Saturday, 08 February 2020 15:03

‹‹ሕዝቡን በጎሳና በሃይማኖት ለያይቶ ለማጋጨት መሞከር በእሳት መጫወት ነው››

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   - ጃዋር ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ቤተ መንግስት እንዲገባ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል
     - ከማንም ባላነሰ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ዝግጁ ነኝ›› - ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

                በፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራውና በቅርቡ ጃዋር መሐመድን በአባልነት የተቀበለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በአንዳንድ ወገኖች ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ ጀምሯል›› የሚል ወቀሳ ቢሰነዘርበትም፣ ፓርቲው ቅስቀሳ አልጀመርኩም ሲል ያስተባብላል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክም ከሰሞኑ ጉባዔውን አካሄዷል፡፡ በዚህ ጉባኤው ምን ውሳኔዎችን አሳለፈ? ለምርጫው እያደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል? የመጪው ምርጫ ስጋቶች ምንድን ናቸው? የመድረክና የኦፌኮ ሊቀመንበር የሆኑት ፕ/ር መረራ ጉዲናን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

           ከሰሞኑ ያካሄዳችሁት ጉባዔ ምን ላይ ያተኮረ ነው?
ያካሄድነው አመታዊ ጉባዔ ነው፡፡ በዚህ ዓመታዊ ጉባዔ በዋናነት የተነጋገርነው በመጪው ምርጫ የ‹‹መድረክ›› ተሳትፎ ምን ይሆናል? በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎችም ላይ ተነጋግረናል፡፡ በተለይም ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስናነሳ የነበረው ብሄራዊ መግባባት ቢፈጠርና ብሄራዊ የአንድነት መንግሥት ቢቋቋም ኖሮ፣ አሁን በአገሪቱ የሚታየው ቀውስ አይከሰትም ነበር የሚል አቋም ወስደናል:: አሁንም ለአገሪቱ የሚበጀው የአንድ ቡድን አመራር አይደለም የሚል አቋም ወስደን ነው ጉባኤውን ያጠናቀቅነው፡፡
በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያስ ምን አይነት አቋም ወስዳችሁ?   
ምርጫ ቦርድ አካባቢ በተለይ በሕግ በኩል እየተፈጠሩ ያሉ አንዳንድ ችግሮችን በተመለከተ ግልጽነት እንደሚያስፈልግና ውይይት ሊደረግባቸው እንደሚገባ አቋም ወስደናል። ለምሳሌ ለአካባቢ ምክር ቤት ምርጫ የሚወዳደር ሰው 1 ሺህ ፊርማ፣ ለፓርላማው 2 ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ያስፈልገዋል የሚለው ድጋሚ ውይይት ይፈልጋል። አስቀድሞ በሕጉ የተካተተውም ሳንወያይበትና ከድርጅታችን ዕውቅና ውጪ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩን በተመለከተም የፖለቲካ ሀይሎች ከመንግሥት ጋር እንዲደራደሩና እንዲነጋገሩ ምርጫ ቦርድ መንገድ እንዲከፍትና መድረክ እንዲያመቻች አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ የመድረክ አባል ድርጅቶችና መድረክ በራሱ መስራት ስላለባቸው ተግባርም ተወያይተናል፡፡ መድረክ ከሌሎች የፖለቲካ ሀይሎች ጋር በተሻለ ሁኔታ ትብብሮችን እንዲፈጥር ተነጋግረን ወስነናል፡፡
የመድረክ አባል የሆነው እርስዎ የሚመሩት ኦፌኮ “ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ ገብቷል” ተብሎ እየተወቀሰ ነው?
