Saturday, 07 March 2020 12:18

የግብጽ መሪዎችና የአባይ ጉዳይ (ታሪካዊ ዳራ በጨረፍታ)

Written by 
Rate this item
(5 votes)

      --የታሪክ ሰነዶች እንደሚያስረዱት፣ የመጀመሪያው የግብጽ መሪ ኸዲቭ እስማኤል፣ የዓባይ ተፋሰስ አገራትን ‹‹ውሃ›› ለማስገበር ወረራ አድርጓል፡፡ የግብጽ ጦር ሠራዊት አስቀድሞ ሱዳንን ያዘ፡፡ በ1868 ዓ.ም. ከከረን ወደ ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ተመመ:: የኢትዮጵያው ንጉሥ አፄ ዮሐንስ አራተኛ፤ ጦርነቱን መግጠም አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተቻለውን ሁሉ ጥረት አደረጉ፡፡ ጥረታቸው ግን አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ አፄ ዮሐንስ ኅዳር 8 ቀን 1868 ዓ.ም. ማለዳ፣ ጉንዳጉንዲ ወይም ጉንደት ላይ ግብፅን ጦርነት ገጠሙ፡፡ የግብጽ ሠራዊት በኢትዮጵያ ወታደሮች ድባቅ ተመታ፡፡
ለግብጻውያን ሽንፈቱ አልተዋጠላቸውም:: ከአራት ወራት በኋላ ለኢትዮጵያ የመልስ ምት ለመስጠት 25 ሺህ ሠራዊት አስታጠቁና ዳግም ለጦርነት ተሰለፉ፡፡ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለሦስት ቀናት እልህ አስጨራሽ ውጊያ ተደረገ:: አሁንም ጦርነቱ በኢትዮጵያ አቸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ይሁንና በሐምሌ ወር ከተካሄደው ጦርነት በኋላ፣ በ1876 ዓ.ም. ወደ ካይሮ የተላኩትን የአፄ ዮሐንስ መልዕክተኛን፣ ብላታ ገብረእግዚአብሔርን ግብፅ አሰረች፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም ያለ ምንም ይቅርታ መልሳ ፈታች፡፡
የጥንቶቹ የግብጽ መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የዝናብ መጠኑ ሲያንስና የዓባይ ወንዝ የውሃ ሙላት ሲቀንስ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ገድበውት ወይም ጠልፈውት ነው›› እያሉ ክፉኛ በስጋት ይናጡ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ የወቅቱ ነገስታት አማላጅ እየላኩ፣ የዓባይ ወንዝ እንዳይገደብባቸው ወይም እንዳይጠለፍባቸው ሲማፀኑ፤ ደጅ ሲጠኑ ኖረዋል፡፡
አፄ ይምርሐነ ክርስቶስ (1077-1117)፤ የግብፅ ክርስቲያኖች በእስላም ገዥዎቻቸው ትዕዛዝ የከፋ ስደትና መከራ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሰማ፡፡ በዚህን ጊዜ ለግብፁ ገዥ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የጀመረውን እኩይ ተግባሩን እንዲያቆም፤ ካላቆመም ዓባይ ወንዝን ከእነ ገባሮቹ ወደ ሌላ በረሃማ አቅጣጫ በመመለስ፣ ግብፃውያንን በውሃ ጥም ለመበቀል የቆረጠ መሆኑን የሚገልፅ መልዕክት ሰደደለት፡፡
የግብፅ ሕዝብ ይህንን በሰሙ ጊዜ በ‹‹ድርቅ ማለቃችን ነው›› ብለው በእጅጉ ተጨነቁ፡፡ የግብፅ ገዢም ዛሬ ነገ ሳይል እጅ መንሻ አሲይዞ፣ የግብፅ ፓትርያርክን አቡነ ሚካኤልን ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ እርሳቸውም አፄ ይምርሐነን  ያሰበው የዓባይ ውሃ ወደ ሌላ አቅጣጫ ቢቀለበስ በሚከሰተው ድርቅ የሚጐዱት ክርስቲያኖችም ጭምር እንደሆኑ አስረዱ:: አፄ ይምርሐነ ክርስቶስ፤ ለግብፅ ሕዝብና ለፓትርያርኩ ክብር ሲል እቅዱን መተውን ነገራቸው፡፡ ፓትርያርኩም የተላኩበትን ተግባር አከናውነውና ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው፤ ለተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ምዕመናን ቡራኬ ሰጥተው በደስታ ወደ ግብፅ ተመለሱ፡፡
በአፄ ዐምደ ጽዮን (1297-1327) እንዲሁም በአፄ ሰይፈ አርእድ (1327-1355) የንግስና ዘመንም፣ ግብጾች “የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ በመቀየር ጉድ እንሰራችኋለን” ተብለዋል፡፡ ግብጾች በ19ኛው ክፍለ ዘመን በዘላቂነት በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁበትን መላ ከመዘየድ አልቦዘኑም፡፡ በመካከለኛ ዘመን ከ1789-1879 እ.ኤ.አ. የግብፅ መሪ የነበረው መሐመድ ዓሊ፤ ‹‹የግብፅ ደህንነትና ብልፅግና የሚረጋገጠው፣ ግብፅ ከፍተኛ ውሃ በምታገኝበት የኢትዮጵያ ግዛት ላይ አሸናፊነቷን ስታስከብር ነው!›› የሚል አቋም ነበረው፡፡ ቀጥሎ የመጣው የግብፅ መሪ ከዲቭ እስማኤል አማካሪ የነበረው የስዊዝ ዜጋ ዋርነር ሙዚንገር ዓባይን በተመለከተ‹‹ኢትዮጵያ ለግብፅ አስጊ ሀገር ናት!›› የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር መለገሱ ይነገራል፡፡
