Saturday, 15 February 2020 11:27

የኦሎምፒክ ችቦና ኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    በ13 ኦሎምፒያዶች 54 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፣ 11 የብርና 21 የነሐስ ሜዳልያዎች)

               54 የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች
• 22 የወርቅ፣ 11 የብር እና 21 የነሐስ ሜዳሊያዎች ናቸው፡፡ የተቀሩት ውጤቶች 4ኛ ደረጃዎች 17 ጊዜ፤ 5ኛ ደረጃዎች 8 ጊዜ፣ 6ኛ ደረጃዎች 11 ጊዜ፣ 7ኛ ደረጃዎች 6 ጊዜ እና 8ኛ ደረጃዎች 32
        በወንዶች
• 12 የወርቅ፣ 6 የብርና 12 የነሀስ ሜዳሊያዎች፣ 4ኛ ደረጃዎች 9፣ 5ኛ ደረጃዎች 3፤ እና 8ኛ ደረጃዎች 30
       በሴቶች
• 10 የወርቅ፣ 5 የብርና 9 የነሐስ ሜዳሊያዎች፣ 4ኛ ደረጃዎች 8፤ 5ኘ ደረጃዎች 5፣ 6ኛ ደረጃዎች 1፣ 7ኛ ደረጃዎች 3 እና 8ኛ ደረጃዎች 2


                  እሁድ የካቲት 8 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የኦሎምፒክ ችቦ ይለኮሳል፡፡ በ2020 እ.ኤ.አ የጃፓኗ ከተማ ከምታስተናገደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የኦሎምፒክ ችቦ ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ እንቅስቃሴን ተምሣሌት ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የጥንታዊ እና የዘመናዊ ኦሎምፒክ ውህደትን ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴው ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ በተለየ ሁኔታ ዝግጅቷን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ለትውልድ የሚተላለፍ 2020 ዘመናዊ የኦሎምፒክ አካዳሚ የመገንባት እቅዱን ለማሳካት የመጀመሪያ ፕሮግራሙ ችቦ ማብራት ነው፡፡ ችቦው ከአዲስ አበባ ተነስቶ በቀጣይ ድሬደዋ፣ ሶማሊያ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሀረሪ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብና ቤንሻንጉልን እንደሚያዳርስ ታውቋል፡፡
የዓለማችን ታላቅ የስፖርት መድረክ ኦሎምፒክ ላይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ክብርና ሞገስ አላት፡፡ ከ1896-2016 እ.ኤ.አ 31 ኦሎምፒያዶች የተካሄዱ ሲሆን፤  ኢትዮጵያ በ13 ኦሎምፒያዶች በመሳተፍ በድምሩ 54 ሜዳሊያዎችን ስትሰበስብ ውጤቱን 31 ኦሎምፒያኖቿ አስመዝግበውታል፡፡ ከኢትዮጵያ 54 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች 22 የወርቅ ሜዳልያዎች ሲሆኑ የተጐናፀፏቸው 13 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች  አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ ቲኪ ገላና እና አልማዝ አያና ናቸው፡፡ 11 የብር ሜዳልያዎችን 10 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች እንዲሁም 21 የነሐስ ሜዳልያዎችን ደግሞ 17 የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ተጐናጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከተሳተፉባቸው 13 ኦሎምፒያዶች በ12ቱ ሜዳልያ ውጤት አላት፡፡ በ1960 ሮም 1 የወርቅ፣ በ1964 ቶኪዮ 1 የወርቅ፣ በ1968 ሜኪሲኮ፣ 1 የወርቅ 1 የብር፣ በ1972 ሙኒክ 2 የነሐስ፣ በ1980 ሞስኮ 2 የወርቅ 2 የነሐስ፣ በ1992 ባርሴሎና 1 የወርቅ 2 የነሐስ፣ በ1996 አትላንታ 2 የወርቅ 1 የነሐስ፣ በ2000 ሲድኒ 4 የወርቅ 1 የብር 3 የነሐስ፤ በ2004 2 የወርቅ 3 የብር 5 የነሐስ፤ በ2008 ቤጂንግ 4 የወርቅ 2 ብርና 1 ነሐስ፣ በ2012 ለንደን 3 ወርቅ 2 ብር 2 ነሐስ እንዲሁም በ2016 ሪዮዲጄነሮ 1 የወርቅ 2 የብር 5 የነሐስ ሜዳሊያዎች ለኢትዮጵያ ተመዝግበዋል፡፡  
