Saturday, 15 February 2020 11:33

የብሔር ማንነት ቅዠት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

     የከረረ ‹‹ብሔርተኝነት›› የሚያራምዱ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በሃይማኖታዊ  የበላይነትን ይዘው አገዛዛቸውን ማስቀጠል ተቀዳሚ ተግባራቸው ነው፡፡ ይኸውም በዋናነት ሕዝብን  ከሕዝብ ጋር ‹‹በብሔርና›› በኃይማኖት ማንነትን እንዲሁም የመሬት ወሰንን መሰረት ባደረገ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር በማጋጨት፣ ጥላቻ እንዲፈጠርና ደም እንዲፋሰስ በማድረግ በተቻላቸው መጠን የማይታረቅ ቅራኔ መፍጠር፣ ከመሰረታዊ ሴራቸው አንዱ ነው፡፡ የዚህ አይነት ሴራ በአሁኑ አለም በዋናነት በአፍሪካ፣ በኢስያ፣ በላቲን አሜሪካና በሌሎች አገራት ላይ የምእራባውያን ቅኝ ገዥዎች ዋንኛ ስልታቸው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን እስከ አሁንም አሻራቸው አልደረቀም፡፡
ይህም በ‹‹ብሔር›› ማንነት ቅዠት ላይ የታቀኘ የቅኝ ግዛት አሻራ እንደተቀበረ ቦንብ ባልታሰበ ጊዜ እየፈነዳ፣ ሕዝብን በአንጻራዊ በሰላም እንዳይኖርና ስለራሱ ሕይወት እንዳያስብ ሁልጊዜ በነውጥና በስጋት እንዲኖሩ እያደረገ ነው። በመሆኑም ምዕራባውያን በ‹‹ብሔር›› ማንነት ቅዠት የቅኝ አገዛዝ ስልት ይገዟቸው ወደነበሩና ወደ ሞከሩት ሀገራት በመዛመቱ፣ ይህ የ‹‹ብሔርተኝነት›› ቅዠት ጦስ እስካሁን ያለቀቃቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካና የእስያ ሀገራት በርካታ ናቸው። የ‹‹ብሔር›› ማንነት ቅዠት ሲከፋ ነቀርሳ ደረጃ ስለሚደርስ ህሊናንና ሰብአዊነትን ፈጽሞ ያሳጣል፡፡
በ‹‹ብሔር›› ማንነት ቅዠት የተለከፉ አምባገነን ገዥዎችና አራማጆች በሚያራምዶት የ‹‹ብሔር›› ማንነታቸው አገዛዝ መተማመን ስለማይኖራቸው ሴራ ዋና መሳሪያቸው ነው፡፡ ‹‹የብሔረተኛ›› ገዥዎች ሥነ አዕምሯቸው የተቃኘው ለጊዜያዊ ጥቅም ብቻ የተደራጁ በመሆናቸው፣ ሕዝብን ከፋፍሎ መግዛትን መርህ ያደረገ፣ የወሮ በላ ቡድን ናቸው፡፡ በመሆኑም በራሳቸው ‹‹ብሔርተኝነት›› የአዕምሮ ቅዠት ሕመም የተጠናወታቸው በመሆኑ፣ አገዛዛቸውን በማስቀጠል በኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው የበላይነትን በማረጋገጥ ላይ ብቻ አዕምሯቸው የተቃኘ በመሆኑ ቅንጣት ያህል ሀገራዊ ዜግነትና ሕዝባዊነት የማይሰማቸው ናቸው፡፡ ለአገዛዛቸው ዘለቄታ ሲሉ ሥነ አዕምሯቸው ለጠላት አገራት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ የተመቸና ራሳቸውም የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ናቸው:: ለአገዛዛቸው ስጋት በሚሆንባቸው ሕዝብ መካከል እነርሱ ባስፈለጋቸው ጊዜ ግጭትና ያለመረጋጋትን ሊፈጥሩ የሚችሉበትን ሴራ ይጠነስሳሉ፡፡
