Saturday, 29 February 2020 11:38

ነፃነት ፍለጋ!…

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(18 votes)

  ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ነው፡፡ ስምረት ግማሽ ገላዋ በቀዝቃዛ አየር እየተዳበሰ፣ ከአልጋው ላይ ሆና፣ የአራት አመት ወዳጇን በናፍቆት አይን እያየችው ነው:: ሀይላብ ልብሱን በፍጥነት እየቀያየረ ነው:: ከውጭ የመኪና ክላክስ ድምፅ ይሰማል:: ሀይላብን የሚጠብቀው መኪና ነው፡፡ ልብሱን ቀያይሮ ከጨረሰ በኋላ ሁሌም እንደሚያደርገው፣ ከአልጋው ስር በርከክ ብሎ በስስት የምትመለከተው ፍቅረኛውን ደግሞ የማያገኛት እስኪመስለው ድረስ ትኩር ብሎ ተመለከታት፡፡ እጆቿን አውጥታ ፊቱን እየዳበሰች ታዋራው ጀመር፡፡
‹‹የት ድረስ እንድወድህ ትፈልጋለህ?›› የምሩዋን ነው የጠየቀችው፡፡ የት ድረስ እንደምትወደው ልታውቅ አልቻለም:: እንዲነግራት ፈልጋለች፡፡ የት ድረስ ብትወደው ነው ያፈቀረችው የሚመስላት፡፡ ጥያቄው ለሱ አልነበረም… ለራሷ ነው፡፡
ፈገግ እያለ መለሰላት… ‹‹ለጊዜው እስከ ዲላ ድረስ ውደጂኝ፡፡ የሚቀጥለው የመስክ ሥራዬ ደግሞ ሲመጣ ርቀቱን እያየን የምንወስነው ነገር ይሆናል፡፡››
ስምረት ያኮረፈች መሰለች፡፡ የመኪናው ጡሩንባ ከስምረት ጥያቄ በላይ ጎልቶ መሰማት ጀመረ። ሀይላብ የስምረትን ግንባር በጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሳመው፡፡ ደግሞ አይኖቿን ተመለከታቸው፡፡
‹‹መሄድ አለብኝ ሳምሪ፡፡ ከዲላ ስመጣ ሰርፕራይዝ ነው የማደርግሽ፡፡ እመኚኝ ልዩ የሆነ ስጦታ ነው የሚመጣልሽ፡፡ አንቺ ደግሞ ምን አድርገሽ እንደምትጠብቂኝ አላውቅም::››
‹‹እጠብቅሀለሁ…›› ይህን ብቻ አለችው፡፡ ሀይላብ ከተንበረከከበት ተነስቶ ሻንጣውን በመያዝ በሩን ከፍቶ ለመጨረሻ ጊዜ በፈገግታ ሲያያት ከቆየ በኋላ ወደሚጠብቀው መኪና ጉዞውን ማድረግ ጀመረ፡፡
ስምረት የዛን ለሊት እንቅልፍ ሳትተኛ አደረች፡፡ አዕምሮዋ ውስጥ እንደ ቀልድ ዘርታው ጊዜውን ጠብቆ የበቀለ የአሜሄላ ተክል አድጎ ያለ ጊዜው ህሊናዋን መጠረቋቆሱን ጀምሯል፡፡ አይኖቿ ላይ የነበሩት በራስ የመተማመኛዋ መንፈሶች ጥለዋት በረዋል፡፡ ሀይላብ እስካሁን ድረስ እንዴት እንዳልተመለከተው ግራ ገብቷታል::
ሀይላብና ስምረት ከአራት ዓመት በፊት፣ አራት ኪሎ የሥራ ማስታወቂያ ሊመለከቱ ሲመጡ ነው የተዋወቁት፡፡ እንደ አጋጣሚ ሀይላብ ሪፖርተር ጋዜጣ ገዝቶ ነበርና፣ ከፖስታ ቤቱ ደረጃ ስር እያነበበ ባለበት ወቅት ላይ ስምረት ቀስ እያለች እሱ በገለጠው ቁጥር፣ ለሷ የሚሆናትን ማስታወቂያ ስትመለከት፣ ሀይላብ አስተውሎ፣ አብረው ማንበብ እንደምትችል ነገራት፡፡ የዛን ቀን አብረው አደሩ፡፡ ሁለቱም ተከራይተው ስለወጡ ነፃነታቸው ላይ የሚደነፋባቸው የትኛውም የቤተሰብ አባል አልነበረም:: ሁለቱም ፍርሀት የሚለቅ መለያየትን የሚያወግዝ ነፍስ እየዘሩ፣ ሕይወትን የሚያጭዱበትን የፍቅር አጥር በዙሪያቸው ሰፍተው ጨረሱ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሀይላብ ለስራ ተጠራ፡፡