የመጀመርያው ኦሎምፒክ በግሪኳ አቴንስ ከተማ ከ124 ዓመታት በፊት ሲካሄድ 14 አገራት ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡ ይህ የመጀመርያ ኦሎምፒያድ ከመከፈቱ አንድ ወር ቀደም ብሎ የዓለም ታሪክ ተቀይሯል፡፡ ኢትዮጵያ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እየተመራች በቅኝ ለመያዝ የወረረቻትን ጣሊያን በአድዋ ድል በማድረጓ ነበር፡፡ ከታላቁ የአድዋ ድል በኋላ 60 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ግዜ ለመሳተፍ  የበቃችው በ1956 እኤአ ላይ በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ነበር፡፡ አፍሪካን የወከሉ ሌሎቹ አገራት ጋና፤ ላይቤርያና ደቡብ አፍሪካ ናቸወ፡፡ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ተሳታፊ ኦሎምፒያኖቹን የመለመለው ከጦር ሃይልና ከተለያዩ የስፖርት ክለቦች ነበር:: ከመጀመርያዎቹ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች በብስክሌት ውድድር  ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የተገኙት ምርጡ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ እና የማራቶን ሯጩ ባሻዬ ፈለቀ በፈረቀዳጅነታቸው ይታወሳሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያኑ ኦሎምፒያኖች በንጉሳዊ ስርዓቱ ለኦሎምፒክ እንዲዘጋጁ በተሰጠ መመርያ ለአገራቸው የሜዳልያ ክብር ካስገኙ ብሄራዊ ጀግኖች ተብለው ትልቅ የክብር ሽልማት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸው ነበር:: ስለሆነም ሁሉም ኦሎምፒያኖች ለኦሎምፒኩ ዝግጅት ሲያደርጉ በታላቅ ወኔ ነበር፡፡ የሜዳልያ ውጤት አልተመዘገበም፡፡
22ቱ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች
ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ  በ1960 እኤአ ላይ በጣሊያን ሮም የተካሄደው ነበር፡፡ በወርቃማ ድል ለአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ታሪክ ተሰርቶበታል፡፡ የክቡር ዘበኛ ታማኝ ወታደር የነበረው አበበ ቢቂላ የሮምን ጐዳናዎች በባዶ እግሩ ሮጦ የኦሎምፒክ ማራቶንን አሸነፈ፡፡ አፍሪካ ዓለምን በአትሌቲክስ ማሸነፍ የጀመረችው በዚህ ታሪካዊና ፈርቀዳጅ ድል ነበር:: አበበ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ በታላቅ ግርማ ሞገስ መሮጡ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሪከርድን መስበሩ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር፡፡ ውድድሩን ካሸነፈ በኋላም 42 ኪሎሜትር የሮጠ ሳይመስል አስደናቂ ጅምናስቲክ መስራቱም መላው ዓለምን አስደምሞታል፡፡ በ3ኛው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ 1964 እኤአ ላይ በጃፓን ቶኪዮ ላይ ነበር፡፡ አበበ ቢቂላ በማራቶን በድጋሚ አሸንፎ የኦሎምፒክ ሻምፒዮናነት ክብሩን አስጠብቆበታል::  እንደ አበበ በሁለት ተከታታይ የኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ሁለት የዓለም ክብረወሰኖች አስመዝግቦ እና ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን  በማራቶን ያሸነፈ አትሌት እስካሁን አልተፈጠረም:: በ1968 እ.