Saturday, 22 February 2020 10:43

የሬድዮ ዲስኩር

Written by  ደ. በ
Rate this item
(9 votes)

      ቀን ሬድዮ ላይ ስሰማው ድንቅ ሆኖብኝ  እንደ ምንም አየር ላይ ሃሳብ ለመስጠት ሞከርኩኝ፤ ስልክ መስመር በማጣቴ ግን አልቻልኩም፡፡ የምችለውን አድርጌ ስላልተሳካ፣ የወዳጄን ቁጥር አውጥቼ መደወል ግድ ሆነብኝ፡፡
የሚያወሩት ነገር አንገብጋቢና ለሃገር የሚጠቅም በመሆኑ ተመስጬ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ለኪነ-ጥበብ ሰዎች ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱ ጋዜጠኞች እየተቀባበሉ ሲያስኬዱት በእውነት ኮራሁ፤ የዚህ ዐይነት ስሜትና ልብ ቢኖረን፣ ሃገራችን የት ትደርስ ነበር!
የኮፒ ራይት ነገር፣ የሃገራችንን ጥበብ አጥንቱን ቆርጥሞ ያሽመደመደና የጥበቡን ሰዎች ተስፋ አስቆርጦ ከሜዳ ያስወጣ በመሆኑ ልቤ ሁሌ እንዳዘነ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ቁስሉ ላይ መድሃኒት አርከፈከፉበት፡፡
አድማጮች እየደወሉ መረጃ ሲጠይቁ፣ በቆራጥነት የሚመልሱት መልስ፣ እጅግ አርኪና ተጨባጭነት ያለው ስለነበር፣ በዚያ አሳማኝ ሃሳብ ልቡ የማይነካ አልነበረም፡፡ በየሬድዮው ደውለው ስማቸውን ለመስማት ሱስ ያለባቸው ተርታ አድማጮች ብቻ ሳይሆኑ፣ የጥበቡ ባለቤቶች ሳይቀር ስልክ እየደወሉ፣ በስሜት እንባ ሲተናነቃቸው ሰማሁ፡፡ የወዳጄ ቁጣ ለጉድ ነበር፡፡ በዚህ ዐይነት ሌብነትና ግፍ ሃገራችን አትዘልቅም!›› እያለ ቀጠለ፡፡ እንደዚህ ሃይለኛ አይመስለኝም ነበር፡፡ ማስጠንቀቂያ አየሰጠ ዳግም በጥበብ ስራዎች መቀለድ የሚፈልጉትን ተረባርበን እናጋልጣለን›› በማለት ዛተ፡፡
ቀጥሎም ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያለውን ሙዚቃ ጋበዙ፡፡
እኔ በዚህ መሃል በውስጥ ስልክ ደወልኩ፡
‹‹ሄሎ››
‹‹አቤት አቤት››
‹‹ድንቅ ነው! ድንቅ ነው!››
‹‹ግድ ነዋ! ግድ ነው! መጋፈጥ አለብን፣ ያደረግነው መሆን ያለበትን ነው››
‹‹በጣም ኮርቻለሁ፤ ሀገር መውደድ የሚገለጠው በዚህ ነው››
‹‹በትክክል! ሙስና ሰማይ ሲነካ እኛም ከፍ ብለን መከላከል አለብን››
‹‹በጣም ደስ ስላለኝ ነው የደወልኩት››
‹‹የሚደወለውን ስልክ ልነግርህ አልችልም‹‹
‹‹ስራችሁ ከዚያም በላይ የሚያሰኝ ነው››
‹‹አመሰግናለሁ ወዳጄ፤ ማምሻ እዚያችው ካፌ እንገናኝና እንጫወታለን››
‹‹መልካም ወንድሜ፣ እናትህ እንኳን ወለደችህ››