እኛ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ አልገባንም:: ዞሮ ዞሮ በየሄድንበት ስለ ምርጫ መነሳቱ አይቀርም፤ ነገር ግን እኛ ያተኮርነው በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ፣ ሕዝቡም ለዚህ መዘጋጀት እንደሚገባው እንዲሁም የሕዝብ ድምጽ መሰረቅ እንደሌለበትና ሕዝቡ የሚፈልገውን ለመምረጥ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ ወጣቶች ከወዲሁ የቀበሌ መታወቂያ አውጥተው ለምርጫው እንዲዘጋጁም ነግረናል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሕዝቡ ለመምረጥ እንዲዘጋጅ ስንናገር ነው የቆየነው፤ እንጂ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ አልገባንም፡፡
መድረክ በምርጫው የሚሳተፈው በቀድሞው አደረጃጀት ነው ወይስ…?
በሰሞኑ ጉባኤያችን የመድረክን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻል ችለናል፡፡ ከሌሎች ጋር በተናጠልም ሆነ እንደ መድረክ በቅንጅት ወይም በትብብር መልክ መስራት እንደሚቻልና እንደሚገባ ተነጋግረን፣ አራት ያህል አንቀጾችን አሻሽለናል፡፡ ለምሳሌ ኦፌኮ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መቀናጀት መተባበር እንደሚችል እንዲሁም በመድረክ ደረጃም ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር መቀናጀት እንደሚቻል ሕጋችንን አዘጋጅተናል፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ የአደረጃጀት ቅርፃችንን ልንለውጥ የምንችልበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው፡፡
መድረክ ጠንካራ የድጋፍ መሰረት አለኝ የሚለው በየትኞቹ አካባቢዎች ነው?      
ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ጠንካራ ድጋፍ አለን፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ መካሄድ አለበት፡፡ ትግራይ አካባቢም ለዚህ አይነት ምርጫ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በደቡብና በኦሮሚያ ጠንካራ የድጋፍ መሰረት አለን፡፡
እርስዎ እንደ ፖለቲካ ምሁርነትዎም ሆነ እንደ ፓርቲ አመራርነትዎ፣ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር በተያያዘ ስጋት የሚፈጥርብዎ ምንድን ነው?
እኛ ከሰሞኑ በአብዛኛው ሃረርጌ አካባቢ ስንቀሳቀስ ነበር፡፡ ሰሜን ሸዋ አካባቢም በተመሳሳይ፣ አርሲና ባሌም እንዲሁ ተንቀሳቅሰናል፣ ሆሳዕና አካባቢም ሄደናል:: በእነዚህ ጉዞዎች ያስተዋልኩት ነገር፤ ትልቁ ችግር የሕዝብ አለመሆኑን ነው፡፡ ብዙ ቦታ እያየን ያለነው፣ ለውጡ እታች አልደረሰም የሚል ቅሬታ እንጂ በሕዝቡ መካከል ብዙም ችግር የለም፡፡ ዋናው ችግር በላተኛ ካድሬው ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ የየራሳቸውን ሕልም ብቻ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሀይሎች ወደ አላስፈላጊ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው ነው ችግርና ስጋት እየፈጠረ ያለው፡፡  አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የየራሳቸውን የፖለቲካ ኪሳራ በሌሎች ትከሻ ላይ ለማስተካከል የሚያደርጉት ሙከራ አለ፡፡ በስም እየጠቀሱ ‹‹እከሌ የጎሳ ድርጅት ነው፤ ጠባብ ነው›› የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እንደነዚህ አይነት ጩኸቶች ኋላ ላይ አደጋ ያስከትላሉ፡፡ ፖለቲካ እስከሚገባኝ ድረስ እነዚህ ድርጅቶች በአሁኑ ወቅት ጠንካራ የድጋፍ መሰረት አላቸው፡፡ ይሄን ማገናዘብ ያስፈልጋል። ሁሉም የየራሱን ሕልም ይዞ ወደ ጨዋታ ሜዳው ከገባ ችግር ይፈጠራል የምለው ለዚህ ነው፡፡ የራስን ሕልም ብቻ ከማድመጥ ይልቅ የሌላውንም ሕልም ማገናዘብና ወቅቱንና ሁኔታውን ተረድቶ መንቀሳቀስ ለሁሉም ይበጃል፡፡ ደጋግሞ ማሰብ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው፡፡ በተለያየ አግባብ የተደራጁ ሀይሎች፣ ህልማቸወን አቻችለው፣ ወደ ብሄራዊ መግባባት ቢገቡ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡ ከወዲሁ “የጎሳ፣ የዘር ድርጅቶች” በሚል መፈራረጁ ለኔ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡ የቃላት ጨዋታው ከወዲሁ መስተካከል አለበት፡። አለበለዚያ ትልቅ ስጋት ይደቅናል፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት፣ በዚህ ምርጫ ስጋት ካለ ምንጩ ሕዝቡ ሳይሆን የፖለቲካ ሀይሎች ናቸው፡፡
እኔ በተዘዋወርኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ከሕዝቡ ሰላም ፈላጊነት ትልቅ ተስፋ ነው ሰንቄ የተመለስኩት፡፡ ይሄን ተስፋ የፖለቲካ ሀይሎች በሚጠቀሟቸው ቃላትና አካሄዶች ወደ ስጋት እንዳይለውጡት ብቻ ነው ስጋቴ:: እኛም በተንቀሳቀስንባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሕዝቡ በብሄር፣ በሃይማኖትና በአካባቢ እንዳይለያይ፣ እንዳይጋጭና በአንድነት እንዲቆም ስናስተምር ነው የቆየነው፡፡ ነገር ግን ሕዝቡን በእምነትም በአካባቢም ለያይቶ ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶች እንዳሉ በሰፊው ተገንዝበናል፡፡ ይሄ ለኔ በእሳት መጫወት ነው:: ይሄን የሚያደርጉ አካላት ከዚህ የእሳት ጨዋታ በጊዜ እጃቸውን ቢሰበስቡ ጥሩ ነው፡፡ ሕዝብ መለያየት አይችልም፡፡ በግድ አጀንዳ እየፈጠራችሁ አትለያዩት፡፡ ለምሳሌ አርሲ ዴራ አካባቢ፣ የስልጤ ማህበረሰቦች፣ እኛን በሥርዓት ተቀብለው፣ ፍቅራቸውን ወዳጅነታቸውን በመግለጽ የሚያኮራ አቀባበል ነው ያደረጉልን፡፡ ሀረር ላይ የአደሬ ማህበረሰብ ደስ ብሎት ነው የተቀበለን፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ዘንድ ችግር የለም፡፡ ችግር ያለው አጀንዳ ፈጥረው ሕዝብን ለማጋጨት በሚጥሩ በላተኛ ካድሬዎችና እነሱን እንደግፋለን በሚሉ ሚዲያዎች አካባቢ ነው፡፡ በተለይ በሃይማኖትና በብሄር ሕዝብን በማጋጨት አጀንዳ እየፈጠሩ ያሉ ሀይሎች፣ ደግመው ደጋግመው ማሰብ አለባቸው፡፡
ካድሬዎችን ደጋግመው ጠቅሰዋል፡፡ ካድሬዎች እንዴት ነው ችግር እየፈጠሩ ያሉት?