ኤ.አ ላይ በሜክሲኮ ከተማ ላይ ኢትዮጵያ ለ4ኛ ጊዜ ኦሎምፒክን ተሳተፈች:: ከአበበ  ቢቂላ በኋላ የኢትዮጵያ የማራቶን ክብር በሶስተኛው ተከታታይ ኦሎምፒክ ያስጠበቀው ደግሞ አትሌት ማሞ ወልዴ ነበር::  ማሞ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ሲያሸንፍ በ43 አመቱ መሆኑ አነጋጋሪ ነበር፡፡ እነዚህ ሶስት ተከታታይ የኦሎምፒክ ማራቶን ድሎች በኦሎምፒክ ታሪክ ኢትዮጵያን በተለየ ደረጃ ያስቀምጧታል፡፡ በማራቶን ለኢትዮጵያ በ3 ተከታታይ ኦሎምፒኮች ከተገኙት 3 የወርቅ ሜዳልያዎች በኋላ ሌላ  የወርቅ ሜዳልያ ከ3 የኦሎምፒክ ውድድሮች በኋላ የተገኘ ነበር፡፡ በ1980 እኤአ ላይ በሞስኮ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት ሩጫ አዲስና ፈርቀዳጅ ታሪክ በመሠራቱ ነው፡፡ ምሩፅ ይፍጠር በ10ሺና 5ሺ አሸንፎ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ በረጅም ርቀት አዲስ ምእራፍ ሊከፍት በቃ፡፡ በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃቱ ማርሽ ቀያሪው በሚል ስያሜ ለመወደስ የቻለው ምሩፅ በኦሎምፒክ ታሪክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ድርብ የወርቅ ሜዳልያዎችን በማግኘቱ የመጀመርያው አትሌት ሆኖ ነበር:: ከምሩፅ በኋላ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪካዊ ውጤታማነት ከበርካታ ዓመታት በኋላ የተመለሰው 1992  እኤአ ላይ በስፔን ባርሴሎና ላይ ነበር፡፡ በዚህ ኦሎምፒክ  ላይ ኢትዮጵያዊቷ ኦሎምፒያን ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺ ሜትር አሸንፋ በረጅም ርቀት የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ወሰደች፡፡ በ1996 እኤአ ላይ ደግሞ በአሜሪካ አትላንታ ኦሎምፒክ ሌላ አዲስ ታሪክ  በኢትዮጵያዊቷ ኦሎምፒያን ፋጡማ ሮባ ተመዘገበ፡፡ ፋጡማ ሮባ በማራቶን አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያውን በመጎናፀፍ  ለኢትዮጵያና ለአፍሪካውያን ፈርቀዳጅ ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ ሰራች፡፡ በአትላንታ ሌላ ትልቅ ኦሎምፒያንም ከኢትዮጵያ ወጥቷል፡፡ በዓለም አቀፍ የረዥም ርቀት አትሌቲክስ ውድድሮች የምንግዜም ምርጥ  አትሌት ለመሆን የበቃው ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ ኃይሌ በአትላንታ ኦሎምፒክ የ10 ሺ ሜትር ሪኮርድ በመስበር አሸንፎ የርቀቱን ክብር ከሶስት ኦሎምፒኮች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሰው  ችሏል::  በ2000 እኤአ ላይ በሲዲኒ አውስትራሊያ በተካሄደው ኦሎምፒክ  ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍተኛ የሆነውን ውጤት ያስመዘገበችበት ነው:: በ10ሺ ሜትር ዓለም ምንግዜም የማይረሳው ትንቅንቅ ኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገብረስላሴና ኬንያዊውን ፓልቴርጋት አሳይተዋል:: ሁለቱ አትሌቶች እስከመጨረሻው የድል መስመር ተፎካክረው በ9 ማይክሮ ሰከንዶች ልዩነት በመቅደም ለሁለተኛ ተከታታይ ኦሎምፒክ ኃይሌ ገብረስላሴ በ10ሺ ሜትር የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያውን