Saturday, 07 March 2020 12:15

“ሆድን በጐመን ቢደልሉት፣ ጉልበት በዳገት ይለግማል”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የቄስ ትምህርት በመማር ላይ የነበረ ዳተኛ ተማሪ በአንድ መንደር ይኖር ነበር፡፡
ይሄ ልጅ ሰበበኛ ልጅ ነው፡፡ አንድ ቀን አባቱ ልጁ እቤት ተቀምጦ ሳለ ድንገት ይመጣል፡፡ አባት፤
“አንተ?!” አለው በቁጣ፡፡
ልጅ “አቤት አባዬ”
“ትምህርት የለም እንዴ?” እቤት ምን ታደርጋለህ?
“አሞኝ ነው፤ አባዬ”
“ለአስተማሪህ ነግረሃቸዋል - መታመምህን?”
“አልነገርኳቸውም”
“ለምን?”
“እሳቸው አልነበሩም፡፡ “ለቅሶ አለብኝ፤ አጥኑ” ብለውን ሄዱ”
“ዋ! ይሄ ያልከኝ ውሸት ይሆንና ወዮልህ የውስጥ ቆዳህ ወደ ውጪ እስኪገለበጥ ነው የምገርፍህ!”
“ሌሎቹን ልጆች ጠይቃቸው ብትፈልግ”
“እሺ፤ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ውሸት ሆኖ ቢገኝ ግን አንተን አያርገኝ!”
ልጁ ይረጋጋል፡፡ አባቱ እስከ ጐረቤት ጥየቃ ድረስ እንደማይደርስ ያውቃል፡፡
በዚህ ሁኔታ ብዙ ዓመታት ቆይተው አንድ ቀን ልጅ እንደለመደው ቤት ተቀምጦ ሳለ አባት ከተፍ ይላል! ልጅ እያለቀሰ ነው፡፡
“አንተ! ትምህርት የለህም እንዴ? ደሞ ምን ያስለቅስሃል?”
“የኔታ መትተውኝ ነው!”
“ምን አጥፍተህ መቱህ?”
“ኧረ ምንም አላጠፋሁ፡፡”
“ያጠፋኸውማ አለ! ተናገር ዛሬ”
“አይ “ሀ” በል ሲሉኝ እምቢ ስላልኳቸው ነው!”
“ኧ! አንት የማትረባ!” “ሀ” ማለት አቅቶህ ትገረፋለህ?
“አይ አባዬ! የየኔታ ጉዳቸው መች ያልቃል እሺ ብለህ “ሀ” ካልካቸው “ሁ” በል ይሉሃል፡፡ ሁ ስትል ደሞ “ሂ” በል ይሉሃል፡፡ እንዲህ እያሉ እስከ “ፐ” ሊያስለፉኝኮ ነው” አለ ይባላል፡፡
***
መከራን መሸሽ ለባሰ መከራ ሊዳርግ እንደሚችል አለማስተዋል ክፉ አበሳ ነው፡፡
ሲቆይ የማይመረቅዝ ቁስል በጣም ጥቂት ነው፡፡
መንገድ ሲያምር መንገደኛን ይወልዳል፡፡ አብዮት ሲሰምር ቀና አብዮተኛን ያፈራል፡፡ መንገደኛ ሌላ አዲስ መንገድ ይቀዳል፡፡ በአዲሱ መንገድ ላይ አዳዲስ እግሮች ይራመዳሉ፡፡ ያኔ አዲስ ህይወት መጀመሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡
ረዣዥም እግሮች ስላሉን ብቻ በአንድ ጊዜ ረጃጅም እርምጃዎችን አንጀምርም፡፡ የመንገዱን ገጽታ እንመዝናለን፡፡ በመንገዱ ላይ የሚራመዱትን እግሮችም እናጠናለን፡፡ ያጠናናቸውን እግሮች እርምጃ መጠን እንለካለን፡፡ ተፎካካሪ ለመሆን በቂ ምጣኔ እንዳለንና እንደሌለን ግንዛቤ እንወስዳለን፤ አቅማችንንም እናጤናለን፡፡
መንገድ ጀምረን እንግዳ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር አናቋርጠው፡፡ ወይም አንቁረጠው፡፡ ይልቁንም ቆርጠን መጓዝን እናዘውትር፡፡ የቆረጠ እግቡ ይደርሳል ይባላልና!
