Saturday, 14 March 2020 11:30

“ኦፌኮ” እና የሰሞኑ ‹‹ሐበሻን አታግቡ” ትርክት

Written by  ደ. በ
Rate this item
(6 votes)

  የማያባራ ጠብና ግጭት ለማስነሳት አንጣደፍ!
                          
            የሰሞኑ ዋነኛ አጀንዳና ማህበራዊ ሚዲያው ቋቅ እስኪለው የተጋተው ትርክት፣ ‹‹ሀበሻን - አታግቡ፣ ያገባችሁ ፍቱ! እኛ እናገባችኋለን›› የሚለው ነው፡፡ ከዚያ ለጥቆ በዶክተር ዐቢይ አህመድና በባለቤታቸው ላይ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “ዘልዛላነት” የተፈፀመው ፀያፍ ድርጊት ነው፡፡
ይሁንና የዛሬ ትኩረቴ፤ የሕጻናት ጨዋታ በሚመስለው የፕሬስ ድርጅቱ አስነዋሪ ተግባር ላይ ሳይሆን በሕዝብና አገር ላይ አደጋ ሊጋርጥ በሚችለውና በየኦምኤን ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት በተላለፈው የአዳማ ከተማ ትርዒት ላይ ነው፡፡ ትርዒቱ በዘመነ ወያኔ ተወልዳ ባደገችው የኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣት ቢገለጥም በአንጋፋው ፖለቲከኛ በፕሮፌሰር መረራና ሌሎችም ‹‹ልሂቃን›› መታጀቡ የበለጠ አሳዛኝ ገጽታ ያላብሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ግራና ቀኙን አይናቸውን እያቁለጨለጩ፣ ፖለቲካውንና ማዕበሉን እንጀራ አድርገው ለሚጋግሩ “ሆድ አደሮች” ትልቅ ሲሳይ ሆኗቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ የፖለቲካ ደላሎችና ሸቃጮች፤ ለየትኛውም ብሔር ወይም ሃይማኖት ደንታ የላቸውም፡፡ ኦሮሞ ቢበላ ወይም ጦሙን ቢያድር፣ አማራው ቢጠግብ ወይም ቢራብ፣ ትግራዩ ቢጠማ ወይም ቢረካ… ጉዳያቸው አይደለም፡፡ የእነርሱ ዓላማ በተከፈተችው ቀዳዳ፣ ነገር አራግቦ፣ ጥቅማቸውን መሸቀል ብቻ ነው፡፡ ለሕዝብ እንታገላለን የሚሉ የየትኛውም ብሔር ፖለቲከኞችም ትኩረታቸው፣ የራሳቸውን የሥልጣን መሰላል ማመቻቸትና በሕዝቡ ልብ ውስጥ በደምና እንባ ተጠቅልለው መግባት ነው፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው ‹‹ይህ ሰው ለእኛ የቆመ ነው›› እንዲባሉ ነገር ያራግባሉ፡፡ ሥልጣን ምን ያህል እንደሚያጓጓ ለማረጋገጥ፣ ሰሞኑን ትልልቁን ሰው ሁሉ እንደ ሕጻን ያደረገውን አጋጣሚ ማየት በቂ ነው፡፡
የአዳማዋ ወጣት ንግግር፣ ለኦሮሞ ጽንፈኞች፣ ሕዝቡን ለጥላቻና ልዩነት ማነሳሺያ ጥሩ ግብአት ሲሆን ለአማራ ጽንፈኞች ደግሞ ‹‹ታጠቅ ተነስ!›› በሚል ቅስቀሳ ሁነኛ ሰበብ ነው፡፡ “ሁለቱም አይመቹኝም” ለሚለው የትግራይ ሕወሓት ደግሞ ወዲያና ወዲህ እያለ ነገሩን በማጋጋል፣ የራሱን ጨለማ የማብራት ዕድሉን ይሞክርበታል፡፡