ተጎናፀፈ፡፡ በሌላ በኩል ደራርቱ ቱሉ በአስደናቂ የአሯሯጥ ውበት በ10ሺ ሜትር ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ወሰደች፡፡ በሲድኒ ኦሎምፒክ ሌሎች ትልልቅ ታሪኮችም ነበሩ፡፡ ከ42 ዓመታት በኃላ የማራቶንን ክብር ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ የበቃው የገዛሀኝ አበራ የወርቅ ሜዳልያ ድል ነበር፡፡ ሚሊዮን ወልዴ በበኩሉ በ5 ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ሀገሩን አስጌጠ፡፡ በ2004 እኤአ ላይ  አቴንስ ባዘጋጀችው 28ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ አዳዲስ ኦሎምፒያኖች አስተዋወቀች:: የመጀመርያው በሴቶች 5 ሺ ሜትር በአትሌት መሠረት ደፋር አማካኝነት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ነው፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ በኃይሌ ገብረስላሴ በ10ሺ ሜ የተገኘውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር በማስጠበቅ ለራሱ የመጀመርያን የኦሎምፒክ ሻምፒዮናነት በማግኘት የወርቅ ሜዳልያውን ክብር ተጎናፀፈ፡፡ ጥሩነሽ ዲባባም የደራርቱ ቱሉ ፈር በመከተል በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ በመጐናፀፍ የመጀመሪያ ኦሎምፒክ ክብሯን ወሰደች፡፡ በ2008 እኤአ በቤጂንግ ኦሎምፒክ ደግሞ በ10ሺ እና  በ5ሺ ሜትር ውድድሮች የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች የበላይነት ተረጋገጠ፡፡ በሁለቱ ርቀቶች ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ እያንዳንዳቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመውሰድ በኦሎምፒክ ታሪክ በምሩፅ ይፍጠር የተሰራውን ክብረወሰን በመስተካከል ኢትዮጵያዊ ብቸኛ የዓለም አትሌቶች ሆኑ፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ላይ በእንግሊዝ ለንደን በተካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ 3 የወርቅ ሜዳልያ ወስዳለች፡፡ ሶስቱም የወርቅ ሜዳልያዎች በሴት ኣሎምፒየኖች ተገኝተዋል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺ መሠረት ደፋር በ5ሺ ሜትር እንዲሁም ቲኪ ገላና በማራቶን የተሸለሟቸው ናቸው፡፡  በ2016 እ.ኤ.አ ላይ በ31ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያን ብቸግ የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበችው በ10ሺ ሜትር አልማዝ አያና ናት፡፡
የዓለማችን ታላቅ የስፖርት መድረክ ኦሎምፒክ የዓለም አገራትና ህዝቦቻቸውን በአንድ መንፈስ የሚያስተባብር ነው፡፡ በስፖርት መድረኩ በብልጽግና እና ቴክኖሎጂ ርቀው የሄዱ፤ ታላላቅ አትሌቶችንና የስፖርት ቡድኖችን የሚያሳትፉ፤ በድህነት የተጎሳቆሉ፤ በበቂ የስፖርት መሰረተ ልማት ዝግጅታቸውን ያላከናወኑ፤ በየአገራቸው ባሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የተረበሹ፤ በጦርነት እና በኢኮኖሚ ቀውስ የሚገኙ አገሮቻቸውን የወከሉ ኦሎምፒያኖች ይሳተፋሉ፡፡ ሁሉም አንድ ዓላማ ይኖራቸዋል፡፡ በሜዳልያ ክብር አገራቸውን ማኩራትና  ሰንደቅ አለማቸውን ማውለብለብ ነው፡፡ የኦሎምፒክ የሜዳልያ ክብር መጎናፀፍ  ደግሞ የየትኛውም የዓለም ስፖርተኛ ህልም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኦሎምፒክ ታሪክ ሙሉ ለሙሉ ከወርቅ የተሰሩ ሜዳልያዎች