Saturday, 29 February 2020 10:47

“እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አባትና ልጅ ስለ አንድ ስላስቸገራቸው ጅብ ይወያያሉ፡፡
አባት - እኔ የምልህ የኔ ልጅ ይሄ የሠፈራችን ጅብኮ ለያዥ ለገራዥ አስቸገረ፤ ምን ይሻላል?
ልጅ - አባዬ፤ እኔም ግራ ገብቶኛል
አባት - እንዴ በቅርቡ ጋሼ ታደሰ ግቢ ገብቶ አንድ ጊደር ወሰደ፡፡ ባለፈው ሰሞን የባሻ እንዳይላሉን ጥጃ ቦትርፎ ሸሸ፡፡
ልጅ - ለምን የሠፈሩን ሰው አስተባብረን ወጥመድ አበጅተን፤ አጥምደን አንጠብቀውም?
አባት - ሰው መቼ ይተባበራል? ገና እርስ በርስ ከመዘራረፍ ያልወጣ ህዝብ መቼ ተሰባስቦ የረባ ሥራ ይሠራል?
ልጅ - ግዴለህም አባዬ “ለአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ” ይባላል፡፡ እንስማማና መላ እንምታ!
አባት - ይሁን ካልክ ከታች ሰፈር አብዬ ገለታን፣ ከላይ ሰፈር እትዬ ቦጌን፣ ከመካከል አቶ ውርጌሣን እንይዝና አንድ ዘዴ እንዘይድ?
ልጅ - አባዬ፤ እኔ አሁኑኑ ሄጄ እጠራቸዋለሁ፤ አለና ወደ አብዬ ገለታ፣ እትዬ ቦጋለችና አቶ ውርጌሣ ቤት ሄዱ፡፡ ሶስቱ ሰዎች ተሰባሰቡና ምን ብልሃት እንደሚያበጁ ተወያዩ፡፡
አቶ ውርጌሣ አንድ ዘዴ ታያቸውና
“እኔ አንድ ፍቱን መፍትሔ ታይቶኛል” አሉ፡፡
እትዬ ቦጌ፡-
“ምን ታየዎት?”
አቶ ውርጌሣ፤
“እኔ ጠመንጃ አለኝ አደለ?”
“እንምታው እንዳይሉ ብቻ?”
“አይደለም፡፡ ለጅቡ ወጥመድ እንስራ”
“እንዴት?”
አቶ ውርጌሣ፤
“እኔ የታየኝ፤ ጠመንጃዬ አፈሙዝ ላይ ሙዳ ሥጋ እናስቀምጥና፤ ሙዳውን በገመድ አሥረን ገመዱን ከጠመንጃዬ ቃታ ጋር እናያይዘው፡፡ ከዛ ጅብ ሆዬ ሥጋውን አገኘሁ ብሎ ሲጐትት ቃታውን አብሮ ይስበውና ያልቅለታል!”
ሁሉም ዘዴው ደስ አላቸውና
“ይሁን! ይሁን! ይሁን!” አሉ፡፡
ሙዳው ከጠመንጃው አፈሙዝ ጋር ታሠረና ጅቡ የሚያዘወትርበት በረት ፊት ለፊት ተጠመደ::
ልጅ “በል ውጤቱን ጠብቅ  ተባለና ይጠብቅ ጀመር፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ አባቱ ሲሮጥ ይመጣና፤
“አባዬ ጉድ ሆነናል”
“እንዴት? ምን ተፈጠረ?”
“ጅቡ ጠመንጃችንን ይዞት ሄደ”
“እንዴት አድርጐ?”
“ጠመንጃውን በአፈሙዙ በኩል ሳይሆን በሰደፉ በኩል ነክሶ ይዞት ሮጠ!”
