Saturday, 15 February 2020 11:28

ቅድመ - አያት ሸረሪት ፀሐይን ሰረቀች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

  አንድ አፈ - ታሪክ “ከዕለታት አንድ ቀን በሚል የሚከተለውን ያወጋል፡፡
በመጀመሪያ ድቅድቅ ጨለማ ነበረ፡፡ ማንም ምንም ነገር ማየት አይችልም ነበር:: ሰዎችም እርስ በርስ ይጋጩ ነበር፡፡
ስለዚህም “ይህ ዓለም የሚፈልገው ብርሃን ነው” አሉ፡፡
ቀበሮ፤ በዓለም በሌላኛው ወገን የሚኖሩ አያሌ ብርሃን ያላቸው ህዝቦች መኖራቸውን እንደሚያውቅ ተናገረ፡፡ ሆኖም ሰዎቹ እጅግ ስግብግብ ከመሆናቸው የተነሳ ለሌላ ለማጋራት ፈቃደኛ አይደሉም አለ፡፡ ፖሰም የተባለው እንስሳም ከዚህ ብርሃን ጥቂቱን ለመስረቅ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጦ ተናገረ፡፡ “እኔ ጭራዬ ቡፍ ያለ ነው” ስለዚህ ያንን ብርሃን በጭራዬ ውስጥ መደበቅ እችላለሁ አለና ወደ ሌላኛው የዓለም ወገን አቀና፡፡
እዚያም ፀሐይን አገኛት፡፡ ፀሐይ ዛፍ ላይ ተንጠልጥላ ለሁሉ ፍጥረት ስታበራ አየ፡፡
ወደ ፀሐይ ሹልክ ብሎ ገብቶ ቅንጣት ብርሃን ወሰደና ጭራው ውስጥ ዶለው፡፡ ሆኖም ብርሃኑ በጣም የጋለ ስለነበረ የጭራውን ፀጉር አነደደው፡፡
ህዝቡ ሌብነቱን አወቀበትና ብርሃኑን መልሶ ወሰደበት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፓሰም ጭራ መላጣ ሆኖ ቀረ፡፡
“ቆይ እኔ ልሞክር” አለ ቡዛርድ፡፡
“የተሰረቀ ብርሃን ጭራ ውስጥ ከመደበቅ የተሻለ መላ አውቃለሁ፡፡ እራሴ ላይ አረገዋለሁ” ብሎ ወደ ሌላኛው ዓለም በረረና ወደ ፀሐይ ሰንጥቆ ገብቶ፣ ብርሃኑን በጥፍሩ ያዘው፡፡ ከዚያ ራሱ ላይ አስቀመጠው፡፡
ሆኖም ብርሃኑ የጭንቅላቱን ላባ አነደደው፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ ፀሐይን ከሱ ነጥቆ ወሰደበት፡፡ የቡዛርድ ራስ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መላጣ ሆኖ ቀረ፡፡
ከዚያም ሴት አያት ሸረሪት “እኔ ልሞክር!” አለች፡፡ በመጀመሪያ ከሸክላ በጣም ጥጥር ያለ ግድግዳ ያለው እንሥራ ሠራች፡፡
ቀጥላም ወደ ሌላኛው ዓለም የሚደርስ ድር አደራች፡፡ እጅግ ደቃቃ ከመሆኗ የተነሳ ማንም መምጣቷን አላወቀም፡፡ አያት ሸረሪት በፍጥነት ፀሐይዋን ሰርቃ የሸክላው እንስራ ውስጥ ከታ፣ አንደኛውን የድር መስመር በመጠቀም፣ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ አሁን እንግዲህ በሷ በኩል ያለው አለም ብርሃን አገኘ፡፡ ሰው ሁሉ ተደሰተ!
እናት ሸረሪት ወደ ቼሮኪ ህዝቦች ያመጣችው ፀሐይን ብቻ ሳይሆን እሳትም ጭምር ነበር፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ለቼሮኪ ህዝብ የእንስራ አሠራር ጥበብን አስተማረች፡፡