ሀይላብ ሥራ እንደተቀጠረ የነገራት ቀን ላይ አብራው እንድትኖር ጥያቄ አቀረበላት፡፡ በደስታ ተቀበለችው፡፡ እውነት አልመሰላትም ነበር፡፡ አንድ ቀን ምን ነበር ያደረኩት? ብላ ራሷን እንደምትጠይቅ፣ የት ነው ያለሁት? ብላ በፍቅር የታወሩ አይኖቿን ከፍታ ዙሪያዋን ማየት እንደምትጀምር አላወቀችም ነበር፡፡
መጀመሪያ ላይ ሀይላብ አይኖች ውስጥ ባየችው የፍቅር ውቅያኖስ፣ እንደ ሀይማኖት ተቀብላው ነው ልትሰምጥበት ካለችበት ከፍታ ላይ ተንደርድራ ዘላ የገባችበት፡፡ ሀይላብ የሹፍርና ስራውን ሲያገኝና ቢያንስ በየሁለት ወሩ አንድ ጊዜ የመስክ ስራ ወጥቶ ገንዘብ ይዞ ያለ ሀሳብ እንደሚያኖራት ስትገነዘብ፣ ከምታውቃቸው ሴቶች ከፍ ያለ ልዕልናዋን ያገኘች ነበር የመሰላት፡፡ መጀመሪያ ምንም እንኳን ሀይላብን በአመት ውስጥ የተወሰኑ ጊዜያትን ብታገኘውም እያኖራት መሆኑ ብቻ ተስፋ እንደሚሆናት ታምን ነበር፡፡ ህሊናዋ ገነት፣ የሀይላብ ፍቅር ደግሞ ሀይማኖቷ ነበሩ፡፡ አሁን በለምለሙ የገነት ምድር ላይ አሜሄላው ማንነቷ ግዛቱን አስፍሯል፡፡
ጠዋት ላይ ነቅታ ለረዥም ሰዓታት ያለ ምንም ሀሳብ፣ አልጋው ውስጥ ሆና ከርቀት ብፌው ላይ ሊወድቅ ብሎ ጫፍ ላይ በጣር የቆመውን የእሷንና የሀይላብን ፎቶ ስትመለከት ቆየች፡፡ እንዲሁ የሆነ… እስከ ዛሬ ድረስ እያባበለና በተስፋ መሰላሉ ያሻት የሀሳብ ሁለንተና ውስጥ እንድትመላለስ የሚያግዛት መንፈስ ከላይዋ ላይ እንደ ደረቀ ቁስል እየተላጠ ሲነሳ ይታወቃታል፡፡
ከመኝታዋ ውስጥ ወጥታ ስልኳን ይዛ ራቁቷ በክፍሏ ውስጥ እንዳበደ ሰው ትመላለስ ጀመር፡፡ እንዲህ ሲያደርጋት ዛሬ ላይ አንድ አመት ተኩል ሆኗታል፡፡ አንዲት ውሳኔ የመወሰን ምጥ ውስጥ ናት፤ ስልኳን አንድ ጊዜ ቆም ብላ ተመለከተችው:: በጨለማው አይኑ የሚመለከታት ስልክ ውስጥ ያ ልጅ እየታያት ነው፤ ሀይላብን ያልሆነው፣ እንደ ሀይላብ ሁሉ ብድግ እያለ ወደ ሌላ አገር የማይሄደው ከሀይላብ አቋም በላይ በሴት ተስፋና በአማልክቶች ጉልበት ተላቁጦ የተበጀ የመሰለ መልክና ሰውነት ያለው፤ በፌስቡክ የተዋወቀችው፡፡ ማበላለጥ መብቷ እንደሆነ ገባት፡፡
የስልኩን ፓተርን ከፈተችው፤ ኢንተርኔት አበራች፤ ፌስቡክ ከፈተች፡፡ ጌች ሀበሻ የሚል ስም ከቻት ሳጥኑ ውስጥ በአይኖቿ ማስና አገኘችው፡፡ ደስተኛ ሆነች፡፡ ባዶ ቤት ውስጥ ድምጿን ከፍ አድርጋ ሳቀች:: የሀጥያት ብዕሯ እዛው ስልኩ ላይ አለ፡፡ መልዕክት ጻፈችለት::
‹‹ዛሬስ ልታገኘኝ አትፈልግም? ዛሬ ጥሩ ቀን ነው፡፡ ከቤት መውጣት እችላለሁ… ምን ይመስልሀል?››
የቻት ሳጥኑ ውስጥ የላከችው መልዕክት እንደታየ የሚጠቁም ጽሑፍ ተመለከተች:: ቅብጥብጥ እያለች አልጋዋ ላይ ተቀምጣ መልሱን መጠባበቅ ጀመረች፡፡ ፌስ ቡኳ ላይ ያለው ፎቶ የእሷ አይደለም፡፡ የጓደኛዋን ነው ያደረገችው፡፡ ሀይላብ ስልክ ጉርጐራ ላይ ከባድ እንደሆነ ስለምታውቅ በተቻላት መጠን መረጃዋን ለመሰወር ጥረት አድርጋለች፡፡ ሆኖም ጌች ባደረገችው ነገር ግራ እንደማይጋባ ተስፋ አሳድራለች፡፡
