Saturday, 08 February 2020 15:40

አዋሽ ባንክ 7ኛ ዙር ከአዋሽ ይቀበሉ ያሸንፉ›› ዕድለኞችን ሸለመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    በግል የባንክ ዘርፍ 25 የስኬት ዓመታትን ያስቆጠረው አዋሽ ባንክ በ7ኛው ዙር ‹‹ከአዋሽ ይቀበሉ ያሸንፉ›› መርሃ ግብሩ ያሸነፉ ባለዕድሎችን ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ጥር 28 ቀን 2012 ልደታ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው የራሱ አዳራሽ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ሸለመ፡፡ አንደኛ ዕጣ ባለ ዕድል 1.4 ሚ. የሚያወጣ አይሱዙ መኪና ተሸልሟል፡፡
ባንኩ ከሰባት አመታት በፊት በሶስት ዋና ዋና ዓላማዎች የ‹‹የአዋሽ ይቀበሉ ያሸንፉ›› መርሃ ግብሩን መጀመሩን ያስታወሱት የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች እነዚህም ዓላማዎች አንደኛ ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት በጣም ወሳኝና አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ፍሰት ወደአገራችን እንዲጨምርና የሕዝቡ ኑሮ እንዲሻሻል ለማድረግ፣ ሁለተኛው በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገራችን የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ እንዲመጣ ለማድረግና የሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ ለአገራችን ልማትና ዕድገት እንዲውል ማድረግ እንዲሁም ሶስተኛው ዓላማ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የተላከላቸውን የውጭ አገር ገንዘቦች በአዋሽ ባንክ በኩል የሚቀበሉ ወይም የሚመነዝሩ ደንበኞች በሽልማት መልክ ማበረታቻ እንዲያገኙ ማድረግ ነው ብለዋል ኃላፊዎቹ፡፡
ከዚህ አኳያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከተከታታይ ዙሮች የተደረጉት የሎተሪ ማበረታቻ ሽልማቶች በአብዛኛው የተቀመጠላቸውን ግቦች ማሳካት መቻላቸውንም ጨምረው ገልጸዋል:: ዘንድሮም በዚሁ በ7ኛው ዙር የሎተሪ ዕጣ ከሀምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም በአዋሽ ባንክ ከውጭ የተላከላቸውን ገንዘብ የተቀበሉና የውጭ አገር ገንዘቦችን የመነዘሩ ባለ ዕድሎች የተሸለሙ ሲሆን ለአንደኛ ዕጣ ባለ ዕድል 1.4 ሚ. የሚያወጣ አይሱዙ ዘመናዊ የጭነት መኪና፣ ለሁለተኛ ዕጣ በስድስት ዕጣዎች ለእያንዳንዳቸው 32 ኢንች ኤል ኢዴ ቴሌቪዥኖችና ለሶስተኛ ዕጣ ሀያ ዕጣዎች ለእያንዳንዳቸው ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎችን ለባለ ዕድሎች ሸልሞ ባንኩ አሁንም ደንበኞች በዚሁ መርሃ ግብር በመጠቀም የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡  


Read 2661 times