በመሠረቱ ኦሮምኛ ተናጋሪዋ ወጣት ‹‹ሐበሻ›› ስትል በተለምዶ ‹‹አማራ››ን ይሆናል ቢባልም አንዳንዶች ‹‹ሐበሻ›› የሚለው ቃል ሁልጊዜ አማራን ብቻ የሚወክል አይደለም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ሩሲያዊው አሌክሳንደር ቡላቶቪች፣ ወደ ደቡብ ስለዘመተው የምኒልክ ሰራዊት በፃፉት መጽሐፍ መግቢያ ላይ ስለዚህ ቃል የሰጡት ትርጉም እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹ቡላቶቪች ‹ሐበሻ› ሲል በአብዛኛው የመሀል፣ ሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች አገር ማለቱ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን በዚህ ስያሜ ሥር የሚያጠቃልለው የአማራን ሕዝብ ብቻ ነው›› ይላል፡፡ በሌላ መጻሕፍት ደግሞ የአማራና የትግራይን ሕዝብ የሚያጠቃልል ስያሜ ተደርጎ ተጽፏል፡፡
ሰሞኑን ‹‹ሀበሻን አታግቡ፣ ወይም ፍቱ!›› ያለችው ወጣት፤ ይህንን በመናገሯ ባንድ ወገን፣ ከፍተኛ ስድብና ዛቻ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከእልልታ ያልተናነሰ አድናቆት ተሰጥቷታል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይቀር እየጠቀሱ፣ በተለይም የአብርሃም ዘር ከሌሎች እንዳይጋባ የተከለከለበትን ቃል ያለ ዐውዱ በመጠቀም ሲያስገርሙን ሰንብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥላቻና መለያየት በየትኛውም እምነትና እውነት፤ የትኛውንም ቀሚስ አጥልቆ ቢመጣ ተቀባይነት የለውም፡፡ ባይሆን “ከሰይጣንም ቢሆን ተስማምተን ልባችን የፈቀደውን እናደርጋለን” ካልን ፈጣሪ አያስገድደንም፡፡ ዋጋው ግን በእጁ ነው፡፡
በእኔ አተያይ፤ ልጅቷ በገዛ ራሷ ያጠፋችው ምንም ጥፋት የለም፡፡ ይህቺ ወጣት ያደገችው ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ በሚሰበክበት የወያኔ አገዛዝ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እርሷና የዕድሜ አቻዎችዋ ሚዛናዊ ሀሳቦችን እንኳ እንዳያስተናግዱ “በሌላ ቋንቋ አትማሩ፤ አትስሙ” በሚል ጥላቻ ውስጥ ነው የኖሩት፡፡ ‹‹አማራ፣ ወይም ደግሞ ‹ሐበሻ›  መሬትህን ወርሮ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ገድሎ፣ አፈናቅሎ፣ ጡት ቆርጦ…” የሚል ጨፍጋጋ ትርክቶችን አዳምጠው ሲያበቁ ይበልጥ እንዲያምኑ፣ በየዕለቱ ምስሉ እንዳይጠፋባቸው ሰቀቀኑ እንዳይርቃቸው፣ በገዛ አገራቸው መንግሥት ‹‹አሞሌ›› የመሰለ ሀውልት ተጠፍጥፎ ቆሞላቸዋል፡፡
የአገሪቱ ሬዲዮና ቴሌቪዥንም እርቅና አንድነት ሳይሆን ልዩነትና የበቀል መንፈስን ለወጣቱ እየመገቡ ነው ያሳደጉት፡፡ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከነገ ተስፋና ብልፅግና ይልቅ የትናንቱ ቁስል እየተጎረጉረ፣ ወጣቱ በደረቅ ደም ልቡ ተፈንክቷል፡፡ ‹‹አማራ›› ሲባል ‹‹ትምክህተኛ›› ነፍሰ ገዳይና፣ ጡት ቆራጭ” እንጂ እነርሱ ሰፈር እንዳለው ደሀ ገበሬ ጦሙን ውሎ ጦሙን የሚያድር፣ ቀደም ባሉት ዘመናት በባላባትና መኳንንት መሬቱን ተነጥቆ ተኮራምቶ የሚኖር ጭቁን ወገናቸው እንደሆነ አያስቡም፡፡ ‹‹አማራ›› ማለት ባላባት፣ ገዥ ነው፡፡ እንዲያ ነው የተሰበኩት፡፡