‹‹ለኔም ለመገናኘት ጥሩ ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት እናድርግ?›› መልዕክቱ ገባ፡፡ ምላሹ አስደሰታት፡፡
‹‹ወደ ከሰዓት እንገናኝ?? ምናልባት ፀሐይ በረድ ሲል??›› በፍጥነት ላከችለት፡፡
ጌች በጥልቅ እያጠናት የሚመልስ ይመስላል፡፡ አሁንም ከሆኑ አመታት ከመሰሏት ደቂቃዎች በኋላ መልሱን ላከላት::
‹‹ወደ ካሳንችስ መምጣት ትችያለሽ?››
‹‹እችላለሁ… የምመጣው ግን ወደ ቤቴ የምታደርሰኝ ከሆነ ነው?››
‹‹መጠጥ ትጠጫለሽ?›› ጥያቄው አሽኮረመማት…
‹‹ያለሁበት ሙድ ይወስነዋል፡፡ እጠጣለሁ ብዬ ግን ቃል አልገባልህም፡፡››
አስራ ሁለት ተኩል ላይ… የሚገናኙበትን ሆቴል ነግሯት… ከኢንተርኔቱ ወጣ፡፡
ከጠዋት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ያሏትን ልብሶች እያወጣች፣ በመልበሻ መስታወቷ ፊት ቆማ መኳኳል ያዘች:: ሁሉንም ልብሶቿን ቢያንስ አራት አራት ጊዜ እያወለቀች ስትቀይራቸው ነበር:: አራቱም ሙከራ የላይዋን ገጽታ እንጂ ስትጠብቀው የነበረውን የመንፈስ እረፍት ሊሰጣት አልቻለም፡፡ መጨረሻ ላይ ደከማትና አልጋዋ ላይ ተደፍታ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች:: ሀይላብን ልታስበው ፈለገች… አዕምሮዋ ውስጥ ዘልቃ የተረፈ… አንድ ቀን ምናልባት ብላ ያስቀመጠችው የሀይላብ ፍቅር ካለ፣ ባቀረቀረችበት ሆና ለማሰብ ሞከረች፡፡ ሀይላብን ልታገኘው አልቻለችም:: ካላፈቀረችው ደግሞ ያሁኑ ውሳኔዋ ጽድቅ ሆኖ እንደሚቆጠርላት ገምታ፣ እንባዋን ጠራርጋ፣ ከአልጋዋ ተነስታ ለመጨረሻ ጊዜ መልኳን በመስታወት አይታው ወጣች፡፡
ካሳንችስ የቀጠራት ሆቴል ደረሰች፡፡ ሰዓቱ ገና ነው፡፡ አስራ ሁለት ከሩብ ይላል:: ምን እንደምታደርግ ግራ ገባት፡፡ ቀድማው መጥታ ልዩ ፍላጎት ያሳየች እንዳይመስለው አስባ ነበር… ሆኖም… የራሱ ጉዳይ አለች፡፡ ወደ ሆቴሉ ገባች፡፡
ሆቴሉ የሚያምር ነው፡፡ ሀይላብ እንደዚህ ያለ ዘመናዊ ቦታ ይዟት መጥቶ አያውቅም ነበር፡፡ በራሷ ቀናች፡፡ ልዕልት የሆነች መሰላት፡፡ የሆነ ስለ እሷ ብቻ እያሰበ የሚውል ወንድ  ልትተዋወቅ ነው:: ምናልባትም አስሮ እየጎተታት ወዳለው እውነተኛው የእድሜዋ የሀሳብ አቀበት ላይ ለመድረስ የጌች መምጣት ወሳኝነት አለው፡፡ ገና ልጅ ናት፤ ብዙ ሕይወት ከሚያተራመሰው ከተማ ውስጥ ሳትቃርም፣ አንድ ቤት ውስጥ ተቀርቅሮ መዋሏ ድንገት እየመጣባት ይረብሻት ነበር:: ሰዓቷን ተመለከተች… ሁለት ሰዓት ተኩል ይላል፡፡ በበሩ በኩል ግን ዝር የሚል የአዳም ዘር አይታይም፡፡ ከፍተኛው ደስታ ላይ ለመድረስ መጀመሪያ ከፍተኛውን ጭንቀት ማለፍ እንዳለባት ሕይወት አስተምራታለች… ሕይወት ግን ሁሌ ልክ ትሆናለች?
