Saturday, 15 February 2020 11:29

ስማቸው እንዲጠቀስ ካልፈለጉ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር የተደረገ ምናባዊ ቃለ ምልልስ

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(4 votes)

  አንዳንድ ፅንፈኛ ፓርቲዎች ምርጫው በግድም ይሁን በውድ ዘንድሮ፣ ከዘንድሮም ደግሞ በግንቦት ወር ላይ ካልተደረገ ሞተን እንገኛለን (እነሱ እኮ መች ሞተው አያውቁም?! አገርም ትፈርሳለች እያሉ ሲያስፈራሩ ብዙዎቻችን ግራ ከመጋባትም ባሻገር በስጋት መወጠራችን አልቀረም:: (እንዴት አንወጠር!) አገር በቀውስ እየተናወጠች ባለችበት ሁኔታ ለምርጫ ይህን ያህል የቋመጡት ምን አስበው ነው? ብለን መጠየቃችንም አልቀረም፡፡ ለነገሩ ከወዲሁ አንዳንድ ፍንጮች እያየን ነው:: ምርጫ ቦርድ የቅስቀሳ የጊዜ ሰሌዳን ከማሳወቁ አስቀድሞ የሞቀ የምርጫ ቅስቀሳ የጀመሩም አሉ ተብሏል፡፡ በዚያ ላይ ገና ከአሁኑ ተፎካካሪያቸውን በአደባባይ በስም እየጠሩ መዝለፍ፣ ማብጠልጠል መፈረጅና ታርጋ መለጥፍም ተጧጡፏል፡፡ የምርጫው አስቀያሚ ገጽታ በሉት!)
ለነገሩ የዴሞክራሲ አስተማሪና እናት እየተባለች በምትሞካሸዋ አሜሪካም ጭምር የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ፤ በጦፈ ስድብና ዘለፋ የታጀበ ሆኖ - አገሪቱን ትዝብት ውስጥ ጥሏታል። ለሁሉም የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ተወዳዳሪዎች፣ ቀንደኛ ጠላታቸው፣ ሰሞኑን ከተመሰረተባቸው (ከስልጣን የመልቀቅ) ክሰ ነጻ የተደረጉት አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሲሆኑ በተረፈ ግን እርስ በርስም እየተናቆሩ ይገኛሉ (ራሳቸው ዴሞክራቶቹ!)
አክራሪው የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኙ አዛውንቱ በርኒ ሳንደርሰን፤ በቅርቡ ቱጃርነታቸውን ተማምነው  (ለቲቪ ማስታወቂያ የቢሊየን ብሮች በጀት በመመደብ!) ወደ ምርጫው ዘው ያሉትን የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባንና የብሉምበርግ ጋዜጣ ባለቤትን፤ ‹‹ምርጫውን በገንዘቡ ለመግዛት እየሞከረ ነው›› ብለው ወርፈዋቸዋል፡፡
 የአሜሪካን የምርጫ ሁኔታ ያነሳሁት ከእኛ ጋር ይመሳሰላል ለማለት ፈልጌ አይደለም (ሺ ጊዜ ብፈልግም እንኳ ሊመሳሰል አይችልም!):: ወዳጆቼ፤ አሜሪካኖቹ ሚሊዮን ጊዜ ቢናቆሩና ቢዘላለፉም እንደኛ ፍሬን አይለቁም፡፡ በምርጫ ማግስትም ቢሆን ለየለት ግጭትና ቀውስ ውስጥ አይገቡም:: በየመሃሉ “በአመለካከት ብንለያይም ሁላችንም አሜሪካውያን ነን” የሚሉ የአንድነት ስሜት የሚፈጥሩ ፖለቲከኞች አይጠፉም:: (የሥልጣኔና የዕድገት ውጤት ነው!) እኛ ግን ምርጫ በመጣ ቁጥር በእንዴት ያለ ሁኔታ ሊጠናቀቅ እንደሚችል አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ (የዘንድሮው ምን ያህል እንደሚከፋ ለመገመት ቢያዳግትም!)