ለምሳሌ እኛ ያላልነውን ነገር ‹‹እንዲህ አሉ፤ እንዲህ ሊያደርጉ ነው›› እያሉ ሕዝብ መሃል ውዥንብር በመንዛት፣ አንዱን ሀይማኖት በሌላው ሃይማኖት፤ አንዱን ብሄር በሌላው ብሔር  ላይ ለማነሳሳት ጥረት ያደርጋሉ:: ያልተገባ ውንጀላ ይወነጅላሉ፡፡ በተለይ የመንግሥት ካድሬዎች፣ ስብሰባ ስናደርግ፣ ከሕዝቡ ጋር የማይመጣጠን ሰራዊት በስፋት በማሰማራትና ሽብር በመፍጠር ላይ ተጠምደው አይተናል:: በፌስቡክም ወደ ፍረጃና አላስፈላጊ የቃላት ጦርነት ቀድመው የሚገቡት ካድሬዎቹ ናቸው፡፡
ሰሜን ሸዋ ላይ ባደረጋችሁት ስብሰባ፣ እርስዎ ‹‹የምኒሊክ ቤተ መንግሥትን የራሳችን አድርገን፣ የጀነራል ታደሰ ብሩን ሀውልት እንገነባበታለን›› ብለዋል፡፡ እስቲ ትንሽ ያብራሩልን? ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ፕ/ር መረራ ‹‹ከዚህ በፊት ከሚታወቁበት አካሄድ በተለየ መልኩ ጽንፈኛ ብሄርተኛ እየሆኑ ነው›› ሲሉ ይደመጣል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ትናንትም ይሁን ዛሬ፣ የኦሮሞን ብሄራዊ ፍላጎትና ስሜት ከኢትዮጵያ ህዝብ ብሄራዊ ስሜትና ፍላጎት ጋር የማጣጣሙን፣ የማቻቻሉን ሁኔታ ማሳካት ላይ ነው የተሰማራሁት፡፡ ጽንፈኛ ብሄርተኛ የሚለው እኔን አይገልፀኝም፤ የፈለጉ ግን ሊሉኝ ይችላሉ፡፡ ፍቼ ላይ ባደረግነው ስብሰባ፣ ካድሬው አላስፈላጊ ችግር ፈጥሮብን ስለነበር፣ እኛም ደግሞ ለዚያ የሚመጥን አንዳንድ ነገር መናገር ነበረብን፡፡ በዚህ የተነሳ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ ገብተን ሊሆን ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ግን በወቅቱ የተሰበሰብንበት ቦታ የጀነራል ታደሰ ብሩ ሃውልት ያለበት ቦታ ነበር፡፡ ጀነራል ታደሰ ብሩ ደግሞ ሞት የተፈረደበት (እኔም ሁለት ሳምንት ታስሬበታለሁ) የምኒልክ ቤተ መንግሥት የሚባለው ትልቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነው፡፡ እኔ ያንን ስናገር ሞት የተፈረደበት ቦታ ላይ ሃውልት እንገነባለታለን እንጂ የምኒሊክ ቤተ መንግሥት ይፍረስ አላልኩም፡፡ የማንም ሀውልት ይፍርስ አላልኩም፤ ለወደፊትም አልልም፤ ነገር ግን የኦሮሞ ሕዝብ ጀግናዬ ነው ብሎ የሚያከብረው ሰው ሀውልቱ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ቢቆም፣ ለምን አንዳንዶችን እንዳስጨነቀ ግራ ይገባኛል። ለምን ያንን ጩኸት እንዳሰሙ አይገባኝም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንዱ የሌላውን እውነት ወደ ማክበሩ ወደ ማቻቻል ካልተሄደ፣ እንዴት ነው የጋራ ቤት እየገነባን የምንሄደው? ለአንዱ ዘላለማዊ ጀግና የሆነ ሰው፣ ለሌላው ወንጀለኛ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን የአንድን እውነት ሌላኛችን መረዳትና መቻልን መለማመድ አለብን፡፡ የጀነራል ታደሰ ብሩ ሀውልት ለምን አዲስ አበባ ውስጥ እንዳይቆም ተፈለገ ብሎ ሰው እንዲጠይቅ ማድረግ አይገባም፡፡ የሌላው ሀውልት ፈርሶ የአንዱ ይገንባ ከተባለ ነው ጤናማ የማይሆነው:: እኔ ይሄን አላልኩም፡፡ ቋንቋንም በተመለከተ ተመሳሳይ ነው፡፡ አማርኛ ይቅርና ኦሮምኛ ብሄራዊ ቋንቋ ይሁን ባልተባለበት ሁኔታ፣ እንዴት ኦሮምኛ ብሄራዊ ቋንቋ ይሁን ተባለ ማለት ጤንነት  አይደለም፡፡ እኛ እያልን ያለነው ኦሮምኛ ተጨማሪ ቋንቋ ይሁን ነው፡፡ ይሄ ሲሆን የተሻለ አንድነትና ቅርርብ ይፈጠራል ነው፤ የኛ እምነት፡፡ ነገር ግን ጠባብ የሆነ የፖለቲካ ስሜት ይዞ መንቀሳቀሱ ለማንም አይበጅም፡፡
‹‹የኦሮሞ ህዝብ በቁመቱ ልክ ስልጣን ማግኘት አለበት›› በማለት የተናገሩትም አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ምን ማለትዎ ነው?