በማታውቀው ሰው ናፍቆት እየበሰለች ያለችበት ወቅት ላይ አንዲት ሴት መጥታ ከፊት ለፊቷ ተቀመጠች፡፡ ስምረት ግራ እየገባት እንግዳዋን ሴት በእንግዳ ስሜት ውስጥ ሆኖ ልታናግራት ሞከረች፡፡
‹‹የኔ እህት፤ ቦታው ተይዟል፡፡ የምጠብቀው ሰው አለ፡፡››
‹‹ብዙ ግራ አላጋባሽ ስምረት…››
ስምረት አላስጨረሰቻትም፡፡ ጉንጮቿ በንዴት ደም እንዳረገዙ ለእንግዳዋ ሴት ጥያቄ ወረወረችላት፡፡
‹‹ስምረት ነው ያልሺኝ? የት ታውቂኛለሽ?›› ጥያቄዋ እንዳላለቀ ብታውቅም፣ ከዚህ በላይ ንዴቷ ሊያስወራት አልቻለም፡፡ እንግዳዋ ሴት የስምረትን ንዴት በተረጋጋ መንፈስ አንብባ ከጨረሰች በኋላ በተረጋጋ መንፈስ መናገሯን ቀጠለች… ‹‹እስካሁን ተቀምጠሽ ስትጠብቂው የነበረው ሰው… ጌች አበሻን ሳይሆን እኔን ነው፡፡››
‹‹ምን?›› ስምረት ሰውነቷ እንደ መንቀጥቀጥ እያደረገው ለመጠየቅ ሞከረች::
‹‹ስምረት ምርጫ ተሰጥቶሽ መርጠሻል:: በሙሉ ተስፋም ምርጫሽን አክብረሽ እንደመረጥሺው አልጠራጠርም፡፡ ምን ያህል ለውሳኔ እንደምትቸኩይ ባውቅም ይሄን ውሳኔ ለመወሰን ግን ጊዜ ፈጅቶብሽ ነበር፡፡››
‹‹ይቅርታ የኔ እህት፤ ሌላ ስምረት ልትሆን ትችላለች… እኔ የምትያት ሴት አይደለሁም:: እናም ከከባድ ይቅርታ ጋር እየጠበቅኩት  ያለሁት ሰው ስላለ ከዚህ ተነስተሸ ሌላ ሰው ፈልገሽ ረብሻሽን ብትቀጥይ ነው የሚያዋጣሽ፡፡ እውነቱን ተናገሪ ካልሺኝም በአሁን ሰዓት በጣም እየተናደድኩብሽ ነው ያለሁት፡፡››
ስምረት በለቀቀችው የመብረቅ ስለት ልክ የሚስተካከል ንግግር ከእንግዳዋ ሴት ተወረወረባት…
‹‹ከሀይላብ ጋር ልንጋባ ስንጠብቅ የነበረው ያንቺን መልስ ነበር፡፡››
‹‹ምን…?›› ስምረት ከተቀመጠችበት ተነስታ አፈጠጠችባት፡፡
እንግዳዋ ሴት ግን መልኳ ላይ ምንም አይነት ድንጋጤ ሳታሳይ ቀና ብላ እየተመለከተቻት ንግግሯን ቀጠለች፡-
‹‹ከሀይላብ ጋር የአንድ አመት ከሩብ የሚሆን የፍቅር ጊዜ አሳልፈናል፡፡ የሚደንቅሽ ግን ሁሌም የሚያወራው ስላንቺ ነው፡፡ የሀሳቡ መክፈቻና መዝጊያው አንቺ ነበርሽ፡፡ ሆኖም አንቺ ማን እንደሆንሽ ላውቅ አልቻልኩም፡፡ በያንዳንዱ የወንድ ነፍስ ውስጥ እንደ  አለት ጠንክሮ ከህሊናቸው ውስጥ የሚዘምን የራስ ወዳድነትና የእኔነት ስሜት እንዳለ አጥብቄ ስለማውቅ፣ ሀይላብን መልሼ ላንቺ ከማስረከቤ በፊት አንቺ ማን እንደሆንሽ ለማወቅ ሙከራ ማድረግ ጀመርኩኝ፡፡ ሀይላብ እጅግ ምስኪን መሆኑ ስለገባኝም፣ ነፍሱን ከየትኛዋ ሴት ልብ ውስጥ ገድሎ እንደቀበረው ለማጥናት ሞከርኩኝ…››