አባትም፤
“አዬ ጉድ! እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው!” አሉ ይባላል፡፡  
የአገራችንም ችግር ይሄን መሳይ ነው፡፡ ለአንዱ ያጠመድነው መልሶ ለራሳችን ወጥመድ ይሆንብናል፡፡ ባለ ቀረርቶ ፎካሪ አለው እንደተባለው ይሆናል ማለት ነው፤ ፎካሪው የሚከተለውን አለ አሉ፡-
‹‹ላይተኩስ ላይመታ
ፎካሪው በረታ
ጥይቱ አግድም ሲሄድ ተኳሹ ሳይነቃ
ኢላማው ሳይሰምር አላሚው ተጠቃ
መሣሪያው ሳያብል ጥይቱ ሳያንሰው
እንዴት ልሙት ብሎ እጁን ይሰጣል ሰው?!››
ላንመታ የምናልመው ብዙ ነው፡፡ ሁለት አይናችንን ጨፍነን እንደ መተኮስ ያለ የእውር የድንበር ጉዞ ነው። ይልቁንም በደምብ አልመንና በሚገባ አውጠንጥነን፤
‹‹አለ አንዳንድ ነገር
አለ ብዙም ነገር
‹‹እኛ መላው ጠፍቶን ስንደነጋገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር››
እንዲል መጽሐፍ፣ ጠንቀቅን አስተውለን እንጓዝ፡፡ የወጣቱን በባዶ መንከራተት እናስብና ከሁሉም በፊት በወጣቱ ላይና ከወጣቱ ጋር እንስራ፡፡ ከትምህርቱ ተፋቶ ያላአንዳች መላ፣ ለቤተሰቡና ለአገሩ ሸክም እየሆነ እንደመጣ እያደርም ከድጡ ወደማጡ እየዘቀጠ እየመጣ መሆኑን ሳንሸነጋገል እንወያይበት፡፡
የትምህርቱ ሁኔታ አሳሳቢ ነው!
የጤናው ሁኔታ አሳሳቢ ነው! ነገ የሚያልፈው ለመጪው የረባ ቅርስ ሳይተው በዋል ፈሰስ ትውልድ ሆኖ እንዲቀር ማድረጋችንን ከልብ እናስብ፡፡ አስፋልት ብለን የሰራነውን መንገድ በነጋታው ሲፈርስ እያየን ‹‹ዱሮም ሹሮ ፈሰስ ነበርኮ!›› እያልን እያሾፍን እስከ መቼ እንገፋለን? በራሳችን እያፌዝን በመንግሥት እያላከክን፣ ተስፋችንን እያጨለምን፣ አገር እየገደልን የቱን የሕይወት ልምላሜ እንጠብቃለን?! እስከ መቼስ መንገዳችን ቁልቁል እያንደረደረን እንዘልቀዋለን? ጎበዝ ሕልውናችን ጥያቄ ውስጥ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ዝም የማይባሉ በርካታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሳንካ መናኸሪያ እየሆንን እየመጣን መሆኑን ለአፍታም አንርሳ፡፡ ለወትሮው  Silver is Golden/ዝምታ ወርቅ ነው/ እንል ነበር፡፡ እየዋልን እያደርን ስናየው ግን ዝምታችን ወርቅ አይደለም! አይበጀንምም፡፡ ኤሊ አዝግማ ጥንቸልን መቅደሟ ዛሬ ተረት ነው፡፡ ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም የሚለውም አባባል ዛሬ ተረት ነው፡፡ ጉዳያችንና ጉዟችን ሁሉ Boumerang ‹‹አንጋጠው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ›› እንዳይሆን ከትላንት እንማር፡፡ ዛሬን እንገንባ፡፡ ነገን ከዛሬ እንጀምረው፡፡ አናመንታ ቆርጠን መጓዝ የነገን ሙሉ ልብ ይፈጥርልናል፡፡ ሕልማችንን እውን ለማድረግ እንትጋ! የነገው ብርሃን ከዛሬው ጨለማ አብራክ መወለዱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ግን ልባችንን ካላጨለምን ነው!
አለበለዚያ አባትየው አሉ እንደተባለው ‹‹እንኳን ጠመንጃ ሰጥተኸው እንዲሁም አልቻልነው›› ይሆንብናል! ጠንቀቅ እንበልና ነገን ከዛሬ እንገንባው!!Read 13464 times