Saturday, 15 February 2020 11:38

ጠብ ያለሽ በዳቦ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“እኔ የምለው… ዓለም ላይ ያለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ‘ሊብራሊዝም’ ምናምን የሚባለው ብቻ ሆነ እንዴ?! አሀ…ግራ ገባና! መቶ ምናምን ከሆኑ የፖለቲካ ‘ፓርቲዎች’፣ መቶ ምናምኑ፣ “የምትከተሉት ፖለቲካዊ መስመር የትኛው ነው?” ተብለው ቢጠየቁ፣ አብዛኞቹ “ሊብራሊዝም ነዋ!” ሳይሉ አይቀርም፡፡ ‘ሶሺሌስ’ ተረሳች ማለት ነው?! ‘ኮሚዬም’ ተረሳች ማለት ነው?! ቀዩዋ ኮከብ፣ ቀዩዋ ባንዲራስ ተረሱ ማለት ነው?!--”
        
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ዘንድሮ በሆነ ጉዳይ ላይ አንዳናችን ለሌላኛችን ምንም ነገር አስረድቶ ማሳመኑ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ሁላችንም በየጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ነው የምንለው ድምዳሜ አለና! እውነቱ እኛ የምናምነው ብቻ ነው፡፡ የሌላው ሁሉም ውሸት ነው! እናማ እንዲህ ሆኖ እንዴት ነው መግባባት የሚቻለው!
ከዓመታት በፊት፣ በአንድ ወቅት፣ አንድ ሰው “ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሚኒዝም ሊታወጅ ነው” ሲል ለወዳጆቹ ይነግራቸዋል:: ምንም አንኳን ሰውየው ‘ብዙ ነገር ያውቃል፣ በሚዲያ እንኳን የማይነገሩ ነገሮችን ያገኛል” የሚባልለት ቢሆንም፣ በኮሚኒዝሙ ጉዳይ ግን አልተቀበሉትም፡፡ (እኔ የምለው… ዓለም ላይ ያለው ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ‘ሊብራሊዝም’ ምናምን የሚባለው ብቻ ሆነ እንዴ?! አሀ…ግራ ገባና! መቶ ምናምን ከሆኑ የፖለቲካ ‘ፓርቲዎች’፣ መቶ ምናምኑ፣ “የምትከተሉት ፖለቲካዊ መስመር የትኛው ነው?” ተብለው ቢጠየቁ፣ አብዛኞቹ “ሊብራሊዝም ነዋ!” ሳይሉ አይቀርም፡፡ ‘ሶሺሌስ’ ተረሳች ማለት ነው?! ‘ኮሚዬም’ ተረሳች ማለት ነው?! ቀዩዋ ኮከብ ቀዩዋ ባንዲራስ ተረሱ ማለት ነው?!)
እሺ ይሁናላቸውና ቢያንስ፣ ቢያንስ ሊበራሊዝም የሚሉት ነገር የጤፍን ዋጋ እንዴት እንደሚቀንስልን፣ ለሚሊዮኖች እንዴት ሥራ እንደሚፈጥርልን፣ ወደ ሞራል ከፍታችን እንዴት እንደሚመልሰን፣ ያለ ሀሳብና ያለ ስጋት በገዛ ሀገራችን እንዴት ከቦታ ቦታ መዘዋወር እንደሚያስችለን…ያስረዱና! አለ አይደል… እያሉት ያለውን በእውነት ያውቁት እንደሆነ ለማለት ያህል ነው፡፡ 
እናላችሁ… ስለ ኮሚኒዝም መታወጅ የነገራቸውን ሊቀበሉት አልፈቀዱም:: በአሁኑ ጊዜ እንደዛ እንኳን አይሆንም፣ ምናምን ነገር ይሉታል፡፡ ምን ቢላቸው ጥሩ ነው… “እኔ ነኝ የማውቀው እናንተ!” አይነት መልስ ይሠጣቸዋል:: ሁሉም ነገር እንዳለቀና የሚጠበቀው በሚዲያ መነገሩ ብቻ መሆኑን ይገልጽላቸዋል፡፡ ወሬውን ከየትም ያምጣው ከየትም፣ እነሱ ሊሆን የማይችሉባቸውን ምክንያቶች ሊያስረዱት ቢሞክሩም አልተቀበለም፡፡ ለምን ቢባል… አለ አይደል… ‘እውነት’ ማለት እሱ የሚያምንበት ብቻ ነዋ!
እናላችሁ… “እውነት ማለት እኛ የምንናገረው ነው” ማለት ብቻ ሳይሆን “እውነት ማለት እኛ ነን!” ለማለት ምንም ያልቀረን ሰዎች በዝተናል፡፡
 “ስማ መኪና ለምን አትገዛም?”