ውድ አንባብያን፡- ለዛሬ የፖለቲካ ሀተታዬን (ወጌን) እዚህ ጋ ገታ ላድርግና ስማቸው እንዲጠቀስ ካልፈለጉ አንጋፋ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጋር ያደረግሁትን ምናባዊ ቃለ ምልልስ ላስነብባችሁ፡፡ (ምርጫውን ምናባዊ ያድርግልን ይባላል እንዴ?) ትወዱታላችሁ:: ትፈሩታላችሁ፡፡ ትማሩበታላችሁ፡፡
ለምንድን ነው ስምዎ እንዲጠቀስ ያልፈለጉት? ላለፉት 30 ዓመታት በተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት የታወቁ አንጋፋ ፖለቲከኛ አይደሉ እንዴ?
የጋዜጠኞች ነገር ትቸኩላላችሁ፡፡ ስሜ ባይጠቀስም ፎቶዬን ታወጣዋለህ። ሆን ብዬ ነው፡፡ እኔ አንተን ብሆን ምን እንደማደርግ ታውቃለህ? “የእኒህን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ትክክለኛ ስም  በአጭር የሞባይል የፅሁፍ መልዕክት አስቀድሞ ላደረሰን የ10ሺ ብር ሽልማት እናበረክታለን” የሚል ማስታወቂያ አወጣና፣ የአንባቢያንን ቁጥርና የጋዜጣዬን ሥርጭት አሳድገው ነበር፡፡ የዛሬ ጋዜጠኞች ግን ፖለቲካም ቢዝነስም አታውቁም!!
እኔ የምለው… 10 ሺ ብሩን ከየት አምጥቼ ነው የምሸልመው? (በድንጋጤና በአግራሞት ተሞልቼ)
It is simple! በስፖንሰር ነዋ!
እዚህ አገር ፖለቲከኛን ስፖንሰር የሚያደርገው ማነው? በቅንጅት ጊዜ የሆነውን እያወቁት ለምን ምርጫ ቦርድ ስፖንሰር አያደርግም?! ወይም ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ… ማለቴ ጽሕፈት ቤታቸው! ተቃዋሚ ሳትሆኑ ተፎካካሪ… ጠላቶች ሳትሆኑ ወንድሞች… ጓዶች… ዘመዶች… ባልደረቦች ወዘተ ሲሉን አልነበር እንዴ! 10ሺ ብር ስፖንሰር በማድረግ… ከልባቸው መሆኑን ያሳዩና!?
እንዴት ነው ጠ/ሚኒስትሩ የምርጫ ተፎካካሪያቸውን ስፖንሰር የሚያደርጉት?
ቀልዴን ነው ባክህ! እኔ ስፖንሰር አደርግሃለሁ፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ታዲያ አንተም ታግዘኛለህ ሰጥቶ መቀበል ነው ትስማማለህ?
ስለ እሱ ከቃለ መጠይቁ በኋላ እንነጋገራለን፡፡ አሁን ወደ ጥያቄዬ ልግባ - ለምንድን ነው በትንሹም በትልቁም የለውጥ ሃይሉን ማብጠልጠል የሚወዱት? ብዙዎች እንደውም “ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር የግል ጠብ ያለባቸው ይመስላሉ” የሚል ትችት ይሰነዝሩብዎታል….
የግል ጠብ እንኳን የለኝም፡፡ የለውጥ ሃይሉን የምተቸው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የሪፎርም ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ የቀዱት ከእኔ ፓርቲ ነው፡፡ ያውም ዕውቅና ሳይሰጡኝ፡፡ ማብጠልጠል ብቻ ሳይሆን ፍ/ቤት ሁሉም ማቆም ይቻል ነበር፡፡ በፕላጂያሪዝም… በኮፒራይት ወዘተ ስርቆትና ዝርፊያ በመከሰስ ችግሩ ግን ፍ/ቤቱም የእነሱ ነው:: … ምን ታደርገዋለህ?…
ለዚህ ምን ማስረጃ ያቀርባሉ?
