Saturday, 14 March 2020 11:03

“ይቺ ጎንበስ ጎንበስ ሳር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነው!”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   ከዕለታት አንድ ቀን ብዙ አህዮች በጠፍ ጨረቃ መንገድ ይጀምራሉ፡፡ አንዲት ቀበጥ አህያ ከመካከላቸው አለች፡፡ ግጦሽ አግኝተው እንደ ልባቸው ከጋጡ በኋላ ይቺ ቀበጥ አህያ፤
‹‹የዚህ አካባቢ ሳር እምብዛም አይጣፍጥም፡፡ ወደሚቀጥለው መንደር እንሂድና የተሻለ ሣር እንፈልግ›› ትላለች
አባወራው አህያ፤
‹‹ሣር ሣር ነው፡፡ ዝም ብለሽ ጋጪ! በዚህ ጠፍ ጨረቃ ጅቦች ያገኙንና ኋላ ደግ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ጥሩው ዘዴ እንቅስቃሴ ሳናበዛ፣ ድምፃችንን አጥፍተን፣ እስከምንጠግብ መጋጥ ነው›› አለ፡፡
ያቺ ጥጋበኛ አህያም፤
‹‹ግዴላችሁም ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል
ደሀ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል› ተብሏል፡፡ የተሻለ ሣር ወደምናገኝበት መንደር ሄደን እንደ ልብ የምንግጠው ሣር እናገኝ ይሆናል፡፡››
‹‹እሺ። በየት አቅጣጫ እንሂድ?›› አንደኛው አህያ
‹‹ወደ ምሥራቅ ጥሩ ጨፌ እንዳለ አውቃለሁ›› ሁለተኛው
‹‹ከሆነስ አይቀር ወደ ደቡብ ከሄድን በጣም ለምለም ሣር በገፍ ይገኛል፡፡›› ሦስተኛው
‹‹እኔም ፈጥነን ሳይመሽብን ወደ ደቡብ እንገሥግሥ ነው የምለው!›› አንደኛው
‹‹ደቡብ አቋራጭ ስለሌለው ይመሽብናል፡፡ የሚሻለው እኔ ያልኩት ምሥራቁ ነው፡፡ ለም ነው፤ ቅርብም ነው፡፡ ከዚያ በላይ ምን ትፈልጋላችሁ?››
ቀበጧ አህያ፤
‹‹ምርጫ  እያለን ለምን አንድ ነገር ላይ ሙጭጭ ትላላችሁ፡፡ በግድ ይሄ ቦታ ካልሆነ ካላችሁ ግን በቃ ዕጣ እናውጣ!››
አንደኛው፤
‹‹እሺ እናውጣ››
ሁለተኛው፤
‹‹እሺ ዕጣ ይለየን››
ሦስተኛው፤
‹‹እኔም በዕጣው እስማማለሁ››
በዕጣ እንዲለይ ተወሰነና ዕጣ ወጣ፡፡ ቀበጧ አህያ ያለችው ምርጫ ላይ አረፈ ዕጣው፡፡
‹‹ዕጣው እንደዛ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል? ዘወር ዘወር ብለን ቦታ እንምረጥ በቃ››
መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡
አንድ ለም ቦታ ደርሰው መጋጡን ተያያዙት፡፡ ጠገቡ፡፡
ያቺ ቀበጥ አህያ፤
‹‹ነፋኝ ቀበተተኝ… አንድ ጊዜ ልጩህ›› አለች፡፡
አባወራው አህያ፤
‹‹ተይ አይሆንም፡፡ ድምፅሽን ተከትሎ ጅብ ሊመጣብን ይችላል፡፡ አደጋ አለው!›› አለና አስጠነቀቀ፡፡ አሁን ቀበጧ አህያ ትንሽ ታገሰች፡፡ ትንሽ ቆይታ ግን፤
‹‹ኧረ እኔ አልቻልኩም፤ ነፋኝ ቀበተተኝ፡፡ እባካችሁ አንድ ጊዜ ልጩህ!››
አባወራው ተይ እመት አህያ… ጦስሽ ለሁላችንም ይተርፋል!”