*    *   *
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1927 እ.ኤ.አ በጣና ሐይቅ መውጫ ላይ ግድብ ለመሥራት ማቀዳቸው ተሰማ፡፡ ይሄን ተከትሎ ግብጾች ሥም የማጥፋት ዘመቻቸውን ተያያዙት፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› የሚለውን ስያሜ የሚጠቀሙት ‹‹ኢትዮጵያውያን የንጉሥ ሰለሞን የእሥራኤል ዘር ስላላቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የእሥራኤል ወዳጅ ናቸው፡፡ ጽዮናዊ የመንግሥት ሥርዓትንም ያራምዳሉ›› በማለት ኢትዮጵያን ከአረብ አገራት ጋር ለማራራቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ንጉሡ ግድቡን በእውን ለመተግበርም በአሜሪካን አገር በሚገኘው ‹‹ዋይት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን›› አማካኝነት ማስጠናት ጀመሩ፡፡ የካርታ ሥራው ከተከናወነ በኋላ ግን በግብፅና በእንግሊዝ መንግሥታት ክፉኛ ተቃውሞ በመነሳቱ ሥራው ሳይተገበር ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የግብጽ ዜጐች በዓለም ባንክ እስከ ምክትል ዳይሬክተርነትና በተባበሩት መንግሥታት እስከ ዋና ፀሐፊነት በያዙት ኃላፊነት በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ለምትሰራው ግድብ፣ እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ሳያሰልሱ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በግብፅ እጅ ጥምዘዛ፣ እ.ኤ.አ በ1929 የግብፅና የሱዳን ስምምነት መሰረት፣ የዓባይ ወንዝ ይኖረዋል ከተባለው አጠቃላይ የውሃ መጠን ግብፅ 92 በመቶ፣ ሱዳን 8 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጋለች፡፡ በዚህ ወቅት በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀችው ብቸኛ አገር ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራት፣ ከዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ድርሻ እንዳይኖራቸው ተደርጐ ከድልድሉ ውጭ ሆነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የላይኛው ተፋሰስ አገራት በግልፅ የውሃ ድርሻ የተነፈጋቸውና እንደ ባለድርሻ ያልታዩበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
እ.ኤ.አ በ1947 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአገራትን የኢኮኖሚ መብቶችና ግዴታዎች ለመደንገግ ያፀደቀው ቻርተር፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን የመጠቀም መብቷን አይከለክልም፡፡ ይህንን እያወቁ ግብጦች ከላይ ታች፤ ከታች ላይ መማሰን ጀመሩ፡፡ ይሁንና ግብጾች በጦርነት፣ እንግሊዝ በውልና በስምምነት ስም፣ የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ምኞታቸውን ማሳካት አልተቻላቸውም፡፡ በ1941 እ.ኤ.አ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጣልያን ጦርነት ምክንያት በስደት ሱዳን ካርቱም በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የነበረው ጋማል አብድል ናስር፣ የዓባይ ወንዝ ከመነሻው እስከ መድረሻው ለመቆጣጠር ‹‹የዓባይ ተፋሰስ አንድነት›› በሚል ሽፋን፣ ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን እንዲዋሃዱ ሀሳብ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ ይሁንና በወቅቱ በሱዳን ካርቱም፣ የኢትዮጵያ ቆንስላ የነበሩት መለስ አንዶም ወደ ካይሮ አመሩ፡፡ በዓባይ ተፋሰስ አንድነት ስም የተጠነሰሰውን ሴራ በማጋለጥም መልዕክታቸውን አድርሰው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡---
(በቅርቡ ለኅትመት ከሚበቃው የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን መጽሐፍ ላይ የተቀነጨበ)

Read 3127 times