***
ከሁሉም ነገር በላይ በዓለም የጨለመ ወገን ብርሃንን ማጋራት ታላቅ ጽድቅ ነው:: ይህንን ደግ ሥነምግባር ይዞ መገኘትም ታላቅ ፀጋ ነው፡፡ የጋን መብራት ላለመሆን መጣር ከጥረቶች ሁሉ የላቀ ነው፡፡ ምነው ቢሉ፤ ያ ብርሃን አንድም ለዓለም ሁለትም ለራስ የሚሆን ነውና ነው፡፡
ሮበርት ብራውኒንግ የተባለው ደራሲ እንዲህ ይለናል፡-
“…ደግሞም ማወቅ ማለት፡-
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ!”
ብዙ ከዋክብት ከመካከላችን አሉ፡፡ ብርሃናቸው ለሁላችንም ይዳረስ ዘንድ መንገዱን መጥረግ ይኖርብናል፡፡ እኛ ነፃነትን የምንፈልገውን ያህል፣ ነፃነትን የተራቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኛ መብታችን ይጠበቅልን ዘንድ ከልባችን የምንፈልገውን ያህል ሌሎችም እንደኛው መብታቸውን እንደ እህል ውሃ ሲናፍቁ ዓመታት አልፈዋል:: እነሱ ስለ መብታቸው መብታቸውን ለማስከበር እንደሚታገሉ እያወቅን እጆቻችንን አጣጥፈን መቀመጥ ፈጽሞ የማይገባ ነገር ነው፡፡ መብታችንን ለማወቅና ለማሳወቅ ሌት ተቀን መድከም፤ ሳያሰልሱም መታገል የዜግነት ግዴታችን፣ የአገርም ኃላፊነታችን ነፀብራቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ምኞታችን ዛሬ ባይሳካ ነገ በእርግጠኝነት ለፍሬ መብቃቱ አይቀሬና አሌ የማንለው ሃቅ ነው! ዱሮ ስናሰግረው የነበርነው መፈክር ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ፈጦ እየታየ ነው “ጉዟችን ረጅም ትግላችን ረጅም ነው” ብለናል፡፡ የምንለኩሰው እሳት አንድም ከድቅድቁ ጨለማ የምንወጣበት፣ አንድም የያዘን ቆፈን እንዲለቅቀን የምንገለገልበት ነው! ዛሬም፤
“ሁሉንም ሞክሩ
የተሻለውን አፅኑ! (“ኩሉ አመክሩ፤ ወዘሰናየ አፅንዑ” ማለት ያባት ነው እንላለን:: በዚህም ትውልድ እናድንበታለን ብለን እናምናለን፡፡
ህዝባችን የኖረውን ያህል ደስታን እንዲጐናፀፍ እየተመኘን፣ አሁንም የተስፋችንን ብርሃን ቀንዲሉን መለኮሳችን ዕውነት ነው፡፡ “ሀ” ብለን የጀመርነውን የዲሞክራሲ እንቅስቃሴ ዳር ለማድረስ፣ ጉዟችንን ከነድክመታችን ተሸክመን፤ የድል ጐዳናችንን እየናፈቅን ዘንድሮም እንደ አምና ካቻምና ውጣ ውረዱን እንያያዘዋለን! ያለጥርጥር “በወርቅ አልጋ፣ በእርግብ ላባ” ላይ እንተኛለን የሚል ቅዠት የለብንም፡፡ ሁሉንም እንደየአመጣጡ መክተን፣
“በፊደል ነው የተለከፍኩት
በትግል ነው ራሴን ያወኩት
ሌላ ባላውቅም እንኳ የራሴን ዋጋ አውቃለሁ ነው ያልኩት!”
…እያልን ወደ ግባችን እናመራለን፡፡
ትግላችን መራራ ነውና፤
“ኧረ ምረር ምረር
ምረር እንደቅል፤
አልመርም ብሎ ነው ዱባ እሚቀቀል” እንላለን፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን “ቅድመ - አያት ሸረሪት ፀሐይን ሰረቀች” የምንለውም አምርረንና ጠንቅቀን ነው!

Read 14021 times