ስምረት ፊቷ ላይ የተረበሸ የደም ፏፏቴ ሲመላለስ የጉንጮቿን ቆዳ ተመልክቶ ማወቅ ይቻላል፡፡ ልታወጣቸው ያሰበቻቸው ቃላቶች ከልቧ እየተነሱ ጉሮሮዋ ውስጥ ሲመክኑ ሿእየታወቃት የቻለችው ያህል አምጣ ልትጠይቃት በአንደበትዋ ቃተተች… ‹‹እና ጌች ማለት…››
እንግዳዋ ሴት ከተቀመጠችበት እየተነሳች መለሰችላት…
‹‹አዎ… ጌች ሀበሻ እያልኩኝ ሳናግርሽ የነበርኩት እኔ ነኝ፡፡››
‹‹መልኬን እንዴት አወቅሺው? ፌስ ቡኩ ላይ ራሱ ፎቶዬን አልጫንኩትም ነበር እኮ…››
‹‹በትክክል… ሆኖም ቅድም እንዳልኩሽ ነው፡፡ ስላንቺ ለአንድ ዓመታት ያህል በሀይላብ ስሰበክ የከረምኩ ሰው ነኝ፡፡ እመኚኝ… ራስሽን ከምታውቂው በላይ ነው እኔ የማውቅሽ፡፡ እናም ስምረት… ካሁን በኋላ ለዘመናት ታስራ ከለታት አንድ ቀን ለቅሶዋ ተሰምቶላት ከእስር እንደተለቀቀች አይነት ወፍ ነሽ፡፡ ወዳሻሽ መብረር ትችያለሽ…››
ስምረት እንባ ያረገዙት አይኖቿ እንዳያምጡ እየታገለች የመጨረሻ ጥያቄዋን ጠየቀቻት፡-
‹‹እሺ ታዲያ ሀይላብስ… አሁን የት ነው ያለው?››
“እኔ ጋ ነው፡፡ ዛሬ መጥቼም እንደማናግርሽ ያውቃል፡፡ ሁሉንም ነገርሽን ያውቀዋል። ካሁን በኋላ ሀይላብ ያንቺ አይደለም፡፡ አንቺም የሱ ልትሆኚ አትችይም፡፡ ደህና ሰንብቺ ስምረት፡፡››
ስምረትን በቆመችበት ጥላት ሄደች፡፡ ስምረት ለመጮህ ፈልጋ ድምጿን አጣችው:: ለመሮጥ ፈልጋ እግሮቿ አመፁባት ለመተንፈስ ፈልጋ ትንፋሿን ፈራቸው:: ሆኖም በስተመጨረሻ የጎሮሮዋን ቃታ እንደ ምንም አድርጋ ስባው በሀይል ጮኸች.. ድህነቷ ላይ ጮኸች፡፡ ሀይላብ ድረሰ ጮኸች:: ሴትነቷ ውስጥ ብቻ ያለው የእርግጠኝነት መንፈሷና ክብሯ ድረስ እንዲደርስ አድርጋ ጮኸች ፈጣሪዋ ላይ ጮኸች… ጠባቂ መልአኳን ረገመችው… ስምረት… እዛ ድረስ ጮኸች፡፡ ዙሪያዋን ተመለከተች፣ ለማንም የማይታይ ሰንሰለት ነፍሷ ላይ መጠምጠም ሲጀምር ታወቃት፡፡ ያ ሰንሰለት ምን እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባትም… ያ ሰንሰለት ‹‹ነፃነት›› ነው፡፡       Read 2696 times