ለአሸናፊዎች ለመጨረሻ ግዜ የተሰጠው በ1912 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ገፅታ በአዘጋጅ አገራት የዲዛይን ፍላጎት እንዲሆን ቢፈቀድም ሜዳልያዎኙ የሚሰሩበት ማእድን በኦሎምፒክ ቻርተር መሰረት የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡ በኦሎምፒክ ለ1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ የሚሸለሙት የወርቅና የብር ሜዳልያዎች 92.5 በመቶ የሚሰሩት ከብር  እንዲሁም 6 በመቶ ከመዳብ ነው፡፡ ለ3ኛ ደረጃ ተሸላሚዎች የሚሰጡት የነሐስ ሜዳልያዎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከነሐስ የተሰሩ ናቸው:: የወርቅ ሜዳሊያዎች በ6 ግራም ወርቅ መለበጣቸው ግድ ነው፡፡ ሁሉም ሜዳልያዎች ውፍረታቸው 3ሚሜ  ዲያሜትራቸው 60 ሚሜ መሆን አለበት፡፡ አንድ የወርቅ ሜዳልያን አቅልጦ ይሸጥ ቢባል ከ706 ዶላር ጀምሮ ዋጋ ይኖረዋል፡፡
ከፍተኛ ውጤት ያላቸው የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ከኢትዮጵያ አትሌቶች ለኦሎምፒክ ውጤቷ ቀዳሚ የሆነችው 6 ሜዳልያዎችን ያስመዘገበችው ጥሩነሽ ዲባባ ስትሆን፤ 3 የወርቅ 3 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በ4 ሜዳልያዎች በ3 የወርቅና በ1 የብር በ2ኛ ደረጃ ይከተላታል፡፡ ምሩፅ ይፍጠር በ3 ሜዳልያዎች 2 የወርቅና 1 የነሐስ፣ ደራርቱ ቱሉ በ3 ሜዳልያዎች 2 የወርቅ 1 የነሐስ፣ መሠረት ደፋር በ3 ሜዳልያዎች በ2 የወርቅና 1 የነሐስ፤ እኩል 3ኛ ደረጃን ይጋራሉ፡፡ ማሞ ወልዴ 3 ሜዳልያዎች 1 የወርቅ፣ 1 የብርና 1 የነሐስ፣ ጌጤ ዋሚ በ3 ሜዳልያዎች 1 የብር፣ 2 የነሐስ፣ አበበ ቢቂላ 2 ሜዳልያዎች 2 የወርቅ፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ በ2 ሜዳልያዎች 2 የወርቅ፣ አልማዝ አያና በ2 ሜዳልያዎች 1 የወርቅና 1 የነሐስ እንዲሁም ስለሺ ስህን በ2 ሜዳልዎች 2  ተከታታይ ደረጃዎች ይወስዳሉ፡፡
4 የኣሎምፒክ ሪከርዶች - በኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች
በኦሎምፒክ መድረክ በወንዶች  በ5ሺ ሜትር እና በ10ሺ ሜትር ሁለት ክብረወሰኖችን የያዘው  ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ሁለቱንም የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች እኤአ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው ኦሎምፒያድ ሲያስመዘገባቸው በ5 ሺ ሜትር 12 ደቂቃ ከ57.82 ሰኮንዶች እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 27 ደቂቃ ከ04.7 ሰኮንዶች የሰፈሩ ናቸው፡፡ ኬንያውያን በ800፤ በ1500፤ በ3ሺ መሰናክልና በማራቶን የተያዙ የኦሎምፒክ ሪከርዶችን በመቆናጠጥ የተሻለ ውክልና አላቸው፡፡ በኦሎምፒክ መድረክ በሴቶች ምድብ በተመዘገቡ ሪከርዶች ኢትዮጵያ በሁለት አትሌቶች ስትጠቀስ ኬንያ ግን አንድም አላስመዘገበችም፡፡ በኢትዮጵያውያን የተያዙት ሁለት የረጅም ርቀት የኦሎምፒክ ሪከርዶች በ2016 እእአ ላይ በሪዩዲጄኔሮ ኦሎምፒክ አትሌት አልማዝ አያና በ10ሺ ሜትር  29 ደቂቃ ከ17.45 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችውና በ2012 እኤአ ላይ በለንደን በተካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ ቲኪ ገላና በማራቶን ስታሸንፍ ርቀቱን የሸፈነችበት 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ07 ሰኮንዶች ናቸው፡፡


Read 1436 times