ይሄ በትክክል የሚገባው ከአማራው አጎራባች ያለው ኦሮሞው ገበሬ ነው፡፡ አብሮ ቡና የሚጠጣው፣ ብሶቱን በጋራ የሚካፈለው፣ ዐውደ ዓመቱንና አዘቦቱን በጋራ ያሳለፈው፣ ሲያጣ የተበዳደረ፣ በልቅሶና በሰርግ ተረዳድቶ የቆየ፣ ልጁን የዳረለትና የተቀላቀለው ሰፊ ማህበረሰብ እውነቱን ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡
በአዳዲሶቹ ወጣቶች ግን ካድሬ የፖለቲካ ቋቱን ሊሞላ፣ የሥልጣን ወንበሩን ሊያመቻች እሳቱ ላይ ቤንዚን እያርከፈከፈ ጥላቻ ሲዘራባቸው ኖሯል፡፡ ይህቺም ወጣት፣ ከሰማችውና ካየችው ነገር ወዲያ ሌላ ሀሳብ ከየት ልታመጣ ትችላለች? ኦነግ የሰበካት እኮ ይህንን ነው፡፡ ወያኔ ያወራትም ተመሳሳይ ነው፡፡ በራሷ ቋንቋ በራሷ ሰዎች የተሳለላት ሥዕል ይህ ነው፡፡ ታዲያ ምን ታድርግ? እንዴት አድርጋ አያቶቿን ከገደለ፣ ካሳደደ፣ ከናቀና ጡታቸውን ከቆረጠ ጋር አልጋ ላይ ትተኛ? … ሌላውስ እንዴት ይህንን ግፍ የፈፀመባትን ወገን አቅፎ ይተኛል?...ልጅቱ  በተነገራት የፈጠራ ታሪክ መሠረት፤ ይህን ማድረግ እርም ነው፡፡ ስለዚህ አንጀቷ ተቃጥሎ መደረግ ያለችውን ተናገረች፡፡ ይህቺ ልጅ ምን ያህል ውስጧ እንደነደደ አስቡት!... ‹‹ፍቅር›› ሳይዘራባት ‹‹ፍቅር›› ከየት ታምጣ? ያ ብቻ አይደለም:: እርሷ ከተናገረችው በላይ የተናገሩላት ጎልማሳ ፖለቲከኛም ፊት ለፊቷ ተቀምጠው ነበር፡፡ እኚህ ሰው የዩኒቨርሲቲ መምህር ስለሆኑያወቁና የበቁ ናቸው፤ ብላ ታስባለች። በሞራልም ቢሆን የወንጌል አማኝ ናቸው፤ ክርስቶስ ፍቅር ያስተማራቸው፤ በሐሰት የማይናገሩ የመርህ ሰው፡፡ በዚያ ላይ ለኦሮሞ ሕዝብ ግንባር ቀደም ተቆርቋሪ ሆነው እስር ቤት የወረዱ! በክብር የምታያቸው ሰው ናቸው “ፖለቲከኛ”፡፡ ጋሼ በቀለ ገርባ ያሉትን የሰበኩትን በተደጋጋሚ ሰምታለች፤ የቅርብ ጊዜ ትዝታዋ ነው፡፡ “ቋንቋችሁን ከማይናገር ሰው ጋር አትገበያዩ፤ ትዳርም አትመስርቱ” ብለው የተናገሩትን ቃል አትረሳውም:: ታዲያ ከታላላቆች (ጎምቱዎች) የተነገራትን መድገሟ ጥፋቱ ምንድነው? የአርስቶትል ሀሳብ ይደግፋታል፡፡ ‹‹ወጣት አድማጮች ቅንነትና አዎንታዊ ስሜት ያላቸው፣ ችኩልነትና በስሜት መገፋፋት የሚታዩባቸው፤ በተናጋሪው ላይ እምነት የሚያሳድሩ፤ አሳማኝ የመሰላቸውን ነገር በቀላሉ መቀበል የሚችሉ ናቸው፡፡” ብሏል፡፡ ይህቺ ወጣት እንደ ጥሩ ተማሪ የተማረችውን በአደባባይ ከመግለፅ ውጭ ያጠፋችው ጥፋት የለም፡፡ እኛ የምናስበውንና ቢሆን የምንለውን ፍቅርና ይቅርታ የሰበካት ሰው አልነበረም፤ አሁንም የለም፡፡ ለዚህ ንግግሯም ትክክለኛነት ትልልቆቹ ሰዎች ማረጋገጫ የሚሆን ጭብጨባ ሰጧት፡፡ ምን ታድርግ! የሰው ባህሪ በራሱ ከባድና በቀላሉ የሚታረምም አይደለም፡፡ በኑሮው በሕይወቱ ላይ ስትመጣ ቁጣው ፈጣን ይሆናል፡፡ ከእየሱስ ክርስቶስ ጋር ለሶስት ዓመታት በፍቅርና በይቅርታ ሕይወት ታጅቦ የኖረው ሃዋርያው ጴጥሮስ፤ ጌታውን ሊይዙበት ሲመጡ ፍቅርና ይቅርታ ትዝ አላለውም፡፡ ሰይፉን መዝዞ ማልኮስ ጆሮ ላይ አሳረፈው፡፡ እነ አቶ በቀለም የዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ የገቡ ይመስለኛል፡፡ ወደ ቀልባቸው እንዳይመለሱም የግራ ቀኙ ጩኸት አዋክቧቸዋል፡፡ የሰሙትን ወንጌል የወደባቸው ይሄ ማዕበል  ‹‹መፋታትን እጠላለሁ›› የሚለውን የእግዚአብሔር ሐሳብ የሚያውቅ ሰው፤ ‹‹ፍቱ!