‹‹የብሔረተኛው›› የአገዛዝ ቡድን ሌላውን የሀገሪቱ ሕዝብ ሀብት የማፍራት መጠን በሴራቸው እየገደቡ በሂደት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመቆጣጠር ሌላውን ሕዝብ እንደ ባሪያ በመቁጠር፣ ምግብ እየበላ በዘላቂነት መገዛትን ያለመ ነው፡፡ ይኸውም ሌባ ተደብቆ እንደሚሰርቅ ተደብቀው የሕዝብን ሀብት፣ ነጻነትና ምርጫ መስረቅ ዋና ሴራቸው ነው:: ሕዝብ ወደ ሴራቸው እንዳያተኩር ሁልጊዜ ትኩረትን ማዘበራረቅ የማያቋርጥ ስራቸው ነው፡፡ በ‹‹ብሔር›› ማንነታቸው ቅዠት፣ ሕዝብን በ‹‹ብሔር›› ማንነት በመከፋፈል ግራና ቀኝ ጽንፍ በማስያዝ ወይም ‹‹እሳትና ጭድ›› እንደሚባለው በማድረግ፣ አክራሪ ማድረግም ከዋና ዋና ሴራቸው አንዱ ነው:: በዚህ ምክንያት ሕዝቡን በመከፋፈል የአገዛዙ ምርኮኛ (State Capture) ያደርጉታል:: ሕዝብን ምርኮኛ አድርጎ የሚገዛ አምባገነን አገዛዝ ሁልጊዜ ማንኛውንም ውሳኔዎች የሚያሳልፈው የአገዛዙንና የኢኮኖሚ የበላይነቱን የሚያስጠብቅለትን በመመርመር ብቻ ነው፡፡
‹‹ብሔርተኛ›› ገዢዎች በአንጻራዊ ከራሳቸው ‹‹ብሔር›› ውጪ የሌላውን ‹‹ብሔር›› ስለማያምኑ ከፍተኛ የጦር አመራሮችን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከራሱ ‹‹ብሔር›› ይሾማል፡፡ በመሆኑም ከገዥው ‹‹ብሔር›› ውጪ አልፎ አልፎ በከፍተኛ አመራር የሚሾሟቸው ቢኖሩም፣ ለአገዛዙ ምርኮኛ የሆኑትን ብቻ ነው:: በዚህ ምክንያት የሀገሪቱን ሀብት እንደ ግላቸው ንብረት በኪሳቸው ውስጥ ጠቅልሎ በመከተት፣ ለአገዛዛቸው ለሚመቻቸው ሁሉ እንደ ግል ሀብታቸው ከኪሳቸው እያወጡ እንደሚከፍሉ፣ የአገሪቱን ሀብት ለፈለጉት ቆንጥረው ይሰጣሉ፤  ላልፈለጉት ይነፍጋሉ፡፡ ለማይመቿቸው የነበራቸውንም ሀብት እንኳ ሳይቀር በሴራቸው ይነጥቋቸዋል፡፡ ለአገዛዝ የማይመቿቸውን ግለሰቦች በሴራና በሃሰት በተቀነባበረ ምክንያታዊና በሕግ ሽፋን ወንጀል እንደሰራ በማስመሰል፣ በማስፈራራትና በማሰር መበቀል፣ የደህንነቱ ዋና ተግባር ነው፡፡ በአጠቃላይ ‹‹የብሔርተኛው›› ገዢ ቡድን የማይደግፏቸው የሚመስላቸውን ከፍተኛ ባለሀብቶች በሴራቸው ያጠፏቸዋል፡፡     
የ“ብሔር” ማንነት ቅዠት”
መጽሐፍ የተቀነጨበ። 2011 ዓ.ም
(ከሰብስቤ አለምነህ)

Read 2891 times