“አሁንም ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን እያየሁ፣ ከየት አምጥቼ ነው መኪና የምገዛው?”
“ተው እባክሀ፣ በአካፋ የሚዛቅ ደሞዝ እንደሚከፍሉህ የማናውቅ መሰለህ!”
“እሺ…እናንተ  ካላችሁ ይሁን!”
እናንተ ሞዴል ስድስት አልደርስ ብሏችሁ ጣር ላይ ናችሁ፣ ብር በአካፋ ስለ መዛቅ ያወራላችኋል፡፡ በዚህ በኩል፤ የኮንደሚንየሙ እዳ ሳይከፈል ሦስተኛ ወር እየደፈነ ነው፣ በዛ በኩል ካቻምና ከመስሪያ ቤት የተበደራችሁት የቁጠባ እዳ ተከፍሎ አልተጋመሰም፡፡ እና ብር በአካፋ ስለ መዛቅ ያወራላችኋል፡፡ ግን እንዴት ታስረዱታላችሁ! በቃ እውነት  የእሱ ብቻ ነቻ! “የደሞዝ ቀን መሥሪያ ቤት አብረን ሄደን፣ የምፈርምበትን ፔይሮል አሳይሀለሁ” አትሉት ነገር፡፡ ስለዚህ ያለው እድል ወይ “እናንተ ካላችሁ ይሁን…” ወይ ደግሞ… “እንደ አፋችሁ ያድርግልኝ…” ማለት ነው እንጂ ለማስረዳት መሞከሩ አስቸጋሪ ነው፡፡
“ገንዘቡን ዝም ብለህ ከምትቀብር መኪና ግዛበት…”
እናማ… አለ አይደል… ከየት አምጥቼ? የትኛውን ካዛና ገልብጬ?”  ምናምን ከማለት የተሻለው ምን መሰላችሁ… “መኪና ምን ያደርጋል፣ ትርፉ መጋጨት ነው!” አሪፍ አይደል!
ምንም ነገር ላይ አንዳችን ሌላኛችንን ለማስረዳት መሞከሩ እንደውም ሌላ ሙግት ውስጥ መግባት ነው የሚሆነው፡፡ አናላችሁ…ሲበዛባችሁ ወይ “አንተ ደግሞ ዘላለም የሚሉህን አትሰማም…” ምናምን ትሉና  ነገርዬው ይጦዝላችኋል፡፡ “አንተ ደግሞ ዘላለም የሚሉህን አትሰማም…” ማለት የምልልሳችሁ አካል ሳይሆን በምን ሊተረጎም ይችላል መሰላችሁ…በትንኮሳ!
ስሙኝማ…የትንኮሳ ነገር ካነሳን አይቀር ረጋ ካልተባለ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች እንደትንኮሳ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ተነስቶ… “በዚህ ቁመትሀ እንዲህ የምትወጠረው ናፖሌኦን ቦናፓርቴ ነህ፣ ማነህ!”  ቢለኝ የአሜሪካና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት የማይፈታው ትንኮሳ ነው የሚሆነው፡፡
ጠብ ያለሽ በዳቦ በዛብንሳ!   
ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ናችሁ፡፡ መስኮቱ ሁሉ ተዘጋግቶ  እፍን ብሏል፡፡ አጠገባችሁ ያለውን መስኮት በጥቂቱ ከፈት ታደርጉታላችሁ፡፡ ከሁለትና ከሶሰት ደቂቃ በኋላ ከጎናችሁ ያለው ሰው ይንጠራራና፣ አየሩ ከብዷል ብሏችሁ መስኮቱን ከፍ ታደርጉታላችሁ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ጎናችሁ ያለው ሰው ይንጠራራና ይጠረቅመዋል:: “ብርድ ያስቸግረኛል…” ምናምን ብሎ ነገር የለ፣ “ሳሌን ይቀሰቅስብኛል” ብሎ ነገር የለ፣ “ነፋሱ ሀይለኛ ነው” ምናምን ብሎ ነገር የለ… እና ይሄ ‘ትንኮሳ’ ካልሆነ ምን ይሆናል! እናላችሁ… ሁሉንም ነገሮች በቀጥታ እኛን ለመጉዳት የሚደረግ ወይም እኛን የመናቅ ነገር ካስመሰልነው በተለይ እንደዚች ከተማ አይነት ስፍራ መኖር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው:: አንድ ኪሎ ሜትር ስትጓዙ እኮ በየመቶ ሜትሩ ልትረገጡ፣ በየሁለት መቶ ሜትሩ ልትገፈተሩ ትችላላችሁ፡፡ እናማ… ሁሉንም ረጋጭና ገፍታሪ “ጠላቶቼ ሆነ ብለው የላኩብኝ ነው”  የሚባል ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ…ነገሬ ብላችሁ እንደሁ ከአንዱ ቦታ ሌላኛው እስክትደርሱ ድረሰ ሁለትና ሦስት ስፍራ ግርግር ታያላችሁ፡፡ የእኔ ቢጤው ሁሉ ሳይቀር በትንሽ ትልቁ ያዙኝ፣ ልቀቁኝ ባይ እየሆነ ነው፡፡
ለገላጋይ አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ እናማ… አንዳንዴ፣ “ተዉአቸውና እስቲ የሚሆኑትን እንይ” አይነት ነገር ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ለምን መሰላችሁ… ገላጋይ በበዛ ቁጥር ሁለቱም ወገኖች ለያዥ ለገናዥ ያስቸግራሉ፡፡
ጠብ ያለሽ በዳቦ በዛብንሳ!   