ስልኩን ዘጋሁትና አሰብኩ፤ እዚህ ሃገር እርስ በርስ መካካብ ወይም በጠላትነት መጠፋፋት እንጂ ለሃገር ማሰብ ቀርቷል፡፡ ይህ ወዳጄ ግን የጥበብና የሃገር ነገር ልቡን ነክቶት ሲቃጠል መስማት አንድ ተስፋ ነው:: ይህ ልብ ቢበዛና ለእውነት ብንቆም የት በደረስን ነበር!! እላይ ፓርላማ ካለው ጀምሮ ለሆዱ እያጨበጨበ በሚኖርባት ሃገር፣. የዚህ ዐይነት መቆርቆር ማዳመጥ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡
ጋዜጠኛውም ቢሆን ወይ ለዝና ወይ ለሽቀላ ካልሆነ ለሃገር መች ግድ ይለዋል! ሁሉም ለሆዱ ነው፡፡ ሰው ትራፊኩና ፖሊሱ ላይ ጣቱን ይቀስራል እንጂ ሌባ ያልሆነ ማነው! መምህሩ ሳይቀር ኤ እና ቢ የሚሰጠው የሴት ገላ ጉቦ እየተቀበለ ሆኗል:: ታዲያ የዩኒቨርሲቲው ሰውዬ ይህንን ካደረገ ፖሊሱ ምን ያድርግ? ሰዎቹ እንዳሉት የበሰበስነው ከላይ ነው፡፡
ጋዜጠኛ ከሆኑ አይቀር እንደ ደምስሰው ነው፡፡
ዛሬ ራቱን መጋበዝ ያለብኝ እኔ ነኝ፡፡ ብዬ አሰብኩ፡፡ ማበረታታት አለብኝ፡፡ ጥሩ የሰሩ ሰዎችን ያለማበረታታት ሌሎች ሰዎች ለበጎ ነገር እንዳይተጉ አድርጓል፡፡ ስለዚህ እኔም ከነርሱ በጎ ነገር ተነስቼ ከማድነቅ ያለፈ ስራ መስራት አለብኝ፡፡ አድንቆ ዝም ማለት በራሱ ችግር አለበት፡፡
በውሳኔዬ መሰረት ራስ ሆቴል ወስጄ ራት ልጋብዛቸው ሄድኩ፡፡ የመረጡትን እንዲያዝዙ አደረግሁ፡፡ የሚጠጣውንም እንደዚያው፡፡ እየተጨዋወትን በልተን ስናበቃ ደስ አለኝ፡፡ ከዚያም ራይድ ጠርቼ፣ እኔ ወደ ሰፈሬ ወደ ካዛንቺስ አቀናሁ:: እነርሱም በበድሉ ህንጻ በኩል ውስጡን ሔዱ፡፡
እኔ ግን ትንሽ እንደሄድኩ ባለቤቴ ያዘዘችኝን ትዕዛዝ ረስቼ ነበር፡፡ ልደታ ሄጄ ከአሹ ስጋ ቤት ለክትፎ የሚሆን ስጋ መግዛት ነበረብኝ፡፡ ለሾፌሩ ነገርኩት፡፡ ስጋ ገዝተን ስንመለስ፣ ሁለቱ ጋዜጠኞች ቨርጂን ካፌ ተቀምጠው ሻይ እየጠጡ ነበር፡፡ ቆም ብለን ስናመነታ ድንገት አንድ ድምጽ ጆሮዬ ጥልቅ አለ፡፡ ባለ ሲዲውን እየጠሩት ነው፡፡ ምን ሊያደርጉ ነው ብዬ አየሁ፡፡
ስም እየጠየቁ የተለያዩ ዘፈኖችን ገዝተዋል፡፡
ልጁ መንገድ ሲሻገር ጠራሁት፤ ዘርዝሮ ነገረኝ፡፡ ብዙ ሲዲ ገዝተውታል፤ራሴን አመመኝ፡፡ ይቺ ሃገር ብዬ አፌ ያመጣልኝን ተሳደብኩ፡፡
የታክሲው ሾፌር በመገረም ‹‹ይህ ምን አዲስ ነገር አለው?!›› አለኝ፡፡
ዝም አልኩት፤ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ እኔም ችግር አለብኝ፡፡ እዚህ ሃገር ማድረግ እንጂ መናገር ብርቅ እንዳልሆነ እያወቅሁ የተሳሳትኩት እኔ ነኝ፤ ብዬ ራሴን ወቀስኩ:: አንዱም ችግር ፈጣሪ በወሬ የሚንሳፈፈው ነው፡፡
“ወዳጄ ንዳው!!”
ለእራት ያወጣኋት ብር ከነከነችኝ፡፡ ሌባ ጋበዝኩባት፤ድንቄም ጋዜጠኛ11

Read 2190 times