ማስረጃ?! ለመሰረቄ?? ራሴን ነዋ! የዛሬ 10 ዓመት ለአንድ ወር በሬን ከርችሜ… ያረቀቅኩት ዶክመንት ነው ለእኔ ማስተር ፒሴ ነው፡፡ ከአዕምሮዬ ያፈለቅኩት፡፡  አየህ ልጄን ነው በጉዲፈቻ ወስደው እያሳደጉ ያሉት… ያለ እኔ… ያለ አባቱ ፈቃድ! ከዚህ ቀደም ኢሕአዴግም ብዙ ሃሳቦችን ሰርቆናል:: የሃሳብ ድርቀት አለበት፡፡  
በዚህ ወቅት የእርስዎ ፓርቲ በሥልጣን ላይ ቢሆን… ሰላም ለማስፈንና የሕግ የበላይነት ለማስከበር ምን ያደርግ ነበር? መንግሥት ሕግ አላስከበረም… ደክሟል… የሚል ወቀሳ ስለሚሰነዝሩ ነው…
ኦኬ! መፍትሄው ቀላል ነው፡፡  ብዙ አይዲያዎች አሉ፡፡ ምን መሰለህ መጀመሪያ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር በኮማንድ ፖስት አጥረዋለሁ፡፡ በተለይ በምርጫው ሰሞን ኮሽታ እንዳይሰማ ቁርጠኛ አመራር ለፀጥታ ሀይሉ እሰጣለሁ፡፡ ያኔ ሰላማችን ይመለሳል፤ ሕግም ይከበራል፡፡ የእኔ ፓርቲ ቅድምያ የሚሰጠው ለሰላምና ለሕግ የበላይነት ነው:: ነፃነትና ዲሞክራሲ… እዬዬ ሲደላ ነው፡፡ መጀመሪያ አገር መኖር አለበት፡፡
ይሄማ ወደ ቀደመው የኢሕአዴግ ዘመን መመለስ ነው?
እኔ ወደ የትኛውም ዘመን ብንመለስ ጉዳዬ አይደለም፡፡ ለምን የጉዲት ዘመን አይሆንም?! አገር ወደ ሰላም እንድትመጣ፤ ሥርዓት አልበኝነትን እንዲጠፋ… በየሰፈሩ የተኮለኮሉ የጎበዝ አለቆች አደብ እንዲገዙ… የፌስቡክ አርበኞች በልካቸው እንዲንቀሳቀሱ… ጽንፈኞች በፈጠራ ትርክት አገር እንዳያተራምሱ “የእርምጃ ፓኬጅ” አዘጋጅቼአለሁ፡፡
ምን ዓይነት እርምጃ… እስር? ግድያ? ወከባ?
መቼም እንደ ጠ/ሚኒስትሩ… ፍቅርና ይቅርታ እንደማልልህ ታውቀዋለህ:: አየህ… ሕግና ሥርዓት በፍቅርና ይቅር ባይነት አይረጋገጥም፡፡ በእርምጃ… በሀይል እንጂ! ሰላም በልምምጥ አይመጣም… በመስዋዕትነት እንጂ! ሁሉም ቁርጠኛ እርምጃ ይፈልጋል፡፡ እኔ እንደ ፖለቲከኛ… በተለይ እንደ መንግሥት ሕግና… ሥርዓት  ማስከበር… የአገር ሉዓላዊነት ማስጠበቅ… ሥራዬ ነው፡፡ ፖሊስ… መከላከያ ሀይል… አየር ሀይል… ልዩ ሀይል… ተስፈንጣሪ… የመንግስቴ ቀኝ እጆች ናቸው፡፡ ሕግን ለማስከበር ሕግ ልጥስ እችላለሁ፡፡ መንግሥት መፈራትም መከበርም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
ይኼማ የለየለት አምባገነናዊነት ነው… አገሪቱን ወደ ኋላ መመለስ ነው? ለውጡንም መቀልበስ ነው…
የፈለከውን ስም ልትሰጠው ትችላለህ፡፡ ሕዝብን ለጠብ እየቀሰቀሱ… ቁርሾ እየፈጠሩ… ሕዝብ እያፈናቀሉ… መንግሥትን በሀይል ለመጣል እያሴረ… በዝምታ መመልከት… በታሪክ ያስጠይቃል! ደሞ አፍሪካ ውስጥ መኖራችንን እንዳትረሳ… አገሪቱ የትጥቅ ትግል ውስጥ በኖሩ የፖለቲካ ሃይሎች ተከባለች፤ ራሳቸውን እንደ መንግሥት የሚቆጥሩ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የነገሱባት አገር ናት፡፡ ሕግና ሥርዓት የማስከብረው… ሁሉንም በሚገባው ቋንቋ እያናገርኩ ነው፡፡ አገር እያፈራረሱ መብትና ዲሞክራሲ አይገባኝም፡፡
እርስዎ ከኮሎኔል መንግስቱ በምንድን ነው የሚለዩት?