ይሄን ስናገር ሁለት ነገር አስቤ ነው፡፡ እርግጥ ከሳሾቼ በዚህ ቢከሱኝ ይሻላል፡፡ አንዳንዶች በፊት ‹‹መረራ ሶሻሊስት ነው›› ብለው ይከሱኝ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ቋንቋቸውን ለውጠው በሌላ እየከሰሱኝ ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ምን መሰለህ፤ አንዱ የድርጅታችን ትልቁ መሠረት፣ የአንድ ሰው አንድ ድምጽ መርህ ነው፡፡ የአንድ ሰው አንድ ድምጽ  ሲባል ደግሞ ለምሣሌ አንድ ኦሮሞ በሀገሪቱ ጉዳይ አንድ ድምጽ አለው ማለት ነው:: ይሄን ታሣቢ በማድረግ ነው፣ እኔ ‹‹ኦሮሞ በቁመቱ ልክ ስልጣን የለውም›› ያልኩት፡፡ የዜጋ ፖለቲካ የሚሉ እንግዲህ በዚህ ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ እኔም የዜጋ ፖለቲካ ካላልኩ በስተቀር ‹አክራሪ› ከታገልኩ፣ ምንም ማድረግ አይቻልም:: እኔ በፖለቲካ ዘመኔ ‹ኢትዮጵያ የምትባለውን አንፈልግም› ብዬ አላውቅም፤ ከማንም ያላነሰ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ዝግጁ ነበርን፤ አሁንም ነን፤ ግን ማንም የፖለቲካ ቡድን የኢትዮጵያዊነት ሠርተፊኬት ለመረራም ይሁን ለኦሮሞ ማህበረሰብ እሠጣለሁ እከለክላለሁ የሚል ጨዋታ ውስጥ ከገባ ነው ችግር ያለው:: በዚህ ደረጃ ራሳቸውን የሾሙ ሰዎች በሚዲያም በሌላውም አሉ፡፡ ይሄ ለማንም አይበጅም፡፡ ተከባብረን ተቻችለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠሪያ ጊዜውን እነዚህ ሃይሎች እንዳያራዝሙት ነው ስጋቴ፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ካለ ‹በአንድ ሰው አንድ ድምጽ መርህ› ብዙ ነገሮች ይፈታሉ ብለን ነው እኛ የምናምነው:: በዚህ ያልተፈቱ ካሉም በድርድሮች ይፈታሉ፡፡ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ግን እነ እገሌ አክራሪ ብሔርተኛ፣ ሌላው ዲሞክራት፣ አንዱ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት ሰጪ ለማድረግ መሞከር የትም አያደርስም፡፡ ግዴለም እንዲህ ያለው አካሄድ ለማንም አያዋጣም:: በተለይ አክራሪ ብሔርተኛ የሚለው አደገኛ ቋንቋ ነው፡፡
ከዛሬ 40 አመት በፊት እኛም ትምህክተኛ፣ ጠባብ የመሳሰሉ ፍረጃዎች እንጠቀም ነበር፡፡ እኔ ከሆነ ጊዜ በኋላ እነዚህን ቃላት ተጠቅሜ አላውቅም፡፡ ሆን ብዬ ያደረግሁት ነው፡፡ ምክንያቱም ማህበረሰቦች አካባቢ እነዚህ ቃላት ከባድ ችግር ነው የሚፈጥሩት፡፡
“ነፍጠኛ” የሚለው ግን አሁንም የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል…?