በከተማችን አንድ ክፍል የሆነ ነው፡፡ መኪና እያጠቡ ያሉ ሁለት ወጣቶች በሆነ ምክንያት ይጋጩና ተያይዘው መሰናዘር ሲጀምሩ ሰዎች ይገላግሏቸዋል፡፡ ወዲያው እንደ ጎረምሳ የሚመሳስሉ ጸጥታ አስከባሪዎች ይደርሳሉ:: አንደኛው እንደደረሰ ስለ ጉዳዩ ምንም ጥያቄ ሳይጠይቅ አንደኛውን ወጣት ይዠልጠዋል፡፡ የሚገርመው ነገር ጠቡን የጀመረው የተመታው ልጅ ሳይሆን ያኛው ነበር፡፡ እናማ…ምን መሰላችሁ? ይህኛው ልጅ ትንሽ በአካል ገዘፍ ስለሚል፣ ጸጥታ አስከባሪው ወዲያውኑ ለራሱ “እጅሬው ነው የረበሸው…” አይነት ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር ማለት ነው፡፡
ታዲያላችሁ …አንግዲህ ጨዋታም አይደል… መቼም ዘንድሮ የምታወሩት አትጡ ብሎናል አይደል…ከዚሀ በፊት እንዳወራነው ዝም ብለን ሌላው ላይ የምናፈጥ ሰዎች አልበዛንም! ኮሚክ እኮ ነው…በፊት እኮ የሆነ ሰው ካፈጠጠባችሁ ወይ በአለባበስ፣ ወይ በሆነ ነገር ለየት ያለ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ቀሚስ መስሏት መሀረቧን እላዩዋ ላይ ጣል አድርጋ የወጣች እንትናዬ ቢያፈጡባት…አለ አይደል… “ተፈጥሮ ነው፣ ምን ማድረግ ይቻላል!” ምናምን ሊባል ይችላል፡፡ (ልጄ ከስንቱ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀን ባለንበት ሰዓት ‘ከባዮሎጂ’ ጋር ተጣልተን የጠላት ቁጥር አናበዛም፡፡) ቂ…ቂ…ቂ…
ዘንድሮ ግን ነገሮች እየተለወጡ ይመሰላል:: አይደለም ሌላ ሰው አፍጦ ሊያያችሁ ይቅርና ራሳችሁ ራሳችሁን ኮስተር ብላችሁ ለማየት የሚያስገድድ ምንም ነገር በሌለበት፣ ያ እዛ ጥግ፣ የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ የተቀመጠ ሰው ያፈጥባችኋል፣ ከመንገድ ማዶ እንትናዋን የምትጠብቅ የምትመስል እሷ ደግሞ ዓይኖቿን የተከለችው ሳይሆን ኤድና ሞል፣ አቫታርን ‘ያለ መነጽሩ’ የምታይ ነው የምትመስለው፡፡ አስቸጋሪ እኮ ነው፡፡ እናላችሁ…እንደው ከሚገባው በላይ አፍጥጦ ከሚያያችሁ ጋር ሁሉ “ምን ታፈጣለህ!” የምትባባሉ ከሆነ…አለ አይደል….ዳማ ከሴና ድንገተኛ ከአጠገባችሁ እንዳይጠፋ፡፡ የየቀኑን ‘ሆድ ቁርጠት’ አትችሉትም፡፡ በየቀኑ ሆድ ቁርጠት ከሚለቁብን ነገሮች የምንገላገልበትን ጊዜ ያፍጥንልንማ!
ጠብ ያለሽ በዳቦ በዛብንሳ!   
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1948 times