“መንገድ መንገድ አለኝ፣ ጐዳና ጐዳና
አልግደረደርም ዘንድሮስ እንዳምና”
ያልነው እንዲያው ለዋዛና በዋዛ አይደለም፡፡
የዐባይን ድልድይ ስንገነባ ይሄንን መንፈስ ሳንለቅ ነው፡፡ አለበለዚያ “መብላቷን ሳታቅ እጇን ታጠበች” የሚለው ተረት ይፋጠጠናል፡፡ አንድም “ባሉ ሳይገኝ ሚዜ ታማርጣለች” እንደሚባለው ተምሳሌታዊ አነጋገር ይሆንብናል፡፡ ከስምንት ዓመት በላይ የፈጀው ዐባይ ድልድይ፤ ግብጽን፣ ሱዳንን፣ የታችኛውን ተፋሰስ አገሮች አይን ከሳበ ቆይቷል፡፡ የሀገራችን የለውጥ ሂደት ብቅ ጥልቅ ይወዳል፡፡ ዳር መድረስ እርም ከሆነብን እጅግ ሰነባብቷል፡፡ የአንድ ሰሞን ግርግር የዓለም ፍፃሜ የደረሰ እስኪመስል ድረስ ያጨናንቀናል፤
የአይነ ስውሩ ብጤ ነው
“አይንህ ነገ ይበራልሃል” ቢሉት፤
“ዛሬን እንዴት አድሬ?!” አለ
እንደተባለው ነው፡፡ ማናቸውንም አዲስ ዕቅድ ከማንሳታችን በፊት ሶስት ነገሮችን ማጤን ይገባናል
1/ ባለሙያን መምረጥ
2/ ባለሙያን ማማከር
3/ ዕድሉን ለባለሙያው መስጠት
ከሦስቱም ነጥቦች የምንገነዘበው ባለሙያ የነገራችን ሁሉ ቁልፍ መሆኑን ነው
የጥንቱ ወዳጃችን ሌኒን፤ በኋላም ዶክተር እሸቱ ጮሌ፤
‹‹To day, is have three message: for you
Organize
Organize
Organize”
እንዳለው ነው (በዛሬው ዕለት ሶስት መልዕክቶችን ይዤላችሁ መጥቻለሁ፡፡
ሀ) ተደራጅ
ለ) ተደራጅ
ሐ) ተደራጅ፤ እንደ ማለት ነው)
ዛሬም የተደራጅ ጥያቄ ሁላችንንም ይመለከተናል፤ ያገባናልም፡፡ በራችንን መክፈት ይኖርብናል፡፡ እዚህ ጋ ኑረዲን ኢሳን መጥቀስ አግባብነት ይኖረዋል፡-
‹‹እኔ ምን አገባኝ፣ የምትሉት ሐረግ
እሱ ነው አገሬን፣ ያረዳት እንደ በግ››
ብዬ ግጥም ልጽፍ ተነሳሁኝና፤
ምን አገባኝ ብዬ፣ ቁጭ አልኩ እንደገና፡፡
ዕውነተኛ ጉልበት፣ ዕውነተኛ ዕውቀት፣
ዕውነተኛ ስብዕና ያስፈልገናል፡፡ ያንን አሟልተን ከተገኘን ለለውጥ ራሳችንን አዘጋጀን ማለት ነው:: ለውጥ እፎይታ እንጂ ወከባ አይደለም፡፡ ለውጥ ይስሙላን አይወድም፡፡ ለውጥ ድለላን አይሻም! ምነው ቢሉ፤
‹‹ሆድን በጎመን ቢደልሉት፣ ጉልበት
በዳገት ይለግማል›› ይሏልና!  

Read 14446 times