻው ላይ ግን “አንድ ኃይል አለ” “There is one Power” እያሉ የጭንቀት ቃላቸውን እየሰጡ ከዚህች ምድር እንደተሰናበቱ አላነበቡ ወይም አልሰሙ ይሆን? ለማንኛውም በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ሆነ ስለተባለ አንድ ነገር ላጫውታችሁና ሐሳቤን ላጠቃልል፡፡

በምሥራቁ ጦርነት ጊዜ ነው፡፡ የፖለቲካ ካድሬው በተደጋጋሚ ጊዜ በማይታይ፣ በማይጨበጥ ወይም በማይዳሰስ ነገር ማመን ተገቢ ስለአለመሆኑ ለሠራዊቱ ያስተምራል፤ ማለትም እግዚአብሔር የሚባል ነገር አለመኖሩን ይሰብካል፡፡

አንድ ቀን ታዲያ የተፋፋመ ጦርነት ድንገት ይጀመራል፡፡

የመትረየሱ፣ የባዙቃው፣ የቦንቡ፣ … መሣሪያዎች ድምጽ ምድሪቱን ቀውጢ አደረጋት፡፡ካድሬ ሆዬ በጭንቀት ተወጥሮ ኖሮ ከአንዲት ስርቻ ሥር ተወሽቆ “እግዚኦ! መድኃኔዓለም፣ እግዚኦ መድኃኔዓለም፣ …አንተ አድነን፡፡” እያለ ሲለፈልፍ አንድ ተዋጊ ወታደር ያዳምጠዋል፡፡ በጦርነት ሣልሥት ይኸው ካድሬ የፖለቲካ ትምህርት ለሠራዊቱ ሰጥቶ ሲያበቃ አንድ ወታደር እጁን በማውጣት “ጥያቄ አለኝ” ይለዋል፡፡ ካድሬውም ይፈቅድለታል፡፡

“ጓድ ካድሬ! ከትላንት ወዲያ በነበረው ጦርነት አንድ ጥግ ይዘህ የመድኃኔዓለምን ስም ደጋግመህ እየጠራህ ስትማፀን ሰምቼህ ነበር፡፡ ታድያ! እኛ እምነት እንዳይኖረን ለምን ታስተምረናለህ?” በማለት ሲጠይቀው ካድሬው ዐመዱ ቡን ይልና የሚመልሰው ያጣል፡፡የዓለሙ ከድርም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

እግዚአብሔር ይሰውራቸው እንጂ አንድ ከበድ ያለ ፈተና ቢደርስባቸው “ፈጣሪዬ! ፈጣሪዬ፣…” በማለት መማፀናቸው አይቀርም፡፡ ያም ሆነ ይህ በተለይ ታዋቂ አርቲስቶች፣ ኳስ ተጫዋቾች፣ ዝነኛ ሯጮች፣ ሠዓሊዎች፣ ዶክተሮች፣ ኢንጂነሮች፣ … የእግዚአሔርን ቸርነት ለመግለጽ እግዚአብሔር ይመስገን፣ አላህ ይክበር፣ ጌታ ኢየሱስ ይባረክ፣ … በማለት እንደ የእምነት ሥርዓታቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ያወገዙት ዓለሙ ከድር፤ አላስፈላጊ ቁጭት ውስጥ ገብተው ነው የለፉት እላለሁ፡፡ አሁን እሳቸውን ምን አስጨነቃቸው?

 

 

Read 2156 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 12:03