አህያይቱ አንዴ አናፋች፡፡
ትንሽ ቆይታ ‹‹አሁንም አንዴ ልጩህ” አለች፡፡
ጮኸችና፤
‹‹ይሄዋ ምንም አልመጣም›› አለችና፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም ጮኸች፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ ልትጮህ ተነሳች፡፡
አባወራው አህያም፤
‹‹እመት አህያ አስተውይ፡-
የመጀመሪያው ጩኸትሽ - መጥሪያ፡፡
ሁለተኛው ጩኸትሽ - ማቅረቢያ ነው፡፡
ሦስተኛው መበያሽ ነው!
አህይቱ ነገሩ ስሜትም ሳይሰጣት
ሦስቴ ጮኸች - ውጤቷ መበላት ሆነ!››
***
ሳያስቡ መጮህ ውጤቱ አያምርም፡፡ የራስን ማናፋት ለማስተንፈስ ስንቃጣ ምን እንደምናስከትል አናውቅም፡፡ ደርግ በዱሮ ዘመን መግለጫው፡-
‹‹በጫጫታና በጩኸት የፈረሰች አገር ብትኖር የመጽሐፍ ቅዱሷ እያሪኮ ብቻ ናት፡፡ እኛ ደግሞ የምትገነባ አብዮታዊት አገር እንጂ የምትፈርስ እያሪኮ የለንም›› ይል ነበር፡፡
ዕውነት ነው፡፡ በጫጫታ ላለመፍረስ የሰከነ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ሕይወትን እንዴት መምራት እንደምንችል ማጤን ተገቢ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ሞላ ሲሉት የሚጐድል፤ ጐደለ ሲሉት የሚሞላ፣ ሁሌም ትኩሳቱ የሚፈላና የሚቀዘቅዝ ነው፡፡ ሰው ሁሉን ችሎ በሁሉ ረክቶ መንቀሳቀስን ልማድ አድርጐታል፡፡ ‹‹ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል›› ይለናል፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ እንዲህ እያለ፡-
‹‹ዛሬ ለወግ ያደረግሺው ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው
ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የተሰለጠነ እንደሁ፣
ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል!››
…እያለ ዛላውን ያስጨብጠናል፡፡
ሁሉም የዘመናችን ገጣሚያን የየራሳቸውን
ረቂቅ ቅኔ ይቀኛሉ፡፡ ገጣሚ መንግሥቱ ለማ በ “ባለ ካባና ባለ ዳባ” ቴአትራቸው አፄ ቴዎድሮስን እንዲህ ያናግሯቸዋል፡-
‹‹ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በእኔ ቤት ጽድቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው፣ ኪኖር በምጽዋት”
የገጣሚ ነፃነት ህይወት - አከል ነው፡፡ ባሻው ሰዓት ነፃነትን ያሰርፃል፤ ራሱ ረክቶ ሌሎችን ያረካበታል፡፡ ዓለም፤ ሰጥቶ መቀበል መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ የሚሰጠውን አይሰስትም፡፡ የሚሰጡትን በምሥጋና ይቀበላል፡፡ መንግሥቱ ለማ እንዲህ ያሳምሩታል፡-
‹‹ደሞም ያ ገጣሚ፣ ልዩ ሥልጣን አለው
ሲያማ ሰው ቀርቶ፣ እዝጌሩም አይተርፈው!››
የሚባለው ደርዝ ባለው ገፁ ነው፡፡
በየጊዜው በአገራችን ላይ የሚከሰቱ አያሌ ጉዳዮች እንደመኖራቸው፣ የየጉዳዮቹ ባለቤት የሆኑ አያሌ ሰዎችም ከክስተቶቹ በየጀርባ ይኖራሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የነቁና ያልነቁ አሉባቸው፡፡ የነቁትን ቁጥር ማብዛት የእኛ ፋንታና ሐላፊነት ነው! ሐሳዊ መሲህን ከመካከል ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በሁሉም መስክ አለን አለን ሲሉ ይገኛሉ፡፡ እንደ ንሥር የነቃ ዐይን ከሌለን ለጮሌና ጨላጣ ብልጠት እንጋለጣለን፡፡ እንዲህ ላሉቱ ሁሉ አንድ ጠንካራ ተረት ያሻቸዋል፡-
‹‹እቺ ጐንበስ ጐንበስ ሣር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነው!››


Read 14829 times