›› ሲባል በጭብጨባ የሚያጅብ አይመስለኝም፡፡ ፍቺ ሲባል ደግሞ ልጅ የወለደ ሰው በልጆች ላይ የሚደርሰውን እንግልትና መከራ መገመት አያዳግተውም፡፡ ምን ጨካኝ ቢሆን የልጁ ጉዳይ ይታሰበዋል፡፡
ባይሆን ፕሮፌሰር መረራ ሁለቱም ብዙ ላይሰማቸው ይችላል፡፡ በአንድ ወገን የኮሚኒስት ዘመን ሰው ስለሆኑ የእምነቱ ነገር ያን ያህል ውስጣቸው ላይገባ ይችላል:: በትግሉ ምክንያት ትዳር መስርተው የልጅን ጣዕም ስለማያውቁት የራሱ ጉዳይ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ፕሮፌሰር መረራን የምጠይቃቸው ‹‹የታሪክ ቁስሎቻችንን ማከም ባንችል እንኳን በ21ኛው ክፍለ ዘመን መነጽር ችግሮቻችንን ማየትና መፍትሔዎቻቸውን መፈለግ እንዳለብን ለማሳየት ነው…›› ብለው በመጽሐፋቸው ያሰፈሩትን ጉዳይ እንዴት ዘነጉት? ያንን ሁሉ ትንታኔና መፍትሄ የፃፉ ሰውዬ ምን ሆነው ነው ወደ ታች የወረዱት? የያ ትውልድን ‹‹ዓለም አቀፋዊ›› አስተሳሰብና ድንበር ተሻጋሪ  ፍልስፍና እንዴት ይህን ያህል ያንሳሉ?! በእርስዎ አያምርምና…ፕሮፌሰር ይመለሱ! ለነፃነትና ፍትህ ሕይወትዎን ሁሉ የሰጡ፣ በግፍ የታሰሩ፣ የተጉላሉና እጅዎን ለካቴና የሰጡ ሰው፤ ዛሬ በትንሽ ቦታ በሰነፎች ሀሳብ ውስጥ ሊዋኙ አይገባም፡፡  ‹‹ኦሮሞ ተበድሏል›› ቢባል እንኳ  ኦሮሞን የበደለው አንድ ብሔር ወይም ህዝብ እንዳልሆነ ራስዎ መስክረዋል፡፡ “ኦሮሞን ረግጦ በኦሮሞ መግዛት” እየተለመደ መምጣቱም አከራካሪ ጉዳይ እንዳልሆነም ገልፀዋል፡፡ አሁን የሚሻለው እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ደህነቱ ያጠቃውን፣ ፍትህ የሚፈልገውን የሌላውን ብሔር ወገን ይዞ፣ ለጋራ ብልፅግና መትጋት ብቻ ነው፡፡
በተለይ  የሰውን ልጆች አንድ ለማድረግ ሕይወቱን የሰጠው የክርስቶስን ወንጌል እያወቁ ሰዎችን በጥላቻና በጥፋት መንገድ መምራት በምድርም በሰማይም ያስጠይቃል:: ከዚህ ይልቅ የሁሉም ወገን ጽንፈኛና አክሪሪ ፖለቲከኞች፤ አገሪቱ በአንድነት የምትበለፅግበትን፣ ሕዝቦች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበትን መንገድ ማመቻቸት ለሁላችንም ይጠቅማል፡፡
ከዚህ ቀደም የተፈፀሙ በደሎችን ይቅር ተባብሎ በሚቀጥለው ምዕራፍ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በመረዳዳት ወደ ተሻለ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድል የሚመነጠቅበት ቀን እንዲመጣ መሰረት መጣል እንጂ ለማያባራ ጠብና ጦርነት ሕዝብን ማነሳሳት መጨረሻው አያምርምና ሁሉን በማስተዋል እናድርግ!  Read 3943 times