በምንም፡፡ ምናልባት በዕድሜ፡፡ በተረፈ አንድ ነን፡፡ አገሩን ይወዳል፣ አገሬን እወዳለሁ:: ቁራጥ ነው፣ ቆራጥ ነኝ፡፡
ኮሌኔሉን ያደንቋቸዋል ማለት ነው?
መጠርጠሩስ! አገሩን የሚወድ ጀግና እኮ ነው፡፡ አንተን አውርደን እኛ እንግዛ አሉ:: አይሞክርም አላቸው፡፡ በአንድ ሰማይ ላይ ሁለት ፀሐይ አይወጣም፡፡ ወይ እኔ እመራለሁ፤ ወይ እነሱ ይመራሉ:: ከተቀናቃኜ ጋር በደቦ አገር አልመራም:: አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ቁርጠኛ አይደለም፡፡ ሆደ ቡቡ ነው፡፡ አምባገነን መባል አይፈልግም፡፡ የሥልጣን ጥመኛ የሚል ቅጽል እንዲለጠፍበት አይሻም! አትታዘበኝና… እኔ ጠ/ሚኒስትሩን ብሆን… በዚህች ሁለት ዓመታት ሁለት ትላልቅ ወህኒ ቤቶች እገነባ ነበር፡፡ መታሰር ያለበት ይታሰራል፡፡ መታጐር ያለበት ይታጐራል ይኸው ነው፡፡
በእርስዎ ዘመን ዴሞክራሲ አይታሰብም በሉኛ…
ወዳጄ፡- እንደኛ ባለ ኋላቀርና ድሃ አገር ውስጥ የመንግሥት ሥራ ዴሞክራሲና ነፃነት ማከፋፈል አይደለም፡፡ ሰላምና ፀጥታ ማስፈን ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ነው፡፡ ትናንሽ የመንደር መንግሥታትን ማፈራረስ ነው፡፡ ዜጎች ሰላም ወጥተው ሰላም መግባታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ እስካሁን ህዝቡ ነፃነት… ዲሞክራሲ.. ሲጠይቅ ሰምተህ ታውቃለህ? በፍፁም! ሕዝቡም ፓርቲዎችም የሚጠይቁት ሰላምና… ፀጥታ… የሕግ የበላይነት፣ የአገር ሉዓላዊነት…ወዘተ ነው፡፡ ዴሞክራሲ… ነፃነት… እዬዬ ሲደላ ነው፡፡ በዚያ ላይ የጠየቀም የለም፡፡
ምርጫውስ?
አገር ሳይረጋጋ ምርጫ የለም፡፡ ጊዜው ሲደርስ ይካሄዳል፡፡ በቀውስ ላይ ሌላ ቀውስ አያስፈልግም፡፡ ይሄን የሚወስነው ደግሞ መንግሥት እንጂ አክቲቪስት አይደሉም፡፡  
(ውድ አንባቢያን፡- እንዲህ አይነት የፓርቲ መሪዎችም እንደሚኖሩ ጥርጣሬ አይግባችሁ፡፡ በምናብ ሳይሆን በእውን!)

Read 4356 times