የነፍጠኛ ስርአት እኮ በግልጽ የነበረ ነው:: የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄና ከዚያ የወጡ ሃይሎች እኮ ያንን ታግለው ነው ስርአቱን የለወጡት እንጂ መሬት ላይ የነበረ ነው፡፡ ችግሩ ያለው ‹‹የአማራ አርሶ አደር ነፍጠኛ ተባለ›› ብለው የሚያስወሩ ሰዎች ጋ ነው፡፡ ይሄን ለምን ጥቅም እንደሚያስወሩ አላውቅም፡፡ አንድ ጊዜ ጐንደር ዩኒቨርስቲ ጋብዞኝ፣ አንድ ውይይት ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ አሁን በእስር ላይ ያለው ክርስቲያን ‹‹ታደለ የአማራ ህዝብ ሁሉ ጨቋኝ ነው ወይ?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ለምን ይሄን ጥቅም ለማስከበር ዝግጁ ነበርን፤ አሁንም ነን:: ትጠይቀኛለህ፡፡ ህዝብ እንዴት ጨቋኝ ይሆን ይችላል? ህዝብ እንደ ሕዝብ ጨቋኝ ሊሆን አይችልም፡፡ የጐንደር ህዝብ የባሌን ወይም የአርሲ ገበሬን ሄዶ የሚጨቁንበት ጉልበትም አቅምም የለውም፡፡ ግን በአማራ ህዝብ ስም የነበሩ መንግስታት፣ የኦሮሞንም የአማራንም ህዝብ ጉልበትና ሃብት እኩል ሲዘርፉ ሲጨቁኑ ነበር፡፡ ዘራፊዎች መንግስታት እንጂ ሕዝብ አይደለም፡፡ ትናንትም ጨቋኝ መንግስታት እንጂ ጨቋኝ ህዝብ አልነበረም፡፡ ህዝብ ዘራፊ ጨቋኝ መሆን አይችልም፡፡ ይሄን እያደበላለቁ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ሃይሎች ያሳዝኑኛል፡፡
በተለይ ያንን ህዝብ የማይመጥኑ ሰዎች ብዙ ሲያወሩ እሰማለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ኪሣራ የደረሰባቸው ናቸው፡፡ በግልጽ ቋንቋ እኔም ሆንኩ ድርጅታችን ፍላጐታችን፣ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ነው፡፡
ለዚያም የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን:: ከዚህ ባለፈ ‹‹እንዲህ ብለው ህዝብን ሰደቡ ተናገሩ›› የሚለው ነገር፣ በኋላ ሁላችንንም ወደ አለመቻቻልና አለመተማመን ውስጥ ከትቶን ዋጋ እንዳያስከፍለን እሰጋለሁ፡፡
የአማራ ህዝብም ማወቅ ያለበት፣ በቂ አባላት እንኳ ሳያደራጁ በሱ ስም እየተነሱ፣ በሌሎች ላይ የማይሆን ነገር የሚናገሩ ሰዎች መኖራቸውን ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ነገ ከነገ ወዲያም ለዚያ ሕዝብ መቆም የማይችሉ ናቸው፡፡ ‹‹መረራ እንዲህ ብሎ የአማራን ህዝብ ሰደበ›› የሚሉ ሰዎች፣ በእውነት ይሄ አካሄዳችሁ አይጠቅመንም ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡
ስስ በሆነው የፖለቲካችን ሁኔታ የምንጠቀማቸወ ቃላት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ብሔራዊ መግባባት የምንሄድበትን መንገድ ማመቻቸቱ የተሻለ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የየራሱን የቤት ስራ መስራት አለበት፡፡ እኛ ለምሣሌ በደንብ ከተደራጁና የአማራ ህዝብን ይወክላሉ ከምንላቸው ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ‹‹አብን››ን ጨምሮ ንግግር እያደረግን ነው፡፡ ይሄ ንግግር ነው ለወደፊትም ጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ትናንሽ ህዝባዊ መሠረት የሌላቸው በሁለቱም ወገን ያሉ ሃይሎች ግን ከድርጊታቸው ቢቆጠቡ መልካም ነው፡፡ አገሪቱን ወደ ኪሣራ ከመክተት በቀር የሚያገኙት ትርፍ የለም ፡፡
ሌላው አነጋጋሪ ሆኖ የቆየው የአቶ ጀዋር ኦፌኮን መቀላቀል ነው፡፡ ‹‹አቶ ጀዋር በ86 ኢትዮጵያውያን ግድያ ላይ እጁ ስላለበት በወንጀል መጠየቅ›› ይገባዋል የሚሉ ክሶች እየቀረቡ ባሉበት፣ የፓርቲያችሁ አባል አድርጋችሁ ስታቀርቡት በፖለቲካ አካሄዳችሁ ላይ ችግር አይፈጥርባችሁም?
እኛ አባላት ስንመለምል የራሣችን መስፈርቶች አሉን፡፡ ጀዋር ደግሞ በተለይ ለውጥ መጣ ተብሎ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሁሉ ከእስር ቤት የወጣው፣ ምኒሊክ ቤተ መንግስት የገባውም ሃይል ያንን እድል ያገኘውና ስልጣን የያዘው፣ በውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡም እጅግ በጣም ሠፊ የሆነ አስተዋጽኦ ካደረጉ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው፡፡ ጀዋር በቦሌ ሲገባም በትልቅ ክብር የተቀበለው የኢትዮጵያ መንግስት ነው፡፡ አሁን አደረገ የተባለውን ነገርም አደረገ ብሎ ያረጋገጠ የለም፡፡ ዋናው ነገር ግን ይሄ ሰው በፖለቲካ ድርጅት ስር ሆኖ ተጠያቂነትን ወስዶ፣ ለሀገሪቱ ፖለቲካ የራሱን አስተዋጽኦ ቢያደርግ፣ በኛ በኩል ተመራጭ ነው፡፡ ለሚጮሁትም ሃይሎች የሚጠቅማቸው ይሄ ተሳትፎ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቡዳ ማን እንደሆነ ተለይቶ እስኪታወቅ ድረስ ጅዋር ለድርጅታችን ጠቃሚ ስራ የሚሠራ ሰው ነው፡፡ ከኦሮሚያም አልፎ ለተጨቆኑ ህዝቦች የሚታገል ሰው ነው፡፡  
ለስልጤዎች፣ አገዎች፣ ቅማንቶች… የሚዲያ ሽፋን እየሠጠ፣ ድምጽ የሆናቸው የተጨቆኑ ህዝቦች ተከራካሪ ሰው ነው፡፡  ነገር ግን ሰዎች ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ሲሉ እየወነጀሉት እየከሰሱት እንደሆነ ይገባል፡፡
ከ‹‹ኦነግ›› ጋርስ ግንኙነታቸው ምንድን ነው?
ከ‹‹ኦነግ›› ጋር የምንመሰርተውን ግንኙነት በተመለከተ ገና እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ምርጫ የሕዝብን ድምጽ ለመከፋፈል አንሄድም፡፡ ሕዝቡም ‹‹ድምፃችንን አትከፋፍሉ›› የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል፡፡ በዚህ መሠረት ድምጽ ሳንከፋፍል የምንወዳደርበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው፡፡Read 2207 times